Monday, 18 December 2017 13:08

“ዲፊቢሪሌሽን” - ለሃገራችን ፖለቲካ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “--እውነት እኔ ሌሎችን ለመምራት ተዘጋጅቻለሁ? አቅሙ፣ እውቀቱና ትዕግስቱ አለኝ? በመንገዴ ከእኔ የተሻለ እኔንና ሌሎችን ሊመራ የሚችል ሲገኝ መንገድ የምለቅ ነኝ? ማንንስ ወዴት ለመምራት ነው የተዘጋጀሁት? እንዳሰብኩት ባይገኝ ወይም ቢገኝ ቀጣዩ ሚናዬ ምን ሊሆን ይችላል የሚሉትን እና የመሳሰሉትን ለእራስ መመለስ የግድ ይላል፡፡--”


    አሪቲሚያ ስለሚባለው የልብ የኤሌክትሪክ ስራዎች እክል ሳነብ፣ ሁሌም ወደ አዕምሮዬ ላይ የሚመጣብኝ የአብዛኞቻችን ኑሮ፣ ይበልጥ ደግሞ የአገራችን ሁኔታ ነው፡፡ አብዛኛው ነገር ከዚህ የልብ የአሌክትሪክ ስራዎች እክል ምክንያቶችና መፍትሔዎች ጋር ትልቅ ቁርኝት ያለው ይመስለኛል። እንዲህ ነው ነገሩ፡- ልባችን እንደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻችን ሴል በሚባሉ ህዋሳት የተገነባች ሲሆን እነዚህ የልብ ህዋሳት (ልባችን የተዋቀረባቸው ማለት ነው) አራት ዋና ዋና ባህሪያቶች አሏቸው። አንደኛው ‘አውቶማቲሲቲ’፣ ይህም ያለ ማንም ትዕዛዝና እርዳታ በእራሷ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ሲሆን የሁሉ ተቆጣጣሪ የሚባለው አዕምሯችን (አንጎላችን) እንኳን በቀጥታ ጣልቃ የማይገባበት ነው፡፡ ሁለተኛው ‘ኤክሳይተብሊቲ’፣ ይህም በመነጨው ኤሌክትሪክ ስራ ለመስራት የመነቃቃት አቅምን የሚገልጽ ነው። ሶስተኛው ‘ኮንዳክሽን’፣ ያገኙትን ኤሌክትሪክ ለሌላውም የልብ ክፍል በቅብብሎሽ የማድረስ ወይም በሌላ ቋንቋ ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ አቅም ነው። አራተኛው ወይም  የመጨረሻው፣ በደረሳቸው የኤሌክትሪክ ንዝረት የልብ ጡንጫዎች በመኮማተር ደምን ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የመርጨት አቅም፣ ማለትም ‘ኮንትራክቴቢሊቲ’ ናቸው፡፡ ታዲያ ሁሉም የልብ ህዋሳት (ክፍሎች) እነዚህ አራቱም ባህሪያት አሉን ብለው፣ በየራሳቸው ኤሌክትሪክ ቢያመነጩ ወይም ቢያስተላልፉ በልብ ውስጥ ዝብርቅርቅ ያለ፣ ያልተደራጀና ደምን ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሊረጭ የማያስችል ሁናቴ ውስጥ እንገባለን፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ሞት ጎዳና የሚወስደን ይሆናል፡፡
 ፈጣሪያችን ሲሰራን ታዲያ ለዚህ መፍትሔ አዘጋጅቶ ነው፡፡ ይህም በልባችን ውስጥ ዋነኛ ስራቸው ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሆኑ የጎበዝ አለቆችን ከመረጠ በኋላ ከእነርሱ የመነጨውን ኤሌክትሪክ ወደተለያዩ የልብ ክፍሎች የሚያደርሱ ማስተላለፊያዎችን (ትራንስፎርመር ልንላቸው የምንችል ይመስለኛል) በማዘጋጀት፣ ወጥ የሆነ የኤሌክትሪክ ፍሰት እንዲከናወንና  ደምን በትክክል መርጨት የሚችል የጡንቻ መኮማተር እንዲኖር በማድረግ ነው፡፡ እነዚህ የጎበዝ አለቆች ኤስ ኤ ኖድ፣ ኤቪ ኖድ እና ፑርኪንጅ ፋይበር (ከአራቱ በበላይነት ኤስ ኤ ኖድ ይህን ስራ ይሰራል) በመባል ይጠራሉ። ወደ ገደለው ግባ ሳትሉ እንደማትቀሩ እገምታለሁ። በመቀጠል ለማነሳቸው ሃሳቦች ደጋፊ ስለሆኑ፣ በደንብ ተከተሉኝማ፡፡ እናላችሁ ከላይ እንደገለጽኩት፣ በሞት እስከምንለይ ያለማቋረጥ ኤስ ኤ ኖድ ከሚባለው ኤሌክትሪክ እየመነጨና ወደተለያዩ የልብ ክፍሎች እየተላለፈ፣ የልብን ጡንቻዎች እንዲኮማተሩ በማድረግና ደምን በመርጨት ህይወት ትቀጥላለች። ይህ ተፈጥሯዊው የልብ አሰራር ሲሆን በተቃራኒው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የልብ ኤሌክትሪክ አሰራር እክል ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህም የእዚህ ጽሑፍ አስኳል ነው፡፡ አሁንም ተከተሉኝማ፡፡
የዚህ የልብ የኤሌክትሪክ እክል (ህመም) ቬንትሪኩላር ፊብሪሌሽን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ችግር የሚከሰተው የጎበዝ አለቆች የተባሉት እነ ኤስ ኤ ኖድ፣ በትክክል ኤሌክትሪክ ማመንጨት ሲያቅታቸውና ደምን ወደተለያዩ ክፍሎች የሚረጩት ቬንትሪክል የተባሉት የልብ ጡንጫዎች ላይ ያሉት ህዋሳት ሲያምጹ የሚከሰት ነው፡፡ አመጹ እንደ ሁከት አይነት ነው፡፡ ልክ መሪዎች በትክክል አልመራ ሲሉ በየአካባቢው ሁሉም እየተነሳ መሪ ልሁን እንደሚለው አይነት ነገር! በቃ ሁሉም ህዋሳት ከተለያዩ ቦታዎች ያልተናበበና የጡንቻ መኮማተርን የማይፈጥር፣ ከዚህም ብልጭ ከዚያም ብልጭ የሚል ኤሌክትሪክ የማመንጨት ስራ ይጀምራሉ። ይህም ልብን በጭንቅ የማንቀጥቀጥ፣ የማራድ አይነት ሰቀቀን ይፈጥራል፤ ወይ እነዚህ ሃይል ኖሯቸውና ተናበው ደም እንድትረጭ አልሆነ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አቅሙና ችሎታው ያላቸው የጎበዝ አለቆች ካንቀላፉበት ተነስተው ልብን ወደተሻለ እንቅስቃሴ አልመሯት፡፡ አቤት በዚህ ጊዜ ያለው የልብ ጭንቀት! ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ በሉት። በነገራችን ላይ ይህ አይነቱ ችግር በድንገተኛ ህክምና ዘርፍ ለአፍታ ጊዜ ከማይሰጣቸው ገዳይ ህመሞች መካከል ዋንኛው ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ነው ሁነኛ የህክምና ባለሙያና የህክምና መሳሪያ የሚያስፈልገው፡፡ እነዚህን ከተለያዩ ስፍራዎች የሚነሱትን ወጀቦች ጸጥ የሚያደርግና ወደቀደመው መልካሙ የመርከቧ (የልባችን) እንቅስቃሴ እንዲመለስ የሚያደርግ መላ! ይህ መላ በህክምና አጠራሩ ዲፊቢሪሌሽን ሲባል፣ ለዚህ የሚረዳን የህክምና መሳሪያ ደግሞ ዲፊቢሪሌተር ይባላል፡፡ ስራው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? በቃ ከተለያዩ የልብ ክፍሎች እዚህም እዚያም እየመነጨ ዘራፍ የሚለውን ኤሌክትሪክ ቀጥ በማድረግ፣ ለጎበዝ አለቆች (ዋንኛ ኤሌክትሪክ አመንጪዎች) እድል መስጠት ሲሆን በዚህም መሪና ተመሪን እንዲደማመጡ በማድረግ፣ ሁሉንም በሚጠቅምና በሚያኖረው የኤሌክትሪክ ፍሰት ተዋረድ ልብን መታደግ ነው፡፡
ታዲያ ልባችንን በአገር ብንመስለው፣ ሃገር የተዋቀረበትን ህዝብ፣ የልብ ህዋስ (ሴል) ብንለው፣ የጎበዝ አለቆች የአገር መሪዎች ቢሆኑ፣ ምሳሌው አሁን ያለንበትን የፖለቲካ ሁኔታ አያሳይ ይሆን?
ተመልከቱ እስቲ! ህዝባችን በትክክል የሚመሩት የሀገር መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የመስሪያ ቤት ሃላፊዎችና የመሳሰሉትን አጥቶ፣ ታግሶ ታግሶ! ጠብቆ ጠብቆ! ቀምበር ሲበዛበት መፍትሔ ይሰጡኛል በሚላቸው የተለያዩ ሃሳቦችና ቡድኖች፣ ከዚህም ከዚያም የመሰለውን እንቅስቃሴ እያደረገ ያለ አይመስላችሁም፡፡ በዚህም መነሾነት ምንም እንኳን እንቅስቃሴው ብሶት የወለደው ቢሆንም በእራሱ ሌላ ችግር እየፈጠረ፣ ፍሬ ያላፈራና አለመደማመጥን እየፈጠረ ያለ እንደሆነ አይሰማችሁም? እንደው በዚህች አጭር ጊዜ እንኳን ስንቱ በተለያየ ቦታ ደሙ ፈሰሰ፣ አካሉን አጣ፣ ተሰደደ፣ እንቅልፉን አጣ፣ ስንቱ ከፈጣሪው ኮበለለ፣ ስንቱ ሃይማኖት ጭራሽ አያስፈልገኝም አለ፣ ስንቱ ንብረቱን በከንቱ አጣ፣ ሃሞቱ ፈሰሰ፣ አረ ስንቱ ስንቱ…
ከወዲህ ገዢው መንግስት ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ሲያቅተው፤ ወዲህ መምራት እንችላለንም ከሚሉት ተቃዋሚዎች ጠብ የሚል ነገር ሲጠፋ፤ በሌላ በኩል ጦማሪዎች (አክቲቪስት) ሃገሪቱን ከወዲህ ወዲያ ከማንቀጥቀጥ በዘለለ ለውጥ ማምጣት ሳይችሉ ሲቀር፤ ከወዲህም አቅሙ እያላቸው “ጎመን በጤና” ብለው እያንቀላፉ ባሉት ሰዎች ሁሉ ድምር፣ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና---- እቺ ሃገር ወደ መቃብሯ እየሄደች ያለ አይመስልም? አረ ዲፊብሪሌተር ወዴት አለህ? ወጀቡን ጸጥ አስደርገህ፣ አቅሙ ላለው በትሩን የምትሰጥ ወዴት አለህ?!!
እስቲ በህዝብ ወገን ሆነን እራሳችንን እንመልከት፡፡ እያንዳንዳችንስ በሚገባን ሚናችንን እየተወጣን ነው? በትክክል የተመሪነት ሃላፊነታችንስ  ስራ እንደሚጠይቅ ተረድተናል? በሃገራችን ጉዳይ እውነት ነው በእኩል ሁላችንም ያገባናል፡፡ ነገር ግን በተሰማራንበት የስራ ዘርፍና ሚና፣ ይህን ያገባኛል ስሜት ካልተወጣነው ምን ዋጋ ይኖረዋል! በትክክል ተመሪ ሆኖ ያላለፈ ሰውስ እንዴት ወደፊት መሪ ሊሆን ይችላል? እስቲ የመሪነት እድሉን ይስጡኝ እና በተፈተንኩ የምንል ብዙ አለን፡፡ በተቃራኒው ግን አሁን እየሰራን ባለነው ስራ ላይ እንኳን ጉድለታችን ብዙ ነው፡፡ የመሪው ወንበር እኮ አይደለም ስራ የሚሰራው፤ እኛ ነን ፈላጭ ቆራጩ! የሃገራችን የአዙሪት የኋልዮሽ ጉዞ ምክንያትም ይህ ተመሳሳይ ስህተትንና አስተሳሰብን ሁሌ በተለያየ ቀለም እየቀቡ መኖሩ ላይ ይመስለኛል። እስቲ አኗኗራችንን፣ አሰራራችንንና አካሄዳችንን እንመልከት! በጣም ቅጥ ያጣ ዲፊብሪሌሽን (አስቁሞ እንደ አዲስ ስራ ማስጀመር) የሚያስፈልገው እየሆነ እኮ ነው፡፡ ሁላችንም እራሳችንን በመሪነት ስፍራ ብቻ ካስቀመጥን ሁሉስ መሪ፣ ሃላፊና አዛዥ ከሆነ፣ ሌላውን የተመሪነት ስራ ማን ይስራው? የተሻለ መሪ ናፍቆን የተሻለ ተመሪ ካልሆንን ለውጥስ እንዴት ሊመጣ ይችላል? የተሻለ የመስሪያ ቤት ኃላፊ ፈልገን፣ የተሻለ ለለውጥ የተዘጋጀ ታታሪ ሰራተኛ ካልሆንን ምን ዋጋ አለው? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ ልክ እንደዛች የታመመች ልብ በተለያዩ ስፍራዎች፣ አስተሳሰቦችና ርዕዮተ አለሞች ተቧድነን፣ ሁላችንም ሃገሪቱን እንምራት እያልን እኮ ነው! ዘንድሮ ያልተገኘ እድል መቼም አይገኝም በሚመስል አስተሳሰብ፣ ሃገሪቱና አለማችን ነገ የማይገኙ እስኪመስል ድረስ መንገብገብ፣ ለወለድናቸው ቀጣዩ ትውልድ አለማሰብም ጭምር ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ የሃገርን ፊብሪሌሽን (መንቀጥቀጥ) ከመፍጠር የዘለለ ምንም ውጤት አያስገኝልንም፡፡ አንዳንዴም እኮ አቅሙ ላላቸውና ሁላችንንም ሊያኖሩን ለሚችሉ አለቆች፣ እድል የመስጠትና የመመራት ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ እሺ ይሁን ግን እንዴት? ካልን፣ መጀመሪያ ሁላችንም አቅማችንን መፈተሽ ይኖርብናል ነው መልሱ፡፡ እውነት እኔ ሌሎችን ለመምራት ተዘጋጅቻለሁ? አቅሙ፣ እውቀቱና ትዕግስቱ አለኝ? በመንገዴ ከእኔ የተሻለ እኔንና ሌሎችን ሊመራ የሚችል ሌላ ሲኖር መንገድ የምለቅ ነኝ? ማንንስ ወዴት ለመመራት ነው የተዘጋጀሁት? እንዳሰብኩት ባይገኝ ወይም ቢገኝ ቀጣዩ ሚናዬ ምን ሊሆን ይችላል የሚሉትን እና የመሳሰሉትን ለእራስ መመለስ የግድ ይላል፡፡ ያለበለዚያ ግን ጊዜው ስለፈቀደልን ብቻ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ድረ-ገጾች አልያም እጃችን ላይ ባለው መሳሪያና አሰራር ብቻ ተማምነን፣ ሃገሪቱን ወደተሻለና ሰላማዊ ወደሆነው ጉዞ በማይወስዳት ጽንፍ ውስጥ መግባት፣ ሃገርን ከማንቀጥቀጥና ከመግደል ውጪ ምንም ውጤት የለውም፡፡
የሃገራችን መሪዎች (ኤስ ኤ ኖድን የመሰላችሁ) ሃላፊነታችሁ ከባድ መሆኑን በትክክል ተረድታችሁት ይሆን? በታሪክ ይህን የመምራት እድል አግኝታችኋል፤ ይህም ማለት በሰውነታችን በየደቂቃው ደምን (ለህዝባችን መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች) አንጋጠው ከልብ እንደሚጠብቁ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ጠባቂያችሁ ብዙ ነው ማለት አይደል፡፡ በትክክል ወቅቱና ጊዜውን የጠበቀ ኤሌክትሪክ (ተፈጻሚ ህግና አሰራር ልንለው እንችላለን) ከእናንተ መመንጨት ካልቻለ፣ ከህዝቡም ተሽላችሁ አገርን ፈር ማስያዝ ካልቻላችሁ፣ የልብ (የሃገር) መንቀጥቀጥና ሞት ተከሰተ ማለት አይደል። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ ልብ ሞታ ደግሞ ማንም አይተርፍም አያተርፍም! ወላ የጎበዝ አለቆች (ኤስ ኤ ኖድና የመሳሰሉት) ሆነ ሌሎች የልባችን ክፍሎች (ህዝባችን) ማንም አይተርፍም፡፡ አሁን የምናየውን አይነት የልብ (የሃገር) መንቀጥቀጥ ሲያጋጥም፣ እራስን እንደ ዲፊብሪሌተር ቆጥሮ፣ ወጀቡን ለማቆም፣ ቆም ብሎ በትክክል ማሰብ አልያም ከታች እንደምገልጸው ሚናቸው የዲፊብሪሌተር ለሆኑ አካላት እድል መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን መንቀጥቀጡ አደገኛ ነውና፣ እንደ ጎርፍ ጠራርጎ ይዞን እንዳይሄድ!
በሃገራችን የዲፊብሪሌተር ስራ የሚሰሩ ብዙ ተቋማትና ስርዓቶች ነበሩን፡፡ በተለይ የሃይማኖት ተቋማቶቻችንና የሽምግልና ባህላችን በአበይትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እንደዚህ አይነት መራር ግርግር ሲያጋጥም፣ በእግዚአብሔር/በአላህ ይዤሃለሁ የሚሉና ወጀቡን ጸጥ የሚያስደርጉ፤ በሌላም ወገን ገና ከወንበራቸው ብድግ ሲሉ ሃገር የሚርድላቸው የሃገር ዋርካ የሆኑ ብዙ ሽማግሌዎችም ነበሩን፡፡ ጎበዝ መሪም ተመሪም መሆን ተቸገርን እኮ! የሃገሬ ዋርካዎች የሆናችሁ ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች- የእኛ ዲፊብሪሌተሮች አረ ወዴት ናችሁ? እኛ እናንተን ማየት አቆምን ወይስ እናንተ ከፊታችን ጠፋችሁ? መልሱ ከሁላችንም የአዕምሮ ጓዳ ውስጥ የሚገኝ ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻ በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ በአንዱ ክፍል የተጻፈውን  ታሪክን ለጽሁፌ መቋጫነት ልጠቀም፡፡ እንዲህ ይላል፡-
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሃዋርያቱ ጋር በታንኳ ሲሄድ አንቀላፋ፣ ማዕበልም ተነሳና መርከቢቱን በጣም አናወጣት፡፡ ሃዋርያቱም አብዝተው በወቅቱ አንቀላፍቶ ወደነበረው ክርስቶስ እየጮሁ፣”ልንጠፋ ነው” ብለው ቀሰቀሱት፡፡ እርሱም ወዲያው ተነስቶ ማዕበሉን ገሰጸው፤ መርከቢቱም ወደቀደመ ሰላሟ ተመለሰች፡፡
ታዲያ በየእምነታችን ከልብ ፈጣሪያችንን ብንለምን፣ እኛም  በሚገባን ሃላፊነታችንን ብንወጣ መርከቢቱ ሃገራችንን የሚታደግ ዲፊብሪሌተር እናጣ ይሆን? ፈጣሪያችን በቸርነቱ ይርዳን!!

Read 1813 times