Monday, 18 December 2017 13:04

ኩራት፣ ኩራት አይልሽም ወይ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)


   “ስሙኝማ…‘አሪፍ’ አይነት ‘ኩራት’ የማን መሰላችሁ… አሜሪካ ልጆቻቸው ዘንድ የሆነች ሦስትም፣ ስድስትም ወር ደረስ ብለው የመሚጡ አንዳንድ እናቶች፡፡ ለምን አይኮሩ! አሜሪካን ሄደው ‘ያልኮሩ’ የት ሄደው ‘ሊኮሩ’ ነው! እናላችሁ…ዋጋው ሁሉ በ‘ናይንቲ ናይን ሴንትስ’ የሚያልቅባት ሀገርን አየር ተናፍሰው ሲመጡ ‘የዚህ አገር አየር’ ሁሉ ‘ይከብዳቸዋል’፡፡…”
       
   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ወይ ቅዝቃዜ!…ወይ ውርጭ! ወይ ብርድ!…በቃ ምንም ነገር በትንሹም አንኳን ላይመቸን ነው! አሁን በዚህ ወራት ከጥቅምት የባሰ ውርጭ ምን የሚሉት ነው…ነገር ፍለጋ ካልሆነ! የምር ግን…አለ አይደል… ደከም ብላችሁ ስትታዩ፣ “ለእሱ ጥፊ ይበቃዋል፣” የምትባሉ አይነት ነገር ስትሆኑ ሁሌም  ነገር ፈላጊው ብዙ ነው…ምናልባትም ተፈጥሮንም  ጨምሮ፣ ሰበብ ፈላጊዎች ስለሆንን… ‘ሰበብ ልፈልግ’ ብዬ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ  ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እዚህ የቱርክ ፊልሞች የሚያሳየው ቻነል ላይ አንድ ፊልም አለ…ጉልሰረን ነው እንደዛ የሚመስል ስም ያላት ገጸ ባህሪይ ያለችበት፡፡ የእሷን ሴትዮ አይነት ‘ኩራት’…አለ አይደል…ምን ያህላችን አለን! ምንም የሌላት ልትባል ትንሽ የሚቀራት፣ ድሀ ብትሆንም ድህነቷ ከሰው በታች እንዳያደርጋት ከአንገቷ ቀና ለማለት እየሞከረች ነው…ቢያንስ እስካሁን ድረስ፡፡
ለመሆኑ ድሀ መሆናችን፣ የሆነ ነገር በእኛ አቅም ማግኘት አለመቻላችን፣ የሆነ ነገር መሻታችን ምን ያህል ጊዜ ኩራት ምናምን የምንለውን ነገር እንደሚያስረሳን ልብ ብላችሁልኛል!
ስሙኝማ… ዘንድሮ ‘ኩራት’ማ አለ… ይሄ “እኔ ዙፋን ላይ ነኝ፣ ሌላው አቧራ እየቃመ ነው፣” የሚል አይነት ኩራት፡፡ “ጫማዬን ለመጥረግ እንኳን ይበዛብሀል የምንለው አይነት ‘ኩራት’፡፡ ሌላውን አሳንሶ ራስን ከፍ የማድረግ ‘ኩራት፡፡’
ኩራት፣ ኩራት አይልሽም ወይ፣ ኩራት አይልሽም ወይ የሙሽራው አይደለሽም ወይ፣ ኩራት አይልሽም ወይ የሚሏት ዘፈን አለች፡፡ በባሏ ብትኮራ ምንም የለበትም፡፡ ግን ‘ኩራቱ’… አለ አይደል… “ከባልሽ ባሌ ይበልጣል” አይነት ሲሆን አሪፍ አይደለም፡፡
በቅርብ ወራት የሆነ ነው፡፡ ዘመዳሞች ናቸው… በሠላሳዎቹ መጀመሪያ የሚገኙ፡፡ እናላችሁ… ሲዝናኑም፣ ምን ሲሉም አይለያዩም። ምንም አይነት ትልቅም ይሁን ትንሽ ምስጢር አይደባበቁም። (በዚህ ዘመን እንዲህ ‘ምንም አይነት ምስጢር የማያደባብቅ’ ወዳጅነት መኖሩ ተስፋ የሚሰጥ ነው።) ታዲያላችሁ …ስንት ዓመት የዘለቀው ዝምድናና ወዳጅነት እንደ ሰሞኑ አይነት ውርጭ ይመታዋል፡፡
በድንገት አንደኛው መራቅ ይጀምራል፡፡ ስልክ አይደውልም፣ ሲደወልለት አይመልስም፣ ለጽሁፍ መልእክት ምላሽ አይሰጥም፡፡ ዘመድዬው ግራ ገብቶት፣ ቤተሰቦቹ መኖሪያ ይሄዳል፡፡ በራሱ ተከራይቶ እንደወጣ ይነግሩታል፣ የሄደበትን ቦታ ግን ገና ‘ወደፊት አሳያችኋለሁ’ ነው ያላቸው፡፡
ትንሽ ቆይቶም ስለ ዘመዱ ‘ኩራት’ ከሌሎች መስማት ይጀምራል፡፡ “ሰው እንኳን ለመጨበጥ እየተጠየፈ ነው” ምናምን አይነት ስሞታዎችን ይሰማል፡፡
ታዲያላችሁ… አንድ ቀን ድንገት እንደጠፋው ድንገት ፊቱ ድቅን አለ፡፡ በአንዱ የከተማችን የሸለለ አካባቢ ሞል ምናምን በሚሉት ነገር በር በኩል ሲያልፍ፣ አንዲት አሪፍ ልጅ ይዞ ከህንጻው ሲወጣ ይገናኛሉ፡፡ መቼም ስንት ዓመት የከረመ ወዳጅነት፣ ያውም በዘመዳሞች መሀል፣ እንዲህ በቀላሉ ስለማይጠፋ ፈገግ ብሎ ይጠጋዋል…እንደለመዱት አንገታቸው ሊቀጭ እስኪደርስ እንዲተቃቀፉ። ፊቱን ቅጭም አድርጎ እጁን ይዘረጋለታል፡፡ ይህኛው በድንጋጤ እጁን ይጨብጠዋል፡፡ ለነገሩ ያቀረበለት ከእጁ ሦስት ጣቶቹን ብቻ ነበር!
“ደህና ነህ? ሥራ ደህና ነው?” ምናምን ብሎት መንገዱን ቀጠለ፡፡
ነገርዬውማ… ሁለቱም ቢሆኑ እንደ አብዛኛው ቀጭን አበሻ ‘ዝቅተኛ ገቢ’ ይባል፣ ‘የዝቅተኛ ዝቅተኛ ገቢ’ ይባል ገና ስም ባልወጣለት የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ይህን ያህል በየሞሉ ገበያ የሚያስወጣ አቅም እንኳን እነሱ ሊኖራቸው፣ ቤተሰቦቻቸውም የጋራ ህብረት ቢፈጥሩ አይኖራቸውም፡፡ ለካስ ‘ምስጢሩ’… በምን ይሁን በምን ሳይታወቅ አጅሬው የሆነ የረብጣ ተራራ ተዘርግፎለታል፡፡ እንዲህ መሽቶ ሲነጋ ሀብት በሀብት የሆነበት ‘ተአምር’ እንቆቅልሽ ነው፡፡ (ለነገሩ እንዲህ አይነት ታሪኮች ዘንድሮ መአት ናቸው፡፡) ለካስ ‘ኩራት’ የመጣው ፍራንኩ ሲመጣ ነው!
የምር እኮ…እንዲህ አይነት ሰዎች ግርም አይሏችሁም! ገንዘብም ሆነ፣ ስልጣንም ሆን ምንም ሆነ አሪፍ ነገር ማግኘታቸው ጥሩ ነው፡፡ ግን ገንዘብ ማግኘት ማለት እኮ በሰውነት ከሌላው ‘መጥቆ’ መሄድ ማለት አይደለም፡፡ ስልጣንም ማግኘት ማለት፣ በተለይ እንደኛ አይነት ሀገር ወንበር ‘ፍሪ ፎር ኦል፣’ በሚመስልበት ምንም ማለት አይደለም። የሆነ የ‘ልዩ ሰውነት’ ሰርተፊኬት ማለት አይደለም። በምንም ነገር መሻልን የማያሳይ ነው፡፡ እናማ… ሦስት ጣት ሰጥቶ ጭበጣ ምን አመጣው፡፡ ግንባርን የሰሞኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ማስመሰልን ምን አመጣው!
በነገራችን ላይ፣ የእግረኛ መንገድ ነገር ከተነሳ…  ግራ የገባን ነገር አለ፡፡ ይሄ በደህና ሁኔታ ላይ ያለውን በአስፋልት  የተነጠፈ የእግረኞች (የእግረኞችና ‘የጉልበተኞች መኪኖች) መተላለፊያ እንዲህ የሚቆፍሩት በምን ሊተካ ነው? ማለቴ… መቼም የታሰበው ከአስፋልቱ በጣም የተሻለ ነገር መሆን አለበት፡፡ ጠቅላላ በእብነበረድ ሊሠሩልን ነው እንዴ! ቂ..ቂ…ቂ… ይሁን ብቻ፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ እኛ ባያምርብን ከተማችን እንኳን ይመርባት!
ስሙኝማ…‘አሪፍ’ አይነት ‘ኩራት’ የማን መሰላችሁ… አሜሪካ ልጆቻቸው ዘንድ የሆነች ሦስትም፣  ስድስትም ወር ደረስ  ብለው የመሚጡ አንዳንድ እናቶች፡፡ ለምን አይኮሩ! አሜሪካን ሄደው ‘ያልኮሩ’ የት ሄደው ‘ሊኮሩ’ ነው! እናላችሁ…ዋጋው ሁሉ በ‘ናይንቲ ናይን ሴንትስ’ የሚያልቅባት ሀገርን አየር ተናፍሰው ሲመጡ ‘የዚህ አገር አየር’ ሁሉ ‘ይከብዳቸዋል’፡፡ ሰላምታቸው ሁሉ በውሀ ልክ ወይም በሆነ ‘ፍጥነት መለኪያ’ እየተመጠነ የሚሰጥ አይነት ይሆናል፡፡
“በቃ፣ ይሄ ህዝብ ዘላለሙን ላይሻሻል ነው!” አይነት አረፍተ ነገሮች የተለመዱ ይሆናሉ፡፡
እናማ ድሮ የነበረችው “ኬሬዳሽ” የምትባል እንግሊዝኛ በምን ትለወጣለች መሰላችሁ…“ኋሳፕ!”
አማርኛዎቹም ይለወጣሉ፡፡ ልክ ነዋ…ለምሳሌ “አበስኩ ገበርኩ” ትለወጥና ‘ኦ ማይ ጋድ!’ ትሆናለች፡  
ደግሞላችሁ… ጦም የሚያውል የ‘ኩራት’ አይነት አለላችሁ፡፡ አሪፍ ምግብ ይቀርባል…አለ  አይደል… “ምራቅ የሚያስውጥ” የሚሉት አይነት። እናላችሁ… ጎረስ፣ ጎረስ ማድረግ እንጀምራለን፡፡ ጋባዣችን ደግሞ ፊት ለፊት ተቀምጠው ይህንንም፣ ያንንም ወሬ ያወራሉ፡፡ “ጎበዝ ተበላህ ማለት ነው!” እንልና ወደ ሰባተኛ ጉርሻችን ላይ እናቆማለን፡፡
“ብላ እንጂ…”
“በቃኝ፣ በላሁ…”
“እንዴ! አሁን ይሄ በላህ ይባላል! ገና ሦስቴ እንኳን ሳትጎርስ!..ምነው፣ ወጡ አልጣፈጠህም እንዴ!”
“ኸረ ጥሩ ነው፣ ስለበቃኝ ነው…”  ሆዳችን እኮ ድምጽ ቢኖረው “ኸረ ውሸቱን ነው፣ ገና ባዶ ነኝ እኮ!” ምናምን ይል ነበር፡፡ እሱ ደግሞ “በደንብ በልቼ በኋላ ሳህኑን ሊሰብረው ነበር ብለው ያስወሩብኝ!” ይላል፡፡
ወሬ ከተፈለገ እኮ ባለመብላቱም ይወራለታል፡፡
“ምን! ያን የመሰለ ምግብ በደንብ ሳይበላ ተወው ነው የምትዪኝ?”
“አምስቴ እንኳን አልጎረሰም ስልሽ!”
“ለነገሩ እንደዛ አይነት ምግብ ቀምሶ ስለማያውቅ አዲስ ሆኖበት ነው፡፡ ይሄኔ እኮ በህልሙ እየመጣበት ይሆናል፡፡”
እናማ ወሬ ከተፈለገ የተለየ ‘ስምምነት የተደረገበት አጄንዳ’ ምናምን ነገር ስለማያስፈልግ በአጉል ‘ኩራት’ ጦም ማደር አግባብ አይደለም፡፡  
በነገራችን ላይ…የህልም ነገር ካነሳን አሁን፣ አሁን ምነው “ህልም አየሁ ፍታልኝ/ፍቺልኝ፣” የሚል ሰው ቀነሰ! ህልም ማየት ላይም ቫት ምናምን አለበት እንዴ!…ወይስ ራሱ  የየእለት ኑሯችን የቀን ቅዠት ነገር ሆነብን!
“ህልሜን ነግሬው ደግሞ ፌስቡክ ላይ ይበትነው! በትዊተር ለቆት ትረምፕ ቢያዩትስ!” ቂ…ቂ…ቂ…  
 “በርበሬ ስወቅጥ አየሁ…”
“ውይ፣ በቃ መንገብገብሽ ነው…” ልክ ነዋ…ካልጠፋ የእህል ዘር በርበሬ ህልም ውስጥ ምን ያደርጋል! ስሙኝማ…ለጥቆማ ያህል “በህልሜ ቆጭቆጫ በሳህን ሞልተው ሲሰጡኝ አየሁ” የሚል ሰው መሄድ ያለበት ህልም ፈቺ ዘንድ ሳይሆን የአእምሮ ሀኪም ዘንድ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3648 times