Monday, 18 December 2017 13:10

ሃይማኖት እንደ ሕያው ነገር

Written by  ዘርይሁን አሰፋ
Rate this item
(2 votes)


   “--በምዕራቡ ዓለም የግልና የማህበራዊ ችግሮች መፍትሔ የሚፈለግላቸው ዘዴዎች በዋናነት በህዝባዊ ምርጫ፣ በዘመናዊ (ነፃ) የህክምና አገልግሎት፣ በሃቀኛ የፖሊስ ሃይልና በሚዛናዊ የፍትሕ ስርዓት ነው። በኔ ግምት፣ የዘመናዊነት ዋነኛ መገለጫዎች እነዚህ ሲሆኑ ከእነሱ ጋር ግብግብ መግጠም “አጉል መንፈራገጥ…” ይሆናል።--”
       

   የሥነ ሕይወት ትምህርት በጣም ሰፊና ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ዋናው መሠረቱ ግን ዝግመተ-ለውጥ (Evolution) የሚባለው ዘርፍ ነው። ምክያቱም ሕይወት ያላቸው ፍጡራን በሙሉ የዝግመተ-ለውጥ አሻራ ስላላቸውና የህጉም ውጤቶች እንደሆኑ ማሳየት ስለሚቻል ነው። የዝግመተ-ለውጥ ዋናው መርህ፣ ተፈጥሯዊ ምርጫ (natural selection) ሲሆን ይህም ግልፅ የሕይወትና ሞት ምርጫ ጉዳይ ነው። ተፈጥሯዊ ምርጫ የሚፈፀመው ባጭሩ እንደሚከተለው ነው። የሚኖሩበትን አካባቢ የተላመዱ ፍጥረታት በደንብ ካልተላመዱት ፍጥረታት የላቀ የመራባት ስኬት (reproductive success) ይኖራቸዋል (በአንጻራዊ ሁኔታ በቂ ጊዜ፣ በሕይወት የመኖርና ብዙ ዝርያዎችን የማፍራት ዕድል ስላላቸው)።
ይህ ብቻም አይደለም፤ ተፈጥሮና ፍጥረታት ሁሌም በግብግብ ውስጥ ስለሆኑ፣ የአካባቢው ሁኔታ (ለምሳሌ፡- የግብዓቶች መጠንና ዓይነት፣ የአየር ፀባይ…) በተቀየረ ቁጥር፣ ፍጥረታት ያን ሁኔታ የሚለምዱበትን አዲስ ባህርይ (የሰውነት ክፍልም ሊሆን ይችላል) በፍጥነት መፍጠርና ለአዲሱ አካባቢ የማያስፈልጉ (አድካሚ ወይም ጎጂ ሊሆኑ የሚችሉ) ባህርያትም ሆኑ የሰውነት ክፍሎችን በዚያው ፍጥነት ማስወገድ አለባቸው። ይህን ወሳኝ ለውጥ ማድረግ ያልቻሉት ጤነኛ ሕይወትና በቂ ዕድሜ መኖር ስለማይችሉ ዘራቸው እየቀነሰ ሄዶ፣ እስከነ አካቴው ከምድረ ገፅ ሊጠፉ ይችላሉ።
የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ዝግመተ-ልውጥን ለመተንተን ሳይሆን ሃይማኖቶችና የሃይማኖት ተቋማት የሕያዋን ፍጥረታት ባህርይ ያላቸው መሆኑ ከታሪካቸው የሚታይ ስለሚመስለኝና በዚህ እይታ ደግሞ አቶ ብሩህ ዓለምነህ፣ በቅርቡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ያስነበቡን “የሃይማኖትና የዘመናዊነት ግብግብ” ፅሁፍ ትንቢት ቢፈፀም አሸናፊውን ካሁኑ ለማወቅ ሌላ ትንበያ እንደማያስፈልግ ለማሳየት ነው። እንደሚታወቀው ነባር የሚባሉት ሃይማኖቶች (ወደፊት ሊኖሩ የሚችሉትም) ሥነ-ዓለምን በሚያሳምን መልኩ ማስረዳት የቻሉትና በማህበረሰቡ አኗኗር ላይ ተጨባጭ ተፅዕኖ ከማሳደር በተጨማሪ ከአኗኗሩ ጋር ይበልጥ መላመድ የቻሉት ናቸው። የዓለማችን ዋና ዋና ሃይማኖቶች ውስን መልክዓ ምድራዊ ስርጭት የሚያመለክተው ይህንኑ ነው።
ይህ ትክክል ከሆነ፣ አሁን ያሉት ሃይማኖቶች፣ የየራሳቸው የተለያየ “ተፈጥሯዊ ምርጫ”፣ በየራሳቸው ዝግመተ-ለውጥ ሂደት ማምለጥ የቻሉት ናቸው ማለት ነው። በዚሁ መሠረት፣ ሃይማኖቶችና የሃይማኖት ተቋማት፣ በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ዘላቂ ፋይዳ ሊኖራቸው የሚችለውና ሊገታ ከማይችለው አቶ ብሩህ “የሰውን ልጅ ባለሥልጣን የማድረግ” ካሉት ተፈጥሯዊ ጉዞ ጋር አብረው ሊራመዱ የሚችሉት፣ ከዘመናዊነት ጋር ግብግብ በመግጠም ሳይሆን የሥነ መለኮት መሠረታቸውን በማያናጋ መንገድ፣ የተፈጥሯዊ ምርጫ ግፊት እንዳለበት ማንኛውም ሕያው ፍጡር፣ የአስተሳሰብና የአሰራር ማስተካከያ ሲያደርጉ ብቻ ነው።
በምዕራቡ ዓለም እስከ 15ኛው መቶ ክ/ዘ ድረስ የካቶሊክ ቤ/ክ ሲቻል በሰበካ፣ ሳይቻል ሲቀር ደግሞ በአፈና ፈር-ቀዳጅ የሆኑ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦችንና እንቅስቃሴዎችን ከሞላጎደል በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ ነበር። ቀስ በቀስ ግን አፈና ያልገታቸው፣ ለግኝታቸው እንዲሁም ለሰው ልጅ “ከውጫዊ ኃይሎች (ከተፈጥሮና ከሃይማኖት) ነፃ” መውጣት ቀናዒ የሆኑ ተመራማሪዎችና ፈላስፎች ባደረጉት ብርቱ ትግልና በከፈሉት መስዋዕትነት፣ የካቶሊክ ቤ/ክ ቀንበር በማያዳግም ሁኔታ ሊሰበር ችሏል። እነሆ ዛሬ በዓለም ሁሉ ዙርያ ያለን ህዝቦች የድላቸው ፍሬ ተቋዳሽ ሆነናል። ለምዕተ-ዓመታት የምድራዊውንም ሆነ የሰማዩን ቤት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጣሪ የነበረች ቤ/ክ (የትኛውን የፖለቲካ ፓርቲ እጩ መምረጥ እንዳለባቸው አዛዥና የገነት ቦታ አከራይ የነበረች) በህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የነበራት ድርሻ እየመነመነ መጥቶ፣በአሁኑ ጊዜ ከቤተ-መዘክርነት (ሙዚየምነት) ያለፈ አገልግሎቷ በጣም ውስን ሆኗል። እንደየ ሃገሩ ቢለያይም በአማካይ አብዛኛው የምዕራብ አውሮፓ ህዝብ ዛሬ ሲጠየቅ፤ “በሕይወት ዘመኔ ወደ ቤ/ክ የምሄደው ቢበዛ ለሁለት ምክኒያት ነው፥ ለሰርግና ለቀብር” ለማለትም በቅቷል። ይህ ሊሆን የቻለውም የሰውን ልጅ “ከውጫዊ ኃይሎች ነፃ” ለማድረግ የሚደረጉት ጉዞዎች አመርቂ ውጤቶች እያስገኙና ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገሩ ሲሄዱ፣ ቤ/ክ ደግሞ በአንፃሩ በነበረችበት ቆማ ስለቀረችና በአዲሱ ማህበረሰብ ውስጥ ለራሷ አዲስ ሚና መፍጠር ስላልቻለች ነው። በአውሮፓ ውስጥ የካቶሊክ ቤ/ክ የተፈጥሯዊ ምርጫ ግፊት ሰለባ ሆናለች ማለት ነው።
ዛሬ በ21ኛው መቶ ክ/ዘ የህብረተሰቡ ምኞትና ከዓለም ኑሮው የሚጠብቀው ምላሽ በፍጥነት በሚቀያየርበት ሁኔታ የኦርቶዶክስ ቤ/ክንን ጨምሮ ሌሎቹ የአምልኮ ተቋማት፣ አሁን አለን ብለው በሚያምኗቸው ተከታዮች (አማኞች) ቁጥርና ተሰሚነት ልባቸውን ካደነደኑ፣ የካቶሊክ ቤ/ክንን ዕጣ አያመልጡም። በእርግጥ በሃገራችን፣ በአህጉራችንና በሌሎችም ሃገራት (ከሙስሊም ሃገሮች እስከ ሩስያ ድረስ) የሚታየው ሥር የሰደደ የሃይማኖት የበላይነት፣ የሰዎች ሃይማኖታዊ ባህርይና ለሃይማኖት ያላቸው እውነተኛ አክብሮታዊ ፍርሃት ድንቅ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክኒያት የእምነቶቹ (የተቋማቱ) ጥንካሬና እውነተኛ መልስ ሰጪነት ሳይሆን የፖለቲካውና የአስተዳደር ስርዓቱ ውድቀት መሆናቸው መታወቅ አለበት። የሃይማኖት ተቋማቱ ይህን ሳይገነዘቡ ቀርተው እንዳይታለሉ እሰጋለሁ። ምክኒያቱም እነዚህ በአጠቃላይ የዲሞክራሲ ጉድለት፣ የፍትህ መጓደል፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች (የትምህርት፣ የጤና ወዘተ) እና የግል ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ አለመኖር ነጸብራቅ ናቸው። ምድራዊው መንግሥት ሊያቀርብ ያልቻለውን አገልግሎት ከሰማያዊው መንግሥት ለማግኘት የሚደረጉ የተስፋ ጉዞ ናቸው ማለት ይቻላል። ጾም፣ ፀሎት፣ ፀበል፣ ስለት፣ ጥንቆላ፣እርግማን፣ ምርቃት ወዘተ-- የመሳሰሉት የዚሁ አካል ናቸው። በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት ከመንግሥት መገኘት የነበረበትን አገልግሎት በከፊልም ቢሆን ለማሟላት ተስፋ እስከሰጡ ድረስ የተከታይና የተሰሚነት ችግር አይኖርባቸውም።
በምዕራቡ ዓለም የግልና የማህበራዊ ችግሮች መፍትሔ የሚፈለግላቸው ዘዴዎች በዋናነት በህዝባዊ ምርጫ፣ በዘመናዊ (ነፃ) የህክምና አገልግሎት፣ በሃቀኛ የፖሊስ ሃይልና በሚዛናዊ የፍትሕ ስርዓት ነው። በኔ ግምት፣ የዘመናዊነት ዋነኛ መገለጫዎች እነዚህ ሲሆኑ ከእነሱ ጋር ግብግብ መግጠም “አጉል መንፈራገጥ…” ይሆናል። እነዚህ ወሳኝ አገልግሎቶች ይቆያሉ እንጂ እንደ ሁኔታው ለእኛም መሟላታቸው አይቀሬ ስለሆነ የሃይማኖት ተቋማት ሳይዘገዩ ሚናቸውን መለየትና መዘጋጀት አለባቸው። ይህ ትልቅ ፈተና ሲሆን የመሳካቱ ጉዳይ ደግሞ እንደየ እምነቱ መሠረታዊ ባህርይ የሚለያይ ይሆናል። ለምሳሌ ብዙ ተከታይ ካላቸው የሃገራችን እምነቶች መካከል እስልምና በ“የሃይማኖትና የዘመናዊነት ግብግብ” ውስጥ በተወሰነ መልኩ በአሸናፊነት ወይም በጥሩ ተፎካካሪነት ረጅም ጊዜ መቆየት ሲችል፣ የኦርቶዶክስ እምነት ቶሎ ቦታዋን ማግኘት የምትችል ይመስለኛል። የፕሮቴስታንት እምነት በአጀማመሩም ሆነ በእድገቱ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ውጤት ስለሆነ ሊመጡ የሚችሉትን ለውጦች ለማስተናገድ ምንም ችግር አይኖርበትም። እምነቱ በጣም የተለያዩ ባህሎች ባሏቸውና በተለያየ የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ ላይ ባሉ የዓለማችን ህዝቦች ዘንድ በስፋት ተቀባይነት ሊያገኝ የቻለው ከሁኔታዎች ጋር በፍጥነት የመላመድ ባህርይ ስላለው ነው።
እስልምና በተከታዮቹ የግል ሕይወት ውስጥ ጉልህ ተፅዕኖ ስለሚያሳድርና የአምልኮም የምድራዊ ኑሮም ዘይቤ ስለሚመስል፣ ቶሎ ለመቀየርና ከለውጦችና ከሰው ልጆች አዳዲስ ፍላጎቶች ጋር ተመቻችቶ ለመሄድ እንደሚያስችግረው ሃይማኖቱ በበላይነት ከሚመለክባቸው የአረብና የኤስያ ሃገሮች ሁኔታ መገንዘብ ይቻላል።
የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ግን በሃገራችን  በጣም ረጅም ጊዜ ብዙ ለውጦችን አስተናግዳ ያለፈች በመሆንዋ
ሊገታ ከማይቻለው ህብረተሰባዊ ለውጥ ጋር ሚናዋን ለማስተካከል በቂ ተሞክሮ አላት። ቤተክርስቲያኒቱን በሃገራችንም ሆነ እንደ ተቋም በራሷ የመጡትን ተግዳሮቶች ተቋቁማ፣ አሁን ላለችበት ደረጃ መድረስ ብትችልም “ለወደፊትስ?” የሚለው መውጠንጠንና መመለስ ያለበት ጥያቄ ሲሆን ከበቂ በላይ ሊቃውንት ያላት በመሆኑ  ከውጭ የሚመጣ ምክርም ሆነ ጫና ምንም ፋይዳ የለውም።
አንድ ነገር ለማለት ያህል ግን “ዓለም መንደር እየሆነች ነው” በሚል ሰበብ፣ የምዕራባውያን ቴክኖሎጂና የባህላቸው ወረርሽኝ ያመጣው ተፅዕኖ አንድ ወጥ የሆነ (አጉል ልማድና) ባህል በዓለም ሁሉ ላይ እንዲንሰራፋ የሚያደርግ ያላሰለሰ ጥረት ይታያል። ዓለምን “መንደር” የማድረግ ጉዞ (globalization) በበጎ ገፅታው ሲታይ፣ ብዙ ገንቢ ከሆኑ ጥቅሞቹ ውስጥ የህዝቦች መቀራረብና መገናኘት፣ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን መለዋወጡ አንዱ ሲሆን ትክክለኛ መልኩ ካየነው ግን በእጅ-አዙር የቅኝ-አገዛዝ የምዕራባዊያንን ሁለንተናዊ የበላይነት ለማስፈን የሚሞከርበት አደገኛ እንቅስቃሴ ነው። የዚህ እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ፣ ነባር አገር-በቀል ሥልጣኔዎችን በማቀጨጭ፣ በጥራዝ-ነጠቅ ለውጥ፣ ለዘመናት ያቆየናቸውን ወጎችና እሴቶቻችንን መሸርሸርና የህዳሴያችንን መሠረት ወደ አሸዋ መለወጥ ነው። እንቅስቃሴው ግን ሊገታ የማይችልና ችላ ሊባል  የማይገባ የዘመናችን ዕውነታ ነው። ስለሆነም ከሃይማኖት ተቋማት የሚጠበቅ አንዱ ሚና፣ በዚህ በኩል ሊመጡ የሚችሉትን መጥፎና እኩይ ልማዶችን መከላከል ብቻ ሳይሆን ነባር ታሪክ፣ ባህሎችንና የጋራ እሴቶችን በሞግዚትነት (የበላይ ጠባቂነት) መንከባከብ፣ ማበልፀግና ማስፋፋት ይሆናል። እንደ ግል አስተያየት ግን ህብረተሰቡ የለውጡ ማዕበል ሰለባ እንዳይሆን ወቅቱን የጠበቀ የማስጠንቀቂያ ምልክት ሰጪ (watchdog) ለመሆን የተሻለ ተዓማኒነት ያላት የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ናት። አቶ ብሩህ፤ “ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ይሄንን ማድረግ ያለባት ከማንም በላይ ለራሷ ስትል ነው” ባሉት የምስማማው በዚህ መልኩ ነው።
(የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ከላይ የተንጸባረቀው ሃሳብና አመለካከት የጸሃፊውን እንጂ የጋዜጣውን ኤዲቶሪያል የማይወክል መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡)

Read 2253 times