Monday, 18 December 2017 13:16

gnesium sulfate …ተፈላጊ መድሀኒት…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹…Magnesium sulfate በአገራችን ቀደም ሲል ያልነበረ እና አስፈላጊነቱ ታምኖበት በረዥም አሰራር ወደአገር እንዲገባ የተደረገ በደም ግፊት ምክንያት የሚሰቃዩ እርጉዝ እናቶችን ሕይወት ለማትረፍ በእጅጉ የሚረዳ መድሀኒት ስለሆነ መቋረጥ እንደሌለበት የሁሉም እምነት ነው፡፡››
ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ
Preeclampsia Eclampsia ህክምና ያለው ሲሆን በፍጥነት ካልተቆጣጠሩት ግን ገዳይ መሆኑ በገሀድ እየታየ ያለ ነው፡፡››
ዶ/ር ልንገርህ ተፈራ
ከላይ ያነበባችሁት ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስትና ለዚህ እትም ማብራሪያቸውን የሰጡን የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻስ ሊስት የሆኑት የዶ/ር ልንገርህ ተፈራ ንግግር ነው፡፡ በዚህ እትም ዶ/ር ገረመው ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ የነገሩንንም እናስነብባችሁዋለን፡፡ በስተመጨረሻም ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ እምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በእርግዝና ወቅት በተከሰተ የደም ግፊት ምክንያት የደረሰባትን ችግር በምስክርነት የተናገረች ሴት መልእክት እንደሚ ከተለው ነው፡፡
‹‹…ሁኔታው ካጋጠመኝ አምስት አመት ገደማ ይሆነዋል፡፡ …እኔ በእድሜዬ ከባለቤቴ ቢያንስ አስር አመት እበልጣለሁ፡፡ ነገር ግን በሰውነቴ የማላሳጣ ወይንም ትልቅ ሰው ስለማልመስል እድሜዬን ቢያውቀውም አግብቶኛል። ታዲያ ለማግባት ሲል ችላ ያለውን የእድሜዬን ትልቅነት ልጅ በማጣቱ ግን ያስበዋል፡፡ …አንቺ እኮ እድሜሽ ትልቅ ነው። ለዚህ ይሆናል የማትወልጂው… ይለኛል፡፡ እድሜዬ ከአንተ ቢበልጥም ገና አርባ አመት መጀመሪያው ላይ ነኝ። በዚህ እድሜ ደግሞ ልጅ መውለድ ይቻላል …እያልኩ እጨቃጨቃለሁ፡፡ ታዲያ እንደ እድል ሆኖ ልጅ ተረገዘ፡፡ እርግዝናው ገና አምስት ወር ሲሆነው ጀምሮ ግን የደም ግፊት የሚሉት ነገር በምርመራው ታየ፡፡ እንደምንም በትግል ወደሰባት ወር ገደማ ስደርስ የማላውቀው ሕመም መጣብኝ። በድንገት ሕሊናዬን ሳትኩ፡፡ በአካባቢዬ ያለ ማንም ሰው ስለሆንኩት ነገር የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ በድንገት ያጋጠመኝ ሕመም ግን የሰውነት መንቀጥቀጥ የመሳሰሉትና እራስን መሳት ጭምር ነበር፡፡ የንሰሐ አባቴ በፍጥነት ተጠርተው ጸበል ቢረጩ መጽሐፍ ቢደግሙ ምንም የተገኘ ነገር አልነበረም፡፡ በሁዋላም ባለቤቴ ተጠርቶ በፍጥነት ወደሐኪም ቤት ሲወስዱኝ ሐኪሞቹ በመሯሯጥ ነበር ነብሴን ያተረፉት፡፡ ለካስ ሕመሜ Preeclampsia ከሚባለው አልፎ Eclampsia ሆኖአል፡፡ በስተመጨረሻ ግን እድል አልቀናኝም፡፡ ያ በስንት ጥበቃና ፍላጎት የተረገዘ ልጅ ሳይወለድ ሞተ፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ከዚያ በሁዋላ ለማርገዝ ሳልታደል የወር አበባዬ ተቋረጠ። እናም ይህ በእርግዝና ጊዜ የሚመጣ የደም ግፊት በጣም አስከፊ ነው፡፡ ሁሉም አስቀድሞ ልብ ሊለው የሚገባው እና ጥንቃቄ ሊያደርግበት የሚገባ ነገር ነው፡፡…››
ምንይሉ አስረስ ከቃሊቲ
ከቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ ዶ/ር ገረመው የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት 4ኛ/ አመት ተማሪ ናቸው፡፡ ለማጋገር ስንፈልጋቸው ከአንዲት ታካሚ ጋር ነበሩ፡፡ ታካሚዋን ማነጋገር አልቻልንም፡፡ ሐኪሙ ግን ስለታካሚዋ እንደሚከተለው ነበር ያብራሩት፡፡
‹‹…ይህች እናት ከጤና ጣቢያ ወደ ሆስፒታሉ የተላከች ናት፡፡ ጤና ጣቢያው ወደ ሆስፒታል ሲልካትም ጽንሱ በሆድዋ ውስጥ እንደሞተ አረጋግጦ እና እስዋም ሀይለኛ የደም ግፊት እንዳለባት ገልጾ ነው፡፡ እኛም ስንመረምራት በደም ግፊት ምክንያት ከሚመጡት ሕመሞች አንዱ በሆነው የእንግዴ ልጅ ከጽንሱ መላቀቅ ስለደረሰበት ጽንሱ ሕይወቱን ሊያጣ ችሎአል፡፡ ከዚያ ያለፈ በእናትየው ላይ ችግር እንዳይፈጠር ስንልም ማግኔዥየም ሰልፌት እየተሰጣት ይገኛል፡፡ ይህች ሴት አሁን ባለችበት ሁኔታ ደህና ነች ፡፡ ነገር ግን ለወደፊቱም ሌላ ልጅ ብታረግዝ ይሔው ችግር ተመልሶ ሊከሰት እንደሚችል አስቀድሞ መገመት ይገባል፡፡›› ብለዋል፡፡
ዶ/ር ገረመው አክለው እንደገለጹት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት ታካሚዎች አብዛኛዎቹ ለሆስፒታሉ ከተመደቡት የጤና ጣቢያዎች ሲሆን የቀሩት ደግሞ በአቅራቢያ ከሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ጤና ጣቢያዎች የእርግዝና ክትትል ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው። እነዚህ ታካሚዎች የደም ግፊታቸው ጨምሮ ስለተገኘ ወደ ሆስፒታሉ የተላኩ ናቸው፡፡ በእርግጥ የተወሰኑት በሆስፒታሉ ክትትል ያላቸው ሲሆኑ የቀሩት ግን ከጤና ጣቢያዎቹ አቅም በላይ የሆኑ ናቸው፡፡ Magnesium sulfate (ማግኔዥየም ሰልፌት) የተባለው መድሀኒትን በሚመለከት በቅርብ ጊዜ በእርግጥ የመድሀኒት እጥረት የለብንም፡፡ ቀደም ሲል ማለትም ከሁለት አመት ወዲህ በየመሀሉ የሚቋረጥበት ሁኔታ ስለነበር ቀደም ሲል ሲሰራበት ወደነበረው መድሀኒት ተመልሰን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ Magnesium sulfate የሚሰጠው የደም ግፊታቸው ለጨመረ ሁሉ ሳይሆን ለሚገባቸው ነው። የመድሀኒቱ አሰጣጥም የተለየ ጥንቃቄን የሚሻ ነው። መድሀኒቱን የሚያዘው ሐኪሙ ቢሆንም መድሀኒቱን የሚሰጡት ደግሞ ነርሶቹ በመሆናቸው በመድሀኒቱ ዙሪያ አስፈላጊውን ስልጠና ያገኙ መሆን አለባቸው፡፡ ቢሆንም ግን ከሐኪሙ ጋር እየተናበቡ የመስራት ነገር ስላለ በመድሀኒት አሰጣጥ ዙሪያ ችግር አላገጠመም። በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የደም ግፊት ለብዙ እናቶች አስቸጋሪ ነው፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በየቀኑ ከሚመጡት እርጉዝ ሴቶች ከ30-40 በመቶ የሚሆኑት በደም ግፊት ምክንያት ነው፡፡ አንዳንዴም ከርቀት ቦታ የሚመጡት እናቶች በመንገድ ላይ በሚያጠፉት ጊዜ እና በተለያየ ምክንያት የደም ግፊታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ስለሚመጡ ለማዳን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ስለዚህም በደም ግፊት ምክንያት ልጆቻቸውንም አጥተው እራሳቸውም ለሕልፈት የሚዳረጉ እናቶች አሁንም አሉ። Magnesium sulfate በጤና ጣቢያዎች  የሚሰጥበት የአቅም ግንባታ ቢደረግላቸው እና ታካሚዎቹ ወደ ከፍተኛ ሆስፒታል በሚሄዱበት ወቅት በሚፈጠረው የተለያየ ምክንያት የተነሳ በመዘግየት የእናቶች ሕይወት እና ጽንሳቸው እንዳይጎዳ ማድረግ ቢቻል ተመራጭ ነው።›› ብለዋል፡፡ ዶ/ር ገረመው፡፡
በአብራክ የእናቶችና የህጻናት ሕክምና ሆስፒታል የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ልንገርህ ተፈራ እንደተናገሩት፡-
‹‹…Magnesium sulfate በእርግዝና ወቅት ለሚከሰት የደም ግፊት ተመራጭ መድሀኒትነቱ በአለም የታወቀ ነው፡፡ ይህ ማግኔዥየም ሰልፌት እንደሌሎች መድሀኒቶች በተመሳሳይ መንገድ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ለምሳሌም በመጀመሪያ ታካሚዋ እንደመጣች መድሀኒቱ ሲጀመር በደም ስር የሚሰጥ ሲሆን ይህም ልብን ቀጥ የማድረግ ወይንም ምቱን የማቆም አዝማሚያ ሊኖር ስለሚችል ቀስ ተብሎ ቢያንስ ከአስር እስከ አስራ አምስት ደቂቃ በሚሆን ጊዜ ውስጥ ስለሚሰጥ ያም ልብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቆጣጠር የሚያስችል ዘዴ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የባለሙያ ስልጠና  ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የሰለጠኑ ባለሙያዎች አሉ ቢባልም አዳዲስ ባለሙያ በየጊዜው ወደ ስራው ስለሚቀላቀሉ እና ከነበሩት ባለሙያዎችም ያልሰለጠኑም ብዙዎች መሆናቸው አይካድም፡፡ ስለዚህ ማግኔዥየም ሰልፌትን ለታካሚዋ ባስተማማኝ ሁኔታ መስጠት እንዲቻል ስልጠናውን ቀጣይ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ የታካሚዎችን ሁኔታ ገጠር እና አዲስ አበባ ብለን ስንከፍለው በአዲስ አበባ ብዙ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዋና ከተማዋ ሲወጣ ግን ችግር ሊኖር እንደሚችል መገመት ያስፈልጋል፡፡›› ብለዋል፡፡
የመድሀኒቱን ክፍፍል በሚመለከት ዶ/ር ልንገርህ የገለጹት እንደሚከተለው ነው፡፡
‹‹…Magnesium sulfate የተባለውን መድሀኒት ….እንደ እውነቱ ከሆነ የእኛ ሆስፒታል ማግኘት አልቻለም። በተደጋጋሚ ብንጠይቅ እና ብንሞክርም አቅርቦቱ በጣም ያነሰበት ሁኔታ ስላለ በመጠቀም ላይ ያለነው ሁለተኛውን አማራጭ ነው፡፡ ያም ማለት ዲያዜፓ የሚባለውን መድሀኒት ማለት ነው፡፡ ማግኔዥየም ሰልፌትን ያገኘነው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ስለነበር አሁን መጥፋቱ የሕክምናውን አሰጣጥ እንዳያውክብን እንሰጋለን፡፡ ሆስፒታሉ ከተከፈተ ገና 11 ወሩ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥም ከ10 ያላነሱ እርጉዝ እናቶች በደም ግፊት ምክንያት ወደ ሆስፒታሉ መጥተው Magnesium sulfate በነበረ ጊዜ በመድሀኒቱ ተረድተዋል፡፡ Magnesium sulfate ባልነበረ ጊዜ ለመጡትም ባለው መድሀኒት እረድተናቸዋል፡፡ ነገር ግን መድሀኒቱን የሚያስመጣው አካል እንዳይቋረጥ ጥረት ቢያደርግ እንላለን፡፡›› ብለዋል፡፡

Read 5274 times