Print this page
Monday, 18 December 2017 13:02

እየፈረሱ መታደስ፣ እየታደሱ መፍረስ -- እስከ መቼ ድረስ?

Written by  ታምራት መርጊያ utdtaman@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

   በቅርቡ የገዢው ፓርቲ የኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቐለ፣ 35 ቀናትን የፈጀ ድርጅታዊ ግምገማ አካሒዶ ማጠናቀቁን ድርጅቱ ባወጣው የአቋም መግለጫ አስታውቋል፡፡ ህወሓት እራሱን የገመገመው ባለ 59 ገፅ፣ የድርጅቱን ቁመና ደካማ ጎን የሚያትት ሰነድ መሰረት አድርጎ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡
ድርጅቱ ባወጣው ድህረ ግምገማ የአቋም መግለጫው እንዳመለከተው፤ “አመራሩ የሐሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፤ ፀረ ዲሞክራቲክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፤ በተልዕኮው ዙሪያ በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር የማይሰጥ፤ ህዝብና ዓላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርና ጥቅም የሚያስቀድም፤ ለህዝብ ያለው ወገንተኝነት እየተሸረሸረ፣ ከኣገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደ ተገልጋይ የሚቆጥር፤ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ የህዝብ ዙሪያ መለስ እንቅስቃሴ ከመጠመድ ይልቅ በተደማሪ ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርቶች ራሱን መሸለም የሚቃጣው፤ በአጠቃላይ ራሱን ወደ ጥገኛ ገዢ መደብ የመሸጋገር አዝማሚያ የተጠናወተው፤ ወዘተ...”
የሚሉ የሰሉ ግምገማዎችን ማካሔዱንም አስታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ባካሔደው የሒስና ግለ ሒስ ክንውኖች መሰረት፣ የእርምት እርምጃ በመውሰድ፣ የአመራር ሽግሽግ አካሒዶ፣ ድርጅታዊ ግምገማውን ማጠናቀቁን በአቋም መግለጫው ጠቁሟል፡፡ ይኽ ግምገማ፥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሲደረጉ  ከነበሩት የይስሙላ ግምገማዎች በዐይነቱና በመልኩ የተለየ፤ ድርጅቱ ያሉበትን ችግሮች በሚገባ ለመለየት ያስቻሉ መተጋገሎች የተካሔደበት እንደነበርም ድርጅቱ በመግለጫው አትቷል፡፡
በስራ ላይ ያሉ ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎችን በተመለከተም ድርጅቱ ሲገልፅ፦
“በገጠርና በከተማ የቀረፅናቸው ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎች ትክክለኝነት ላይ የሚያጠራጥር ነገር ባይኖርም፥ ኣፈፃፀማችን የደረሰበት ደረጃ ባቀድነው ልክ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ፣ በሕዝባችን ዘንድ ምክንያታዊ ጥርጣሬ እንዲዳብር ማድረጉም በትክክል ለይቷል”፡፡ የሚልም ይገኝበታል።
A Global Initiative for Political Reforms የተባለ ዓለማቀፍ ተቋም እንዳስቀመጠው፤ የፖለቲካ ተሐድሶ ማለት፦ የአንድን ሐገር ሕገ መንግሥት ጨምሮ  በስራ ላይ ያሉ ሕጎችን በሕዝቦች ፍላጎት መሰረት ማሻሻል  (improving the laws and constitutions in accordance with expectations of the public) መሆኑን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይኸው ተቋም አክሎ እንዳስቀመጠው፤ የሕዝቦች ፍላጎት (public expectations) ሲባል፥ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ (Requirements of all the segments of the society) ማለት እንደሆነም ያመለክታል፡፡ እንግዲህ የህወሓትን ግምገማ ከዚህ አንፃር ከተመለከትነው፥ ድርጅቱ የቀረፃቸውና አሁን በሀገሪቱ በስራ ላይ ያሉ ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎች ትክክለኛ ናቸው ብሎ ስለሚያምን፥ በዚህ ረገድ የሚደረጉ ማሻሻያዎች እንደማይኖሩ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው ማለት ነው፡፡
እንደሚታወቀው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ማለትም፦
በፖለቲካው መስክ (The political sphere)
በህዝብ አገልግሎት (The Civil service) እና
በምጣኔ ሐብት  (The Economic Sphere)
ዙሪያ መሰረታዊ ለውጦችና ማሻሻያዎች (Reform) ለማምጣት አቅዶና ቃል ገብቶ፣ አነሰም በዛ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወቃል። Sida የተባለ ተቋም፣ በማርች 2003  ኢትዮጵያን አስመልክቶ  ባስጠናው ጥናት ላይ እንደተገለፀው፥ እነኚህ የታቀዱ ለውጦችና ማሻሻያዎች (Reforms) አመርቂ በሆነ መንገድ መካሔዳቸው ላይ ግን ከፍተኛና አግባብነት ያለዉ  ሕዝባዊ ጥርጣሬ የፈጠረ ጉዳይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ለነኚህ የለውጥና የማሻሻያ እቅዶች በበቂ መልኩና ሕዝባዊ እርካታን ባረጋገጠ መንገድ አለመከናወንና አለመሳካት በስራ ላይ ያሉ ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎች ምቹ ከባቢ (enabling Environment) ካልፈጠሩ  ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ማነቆዎች ውስጥ በተለያዩ ወገኖች የሚጠቀሱና የሚነሱ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በ35 ቀናት ድርጅታዊ ስብሰባው፣ እነኚህን ጉዳዮች በጥልቀት ያለመመልከቱ ከግምገማው መሀከል አንዳች ጎደሎ እንደነበር አመላካች ነው፡፡
ምናልባት በቅርቡ ይካሔዳል ተብሎ በሚጠበቀውና ህወሓትን ጨምሮ ሌሎች የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በሚሣተፋበት የግንባሩ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ እነኚህ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቷቸው ይታዩ ይሆን? አብረን የምንመለከተው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ባጠቃላይ ህወሓትም ይሁን ሌሎቹ የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ በየወቅቱ ችግሮች ባጋጠሙ ቁጥር እንዲሁ አፀፋዊ ግምገማና ተሐድሶ፤ ከዚያም ሲያልፍ ጥልቅ ተሐድሶ ማካሔድ እንደሚቀናቸውና እንደ አይነተኛ መፍትሔ እንደሚወስዱ ያለፈውን ተሞክሮአቸዉን መመልከት በቂ  ይሆናል፡፡ ለዚህም ድርጅቱ (ኢህአዴግ) እራሱን ለማደስና እራሱን ለመገምገም የሚያስችለው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ድርጅታዊ ባህል እንዳለው  በተደጋጋሚ ምክንያት ይሰጥበታል፡፡
በርግጥ  ይኽ ባህል በራሱ በበጎ ጎኑ ሊታይ የሚገባው ተሞክሮ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄ የሚያስነሳው ጉዳይ በድርጅቱ የሚከናወኑት እነዚህ ግምገማዎችና ተሐድሶዎች ምን ያህል ሐቀኛና እራስን ለማሻሻል የሚያስችሉ ናቸው የሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ድርጅቱ የሚያካሂዳቸው ግምገማዎችም ይሁኑ ተሐድሶዎች እምርታዊ (Progressive) አለመሆናቸውን በየወቅቱ በግንባሩ ድርጅቶች የሚካሂዱትን ገምገማዎች ተከትሎ፣ ድርጅቶቹ በተናጠልና ኢህአዴግ እንደ ግንባር ከሚያወጣቸው ተመሳሳይ ይዘት ካላቸው መግለጫዎችና ትርክቶች መገንዘብ ይቻላል። ግንባሩ በየወቅቱ እንደ ችግር ለየኋቸው የሚላቸው ድርጅታዊም ይሁኑ ሀገራዊ እክሎችና ተግዳሮቶች ባመዛኙ በይዘት (Content)ተመሳሳይ የሆኑ ትርክቶችን ያዘሉ የመሆናቸው ነገር በተደጋጋሚ የሚስተዋል ነው። በመሆኑም ይህ በራሱ ድርጅቱ (ኢህአዴግ)፤ ሐገራዊና ድርጅታዊ ችግሮቹን በመሠረታዊነትና በማያዳግም መልኩ ከመቅረፍ ይልቅ፥ ለየኋቸው ለሚላቸው ችግሮች ቅጽበታዊ አፀፋ የዕርምትና የማሻሻያ አቀራረብ (reactive approach) እንደሚከተል አመላካች ነው። በዚህም መነሻ ድርጅቱ “እየፈረሱ መታደስ እና እየታደሱ መፍረስ” አይነት “ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ”  የችግር አፈታት ስነ ዘዴ ይከተላል ብሎ ለመደምደም ያስደፍራል፡፡
እንግዲህ ይህ “በዐይነቱና በመልኩ የተለየ” የተባለለት የህወሓት ግምገማ፣ በቀጣይ እንደተባለለት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉንና እንደተነገረለት የተለየ እንዲሁም የማያዳግም መሆኑን በጊዜ ሂደት የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡
ሆኖም ግን በቅርቡ ወደ ህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው የመጡት አቶ ጌታቸው አረዳ፣ ለአንድ የሀገር ውስጥ ሚዲያ እንደገለፁት፤ “እንደ ተፈሪ ሱሪ ከላይ ሰፋ ከታች ጠበብ ያለውን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ”፤ ቢቻል ከላይም፥ ከታችም ሰፊ የሚያደርግ፤ ካልሆነም ደግሞ በድሮ የሙዚቃ ክሊፖች ላይ ጥላሁን ገሠሠ ለብሶት ሲያቀነቅን እንደምናየው፥ ከላይ ጠበብ ከታች ሰፋ ያለ ሱሪ (በአሁኑ አጠራር ቬል ይሉታል) አይነት ቅርፅ ያለው የዴሞክራሲ ስርዐት የሚሰፍንበት ለውጥ እንዲመጣ የሁሉም ዜጋ ምኞት ነው፡፡”
በአጠቃላይ ገዢው ፖርቲ ደራሽና አፀፋዊ ከሆኑ የመፍትሔ አቅጣጫዎች እራሱን አላቆ፥ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ  አስቀድሞ በመተንተንና በማስተንተን (proactive approach ተከትሎ) በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ በሆነ የፖለቲካ አጣብቂኝና አዙሪት ውስጥ የምትገኘውን አገር፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ሊታደጋት ይገባል፡፡ ይኽን ማድረግ ከተሳነው ግን፤ ድርጅቱ እራሱን ከታሪክ ተጠያቂነት ነጻ ሊያደርግ  እንደማይችል ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዛሬ በሐገራችን በሰፊው ተንሰራፍተው የሚገኙት ፖለቲካዊም ይሁኑ ማሕበራዊ ስንክሳሮች፥ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ የወረዱ መዓቶች ወይም የጥፋት ውሃ አይነት የፈጣሪ ቁጣዎች አይደሉም፡፡ አነሰም አደገ እነዚህ ችግሮች በሌሎች አገራትም የሚከሰቱና ሲከሰቱም የኖሩ ኹነቶች መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡
እዚህ ላይ በአገራችን ኢትዮጵያ ባለፋት 25 ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ የመሰረተ ልማት እድገቶች መኖራቸው  የማይካድ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የልማት እድገቱ የተደራሽነትና  የፍጥነት ወሰን (the pace of development) ብሎሞ ፍትሐዊ የዜጎች የጋራ የልማትና የእድገት ተቋዳሽነትን በማረጋገጥ ረገድ ጥቂቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ በዘለለ ፋይዳው እምብዛም የነበረ’ በእጅጉ ደካማ፥ እንዲሁም በሚገባው ደረጃ ያልነበረ የመሆን ጉዳይ፣ የአገዛዙን ባለስልጣናት ጨምሮ ሁሉም የሚስማማበት ሐቅ ነው፡፡
እናም የሕወሓትም ይሁን የኢህአዴግ በየጊዜው “ታድሻለሁ ተለውጫለሁ፣ ችግሬን አውቄያለሁ፣ ከአሁን በኋላ ስህተቴን አልደግምም እና አይለመደኝም” የሚሉ ትርክቶች፥ “ተጨፈኑ ላሞኛችሁ” አይነት ተራና ለዘወትር የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ያክል የሚቀርብ ካልሆነ በስተቀር፤ መች ነው በተጨባጭ ተግባራዊ የሚሆነው? ለውጡስ በተጨባጭ ካልታየ እስከ መቼ ነው በቃላት ሽንገላስ የሚቀጠለው? መቼስ ነው ኢህአዴግ የምር ታድሶ፣ በምስኪኑና ጎስቋላው ሕብረተሰብ ሕይወትና የዕለትተዕለት ኑሮ ላይ የተሃድሶው ፍሬና ለውጥ የሚታየው? የሚሉት፣ ሁሌም በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ አዕምሮ ውስጥ የሚመላለሱና መልስ ያልተገኘላቸው፤ የዜጎች መሠረታዊ ጥያቄዎች  ሆነዉ ቀጥለዋል፡፡
 ለማንኛውም በጎውን እንዲያመጣልን ምኞታችን ነው፡፡ መልካም ክራሞት!!!

Read 1939 times