Monday, 18 December 2017 12:36

በጨለንቆ 15 ሰዎች የገደሉ የፀጥታ ኃይሎች ለህግ እንደሚቀርቡ ተገለጸ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የፀጥታ ኃይሎችን ድርጊት አውግዘዋል
            በዩኒቨርሲቲዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች አሳሳቢ ሆነዋል ተባለ

    በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌ ዞን፣ በጨለንቆ ከተማ 15 ሰላማዊ ሰልፈኞች በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ተከትሎ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የሃይል እርምጃውን አውግዞ፣ ድርጊቱን የፈፀሙ አካላት ለህግ እንደሚቀርቡ አስታውቋል፡፡  
በጨለንቆ ለተፈፀመው ግድያ መነሻ ምክንያት የሆነው አህመዲን አህመድ አሳሳ የተባለ ግለሰብ በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መገደሉን በመቃወም የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ አደባባይ መውጣታቸው መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስታውቀዋል፡፡
“እኛ በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች የተፈፀመው፣ ወንጀል ነው ብለን ነው የምናምነው” ያሉት የኮሚኒኬሽን ኃላፊው፤ “የሰላማዊ ዜጋ ደም ፈሶ መቅረት ስለሌለበት፣ የክልሉ መንግስት ድርጊቱን የፈፀሙና ያስፈፀሙ በህግ እንዲጠየቁ  ግልፅ አቋም ይዟል” ብለዋል፡፡  
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) በሰጡት መግለጫ፤ በጨለንቆ 15 ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን በመጥቀስ፣ የክልሉ መንግስት በሁኔታው በእጅጉ ማዘኑን አስታውቀዋል፡፡ በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው እርምጃ በክልሉ መንግስት ተቀባይነት እንደሌለውም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። “ሰዎች ሲያጠፉ በህግ የሚጠየቁበት ሥርአት አለ፤ ከዚህ ባለፈ እንዲህ ያለው የሃይል እርምጃ በህብረተሰባችን ላይ መፈፀሙን አጥብቀን እናወግዛለን፤ አንቀበለውም” ብለዋል - አቶ ለማ መገርሳ፡፡
በህገ መንግስቱ በአንድ ክልል ውስጥ የፀጥታ ችግር ሲያጋጥም የክልሉ ፖሊስ የማረጋጋት ስራ እንደሚሰራና ከአቅሙ በላይ መሆኑን ሲያመለክት ብቻ የፌደራል ጣልቃ ገብነት እንደሚኖር የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ”የጨለንቆው የሃይል እርምጃ  በማን ጥሪና በማን ትዕዛዝ እንደተፈፀመ አናውቅም” ብለዋል፡፡  
ይህም የህግ ጥሰት መሆኑን በመጠቆም፣ የክልሉ መንግስት ድርጊቱን የፈጸሙና ያስፈፀሙ አካላትን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጣርቶ ለህዝብ እንደሚያሳውቅና ህግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡ “የኦሮሚያ ክልል መንግስት ህዝቡ ሲጠቃ ዝም ብሎ አያይም” ያሉት አቶ ለማ፤ ”የኦሮሚያ የፀጥታ አካላትም ሆኑ ሌሎች የፀጥታ አካላት ከምንግዜውም በበለጠ ከህዝቡ ጎን ሊቆሙ ይገባል” ብለዋል፡፡
 በሰላማዊ መንገድ መሳሪያ ሳይዙ ተቃውሞ በሚያሰሙ ሰዎች ላይ ሌሎች አማራጮች እያሉ መሳሪያ መተኮስን አጥብቀው እንደሚያወግዙትም የክልሉ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አዲሱ በበኩላቸው፤ ከማክሰኞ ጀምሮ ጠንካራ ግምገማ እያደረገ ነው የተባለው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ጉባኤም ድርጊቱን ያወግዛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ የፌደራል የፀጥታ ኃይሎችና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት በመሳሪያ የታገዘ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል። በግጭቱም በፀጥታ አካላቱ ላይ ጉዳት መድረሱ የተጠቆመ ሲሆን ስለ ጉዳት መጠኑ ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡    
ሰሞኑን በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተቀሰቀሰው ብሄር ተኮር ግጭት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን በአዲግራትና በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉ ታውቋል፡፡ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ብሄር ተኮር በሆነ ጥቃት የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን ተከትሎ በወልዲያ በጎንደር፣ በወለጋ፣ በመቀሌ፣ አምቦና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ተቃውሞና ውጥረት ነግሶ መሰንበቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፤በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ የተፈፀመውን ግድያ በፅኑ እንደሚያወግዙ ገልጸው፣ አጥፊዎች ተጣርተው ለህግ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል። የኦሮሞ ወጣቶች በመደማመጥና በበሰለ አካሄድ መጓዝ አለባቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “ወጣቶች ስሜታዊ ከሆኑ የምንሰራውን ስራ ያበላሽብናል” ብለዋል፡፡ ወጣቶች ተረጋግተው መማር እንዳለባቸውም ፕሬዚዳንቱ  አሳስበዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን በጉዳዩ ላይ በሰጠው ማብራሪያ አለመረጋጋቱ የተፈጠረው በፖለቲካዊ ችግር ነው ብሏል፡፡ በዩኒቨርስቲዎች የተፈጠረው አለመረጋጋትና ግጭት ፖለቲካዊ ችግር መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ ያስታወቁ ሲሆን ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ “ችግሩ የተወሳሰበና ዘላቂ መፍትሄ የሚፈልግ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ የሃገሪቱን ሰላም ለማወክ የተነሱ ኃይሎች ተማሪዎችን መጠቀሚያ እያደረጓቸው ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ፤ሰሞኑን በጨለንቆና በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰቱ  ግጭቶችና የዜጎች ሞት እንደሚያሳስበው ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎች ደህንነት መረጋገጥ ዋስትና መስጠት ይገባዋል ያለው ኤምባሲው፤በጨለንቆና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተነሱ ግጭቶች ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች ጉዳይ አሳዝኖኛል ብሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለዓመታት የዘለቀውን እርስ በእርስ የመከባበርና የመዋደድ ባህላቸውን ሊጠብቁት እንደሚገባም ኤምባሲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡  
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሃሳብ በመስጠት የሚታወቁት አምባሳደር ኸርማን ኮኸን በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሀገሪቱ ያሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ተባብሰው፣ አገሪቷ ከመፈራረሷ በፊት አሜሪካ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት አዲስ ጉባኤ አዘጋጅታ፣ አዲስ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Read 6874 times