Monday, 18 December 2017 12:51

“በዩኒቨርሲቲዎች የብሄር ግጭት አለ ብሎ መደምደም አይቻልም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

· “የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውን መጠበቅ አለባቸው”
          · “መሳሪያ ባልያዙ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ ኃይል መጠቀም የሚወገዝ ነው”
               ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ

    “በዩኒቨርሲቲዎች ብሄርን ማዕከል ያደረገ ግጭት አለ ብሎ መደምደም አይቻልም” ያሉት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ በሃረር ጨለንቆ ከተማ 15 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን በተመለከተ የፀጥታ ም/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች ለተፈጠረው ብሄር ተኮር ግጭት መነሻ ምክንያቶችን በተመለከተ ለአዲስ አድማስ ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር ነገሪ፤ በአጠቃላይ 18 የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንደቀጠለ መሆኑን፣ ነገር ግን በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ችግር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ “የዚህ ችግር መነሻ ወልዲያ ላይ ከስፖርት ጋር በተገናኘ ችግር ተፈጥሮ የሰው ህይወት አልፎ ነበር፡፡ ሁለቱ የብሄር መልክ እንዲይዝ የተደረገበት ሁኔታም ነበር፡፡ ችግሩ ወደ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተዛምቶ መልኩን እየቀየረ በመምጣት ወደ ወለጋ ሻምቡ ዩኒቨርሲቲ በመስፋፋት ግጭት ተፈጥሮ ጉዳት ሊደርስ ችሏል፡፡” ብለዋል ዶ/ር ነገሪ።
በዚህ ምክንያት ተማሪዎቻችን ስጋት ውስጥ ወድቀው የመረበሽ ሁኔታ ተፈጠረ እንጂ በዩኒቨርሲቲዎቻችን ብሄርን ማዕከል ያደረገ ግጭት አይደለም ያለው፤ በአጠቃላይ ብሄርን ያማከለ ችግር አለ ብሎ መደምደም አይቻልም” ብለዋል፡፡
ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በሰላማዊ መንገድ የመማር ማስተማር ሂደታቸውን ቀጥለዋል። ሁነቱ በእጅጉ የሚያሳዝንና መደገም የሌለበት መሆኑን፤ መንግስትም ከክልል መስተዳደሮች ጋር በመሆን የፀጥታ አካላት ችግር ባለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ፣ የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር አካላትም ስጋት ላለባቸው ተማሪዎች አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸውና ለዚህ ግጭት ምክንያት የሆነው የአመለካከት ችግር በውይይት እንዲስተካከል ይደረጋል” ብለዋል፤ ሚኒስትሩ፡፡
በችግሩ ስጋት አድሮባቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው የወጡ ተማሪዎችን ትምህርት ሚኒስቴር ራሱ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት በማቅረብ ጭምር ወደ ዩኒቨርሲቲያቸው እንዲመለሱ ያደርጋል፣ የተመለሱም አሉ” ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ “ዛሬ (አርብ) የተደረገው ግምገማችንም አሁን በዩኒቨርሲቲዎች መረጋጋት እንዳለ ያሳያል” ብለዋል - ለአዲስ አድማስ፡፡
“ይሄ ግጭት ማንንም አይጠቅምም” ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ አመለካከትን በመቀየር ችግሩ የብሄር መልክ እንዲይዝ በማድረጉ በኩል “የጠላትም እጅ” እንዳለበት ነው የተገመገመው ብለዋል፡፡
በየጊዜው ለሚከሰቱ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄው ምንድን ነው በሚል የተጠየቁት ዶ/ር ነገሪ፤ “አሁን ትኩረታችን ቀውሱን መፍታት ነው፤ በዘላቂነት በአመለካከት ለውጥና በእውቀት ማጎልበት ላይ ስራ መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
“የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውን መጠበቅ አለባቸው” ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ ክልሎችም የራሳቸው ሃገር መሆናቸውን አውቀው፣ ከአካባቢው ተወላጆች ጋር ወንድማማችነት መፍጠርና ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡
በፀጥታው በኩል ያሉ ችግሮች አሁን ባሉበት አይቀጥሉም፤ መንግስት ከህዝብ ጋር በመተባበር ይፈታቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በየዩኒቨርስቲዎቹ ህይወት ያጠፉ ወንጀለኞችን ወደ ህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፣ አሁንም በቁጥጥር ስር የዋሉ አሉ ብለዋል፡፡
ትምህርት የተቋረጠባቸው ዩኒቨርሲቲዎችም ትምህርት በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑንና ተማሪዎች ወደየ ዩኒቨርሲቲያቸው ተመልሰው እንዲማሩ ትምህርት ሚኒስቴር ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሃረር ጨለንቆ የተፈፀመውን ግድያና የኦሮሚያ ክልል አቋምን በተመለከተ የፌደራል መንግስቱ ምን ይላል ስንል የጠየቅናቸው ሚኒስትሩ “ግድያው በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የለውም፤ የሚወገዝ ነው፤ ነገር ግን መንስኤዎቹንና የተወሰደውን እርምጃ በማጣራት ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
“የፌደራል መንግስቱ በሟቾች ህይወት ማለፍ ጥልቅ ሃዝን ተሰምቶታል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው አይደለም የሚለውን የፀጥታ ም/ቤቱ መርምሮ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡
“መሳሪያ ባልያዙና ባዶ እጃቸውን ባሉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ ኃይል መጠቀም የሚወገዝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ “ከዚያ ይልቅ ሌሎች የከፋ ጉዳት የማያደርሱ አማራጮችን በመጠቀም፣ ሁኔታዎችን ማረጋጋት ይገባል ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡

Read 6361 times