Monday, 18 December 2017 12:57

የብሔር ፖለቲካ መዘዙ--?! (ልዩነት እና አንድነት)

Written by  መሐመድ ነስሩ (ሶፎንያስ አቢስ)
Rate this item
(3 votes)

     የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ሰመራ ከተማ ተከብሯል፡፡ የዘንድሮው ለአስራ ሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ይህን በዓል መነሻ በማድረግ ልቦተልክ ፈለግሁ፡፡ ልታነቡኝ የፈቀዳችሁ ተከተሉኝ! ያልፈቀዳችሁ በሊማሊሞ ….. ሃሃሃሃ!
በ1950ዎቹ የኮሌጅ የግጥም ንባብ ፕሮግራም ላይ ኦሮሞው ኢብሳ ጉተማ፤ “ኢትዮጵያዊ ማነው?” ሲል ጥያቄ አዘል ርዕስ የሰጠውን ግጥም አቀረበ፡፡ በወቅቱ በኢብሳ ተቃራኒ ቆሞ የሞገተው ወሎዬው ዋለልኝ መኮንን፣ በዓመቱ “የብሔር ጭቆና አለ፤ ስለዚህ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር አለበት” ሲል ሞጋች ፅሁፍ አስነበበ፡፡
ጀበሀ፣ኦነግና ሕወሓትን የመሳሰሉትም ተጨቆነ ያሉትን ብሔራቸውን ነፃ ሊያወጡ (አዕምሯቸውንና ራሳቸውን ነፃ ሳያወጡ!) ጫካ ገቡ፤ ነፍጥ አነሱ። እነሆ ከዛን ዘመን የጀመረው ጎጠኝነት፣ አብቦና ጎምርቶ በዘመናችን የፖለቲከኞች መጫወቻ ካርድ ለመሆን በቃ፡፡
“ልዩነት ውበት ነው” ይሉናል፡፡ እኛ “አይደለም” አላልንም፡፡ በአንድነት ውስጥ ስላለው ልዩነት አግዝፎና አግኖ ከማውራት፣ በልዩነት ውስጥ ስላለው አንድነት ድምፃችንን ከፍ አድርገን እናውጋ (ሳንወጋጋ!)፡፡ ብዕራችንን አንስተን እንከትብ (ነገር አንከታተብ!)፡፡ በብርታትና ጮክ በማለት ስለ አንድነታችን እንተርክ (ስለ ልዩነት አንነታረክ!)። ጉሮሯችንን ሞርደን፣ አንደበታችንን ስለን፣ ስለ መለያየት ሳይሆን ስለ ህብረት፣ ስለ ብቸኝነት ሳይሆን ስለ ብዝሐነት እናዚም (ሰውን እንደ ጨርቅ እንዘምዝም!) ነበር የኛ እሪታ፤ ነበር እያልን የነበረው፡፡
ብዝሐነት ስንልም እናንተ ለማሳየት እንደምትሞክሩት፣ የተለያየን ሳንሆን አንድ መሆናችን ጎልቶ ይውጣ፤ አንድ ህዝብ እንደሆንና አንድ ሀገር ብቻ እንዳለን ይደስኮርልን፤ ነው ያልነው። ያልነው ብቻ ሳይሆን እያልን ያለነው፡፡ እያልን ያለነው ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የምንለው፡፡
አምናለሁ፤ ልዩነት ውበት ነው፡፡ ልዩነታችን ግን እርስ በርስ እንድንናጭ (እንድንነጫነጭ) ሳይሆን በአንድነት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን እንድንደጋገፍ (እንድንተቃቀፍ) ሊያደርገን ይገባል፡፡ ነጠላ እንሁን እያልኩ ነው፡፡ ነጭነቱ አንድነታችንን ይወክላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ጥለቱ የተለያየ ዓይነት ቀለም ሊኖረው ይችላል፡፡ ጥለቱ በልዩነት ውስጥ፣ ሳንራራቅና ሳንለያይ አጠገብ ለአጠገብ ሆነን፣ እየተደባበስንና እየተጨባበጥን፤ በዳበሳው (በንክኪው!) እና በመጨባበጡ (ቀርቶብን ጭንቁ!) ሂደትም የየራሳችንን ስሜትና የሀገር ፍቅር እያስተላለፍንና እየተቀባበልን እንኑር፤ ነው የምንለው፡፡ …
በነገራችን ላይ ከላይ ስለ ነጠላ ነጭ ክፍል ያነሳሁት ነጥብ ስህተት መሆኑ ዘግይቶ ተገለጠልኝ። ለምን?! እንዴት?! … ብላችኋል፤ ጥሩ ነው፡፡  
ታዲያ መልሴ የሚከተለው ነው፡-
ነጩ ክፍል ሊወክል የሚችለው አንድነትን ሳይሆን የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለውን የአንድነት ሀሳብና ስሜት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትገለፀው በነጩ የነጠላ ክፍል ወይም በጥለቱ ሳይሆን በመላው ነጠላ ነው፡፡ የአንድነት አቀንቃኞችም ሆኑ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች የሚኖሩባት!! ብሔር የለኝም ብሎ የሚያምነውም ሆነ፤ የምገለፀው በጎሳዬ ነው፤ ማንነቴ የጎሳዬ ማንነት ነው፤ ብሎ የሚያስበውም በህብረት ውለው የሚያድሩባት ሀገር!!! …
ይህን የሚክድ ካለ ወይ ሀገሪቱን ጠንቅቆ አያውቃትም ወይም ጤነኛ አይደለም፡፡ … ይመስለኛል፡፡ ከመሰለኝ ደግሞ ሊሆን ይችላል፡፡ ሊሆን ይችላል ሳይሆን ነው፡፡ ነው!!!
… የዛሬ ሁኔታችንን ስናይ ማዘናችን አልቀረም፡፡ ወይም አይቀርም፡፡
ለምን??!!
እርስ በርስ እየተጋጨን ነው፡፡ በእርግጥ ግጭቱ ብዙም ላያስደንቅ ይችላል፡፡ ምክንያቱም እንኳን ሰው ከሰው፣ እግር ከእግርም ይጋጫል … ብለን ድሮ ተርተናል፡፡ ችግር የሚሆነው ግጭቱ የሀሳብ መሆኑ ቀርቶ የጉልበት ሲሆን ነው፡፡ አስገራሚ በሆነ መልኩ በተራና ቀላል ልዩነት ምክንያት እርስ በርስ ስንገዳደልና ስንጨራረስ!! … ይህ እንደተሰቀለ ሰው አንገታችንን እንድንደፋ ቢያደርገን አይገርምም፡፡
ዛሬ ጎጥ ከሀገር በላይ ገንኗል፡፡ ባንኮቻችንን ተመልከቱ፤ ብሔርን ማዕከል አድርገው፤ የብሔርን ወይም የክልልን መጠሪያ ስማቸው ያደረጉ በሀገሪቱ ውስጥ እንደ አሜባ ተራብተዋል፡፡ ክለቦቻችንም ጋ ይህንኑ ታያላችሁ፡፡ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ውስጥም ይህ መሰረታዊ ችግር ጎልቶ ይታያል። መጠሪያቸው ሕወሓት፣ ደኢህዴን፣ ኦህኮ፣ አረና፣ብአዴን፣ ኦህዴድ … ወዘተ … ነው፡፡
የጋራ ሥነ ልቦናችን ተሰልቦ፣ ስልብ ጎሰኞች የሆንን ጥቂት አይደለንም፡፡ መንግስት የሚያደራጀን በጎሳ ነው፡፡ እኛም ስንደራጅ ወይም የሆነ ድርጅት ልናቋቁም ስናስብ፣ የምናሰባስበው ‹የሚመስሉንን› የጎሳችንን አባላት ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ሽል ጨንግፏል!! …. ይህ ከማሳዘንም አልፎ ያስቆዝማል። ማስቆዘም ብቻ ሳይሆን ከልብ ስለ ሀገራችን የምናስበውንና የሚገደንን ዜጎች፣በበርሜል የሚቀዳ እንባ እንድናፈስ ያደርገናል፡፡ ወይም ሊያደርገን ይችላል፡፡ ወይም …
ይህን ሁሉ የምለው ተስፋ እንድትቆርጡ አይደለም፡፡ ተስፋ መቁረጥ ስለ ሀገር ከማሰብ ሊያርቀን ይችላል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም። ሀገራችንን ለአምባገነኖችና ጎጠኞች ትተን፣ የበይ ተመልካች እንድንሆንና እነሱ ብቻቸውን የመሰላቸውን እንዲወስኑብን (መቼም ወስነውብን እንጂ ወስነውልን አያውቁም!) ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ሀሳባችንን መግለፅና ፊት ለፊት መጋፈጥ ይኖርብናል። ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣምና!!
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አይከበር አልልም። ምክንያቱም የተጨቆኑ ወይም ተጨቁነናል ብለው የሚያምኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ይገባኛል። ይህ ማለት ግን ከእነሱ የታሪክ አረዳድ ጋር እስማማለሁ ማለት አይደለም፡፡ እኔ በኢትዮጵያ ውስጥ በደንብ አስቦና አስልቶ የጨቆነ ጎሳ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ማንም ማንንም አልበደለም ማለት ሳይሆን ሆነ ብሎ የበደለ ያለ አይመስለኝም። ይህም ወደ ሁለተኛ አቋሜ ይወስደኛል፡፡ ሆነ ተብሎ የተበደለ ብሔር ወይም ጎሳ የለም፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የተረገጡና የተገደሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ግን ታሪካችን የጭቆናና የበደል ብቻ ነው እንዴ? የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሁም የአንድነት ታሪክስ የለንም? ታዲያ ምነው ኢህአዴግና ሌሎች የጎሳ ድርጅቶች ይሄን አይነግሩንም?!... ለምን ክፉ ክፉውን ብቻ እየነጠሉ ሲተርኩልን ከረሙ?!... ግልፅ ነው፡፡ የሚፈልጉት በጎጥ አጥር ውስጥ ተወስነን፣ ትልቁን ስዕል (ኢትዮጵያዊነትን!) እንዳናይ ነው። ካየን ስልጣን ላይ ልናቆያቸው እንደማንችል ያውቃሉ፡፡ ከተባበርንና ካመንን ተራራን የመናድ አቅም እንዳለን ስለሚገነዘቡ፣ ከመጠናችን ጠበን፣ በጠባብ ጎጠኝነት እንድንጠፈር ቀን ከሌት ይሰራሉ።
ለማናቸውም የብሔር ብሔረሰብ ቀን መከበሩ ክፋት ላይኖረው ይችላል፡፡ ክፋቱ፤ ስለ ልዩነት አብዝቶ ማውራቱ! ክፋቱ፤ ስለ ልዩነት አብዝቶ መስማቱ! ክፋቱ፤ የጎጥ አጥር ማበጀቱ! ክፋቱ፤ ኢትዮጵያዊነትን ማስረሳቱ! ክፋቱ….
ሌላው ችግር ታሪካችን ይሄ ብቻ ይመስል፣ አንድ ሳይሆን የተለያየንና የተበዳደልን እንደሆን እንድናምን እየተተረከልን፤ አንዳችን ሌላችንን ላይ በቂም በቀል እንድንነሳ ሆነ ተብሎ እየተሰራብን የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን መዘመር ወሳኝ ነው፤ እላለሁ፡፡ አንድነት ከሌለ ምንም የለም፡፡ አንድነት ካለ ሁሉም አለ፡፡
ከሚለያየን ነገር በላይ አንድ የሚያደርገን ነገር ይበዛልና!
የዳኛቸው ወርቁ ገፀ-ባህርይ የሆኑ ቄስ እንዲህ ይላሉ፡-
“…የስልጣኔ ኩርንችት የኑሮ አሽክላ፣ የመወያየት እንቅፋት፣ የፍቅር ሻህላ እየሆኑ፣ በጥራዝ ነጠቅነት በተመረዘው ወጣት መካከል፣ እንቁራሪት በሆዱ እንደቋጠረ እባብ ተቋጥረው የሚታዩትን አንዳንድ አጉራ ዘላይ፣ አጥንተ ብልዝ ሰዎች፣ የሚሻለውን መንገድ አስይዞ፣ ከግብ የሚያደርሳቸው አንድነት ነወ፡፡… ሳቅን በደስታ፣ ጭብጨባን በማጎልመሻ፣ ለቅሶን በሐዘን፣ መጎሳቆልን በድህነት፣ ያለ ጊዜ ማርጀትን በብስጭት ተርጉሞ፣ ከሰው እኩል የሚያራምድ አንድነት ነው … ነፃነትና አንድነት መንትዮች ናቸው፡፡ ….”
በእርግጥ ይሄ የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” የተሰኘ ረጅም ልብ ወለድ የተፃፈው የብሔር ፖለቲካ ስልጣን ላይ ሳይወጣ ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬ የተባለ ያህል ልባችንን ሰቅዞ ይይዘዋል፡፡
ያለ አንድነት ስኬት ከባድ ይመስላል፡፡ ሀገሮች እንጂ ጎጦች አድገው አያውቁም፡፡ ሊያድግ የሚችለው የብሔር አስተሳሰብ እንጂ ብሔር ሊሆን አይችልም፡፡ ከጎጠኝነት በላይ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝት እንዲስፋፋና እንዲዘመር መመኘት መልካም ነው፡፡ መመኘት ብቻ ሳይሆን መስራት ጭምር! …. የሚያዋጣን ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡
ከአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ፣ገፀ-ባህርይ አንዱ የሚናገረው ነገር፣ የፅሁፌ ማዕከላዊ መልዕክት ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ እነሆ፡-
“የኢትዮጵያ ህዝብ ጨርሶ ሳይሞት በነፍሱ መድረስ አለብን፡፡ መቃብር ከወረደ በኋለ፤ ለማስነሳት ተዓምራት ማድረግ አንችልም፡፡”
የኢትዮጵያ ህዝብን ለማነቃቃትም ሆነ የኢትዮጵያዊነት መንፈስን ለማፅናት ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥበብ ታላቅ ድርሻና አቅም አላትና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ወደ አደባባይ ውጡ፤ ህዝቡን ለማነፅም በትጋት ስሩ፣ ማለት ተገቢ ይሆናል፡፡
በእርግጥም የብሔር ብሔረሰብ ቀን መከበሩ ክፋት ላይኖረው ይችላል፡፡ ክፋቱ፤ ስለ ልዩነት አብዝቶ ማውራቱ! ክፋቱ፤ ስለ ልዩነት አብዝቶ መስማቱ! ክፋቱ፤ የጎጥ አጥር ማበጀቱ! ክፋቱ፤ አንድነትን ማስረሳቱ! ክፋቱ ኢትዮጵያዊነትን ማዘንጋቱ! ክፋቱ….!!

Read 1088 times