Monday, 18 December 2017 12:45

‹‹ሳንጠራ ስማችን ተጠቅሷል››

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው እሁድ በአምባሳደር ሲኒማ አዳራሽ “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት” በሚል ርዕስ ያካሄደውን ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ  መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ፓርቲው  አንጋፋ ምሁራን፣ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች በህዝባዊ ስብሰባው ላይ እንደሚገኙና በደብዳቤ ጥሪ እንደደረሳቸው የገለጸ ሲሆን ስማቸውንም በዝርዝር መጥቀሱ አይዘነጋም፡፡
እሁድ በሰማያዊ ፓርቲ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የተገኘው ሪፖርተራችን እንደታዘበው፣ ፓርቲው የገመተውን ያህል ታዳሚ አልተገኘለትም፡፡ ፓርቲው በመድረኩ እንደሚገኙ ከዘረዘራቸው ግለሰቦች መካከልም ጥቂቶች ብቻ መገኘታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል። አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣የስብሰባው ጥሪ እንደደረሳቸው ነገር ግን በግል ምክንያት ሊገኙ አለመቻላቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ አቶ ክቡር ገናም በተመሳሳይ ጥሪው ደርሷቸው፣ ከሃገር ውጪ በመሆናቸው መገኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ሞሼ ሰሙ ደግሞ ጥሪው አልደረሰኝም ብለዋል - ጥሪው ቢደርሳቸው ኖሮ ይገኙ እንደነበር በመግለጽ፡፡ ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ በበኩላቸው፤ጥሪው እንዳልደረሳቸውና አዲስ አድማስም ጥሪው ባልደረሳቸው ሁኔታ ፎቶግራፋቸውን ጭምር በመጠቀም ባሰራጨው ዘገባ ቅሬታ እንደተሰማቸው ለዝግጅት ክፍሉ አስታውቀዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ባለፈው ሳምንት በስም ተጠቅሰው ለተዘረዘሩት ታዋቂ ምሁራንና ግለሰቦች በሙሉ የጥሪ ደብዳቤ መላኩን ጠቁሞ፣ በትክክል መድረስ አለመድረሱን ግን ለዚህ ሥራ ከተመደቡት ሰዎች ጋር እንደገና እንደሚነጋገርበት ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡


Read 4457 times