Print this page
Monday, 18 December 2017 12:56

“ሥርአቱ ከተሃድሶ አዙሪት ውስጥ መውጣት አለበት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • ህዝቡ በፖለቲካ ቁማርተኞች ተታሎ፣ ለእርስበርስ ግጭት መዳረግ የለበትም
       • ሦስቱ የመንግስት አካላት፣ በሥራ አስፈጻሚው ጫና ሥር ናቸው
       • ትልቁ የአገሪቱ በጎ ተስፋ የህዝቡ አስተዋይ መሆን ነው
       • አዲሱ ትውልድ አገሪቱን ከአዛውንቶች መንጠቅ አለበት

     የቀድሞ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መሥራችና አመራር አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ አሥራት ጣሴ፣ በሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች እንዲሁም መፍትሄዎች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

   በሀገሪቱ ውስጥ የፖለቲካና ያለመረጋጋት ችግሮች የቀጠሉበት ምክንያት ምንድን ነው?
በሀገሪቱ የተፈጠሩትን ችግሮች የሁለትና ሦስት ዓመት ችግሮች አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው፡፡ ችግሩ የጀመረው የሥርአት ለውጡ ከመጣ ጀምሮ ነው፡፡ ገና ከመነሻው ኢህአዴግ ለመድበለ ፓርቲ ስርአት  የተመቸ አልነበረም፡፡ የምዕራቡ ዓለም የሚሰጠውን የገንዘብ እርዳታ ለማግኘት የመድበለ ፓርቲ መርህን ህገ መንግስቱ ውስጥ ቢያስገባም በተግባር ግን አልተተረጎመም፡፡ ለመተርጎምም አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም አይፈቅድም። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ሊካሄድ አይችልም፡፡ በዚህ ሁኔታ በምርጫ ስልጣን የሚያዝበት እድል ነው የጠበበው። በ1997 ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ትንሽ ለምርጫ ሂደት ከፈት ብሎ ነበር፡፡ ለምን ተከፈተ ከተባለ በወቅቱ ገና ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያገገምንበት ስለነበረና በውስጣቸውም ክፍፍል የተፈጠረበት ወቅት ስለነበረ ነው፡፡ በጦርነቱ ወቅት ህዝብ ለሃገሩ ያሳየውን ድጋፍ በምርጫውም ለእነሱ የሚሰጥ መስሏቸው ነበር፡፡ ውጤቱ ግን በተቃራኒው ነበር የሆነው፡፡ ይሄ ደግሞ ዱብ እዳ ነበር የሆነባቸው። ከዚያ በኋላ የምርጫ ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፣ ራሱ መቶ በመቶ የሚያሸንፍበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡
በሌላ በኩል ስርአቱ መሰረት ያደረገው የብሄር ፌደራሊዝም፣ አሁን ላይ ቅቡልነት የማጣቱ ጉዳይ ነው፡፡ የልዩነት ግንቦችን ደርምሶ ህዝቡ “የእገሌ ደም የኔ ደም ነው” መባባል ነው የጀመረው፡፡ ይሄ የከፋፍለህ ግዛው ሴራ እየፈረሰ መምጣቱን ያመላክተናል፡፡ ሌላው አንድ መንግስት ተመርጫለሁ ባለ በማግስቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ማለት ፖለቲካዊ ትርጉሙ የተለየ ነው፡፡ በአጠቃላይ በተለይ በሀገሪቱ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮች የሚያሳዩን፣ ኢህአዴግ፣ ለህዝብ የዲሞክራሲ ማስረፅ ያልቆመ መሆኑን ነው፡፡ ህዝቡ በመድበለ ፓርቲ ስርአት ላይ የነበረውን ተስፋ ማጣቱን የሚያመላክት ነው፡፡ የህዝብ እምቢተኛነት መገለጫው፣ ፓርቲዎችን ጠቃሚ እንዳልሆኑ አድርጎ፣ መብቴን እኔ ራሴ ነኝ የማስከብረው ብሎ መነሳቱ ነው፡፡
በህዝቡ ጥያቄዎች ዙሪያ ጥርት ያለ መግባባት ላይ የተደረሰ አይመስልም፡፡ መንግስት ጥያቄው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ይላል፡፡ ተቃዋሚዎች ደግሞ የዲሞክራሲና የነጻነት ጥያቄዎች ናቸው ይላሉ፡፡ እርስዎ የህዝቡ ጥያቄዎች  ምንድን ነው ይላሉ?
አሁን በአብዛኛው ህዝቡ የሚያነሳው ጥያቄ የነፃነት ነው፡፡ የለውጥ ጥያቄ ነው እንጂ የተሃድሶ አይደለም፡፡ ዜግነቴን መልሱልኝ ነው ጥያቄው፡፡ ዛሬ ላይ ከዜግነት በላይ ትልቁ ተጠቃሚ የሚያደርገው የገዥው ፓርቲ አባል መሆን ነው፡፡ በዚህ ሰበብ ለሚደርሰው ጥፋትና ውድመት፣ የሰው ህይወት ህልፈት ተጠያቂው ደግሞ “ከኔ ውጭ ለዚህች ሀገር የሚበጅ የለም” በሚለው አቋሙ የፀናው ገዥው ፓርቲ ነው፡፡
ህዝቡ ያነሳው የነፃነት ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ የነፃነት ጥያቄ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
የነፃነት ጥያቄ ግልፅ ነው፡፡ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሣይጓደሉ መጠበቅ ማለት ነው፡፡ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የሚያስፈልጉ የማዕዘን ድንጋዮች ያለ ገደብ በነፃነት ይስሩ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፕሬሶች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ፍርድ ቤቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሙያ ማህበራት ወዘተ-- ያለ ጣልቃ ገብነት በነፃነት ይስሩ፣ ሁሉም ያመነበት የምርጫ ቦርድ ይቋቋም ማለት ነው - ነፃነት ማለት፡፡ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄድና ህዝብ የመረጠው ወደ ስልጣን ይምጣ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ነፃነት ስል፣ የፍትህ የበላይነት ይጠበቅ ማለት ነው፡፡ ሦስቱ የመንግስት አካላት፡- ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው ራሳቸውን ችለው (ቼክ ኤንድ ባላንስ እየተደራረጉ) ይስሩ ማለት ነው፡፡ አሁን ሦስቱም ያሉት በሥራ አስፈፃሚው ጫና ስር ነው፡፡ ነፃነት ስንል ዳኞች፣ የፓርላማ አባላት፣ ለህገ መንግስትና ለህሊናቸው ብቻ ታማኝ የሚሆኑበት ሥርአት ይፈጠር ማለት ነው፡፡
ኢህአዴግ እንዲህ ያለውን ሥርዓት ለመፍጠር ያቃተው ለምንድን ነው? እርስዎ ይሄ ዓይነቱ ሥርዓት ሊፈጠር የሚችለው እንዴት ነው ይላሉ?
ይሄ ሊመጣ የሚችለው የተለያዩ ሃገራት ተሞክሮዎችን በማጥናት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በደቡብ አፍሪካ እነ ኔልሰን ማንዴላ የተጠቀሙበት የሠላምና የእርቅ ጉባኤ አለ፡፡ የሌሎች ሃገራት ተሞክሮዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ የባለአደራ መንግስት ማቋቋም፡፡ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ የደረሰባቸውን ሃገራት ተሞክሮ በማጥናት፣ መፍትሄዎችን በየጊዜው ማመላከትም አንዱ የለውጡ እርምጃ ነው፡፡ በዋናነት የእርቅና የብሄራዊ መግባባት ጉባኤ፣ ሁሉን በይቅር ባይነት አልፎ፣ ወደ መግባባት የሚወስድ ስለሆነ ሊተኮርበት ይገባል። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ላይ ሙጭጭ እንላለን ከተባለ ግን ጊዜው ያለፈበት በመሆኑ  ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ይህ ርዕዮተ ዓለም አይሰራም፡፡ ስለዚህ ከጥገናዊ ለውጥ በመውጣት ወደ ሥር ነቀል ለውጥ መምጣት ያስፈልጋል፡፡  
ኢህአዴግ “ጥልቅ ተሃድሶ” በማድረግ፣ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠሁ ነው ይላል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ሁልጊዜ ችግር እንዳለ እነሱም ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን ሌላው ወገን፣ ይሄ ችግር፣ ሀገር ሊበታትን ይችላል የሚል ሃሳብ ሲያንጸባርቅ እነሱ ግን “ዛሬም ችግሩ ከቁጥጥራችን በላይ አይደለም፤ ዛሬም ሃያል ነን፤ መቆጣጠር የምንችለው ነው” እያሉ ነው፡፡ የመንግስት አካላት ትልቁ ችግር፣ ነገሮችን አቃሎና አሳንሶ የማየት ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በኃይል ፀጥ ማድረግ እንደሚቻል ነው የሚያምኑት፡፡ በዚህ የተነሳ የችግሩን ግዙፍነት ቢረዱም በቀጥታ መረዳታቸውን እንዳይገልጹ አድርጓቸዋል። የህዝቡን ጥያቄዎች በሙሉ ከስራ አጥነትና ከመልካም አስተዳደር አንፃር፣ አሳንሰው ነው መመልከት የሚፈልጉት፡፡ እርግጥ ነው ወጣቱ ሥራ ይፈልጋል፤ ግን ከዚህም በላይ ነፃነትና ዲሞክራሲ ይፈልጋል፡፡ ችግሩን ይረዳሉ፤ግን የሚረዱበት ጥልቀት አነስተኛ ነው፡፡ ለዚህ ነው ትርጉሙ የማይታወቅ ጥልቅ ተሃድሶ አድርገናል የሚሉት፡፡ አሁን ይሄ ስርአት በተሃድሶ አዙሪት ውስጥ ነው ያለው፡፡ በግለሰቦች መለዋወጥ ብቻ የሚያምን ስርአት መፍትሄ ማምጣት አይችልም። አሁን ኢህአዴግ እየወሰደ ያለው እርምጃ  ጥገናዊ ለውጥ እንኳ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ እየሄደበት ያለው መንገድ ለሃገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ትክክለኛ መፍትሄዎችን የሚያመጣ አይደለም፡፡ ይሄ ደግሞ እነሱንም ሃገርንም አደጋ ላይ ይጥላል፡፡
በዚህ መሃል የሃገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንዴት ይመለከቱታል?
ሲጀመር እኔ በአሁኑ ወቅት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ጠንካራ የነበሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀቶችን ደግሞ ወደ አዘቅት የከተተው ይኸው ስርአት ነው። ለኢትዮጵያ ህዝብ ችግር መፍትሄ የሚያመጣ የፖለቲካ ድርጅት፣ በሀገሪቱ እንደገና ካልተዋቀረ በስተቀር አሁን የሀገሪቱን የፖለቲካ ኃላፊነቶች መሸከም የሚችል ፓርቲ አለ ለማለት እቸገራለሁ፡፡
አሁን ሥልጣን ለመረከብ ዝግጁ የሆነ ፓርቲ የለም ማለት ነው?
በፓርቲ ወይም በድርጅት አይደራጁ እንጂ በአገር ውስጥም በውጪም የአይምሮ ብስለትና የመንፈስ ጥንካሬ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ የእርቅና የመግባባት ኮንፍረንስ ቢካሄድ፣ ከዚህ ኮንፍረንስ የሚገኙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አገሪቱ‘ኮ የምሁራን መካን አይደለችም፡፡ አቅም ያላቸው እድሉ ቢሰጣቸው ሊሰሩ የሚችሉ ሺዎች ይገኛሉ፡፡ አገሪቱ የሰዎች ድሃ አይደለችም፡፡
ብዙ ጊዜ ይሄ የእርቅና ብሔራዊ መግባባት ጉባኤ እንደ መፍትሄ ተደጋግሞ ይጠቀሳል። ለመሆኑ ጉባኤውን ማነው ያዘጋጀዋል ተብሎ የሚታሰበው?
የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የሙያ ማህበራት ይኖራሉ፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ህብረት፣ የሃይማኖት ተቋማት ይሄን ስራ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ገዥው ፓርቲም ቢሆን ይሄን በቀናነት ማዘጋጀት ይችላል። በገዠው ፓርቲ ውስጥም እኮ ቀናነት ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ሀገርና ህዝብን ለማዳን ጀግና እንሆናለን ካሉ፣ ራሳቸውም ይሄን ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይሄን በማድረጋቸው ደግሞ ሃገርንም፣ ህዝብንም ሆነ ራሳቸውን ያድናሉ፡፡ አሁን ከተሃድሶ አዙሪት መውጣትና አዲስ መንገድ ወይም አማራጮችን ማጥናት አለባቸው፡፡ ዋናው ቅንነትና ክፍት አዕምሮ የመኖሩ ጉዳይ ነው እንጂ ይሄን ማድረግ  ቀላል ነው።
አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
እንደ አገር የመቀጠል አደጋ ውስጥ እንዳለን ዓለም አቀፍ ጥናቶችም እያመላከቱ ነው፡፡ Forign Policy Megazin Fund for Peace የተባለ ድርጅት እ.ኤ.አ በ2011 የዓለም አገራት የሚገኙበትን የመረጋጋት ሁኔታ በ177 ሃገሮች ላይ ጥናት አካሂዶ ሪፖርት ያደረገው መረጃ አለ። አንድ ሃገር የመከነ ወይም የፈረሰ አገር ከመሆኑ በፊት ያሉትን ቅድመ ማስጠንቀቂያ በ5 ከፍለው አቅርበውት ነበር፡፡ ሃገራት ያሉበትን ሁኔታም አሳሳቢ፣ አደገኛ፣ መካከለኛ፣ ያልተረጋጉ፣ የተረጋጉ በሚል አስቀምጠውታል፡፡ ከተጠቀሙባቸው መመዘኛዎች መካከልም የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የፍትህና የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የስደተኞች ብዛት፣ ያልተመጣጠነ ልማት፣ የመንግስት በህዝቡ ተቀባይነትና አመኔታ ማጣት ወይም ህዝብ የመንግስትን ህጋዊነት ያለመቀበል፣ የቡድኖች የመጨቆንና የመከፋት ስሜትና በቡድን መከፋፈል እንዲሁም የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ናቸው፡፡ በዚህ ጥናት ላይ ኢትዮጵያ የመከኑ ሀገራት ለመሆን “አሳሳቢ” በሚለው ዘርፍ ከተመደቡት ሃገሮች ቀጥሎ ባለው “የአደጋ ዞን” ውስጥ ከተመደቡት መካከል ትገኛለች፡፡ ይህ ጥናት በተደጋጋሚ የወጣ ነው፡፡
የተዘረዘሩት ችግሮች ደግሞ አብዛኞቹ ማንም ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው፣ በሀገራችን የታዩ ናቸው፡፡ ይሄ ጥናት እንግዲህ ከ6 አመት በፊት የተደረገ ነው፡፡ ካጠኑት ሰዎች  በላይም ደግሞ እኛ በሃገሪቱ የምንኖር ዜጓች ችግሩን የበለጠ እያየነው ነው፡፡
አገሪቱ በቀጣይ ያላት መልካም እድልና አጋጣሚስ ምንድን ነው?
ትልቁ የሃገሪቱ በጎ ተስፋ የህዝቡ አስተዋይ መሆን ነው፡፡ በጎሣ ያለውን ግጭት መቋቋም ስንችል ነው ተስፋችን የሚለመልመው፡፡ የመከባበር የመተሣሠብ ባህል አለን፡፡ እነዚህ እሴቶቻችን መሸርሸር የለባቸውም፡፡ እንደ ህዝብ የመተዛዘንና የመተሣሠብ እሴቶቻችን ከአደጋ ይጠብቁናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ህዝብ ከመንግስት ህግን የሚነጥቅበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አሁን በጀምሩም ቢሆን ይህ አይነት ነገር አለ፡፡ ይሄ ከባድ ነው፡፡ በህዝብ መካከል የሚደረጉ ግጭቶች ሆን ተብለው በስልትና በዘዴ የሚፈጠሩ ስለሆነ ህዝብ መንቃትና ከእንዲህ ያሉ ሁነቶች ራሱን ማራቅ አለበት፡፡
ህዝቡ በፖለቲካ ቁማርተኞች ተታሎ፣ ለእርስ በርስ ግጭት መዳረግ የለበትም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የነበረን የአብሮነት እሴት በፖለቲከኞች መጭበርበር የለበትም፡፡ እኛ ከሌለን ህዝብ እርስ በራሱ ይጫረሳል የሚል ስዕል ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ስለሆነ፣ ህዝቡ ከእንዲህ ያሉ ግጭቶች መራቅ አለበት፡፡
አንድ የሠማሁት የሰዎች የአስተሣሠብ አይነት አለ፡፡ አራት አይነት ሰዎች አሉ፡፡ የመጀመሪው አይነት ሰው “የኔ የራሴ ነው፣ ያንተም የራስህ ነው” ይላል፡፡ ሁለተኛው አይነት ሰው ደግሞ “ያንተ የእኔ ነው፣ የኔም ያንተ ነው” ይላል፡፡ ሦስተኛው አይነት ሰው “የአንተ ያንተ ነው፣ የኔም የአንተ ነው” የሚል ነው፡፡ አራተኛው አይነት ደግሞ የህወኃት/ኢህአዴግ ባህሪን የሚገልፅ ነው፤ “የእኔ የኔ ነው፣ ያንተም የኔ ነው” ይልሃል፡፡ ይሄ ባህሪ ነው የችግሩ ሁሉ ምንጭ።
ለአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች የ60ዎቹን “አብዮታዊ ትውልድ” ተጠያቂ የሚያደርጉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
እኔ ሁልጊዜ ያንን ትውልድ አሁን ላለው ችግር መውቀስ ተገቢ ነው አልልም፡፡ የፈጠረው ጫና የለም ባልልም ለሁሉም ችግሮች ተጠያቂ ማድረግ ግን ትክክል አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ያ ትውልድ ተጎዳድተን፣ ተጠፋፍተን በመሃል ለአምባገነኖች ነው እድል የሰጠነው፡፡ ይሄ መጥፎ ገፅታው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መስዋዕትነትና የአላማ ፅናትም ያሳየና ያስተማረ ትውልድ ነው፡፡ ወጣቱ የኛን አሉታዊ ተፅዕኖዎች በማስወገድ ወደፊት መራመድ አለበት፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የወጣት ትውልድ ነች። የ60ዎቹ ትውልድ ምናልባት ያለፈውን ታሪክ በመፃፍ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡ አዲሱ ትውልድ ግን አገሪቱን  ከአዛውንቶች መንጠቅ አለበት፡፡ በሀይል ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ ተሳትፎአቸውንና ሀገራዊ ፍቅራቸውን በመጨመር ነው ይሄን ማድረግ የሚችሉት፡፡ ያለፈ ታሪክን በማወቅ፣ ለፍትህ በመቆም፣ ለእውነት በመቆም ወጣቱ አገሪቱን የራሱ ማድረግ ይችላል፡፡

Read 2076 times