Sunday, 10 December 2017 00:00

በ“አቶ መልከ-ጥፉ” የቁንጅና ውድድር ማስቪኑ ሃትሪክ ሰርቷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


        “የአለማችን ቁጥር አንድ ፉንጋ ተብዬ፣ የአገሬን ስም አስጠራለሁ!” ብሏል

   ባለማማር ውስጥ ያለውን ውበት የማሳየት ዓላማ ይዞ በዚምባቡዌ በየአመቱ በሚካሄደው የ“አቶ መልከ-ጥፉ - ዚምባቡዌ” የቁንጅና ውድድር ለሁለት ጊዜያት አሸናፊ የነበረው ሚሊያም ማስቪኑ የተባለው የአገሪቱ ዜጋ፤ዘንድሮም ክብሩን በማስጠበቅ ሃትሪክ መስራቱንና የፉንጋነቱን ዘውድ መድፋቱን ኦል አፍሪካ ዶት ኮም ዘግቧል፡፡
በመዲናዋ ሃራሬ ባለፈው እሁድ ምሽት ለአምስተኛ ጊዜ በተከናወነው የ2017 “አቶ መልከ-ጥፉ” የቁንጅና ውድድር ላይ በዕጩነት ከቀረቡ አራት ተወዳዳሪዎች መካከል አንደኛ በመውጣት ብሄራዊውን የፉንጋነት ዘውድ የደፋው ማስቪኑ፤ ከውድድሩ አዘጋጅ ድርጅት የ500 ዶላር እና የአንዲት ላም ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
“በመላው ዚምባቡዌ ከእኔ ጋር የሚስተካከል አስጠሊታ ሰው እንደሌለ ሳይታለም የተፈታ ነው!... በቀጣይ ይህንን ፉንጋ መልኬን ይዤ አገሬን በአለም መድረክ ላይ በኩራት ለማቆምና ስሟን ለማስጠራት የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ፤ የ2018 የአለማችን ፉንጋ ክብርን በመጎናጸፍ፣ የአገሬን ስም በአለም አደባባይ አስጠራለሁ!” ብሏል ማስቪኑ፤ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረገው ንግግር፡፡
የ2018 የአለማችን “አቶ መልከ-ጥፉ” የቁንጅና ውድድር በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድ የጠቆመው ዘገባው፤ በብሄራዊ ደረጃ አሸናፊ የሆኑ የተለያዩ አገራት መልከ-ጥፉዎች፣ አገራቸውን ወክለው እንደሚወዳደሩና ከፍተኛ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2687 times