Monday, 18 December 2017 12:48

ኢዴፓ “የወቅቱ ጥያቄ አገርን ከመፍረስ አደጋ ማዳን ነው” አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በስፖርት ማዘውተሪያዎች የታየው ብሄር ተኮር ግጭት በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት አገራችንን ወደማትወጣው አዘቅት እንዳይከታት ከፍተኛ ስጋት አድሮብኛል ያለው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፤ የወቅቱ ጥያቄ አገርን ከመፍረስ አደጋ ማዳን ነው ብሏል፡፡
ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳይ ባወጣው የአቋም መግለጫው፤ የብሄር ተኮር ግጭቶች መንስኤ የፌደራል አደረጃጀቱ መሆኑን በመግለፅ፣ በተደጋጋሚ እንዲፈተሸ ሲያሳስብ መቆየቱን በመጥቀስ፣ መንግስት በመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ቸልታ በማሳየቱ፣ አደጋው አሳሳቢና አሳዛኝ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡
በአሁን ወቅት በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የስፖርት ማዘውተሪያዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ዘርና ብሄርን መሰረት አድርገው በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያስፈልጋቸው ያሳሰበው ፓርቲው፤ በዘላቂነትም የፌደራል ስርአቱን በጥልቀት ፈትሾ፣ ኢትዮጵያንና ህዝቧን የሚመጥን የፌደራል አደረጃጀት እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር አለበት ብሏል፡፡
የሃገሬ ጉዳይ ያገባኛል፣ ያስጨንቀኛል የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙኃን፣ የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት አገሪቱ ወደማትወጣበት አዘቅት ከመግባቷ በፊት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ፓርቲው አሳስቧል፡፡

Read 3435 times