Monday, 18 December 2017 13:14

አገር፣… በዘፈቀደ ዘላለም የሚቀጥል፤… ወይም ዛሬ ተነቅሎ ነገ የሚበቅል ቁጥቋጦ ይመስላቸዋል።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(7 votes)

 ስታድዮም የጦር አውድማ ለመሆን ዝግጅት የሚጠናቀቀው መቼ ይመስላችኋል? የስታድም ትልቁና ዋናው ነገር፣ “ብቃትን አጉልቶ የሚያሳይ የስፖርት ውድድር” እንደሆነ የተረሳ ጊዜ ነው። ስታድዮም የምገባው “የቲፎዞዎች ቀልድ፣ የተመልካቾች ጨዋታ ስለሚያዝናናኝ ነው”… እንዲህ ሲባል የሰማችሁ ጊዜ፣ ከትንሽ ጊዜ በኋላ፣ ነገር እንደሚበላሽ ጠብቁ።
“የስፖርት ብቃት፣ የተወዳዳሪዎች ጨዋታ ስለሚያዝናናኝ ነው”…. የሚል ሰው ሲመናመን፣… ያኔ ችግር ይመጣል።  የተመልካች ቀልድ ለመስማት፣ የቲፎዞ ቧልትና ጨዋታ ለማየት? ትያትር ቤት የምንገባውስ? የፊልም  ተመልካች ሆነን የምንታደመውስ? የተመልካቾችን አቀማመጥ ለመመልከት? የታዳሚዎችን ቀልድ ለመስማት?
ዋናዎቹ ነገሮች ተረስተው፣ ተቀጥላ ነገሮች እንደ ዋና ነገር መግነን ሲጀምሩ፣… መዘዝ እንደሚከተል አትጠራጠሩ። አሃ፣ የተዘነጉት ነገሮች፣… የስፖርት ብቃትና ውድድር፣… የትያትርና የፊልም ስራና ፈጠራ፣ ጥበብና ውበት እንዴት እንዲቀጥል እንጠብቃለን? ብንጠብቅ እንኳ፣ ራስን የማታለል ከንቱ ጥበቃ ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይኖረውም።   
ቀስ በቀስ፣ ቧልትና ቀልድ፣ ወደ ተረብና ስድብ፣ ወደ ጥላቻና ፀብ፣ ወደ ትርምስና መጠፋፋት ይለወጣል።
አገርም እንደዚያው ነው። አገር ስንል፣ ዋናው ትልቁ ቁም ነገር ምን እንደሆነ ከዘነጋን፣ ቀስ በቀስ… ያው፣… እንደድሮው እንዲቀጥል መጠበቅ፣ ከንቱ ተስፋ ይሆናል።

አገር ይለወጣል፤ (ይሻሻላል ወይም ይፍረከረካል)።
የአገር ትርጉሙ ህግና ስርዓት ነው።  ወንዝና ሸንተረሩማ ለምዕተ ዓመታት ነበር፣ ይኖራልም። ዩጎዝላቪያ የሚባል አገር ዛሬ ባይኖርም፣ ተራራዎቹና ሸለቆዎቹ ግን አሉ። ሜዳውና ቁጥቋጦውን ከሆነ አገር የምንለው፣ አዎ፣… ዛሬም ዩጎዝላቪያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሶማሊያ… እያልን ልንጠራቸው እንችላለን - ሁሉም አገር በግዑዝነት ለዘላለም የሚቀጥል ይመስል።
ይሄ፣… የአገርን ምንነት በቅጡ አለመገንዘብ ነው። አገር፣ ብንቆፍረውም ሆነ ብንዘነጋው የማይጠፋ፣ እንደ ተራራ ቋሚና ግዑዝ ቁስ አይደለም። ስንቆርጠው ራሱ ተመልሶ የሚበቅል ወፍዘራሽ አረምም አይደለም። እንደ አሸዋና አፈር፣ የጎርፍና የነፋስ ውጤት እንደሆነ አድርጎ፣ አቅልሎና አጣጥሎ ማየትም አላዋቂነት ነው። ግን የሚመስላቸው ሰዎች አሉ - ዋናውን ነገር የማያውቁ፣ የሚዘነጉ ወይም የሚያድበሰብሱ።
አለበለዚያማ፣ አገርን ቀይዶ የመሻሻል እድልን የመዝጋት አባዜ፤… አልያም አገርን እንደጠላት ቆጥሮ ለማፍረክረክ የመዝመት ሱስ… አይበራከትም ነበር። አገር፣ እንደ ተራራ፣ እንደሸንተረር ጉራንጉሩ፣ “ዘላለም” የሚኖር ስለሚመስላቸው፣… ወይም እንደ ቁጥቋጦ ዛሬ ቢነቀል ነገ እንደዘበት የሚበቅል ስለሚመስላቸው ነው፤… በእልህ ተነሳስተውም ሆነ እንደ ቀልድ እንደ ጨዋታ፣ የአገር መሰረቶችን ለመቦርቦር፣ ለመሸርሸር፣ ለመቆፈር፣ ለማፈራረስ ሲጣጣሩ ቢውሉ፣… ክፉ ጥፋትን እየደገሱ እንደሆነ ለመገንዘብ የማይፈቅዱት። ምን ችግር አለው? አሸዋውና አፈሩ እንደሆነ፣ ጎርፍና ነፋስ ይወስደዋል፤ ያመጣዋል። ያው፣… አገር ቢሄድ፣ አገር ይመጣል?
አገር ግን… ከዚያ ሁሉ በላይ ነው። አገር… ህግና ስርዓት ነው። ግን ህግና ስርዓት ማለት ብቻ አይደለም። በየጊዜው በመልካም አቅጣጫ እየተሻሻለ እንዲጓዝ ልንጥርለት የሚገባ፣… ትክክለኛ ህግና ትክክለኛ ስርዓት ማለት ነው - አሪፍ የሚያዛልቅ አገር ማለት።
(በሌላ አነጋገር፣ አገር እንደ ዘበት አይገኝም፤ ሊፈርስ ይችላል። ነገር ግን ደግሞ፣ አገር፣ ሊሻሻል፣ ይበልጥ ሊምር፣ ሊሰለጥን ይችላል። እንደ ግኡዝ የተራራ ቁመትና እንደ ሸለቆ ጥልቀት… ምንም ቢደረግ የማይለወጥና የማይፍረከረክ አይደለም። የማይለወጥና የማይሻሻልም  አይደለም። ይለወጣል - ይፍረከረካል ወይም ይሻሻላል።)
በአንድ በኩል፣ አገርን መጠበቅ ማለት፣ ህግና ስርዓትን ማክበር ማለት፣… አገርን የስልጣኔ አገር ማድረግ ማለት እንጂ፣ አገር እንዳይሰለጥን፣ ህግ እንዳይስተካከል፣ ስርዓት እንዳይሻሻል ቀይዶ መያዝ ማለት አይደለም።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ አገርን መለወጥ ማለት አገርን ማጥፋት ማለት አይደለም።
ማሻሻል ማለት፣ አገርን የስልጣኔ አገር ማድረግ ማለት እንጂ፣ አገርን ማደፍረስና መሸርሸር፤ ማንጠፍጠፍና ማፈራረስ፣ አገርን እንደ ጠላት መቁጠር ማለት አይደለም። አገር ከደፈረሰና ከተፍረከረከ በኋላ፣ በራሱ ጊዜ ተረጋግቶ ጥርት የሚል ኩሬ፣ በራሱ ጊዜ የሚበቅልና የሚያቆጠቁጥ… ባንፈልገው እንኳ ተመልሶ የሚበቅል አረም አይደለም። ህግን ማሳጣትና ስርዓትን ማተራመስ አይደለም፤ ህግን… ትክክለኛ ህግ፣ ስርዓቱን ትክክለኛ ስርዓት ማድረግ ማለት እንጂ።

አገር፣ የጅምላ አዋቂነትን፣ የጅምላ አላማን፣ የጅምላ ማንነትንና ክብርን ስላልሰጠች እንደጠላት?
አገር፣… ለእውቀትና ለእውነት፣ ለመማማር፣ ለተሰሚነት … ለአለማዊ የኑሮ አላማ፣ ለሙያ፣ ለስራ፣ ለምርት፣ ለግብይት፣ ለብልፅግና፣… ለግል ማንነት፣ ሰብዕናና ብቃት፣ ለሕይወት እርካታና ለፍቅር… ምቹ እድል ይሰጣል፣ መሰናክልን ያስወግዳል፣ ነፃነትን ያስገኛል፣ በዚህም ምክንያት እፁብ ድንቅ፣ ብሩክ ቅዱስ አገር ተብሎ እጅጉን ይወደሳል፣ በአእምሮ፣ በአካልና በመንፈስ ይወደዳል፣ በፍቅር ይደነቃል፤…  እንጂ አሪፍ አገር፣… እውቀትንና እውነትን በጅምላ ለአገር ተወላጅ ሁሉ አይግትም። የጅምላ አእምሮ የለም። እውቀትና እውነት የእያንዳንዱ ሰው ሃላፊነት ነው፤ የየራሱ የግል አእምሮ አለውና።
አሪፍ አገር ማለት በጅምላ፣… የኑሮ አላማንና ስኬትን በጅምላ ለአገሬው ሰው ሁሉ አያዘንብም። መልካም የኑሮ አላማን መምረጥና ለስኬትም እንደየሙያው በፅናት ተግቶ መስራት የእያንዳንዱ ሰው የግል ምርጫና ሃላፊነት ነው። የጅምላ አካል፣ የጅምላ እጅና እግር የለም። አሪፍ አገር ማለት፣ “ለአገር ልጅ” በሙሉ በአንዳች ተአምር ያለጥረት ተገንብቶ የተጠናቀቀ ብቃትን፣ ጠንካራ ሰብዕናንና የማንነት ኩራትን በጅምላ አያለብስም። ይሄም፣ የእያንዳንዱ ሰው ሃላፊነት ነው። የጅምላ ብቃትና ማንነት ብሎ ነገር የለም።
በዚህ ምክንያትም… አዋቂነትንና ተሰሚነትን አልሰጠኝም፤ የኑሮ አላማና ብልፅግናን አልሰጠኝም፤ የጅምላ ማንነትን አላስገኘልኝም፤ ክብርን፣ ኩራትን፣ የሕይወት እርካታን አላንበሸበሸኝም በማለት አገርን መጥላትና ማጥላላት፣ ማደፍረስና መሸርሸርስ?… በምትኩም… በሃይማኖትና በቋንቋ፣ በብሄር ብሄረሰብና በትውልድ አካባቢ ተቧድኖ አዋቂነትንና ተሰሚነትን ለማግኘት መሞከር? ጭራሽ… የዚህኛውና የዚያኛው ቡድን ቲፎዞ በመሆን፣… የጅምላ ተቀባይነትና ተሰሚነት፣… በጅምላ የኑሮ አላማና ትርጉም፣… በጅምላ የማንነት ክብር ለማግኘት መሞከር!   
እንዴ? ይሄኮ፣ ወደ ጥንቱ ኋላቀር የጎሳና የዋሻ ኑሮ እንደመመለስ ነው። ወይም ደግሞ፣ እንደ ሰው የተፈጠረ፣ እንስሳ ለመሆን የተመኘ አጉል ፍጡር ለመሆን መሞከር… በሉት።
እንደ ሰው የተፈጠረና፣ ሰው ለመሆን የሚፈልግስ፣ ምን ይሻለዋል። ለዚህ ሁነኛ መፍትሄዎችና መርሆች አሉ - ከጥንት እስከ ዛሬ።
 
አትዋሽ፣ አትስረቅ፣ አትግደል - እውነትን፣ ንብረትን፣ ብቃትን አክብር
ውሸታምና እውነተኛ መሆን፣… ከምር በአስተዋይነት ማንበብ፣ ለይስሙላ እንደነገሩ ማንበብ፣ አለማንበብ፣ እንዳነበበ ሆኖ በጭፍን መደገፍና መቃወም፣… አዋቂ፣ አላዋቂና አደናጋሪ መሆን፣… እነዚህ ሁሉ በጅምላ የሚገኙ ነገሮች አይደሉም።
መልካም የኑሮ አላማ ይዞ በፅናት የሚተጋ፣ አልያም በአላማ ቢስነት እየተንከላወሰ የሚባክን፣ ወይም ለማምታታት፣ ለመስረቅ አልያም ለመዝረፍ እየተቅበዘበዘ የሚደናበር፣… እነዚህ ነገሮች፣ በሁለት ሰዎች አልያም በሁሉት ሚሊዮን ሰዎች ቢፈፀሙ እንኳ፣ ያው፣ ሁለት ሰዎች ወይም የሁለት ሚሊዮን ሰዎች የግል ምርጫዎችና ድርጊቶች እንጂ፣ የጅምላ ልክፍት አይደሉም። የሚዳኙትም እንደየምርጫቸውና ተግባራቸው ነው። “ስራው ያውጣው”፣ “ስራ ከመቃብር በላይ ነው”… ይባል የለ!
በእውቀትና በሙያ፣ በሃሳብና በተግባር የስኬት ብቃትንና ጠንካራ ሰብዕናን እየገነባ በዚህ የግል ማንነቱ የሚኮራ፣ ወይም በአቋራጭ አዋቂና ስኬታማ፣ የሙያና የብቃት ባለቤት በመምሰል… በማስመሰል፣ በሰው ዘንድ ተሰሚነትን፣ ተቀባይነትንና አድናቆትን ለማግኘት በመሟሟት “የግል ማንነትንና ኩራትን” ለማግኘት የሚማስን ሚስኪን፤ አልያም… ሌሎች ሰዎችን በማንቋሸሽ፣ በማጥላላት፣ በጅምላ በመፈረጅና በማዋረድ፤ በዚያው ልክ ማንነትንና ክብርን የሚያገኝ እየመሰለው፣ በዘር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ በቋንቋ፣ በትውልድ ሰፈር፣ በክለብ ቲፎዞነት ሳይቀር ለመቧደን የሚፍጨረጨር እንስሳ መሆን… በጅምላ የሚለጠፉ የማንነት ልገሳ ወይም ፍርጃ አይደሉም። የእያንዳንዱ ሰው የግል ሃላፊነትና የግል ማንነት ናቸው። …የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው ማለት ነው።
ፍትህ ማለትም፣ እያንዳንዱን ሰው፣ የግል ብቃቱን ጨምሮ በግል ባህርይውና በግል አኳሃኑ መመዘን ማለት ነው። “Justice” is the virtue of judging men’s character and conduct objectively and… granting to each man that which he deserves. (Objectivism - The Philosophy of Ayn Rand)።
ታዲያ፣ ለመፍረድ የመቻኮልና ለመጥላት የመቸኮል ጉዳይ አይደለም። የማውገዝ፣ የመወንጀልና የመቅጣት ጉዳይ ብቻ አይደለም። እንዲያውም ከሁሉም በላይ፣ የማድነቅ ጉዳይ ነው - ፍትህ።
አዎ፣ አንዱን በከንቱነቱ ቸል የምንለው፣ አንዱን በክፋቱ የምንፀየፈው፣ በየግል ባህርያቸውና በግል ብልሽታቸው ምክንያት ስለሆነ፣ ፍትሃዊ ነው። ነገር ግን፤ እነዚህ ተቀጥላዎች ናቸው። ዋናው ነገር፣ በላቀ ብቃቱና በሰብዕና ጥንካሬው፣ ጀግናን ከምር የምናደንቅ ሲሆን ነው… ትልቁ የፍትህ ትርጉም፣  በእውን ሕይወት የሚኖረው።
ይሄን ይሄን… አለማስተዋል፣ አለማወቅ፣ መዘንጋት፣ ቸል ማለት…  እልፍ አእላፍ ችግሮችን ያስከትላል። በአገራችን በየእለቱና በየአካባቢው የምናየውም ይህንኑን ነው።
እንዴ! 3ሺ ዓመት፣ 4ሺ ዓመት ወደኋላ መመለስ አለብን እንዴ?
እውነትን ያዝ፣ በእውነት ተመራ ለማለት አይደለም እንዴ፣ “አትዋሽ፣ በሃሰት አትመስክር” የተባለው?
የኑሮ አላማህን በራስህ ጥረት ተግተህ አሳካ፣ የግል ንብረትን አክብር ለማለት አይደለም እንዴ፣… በሌሎች ንብረት ላይ አታሰፍስፍ፣ የሌሎችን “አትመኝ”፤ “አትስረቅ” የተባለው?
ባለንጀራህን እንደራስህ መዝን፣ መልካምን ሰው ውደድ፣ አንዱ የሌላውን ሕይወት አይድፈር ለማለት አይደለም እንዴ፣ “ባለንጀራህን እንደራስህ ውደድ። አትግደል” የተባለው?
አርአያዎችን፣ የበቁ ሰዎችን፣ ቅዱስን አድንቅ፣ አክብር፣ አወድስ፤… አታርክስ፣… ለማለት አይደለም እንዴ፤… ራስህንና ፍቅርን አክብር፣ አታርክስ ለማለት አይደለም እንዴ፣ “አታመንዝር” የተባለው። ሌሎችን አታርክስ - ይህን ሁሉ የሚያስተምሩህን አክብር ለማለት አይደለም እንዴ፣ “ወላጆችህን አክብር” የተባለው? ቅዱስን አክብር የተባለው?
እነዚህ መርሆችኮ፣ ድሮ ጥንት፣… ከአራት ሺህና ከሁለት ሺህ አመታት በፊት በኢትዮጵያና በግብፅ ስልጣኔ፣ በሜሶፖታሚያ በባቢሎን ስልጣኔ… መልክ ይዘው የሰፈሩና እጅጉን የሚከበሩ ቀዳሚ መርሆች ነበሩ።
በዛሬ ዘመን፣ ይህንንም አጥተን፣ እንጠፋፋ እንዴ?

Read 2132 times