Saturday, 09 December 2017 14:00

ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድር ዲያሬክተርና መሐንዲስ ኤርሚያስ አየለ ጋር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

17ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ከ 2 ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በድምቀት መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡ ከእቅድ አንስቶ በዝግጅትና በቅደምተከተል በሚከናወኑ ስራዎች ሙሉ 1 ዓመት የሚፈጀው ዋናው የ10 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫን በየዓመቱ ለማዘጋጀት የውድድሩ አዘጋጅ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ወጭ የሚያደርገው በጀት ከ7.5 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ታዋቂ አትሌቶችና ህዝብ አሳታፊ የሩጫ ውድድሮችን በማዘጋጀት ያለፉትን 17 ዓመታት በከፍተኛ እድገት የሚንቀሳቀሰው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከውድድሮቹ ጋር በተያያዘ የሚንቀሳቀስበት ሙሉ ገቢ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  በየዓመቱ የሚካሄዱ ከአስር በላይ ውድድሮችን በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄዱ  እየተሰባሰቡ የሚሰሩ፤ የሚያስተናግዱ ፤የሚያስተባብሩና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ከ200 በላይ ናቸው፡፡ ከእነሱ መካከል 60 ያህሉ  በቋሚነት እና በየጊዜዊነት በውድድር አዘጋጅነት እንደ ቡድን ተሰባስበው የሚሰሩ ናቸው፡፡ ይህን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተቋም በዋና ስራ አስኪያጅነት የበላይ ሃላፊ ሆኖ የሚመራው ከ5ኪሎ ዩኒቨርስቲ በመካኒካል መሐንዲስነት የተመረቀው  ኤርሚያስ አየለ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የውድድር ዲያሬክተር እና የበላይ አዘጋጅ ተብሎ በሚጠቀስ ማዕረግ የሚጠራው ኤርሚያስ፤  ላለፉት 7 ዓመታት  የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ሆኖ በወር 35432 ብር  ሙሉ ደሞዝ እየተከፈለው እየሰራ ሲሆን በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆኖም ያገለግላል፡፡ አቶ ኤርሚያስ አየለ  ስለ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  ከስፖርት አድማስ ጋር በስፋት ያደረገው ልዩ ቃለምልልስ ከዚህ በታች እንደቀረበው ነው፡፡

   ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር የተዋወቅክበት የመጀመርያው መነሻ አጋጣሚ ምንድነው?
ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተዋወቅኩት በ2001 እኤአ ውድድሩ በመጀመርያው ዓመት ላይ ሲካሄድ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመካኒካል ኢንጅነሪንግ ተመርቄ ስራ እያፈላለግኩ ነበር፡፡ በካምፓስ ቆይታዬ ከስፖርቱ ጋር ቅርበት ስለነበረኝ  ኳስን አዘውትሬ እጫወታለሁ፡፡ በተለይ በተማርኩበት የአምስት ኪሎ ካምፓስ የእግር ኳስ ቡድንን በማስተባበርና በውድድር በማሳተፍ ንቁ ተሳትፎ አደርግ ነበር፡፡ እናም በአምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ በነበርን የኢንጅነሪንግ ተማሪዎች መካከል በግቢ ውስጥ በግማሽ ሜዳ በምናደርገው ውድድር ስንሳተፍ በተለይ የምታወቀው በጣም በመሮጥ ነው፡፡ ኳስ ከያዝኩ በቃ የሚደርስብኝ  አልነበረም፡፡ በዚህ ውድድር ላይ የ4ኛ ዓመት ተማሪ በነበርኩበት ዓመት ኮከብ ግብ አግቢም መሆኔም ይታወሰኛል፡፡  ስለዚህም በካምፓስ ቆይታዬ ከእነዚህ ልምዶች በተያያዘ  ስፖርቱን በማዘወተሬ የተሟላ የአካል ብቃት ነበረኝ፡፡ እናም ተመርቄ ስራ በማፈላልግበት ጊዜ የነበረኝ ጉልበት እና ኃይል አነሳስቶኝ  ልክ እንደተመረቅኩ በመጀመርያው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ለመሳተፍ ፍላጎት ተፈጠረብኝና በቂ ዝግጅት እና ልምምድ መስራት ጀመርኩ፡፡ ሰፈሬ ጃን ሜዳ አካባቢ ስለነበር ሁሌም ጠዋት ወደ ሜዳው እየሄድኩ 2 ኪሎሜትር ስሮጥ እንዴት ይከብደኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡  ሯጮች በየቀኑ ለውድድር ሲዘጋጁ የሚያሳልፉትን ፈተና እመለከት ነበር፡፡ ጎን ለጎን በታላቁ ሩጫ ውድድር ለመሳተፍ እየተነሳሳሁ ማለት ነው፡፡ እናም ከውድድሩ ጋር የተዋወቅኩት ለመሳተፍ ከወሰንኩ በኋላ ነበር፡፡
የመጀመርያው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር የተዘጋጀው እንዴት ነበር? ከውጭ ሆነህ እንደተሳታፊ ስትታዘበው ማለቴ ነው?
1ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተዘጋጀው ሙሉ ለሙሉ ከውጭ በተገኘው ተመክሮ እና አሰራር እንደነበር አስታውሳለሁ። በጎዳና ላይ ሩጫው ለመሳተፍ የሚቻለው የመወዳደርያ ቁጥር በመግዛት ነበር፡፡ ይህ የውድድር ሂደት ዛሬም ቢሆን በብዙ አገራት  እንደዚያ ነው የሚሰራው፡፡ ተሳታፊ ሲመዘገብ ቁጥር ይገዛል ከዚያም በየራሱ ቲሸርት ላይ በ50 ብር የገዛውን የመወዳደርያ ቁጥር ለጥፎ ይወዳደራል፡፡  ያኔ ለተሳታፊዎች የታላቁ ሩጫ ቲሸርት የተሰጠው እንደሽልማት ከሜዳልያ ጋር  ውድድሩን ሲጨረስ ነበር። ይሁንና ይህ አይነቱ አሰራር አላስፈላጊ ግርግር ነበር የፈጠረው፡፡ ያልተወዳደረ ሁሉ በሽሚያ እና በግፊያ ቲሸርቱን ለመውሰድ ትርምስ ገባ። ስለሆነም ሜዳልያና ቲሸርቶቹን  በትክክል ተመዝግበው ለነበሩ ተሳታፊዎች መስጠት ባለመቻሉ  እንዲቋረጥ አስገድዷል፡፡ በአምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ የመካኒካል ኢንጅነሪንግ ዲን የነበሩ አቶ አዲስ የተባሉ ስፖርተኛ እና እጅግ ጥሩ ሰው በውድድሩ ተሳትፈው በነበረው ግርግር ቲሸርት እና ሜዳልያ ለመውሰድ ሳይችሉ በመቅረታቸው የተሰማቸውን ቁጭት ሲነግሩኝ ትዝ ይለኛል፡፡ በመጀመርያው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር አጨራረስ ላይ የነበረው ግርግርና ትርምስ ግን የተቋሙን የውድድር አመራር ሂደትና አሰራር ለመቀየር ምክንያት ሆኗል፡፡ በጎዳና ላይ ሩጫው በትክክል ምዝገባ አድርጎ የሚሳተፈውን ለመለየት ሲባልም  ተሳታፊዎች በተመሳሳይ የቲሸርት እንዲሮጡ ተወስኖ ዛሬ የውድድሩ አብይ መገለጫ ሊሆን ችሏል፡፡
በውድድር በመሳተፍ ከነበረህ ትውውቅ በኋላ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስራ ማስታወቂያ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ መውጣቱ  ወደ ተቋሙ በሰራተኝነት ለመቀላቀል ምክንያት እንደሆነህ በአንድ ወቅት ነግረሀኝ ነበር፡፡
በታላቁ ሩጫ የመጀመርያው የውድድር ዓመት ከተሳተፍኩ በኋላ ከ5 ኪሎ ዩኒቨርስቲ በመካኒካክ መሐንዲስነት በተመረቅኩበት ሙያ የኢትዮጵያ አየርመንገድ ሰራተኛ ሆኜ ተቀጠርኩ፡፡ በሁለተኛው ዓመት አልተሳተፍኩም ነበር፡፡ ከዚያም በ2003 እኤአ በ3ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እሮጥኩና ወደ ጎዳና ላይ ሩጫው ደንበኛነት ተመለስኩ፡፡ ከዓመት በኋላ 4ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ የአየር መንገድ ሰራተኛ  እንደሆንክ ቀጥያለሁ፡፡ በጎዳና ላይ ሩጫው በምርጥ ብቃት ለመሳተፍ ልምምድ እየሰራሁበት በነበረው ሰሞን አዲስ አድማስ ላይ አንድ ማስታወቂያ አነበብኩ። ምን ይላል? በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ውድድር ለ1 ሳምንት በበጎ ፈቃደኝነት ለሚሰሩ ባለሙያዎች የቀረበ የስራ ማስታወቂያ ነበር፡፡ የተጠየቀው መስፈርትም ዲግሪ ያለው፤ በፕሮፌሽናል ደረጃ ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ፤ ከኃይሌ ገብረስላሴ ጋር በቅርበት ተገናኝቶ ልዩ ልምድ የሚቀስምና የሚሰራ  የሚል ነበር፡፡ እንዳልከውም በአዲስ አድማስ የወጣው ጋዜጠኛ ወደ ተቋሙ በሰራተኝነት ለመግባት ወዲያኑ ፍላጎት ያሳደረብኝ ነበር፡፡ ከዚህ ፍላጎት በፊት በታላቁ ሩጫ የመጀመርያ እና 3ኛ ዓመት ውድድሮች ተሳትፊያለሁ፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት ከተቋሙ ጋር የምሰራበት እድል ከተፈጠረ ከኃይሌ ጋር የምገናኝበት እድል እንደማገኝ ከቢቢሲ ጋዜጠኞች ጋር ልሰራ የምችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር መገለፁ እጅግ አጓጓኝ፡፡ ከምሰራበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአንድ ሳምንት እረፍት ወስጄ በማስታወቂያው መሰረት የትምህርት ደረጃና የስራ ዘመኔን የሚገልፅ ሲቪ ፃፍኩ ለማመልከት ምሳ ሰዓት አካባቢ ታላቁ ሩጫ ቢሮ ሄድኩ፡፡ ሪቻርድ ኔሩካን ነበር በሩን ከፍቶልኝ ማመልከቻዬን የተቀበለኝ፡፡ በወቅቱ ያመለከትነው 6  ነበርን፡፡ ለቃለምልልስ ተቀጥረን በዚያው የቅጥ ሂደቱ ቀጠለና በመጨረሻው ሁለት አመልካቾች ተመረጥን፡፡ የሚገርመው ሁለታችንም መሃንዲሶች ነበርን እኔ መካኒካል ኢንጅነር ይደነቅ የተባለው ጓደኛዬ ደግሞ ሲቪል ኢንጅነር ፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮ ሁለታችንንም ቀጠረን፡፡
አስቀድሞ እንደነገርኩህ ስፖርት ውስጤ ያለ ነገር ነው፡፡ ከዩኒቨርስቲ ወጥቼም የስፖርት እንቅስቃሴ የማዘወትረው ዝንባሌዬ ነበር፡፡  በአየር መንገድ ፕላኒንግ እና ኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት  መስራት ከጀመርኩ በኋላ  በተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች ቀዝቃዛ ተሳትፎ የነበረውን ዲፓርትመንት ወዲያውኑ ነው የቀየርኩት፡፡ ያሉትን የስራ አጋሮች አስተባብሬ ቡድን በመመስረት ንቁ ተሳትፎ አድርጌ በውድድሮች እንዲሳተፍ ማድረጌን አስታውሳለሁ፡፡ ያኔ የፓይለቲንግ እና የማስተር ቴክኒሻን ዲፓርትመንት ጠንካራ ቡድን እንደነበራቸው አስታውሳለሁ፡፡ የእኛ ቡድንም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆን ችሏል፡፡ በአየር መንገድ በዚህ መልክ እየሰራሁ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ከገባሁ በኋላ ውድድሩ ከመካሄዱ በፊት በነበረው ሳምንት ለምንሰራቸው ተግባራት ከአየር መንገድ የእረፍት ፈቃድ ወስጄ ነበር የታላቁ ሩጫን ቢሮ ተቀላቀልኩ፡፡ እኔና ይደነቅ የተባለው ሌላው ተቀጣሪ ተቋሙን በበጎፈቃደኝነት ለማገልገል የገባን ቢሆንም ለሰባት ቀናት 800 ብር አበል ተከፍሎናል፡፡ የመጀመርያ ስራችን የነበረው  በውድድሩ የኦፕሬሽን እንቅስቃሴዎች ድጋፍ ሰጭ በመሆን መስራት ነው፡፡ ይህም የሆነው በ4ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ሲሆን በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ ውድድሩን ማስጀመራቸው እና ሽልማት መስጠታቸው የማስታውሰው ነበር፡፡  
ያኔ በ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫው በበላይ ሃላፊነት የውድድሩን አጠቃላይ የኦፕሬሽን ስራዎች ያከናውኑ የነበሩት ከእንግሊዝ የሚመጡ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች  በኢትዮጵውያን ባለሙያዎች አደራጅቶ ለመቀየር እንዴት ተቻለ?
ከእንግሊዝ አገር ከግሬት ኖርዝ ራን የሚመጡት ባለሙያዎች በ2001 እኤአ ከተደረገው 1ኛው ውድድር ጀምሮ እስከ 4ኛው ድረስ በሙሉ ሃላፊነት የኦፕሬሽን ስራዎችን ያከናውኑ ነበር፡፡ በወቅቱ ስራ አስኪያጅ ከነበረው ሪቻርድ ኔሩካር እና በምክትልነት አብሮት ከነበረው ጋሻው ዘርጋው እና ሌሎች 4 ኢትዮጵያውያን ጋር በውድድሩ የዝግጅት ሂደት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከግሬት ኖርዝ ራን የሩጫ ዝግጅት እና ኦፕሬሽን ቡድን ጋር ተቋሙ እየሰራ ቢቆይም ይህንን በኢትዮጵያን ባለሙያዎች አደራጅቶ ለመቀየር ፍላጎት እንደነበር ግን አስታውሳለሁ፡፡ በ2005 እኤአ ላይ 5ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ዝግጅት ሲጀመር ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ ከግሬት ኖርዝ ራን የሚመጣው ቡድን ተሳትፎውን እንደሰረዘው አሳወቀ፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የነበርን በጎ ፈቃደኞች እና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ውድድሩን የምናካሂድበት  አጋጣሚ ሊፈጠርም ቻለ፡፡ አስቀድሞ በተካሄዱት 4 የታላቁ ሩጫ ውድድሮች ስለ ውድድሩ የዝግጅት እና አፈፃጸም ሂደት በቂ እውቅት፤ ፍላጎት እና ልምድ ስለነበረን የግሬት ኖርዝ ራን ቡድን ከእንግሊዝ ድረስ በመምጣት የሚሰራውን ሁሉ ከእቅዱ ጀምርን ለማከናወን ብዙ አልተቸገርንም ነበር፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ በ2004 እኤአ ላይ የገባሁ ግዜ በኦፕሬሽን ስራው ለመሳተፍ ከእንግሊዝ ከግሬት ኖርዝ ራን የሚመጡት ከ15 እና ከ20 ዓመታት በላይ በጎዳና ላይ ሩጫ የኦፕሬሽን ስራ ከሚሰሩ 6 እና ሰባት ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ድሮ ኖቫ  የሚባለው ሲሆን አሁን ግሬት ራን ካምፓኒ ነው፡፡ ከለንደን ማራቶን አዘጋጆች ቀጥሎ ግሬት ኖርዝ ራን የዓለም ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ አዘጋጆች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ በዓለም በግዝፈቱ ሁለተኛ ደረጃ ያለውን የኒውካስትል ግማሽ ማራቶን የጎዳና ላይ ሩጫ በሚያዘጋጀው ግሬት ኖርዝ ራን የሚመራው ኒውካስትል ማራቶን ላይ ትልልቅ የኢትዮጵያ አትሌቶች በተደጋጋሚ ተሳትፈዋል፡፡ እነ ጥሩነሽ፤ ቀነኒሳ ያሸነፉበት እነ ኃይሌ የሮጡበት፤ በአይኤኤፍ ወርቃማ ደረጃ ያለውና በተሳታፊዎቹ ብዛት የዓለማችን ግዙፍ ግማሽ ማራቶን ነው፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ እስከ 2004 እኤአ  ከሰሩት የግሬት ኖርዝ ራን 6 እና 7 ባለሙያዎች ጋር  በእኛ በኩል ሪቻርድ ኔርኳር፤ ጋሻው ዘርጋው ፤ እኔ እና ሲቪል መሐንዲስ የሆነውና ከእኔ ጋር በበጎ ፈቃደኝነት ተቋሙን የተቀላቀለው ይደነቅ ሌላ ሁለት ድጋፍ ሰጭዎች 5 እና 6 ነበርን ማለት ነው፡፡ በ4ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ ከእንግሊዛዊያኑ ጋር ከሰራን ከ1 ወር በኋላ  የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ ለእረፍት ወዴት ለመሄድ ትፈልጋለህ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እሰራ ስለነበር ነፃ ትኬቶች እንዳሉኝና  ወደ አውሮፓ የመሄድ ፍላጎት እንዳለኝ ለሪቻርድ ስነግረው ኃይሌ በግሬት ማንችስተር ራን ስለሚሳተፍ ከእሱ ጋር ለምን አብረህ አትሄድም የሆቴልና የምግብ ወጭዎችን እንሸፍናለን አለኝ፡፡ በግሬት ማንችስተር ራን በሚኖርህ ልምድ ስለውድድር አዘገጃጀት ብዙ ትምህርቶች ታገኛለህ ነበር የሪቻርድ ምክር፡፡ ሁሉ ነገር የተመቻቸቸ በመሆኑ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ድጋፍ  በማንችስተር ግሬት ራን ከኃይሌ የውድድር ተሳትፎ ጋር በማያያዝ የእረፍት ጉዞዬን ለማድረግ ተስማማን፡፡ በጉዞዬም ብዙ እውቀቶችን በውድድር አዘጋጅነት  ተማርኩና ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ፡፡ ከዚያም በኋላ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሌሎች ውድድሮች የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን መስራቴን ቀጠልኩ፡፡ በዚያው ዓመትም ሪቻርድ  በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ  የሚካሄድ ሩጫ ውድድርን ሙሉ ለሙሉ በመምራት እንዳስተናግድ መደበኝ፡፡ በብዙ ሃላፊነት ልሰራ የቻልኩበት የመጀመርያው የታላቁ ሩጫ ውድድር ሲሆን ይህን ሃላፊነትም በአግባቡ ተወጣሁኝ። ከዚያም 5ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሊካሄድ  ሁለት ወራት አካባቢ ሲቀሩ  በውድድሩ አዘጋጅነት ይሰራ የነበረው ጋሻው ዘርጋው ለትምህርት ወደ ካናዳ መሄዱን ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ ተቋሙን እንድቀላቀል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ ወዲያውኑ ምላሽ ለመስጠት የሚከብድ ሆነብኝ፡፡ በተማርኩበት የመካኒካል ኢንጅነሪንግ በአየር መንገድ ‹‹የሜንተናንስ ፕሮግራም ኢንጂነር›› ሆኜ እየሰራሁ ነበር። በዚህ ሙያ በፈጣን እድገት ላይ ስለነበርኩ እሱን ትቼ ሙሉ በሙሉ ወደ ስፖርት እና የማርኬቲንግ ስራዎች ለመግባት መወሰን ይጠበቅብኛል፡፡ ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሃላፊዎች  ውሳኔዬን ለማሳወቅ በደንብ ማሰብ አለብኝ  አልኳቸው፡፡ ያቀረቡልኝን ጥያቄ ለመቀበል ከጅምሩ ተፈታትኖኛል፡፡ ምክንያቱም በአየር መንገድ ስሰራ የውጭ ጉዞ እድል እለ፤ ለቤተሰብ ብዙ ጥቅማጥቅሞች ይገኛል፤ የሙያ  እድገቱ እና የተሻለ የደሞዝ ክፍያውም ለመተው የሚከብድ ሆኖብኝ ነበር። ከታላቁ ሩጫ ግን የቀረበልኝን ሃላፊነት ለመቀበል በአየር መንገድ ያለኝን ስራ ወዲያውኑ ከመተዌ በፊት ሁለት ወራት እንዲሰጠኝ ጠየቅኩ፡፡ እነ ኃይሌ እና ሪቻርድ በሙሉ ተቀጣሪነት በታላቁ ሩጫ ለመስራት ከወሰንኩ በሁለት እና በሶስት ዓመት ውስጥ በተለይ ከስፖርት ማኔጅመንት ጋር በተያያዘ በውጭ ከፍተኛ የትምህርት እድል እንደማገኝ  ገለፁልኝ፡፡ በመጨረሻም ተስማማን፡፡ በ2005 እአኤአ በ5ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ሩጫ  ስራ ጀመርኩ፡፡ ከ2 ዓመት በኋላ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ድጋፍ sport and Leisure Management ወይም በስፖርት እና መዝናኛ አስተዳደር ላይ የሚያተኩር ከፍተኛ ትምህርት በስኮትላንድ ኤደንብራ ዩኒቨርስቲ ለ1 ዓመት የተማርኩበትን እድል አገኘሁ፡፡ በምማርበት ወቅት ጎን ለጎን ከትልልቅ የውድድር አዘጋጆች ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች በመገናኘት ከፍተኛ ልምድ ማካበት የቻልኩ ሲሆን እንደጨረስኩም በስኮትላንድ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለ3 ወራት የሰራሁበትን ልምድ አግኝቺያለሁ፡፡
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሃላፊነት መስራት  መስራት እንዴት ጀመርክ? ከፈጠርካቸው አዳዲስ አሰራሮች መካከል የቱን ትጠቅሳለህ?  በአጠቃላይ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ስለምትከተሉትን የቡድንና የኦፕሬሽን እንቅስቃሴዎች አብራራልኝ?
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ በከፍተኛ ሃላፊነት መስራት የጀመርኩት በ2010 እኤአ ላይ የተቋሙ የውድድር ዲያሬክተር እና ስራ አስኪያጅ የሆነው  ሪቻርድ ከሃላፊነቱ መልቀቁን ተከትሎ ነው፡፡ 10ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  ሊካሄድ 5 ወራት ይቀሩ ነበር፡፡ የውድድር ዲያሬክተር እና ስራ አስኪያጅ ሆኜ ሃላፊነቱን በመረከብ ዝግጅታችን ቀጠለና በተሳካ ሁኔታ የመጀመርያውን የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርን በሙሉ ሃላፊነት ከተቋሙ የሰራተኞች ቡድን ጋር ለማካሄድ በቃን፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ 2017 እኤአ  ድረስ የተካሄዱትን 7 የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫዎችን በበላይ ሃላፊነት ለመምራት ችያለሁ፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በዓመት ውስጥ በሚካሄዱ የተለያዩ ውድድሮቻችን በቋሚነት እና በጊዜያዊነት አብረውን የሚሰሩ ሰራተኞች ቡድን በዘላቂ ልምድ እና ተመክሮ እየሰሩ የሚቀጥሉበትን የአሰራር ሂደት በማይናወፅ መሰረት መገንባት ችለናል፡፡ እንግዲህ ዛሬ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮ ቋሚ ሰራተኞች ብዛታቸው 13 ነው፡፡ በውድድር አዘጋጅ ቡድን ውስጥ ደግሞ ከ25 እስከ 30 የሚሆኑና በጊዜያዊነት ከተቋሙ ጋር የሚሰሩ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎችን በማሰባሰብ እንሰራለን፡፡
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ብዙዎችን ስራዎች በቡድን ነው የምንሰራው፡፡ ከፈጠርካቸው አዳዲስ አሰራሮች መካከል ላልከው ለምሳሌ ከኮካ ኮላ ጋር በመተባበር በ3 ተከታታይ ውድድሮች በሰራንበት ወቅት በወቅቱ ከነበረው የዓለም አቀፉ ኩባንያ ከፍተኛ ስራ አስፈፃሚ ደቡብ አፍሪካዊው ግሬክ ኤልሰን ጋር ሆነን የፈጠርናቸው አዳዲስ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል። የኮካ ኮላው ውድድር ልክ እንደ ዳይመንድ ሊግ በተለያዩ ከተሞች ያካሄድንበት፤ ተሳታፊዎች የውድድር ርቀቱን ጨርሰው የሚገቡበትን ሰዓት የሚመዘግብ ቺፕ የተጠቀምንበት ፤ በሽልማት አሰጣጣችን በ3 ከተሞች በተካሄዱ ውድድሮች የተሳተፉትን በእጣ አወዳድረን ላፕ ቶፕ፤ ቲቪ ፤ ብስክሌት እና ሌሎች ስጦታዎች የሸለምንበት እና እንደፕሮጀክት የሰራንበት ነበር፡፡ በውድድር ቀን ዋናዎቹ የኦፕሬሽን ስራዎች የሚባሉት የተሳታፊዎችን አጀማመር በመቆጣጠር በአግባቡ ማሰለፍ፤ የውድድሩ ስፖንሰሮች ልዩ ልዩ የንግድ ምልክቶችና መልዕክቶች በተመረጡ ቦታዎች ላይ በአግባቡ መሰቃቀል፤ ተሳታፊዎችን በስነስርዓት አሰልፎ ውድድሩን ሙሉ ለሙሉ ማስጀመርና ከዚያም ሁሉም መነሻውን ሲያልፍ ወዲያውኑ የውድድር መጨረሻ መግቢያውን ማዘጋጀትን የሚያካትት ነው፡፡ በኦፕሬሽን እንቅስቃሴው ሁለት ዋና ዋና ተግባራት አሉ፡፡ የመጀመርያው ስራ ውድድር በሚካሄድበት መስቀል አደባባይ መንገዱ ከተዘጋ በኋላ ተወዳዳሪዎች ከመምጣታቸው በፊት እሁድ ጠዋት የምንሰራው ነው፡፡ ከ11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ በአደባባዩ ተገኝተን የምናከናወናቸው ስራዎች set up ይባላል፡፡ የውድድሩ መነሻና መጨረሻ አካባቢ የተለያዩ መልክቶች እና የብራንዲንግ ቢልቦርዶችና ፖስተሮች የምንሰቅልበት ነው፡፡ ልክ ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ ሁሉም ሰው ከሄደ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሁለተኛው ስራ እንገባለን፡፡ የውድድሩን የመጨረሻ መግቢያ፤ የሚዲያ፤ የቪድዮ እና የፎቶ ባለሙያዎችን ቦታ ቦታ በማስያዝ የምናሰናዳበት ነው፡፡
አንድ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ከእቅድ አንስቶ እስከ ውድድሩ ቀን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ 1 ሙሉ ዓመት እንሰራለን፡፡ በ1 ዓመት ውስጥ በመጀመርያ መጨረሻ ላይ ያካሄድነውን ውድድር የነበሩ ተመክሮዎችን በዝርዝር በመመልከት የምንገመገምበት ስራ ነው። ከዚያም ከስፖንሰሮቻችን  ጋር ያሉትን በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚተገበሩ የውል ስምምነቶችን የምናፀናበት እና በአጋርነት አዳዲስ ውሎችን ለመፈፀም እንቀሳቀሳለን፡፡ አሁን ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም ለምናካሂደው 18ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር የተሳታፊዎች ምዝገባ የምንጀምረው ከ6 ወራት በኋላ ነው፡፡ ለምዝገባ ዝግጅት ስፖንሰሮችን መሰብሰብ፤ የተሳታፊዎችን ቁጥር መወሰን እና ቅድሚያ የምሰጣቸው የስራ ሂደቶች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ለዋናው የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ግብዓት የሚሆኑና በብዛት የምንጠቀምባቸውን መሳርያዎች፤ ቁሳቁሶች  ወቅታዊ ዋጋ እና አቅርቦት በማጥናት ለውሳኔ የምንዘጋጅባቸው ስራዎች ይኖራሉ። 40 እቃ አቅራቢዎች፤ 46 የፅዳት ሰራተኞች እንዲሁም 10 ዲጄዎች እና ባንዶች የውድድሩ አካል ሆነው አብረውን የሚሰሩ ሲሆን እነዚህ አጋሮቻችን በተለያዩ በትዛዝ የሚሰሩአቸውን ስራዎች ላይ አስቀድመን ማነጋገገር ለውሳኔያችን ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ በተለይ የቲሸርት ዲዛይን እና ህትመት፤ የሜዳልያ ቀረፃ እና አመራረት በአንድ ዓመት እቅድ የሚሰሩ ናቸው፡፡ የመሮጫ ቲሸርቶችን የሚሰሩበትን ማቴርያል፡ ቀለም፤ ዲዛይን በየዓመቱ ልዩ እንዲሆን ተጨንቀን ነው የምንሰራው፡፡ ላለፉት 4 ዓመታት በቲሸርቱ ጨርቅ ላይ ከአንድ ኩባንያ ጋር በስምምነት እየሰራን ቆይተናል፡፡ ከዚህ ኩባንያ ብዙ አማራጭ ቲሸርቶች ቀርበው ነው  ከስምምነት የምንደርሰው፡፡ በውጭ ምንዛሬ ችግር ነው እንጅ  በፎርጅድና በህገወጥ የሚሰራ ቲሸርት እንዳይኖር ጨርቆችን ከውጭ የማስመጣት ፍላጎት ነበረን፡፡
አስቀድመን ከሰራናቸው በተለየ ሁኔታ  የምጠቅሰው ዘንድሮ ቀጣዩ ውድድር የሚካሄድበትን ቀን  በ17ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማግስት መወሰናችንን ነው፡፡ ጎን ለጎን ከውድድሩ በኋላ በየዓመቱ ለማካሄድ በወሰንነው  ግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት ተያይዞ ነው፡፡ ዘንድሮ ውድድሩንና ኮንሰርቱን ያካሄድነው በፆም ወቅት ነበር፡፡ በሚቀጥለው ዓመት በፆም ቀን እንዲሆን አልፈለግንም። ስለዚህም  ቀኑን አሸጋሽገን ውድድሩና ኮንሰርቱ በተመቸ እለት እንዲካሄድ ወስነናል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አይኤኤኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫውን  በሞናኮ ከሚካሄድበት ቀን ጋር ተገጣጥሞ የፕሮግራም መደራረረብ እንዳይፈጠር በማለት ቀኑን ወስነናል፡፡
በ17ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ ሁለት ተሳታፊዎች በድንገተኛ ህመም ህይወታቸው አልፏል፡፡ ይህ አይነቱ አሳዛኝ አጋጣሚ ወደፊት እንዳያጋጥም ምን ለመስራት አስባችኋል?
በ17 ዓመታት ታሪካችን እንዲህ አይነት አሳዛኝ ክስተት አጋጥሞን አያውቅም፡፡ ከሟቾቹ አንደኛው ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ መኮንን አምዴ የሚባሉ ናቸው፡፡ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት የሚያስተምሩ፤ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመስራት  በአንድ ወቅት ማንዋልም አዘጋጅተውልናል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ለብሄራዊ ቡድን ለመጫወት የበቃ የቦክስ ስፖርተኛ ነው፡፡ ስለዚህም ለኃይሌና ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሰራተኞች በውድድር ላይ ሁለቱ ሰዎች የህመም ችግር ገጥሟቸው በሆስፒታል መሞታቸው ያልተጠበቀና አሳዛኝ ዜና ነበር፡፡ በሰዎቹ ሞት ላይ የእኛ የውድድር አዘጋጆች ጥፋት የለበትም፡፡ ከጤና ችግር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ግን እንደዚያም ባይሆን ሁለቱም ተሳታፊዎች በደረሰባቸው ሞት ሃዘናችንን በመግለፅ እና የቤተሰብ አስተዳዳሪነታቸውን ከግምት በማስገባት በታላቁ ሩጫ በኩል ለቤተሰቦቻቸው ለእያንዳንዳቸው 100ሺ ብር ሰጥተናል፡፡ በቀጣይ ዓመት ከውድድሩ በፊት የሚደረጉ የ 1 ሳምንት የልምምድ ዝግጅቶችን በማጠናከር  እና ቲሸርቶችን በምናከፋፍልበት የስፖርት ኤክስፖ ላይ ለሁሉም ተሳታፊዎች የጤና ምርመራ የምናደርግበትን አሰራር ለመዘርጋት ወስነናል፡፡ ይህን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድም ከተለያዩ የጤና ተቋማት ጋር ምክክር ማድረግ ጀምረናል፡፡
የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው 10ሺ ተወዳዳሪዎች በማሳተፍ ከ17 ዓመታት በፊት እንደተጀመረ ይታወቃል፡፡  ከዚያ በኋላ  የተሳታፊዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነበር፡፡ ከ10ሺ ወደ 18ሺ፤ 25 ሺ፤ 35 ሺ፤ 38ሺ፤  40ሺ፤  42ሺ እያለ ዘንድሮ ደግሞ 44ሺ ደርሷል፡፡ በየዓመቱ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው እየበዙ መጥተዋል… ለምን ተሳታፊዎችን 50ሺና ከዚያ በላይ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በእናንተ በኩል ምን የታሰበ ነገር አለ?
የተሳትፎ ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ዘንድሮ ምዝገባውን ጨርሰን ከዘጋን በኋላ ከ15 እስከ 20ሺ የሚደርስ ተሳታፊ ለመመዝገብ ያቀረበውን ጥያቄ ሳንቀበል ቀርተናል፡፡ ይህም በድርጅት 30 እና 400 ሆነው የሚመጡ፤ በግላቸው ምዝገባ ለማረግ በየቀኑ ወደ ቢሯችን የሚመጡትን በመገመት ነው፡፡ የመጣውን ተሳታፊ ሁሉ መዝግበን ብናሳተፍ ገቢያችንን የሚጨምር ሊሆን ይችላል፡፡ በውድድሩ ላይ የምናሳትፋቸው ብዛታቸው 60ሺ ቢደርስ በኒውዮርክ ጎዳናዎች ከሚካሄደው ውድድር በመብለጥ በዓለም ግዙፉ የጎዳና ላይ ሩጫ እንሆናለን፡፡ ይሁንና  የተሳታፊዎችን ቁጥር  አላግባብ በመጨመር የምንሰራበት ሁኔታ የለም፡፡ ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ በሚያስችሉን ቅድመ ሁኔታዎች የተሳታፊዎችን ብዛት ስለምንወስን ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ  የውድድሩ መነሻና መድረሻ የሆነው መስቀል አደባባይ  አሁን 44ሺ ሰዎችን ለማስተናገድ መብቃቱን አስቀድመን በማቀድ በፈጠርነው የውድድር ሂደት የፈተሽንበት ነው፡፡ ስለዚህም የጎዳና ላይ ሩጫው በሁለት ምድብ በተካፋፈለ አዲስ አሯሯጥ እንዲካሄድ አድርገነዋል። የመጀመርያዎቹ በአረንጓዴ መነሻ የሚሮጡትና ከ1 ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 10 ኪሎ ሜትሩን የሚጨርሱ ሲሆኑ ብዛታቸው 7000 ነበር፡፡  በሌላ በኩል በሁለተኛው ምድብ በአቀይ መነሻ ለመሮጥ 37ሺ ተሳታፊዎች ተመዝግበውበት  ውድድሩን ለመጨረስ ከ1 ሰአት በላይ ጊዜ የሚወስድባቸው ሆነዋል፡፡ ከፀጥታ እና ከደህንነት አንፃር፤ ውድድሩ የሚካሄድባቸው ጎዳናዎች በተወሰነ ጊዜ ተዘግተው የሚቆዩበትን ሁኔታ አመዛዝኖ ለከተማዋ እንቅስቃሴ ከፍት ለማድረግ ነው፡፡
በሚቀጥለው ዓመት እንደውም በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን እስከሚጨርሱ ድረስ የምንሰራበትን የግዜ ገደብ በይፋ በመወሰን ለመስራት አስበናል፡፡ ተሳታፊዎች ውድድሩን በአግባቡ ሰዓታቸውን ተጠቅመው እንደመጨረስ በተለያዩ ሁኔታዎች እና ተግባራት እየዘገዩ ጎዳናዎች ተዘግተው የሚቆዩበትን ጊዜ በማራዘም ተፅእኖ መፍጠራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ስለዚህ በውድድሩ  ላይ ተሳታፊዎች ውድድሩን እስከስንት ሰዓት እንደሚጨርሱ በመወሰን እንደአዘጋጅ የምንጠብቅበትን ሰዓት እንወስናል፡፡ ከዓለም አቀፍ ውድድር ለመረዳት እንደሚቻለው በብዙ የማራቶን ውድድሮች ከጅምር አንስቶ እስኪያልቅ ለ7 ሰዓታት ይጠበቃል፡፡ ለግማሽ ማራቶን ደግሞ ከ3 ተኩል ሰዓታት የማይበልጥ የጥበቃ ጊዜ ነው የሚሰጠው፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ10 ኪ ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ተሳታፊዎችን ሙሉ ለሙሉ እስኪጨርሱ ለ6 ሰዓታት ጠብቀን ሰርተናል፡፡ ደረጃውን በጠበቀ አሰራር የውድድሩ አዘጋጆች ሁሉም ተሳታፊዎች እንዲጨርሱ መጠበቅ ያለብን 2 እና 2 ተኩል ሰዓታት ብቻ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም በሚቀጥለው ዓመት በዋናው ውድድር 2 ሰዓት ተኩል ጀምረን 5 ሰዓት ተኩል ላይ ሙሉ ውድድሩን ጨርሰን ለመነሳት አቅደናል፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ ከመደበነው ውድድር የመጨረሻ ሰዓት ውጭ ዘግይቶ ለሚገባ ተሳታፊ ሃላፊነቱን አንወስድም ነው፡፡  በአጠቃላይ በታላቁ ሩጫ የሚሳተፍ ሁሉ ሳይቆም በርምጃ ሆነ በሶምሶማ ሮጦ ውድድሩን በ2 ሰዓት ጊዜ ውስጥ እንዲጨርስ ነው፡፡ ይህም  ውድድሩን በተገቢው ጊዜ ጨርሰን የተዘጉ መንገዶች ተከፍተው የከተማው እንቅስቃሴ ሳይስተጓጉል እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡
ወደፊት የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫውን በተለይ በክልል ከተሞች የማካሄድ እቅድ አላችሁ?
ከዋናው የ10 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ባሻገር ሌሎች የተለያዩ ውድድሮች በተለያየዩ የአገሪቱ ከተሞች እና ክልሎች እየተስፋፉ መምጣታቸውም ሌላው የስፖርት ባህል መስፋፋትን የሚያመለክት ነው፡፡እንደሚታወቅው በየዓመቱ ከዋናው የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ባሻገር በዓመት ውስጥ ከ10 በላይ ውድድሮች በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚዘጋጁ ሲሆን  እስከ 60ሺ ስፖርተኞችን የሚያሳትፉ ሆነዋል፡፡ በአዲስ አበባ ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሜ ሩጫ፤ ለመንገድ ደህንነት የምናዘጋጀው የቀለበት መንገድ ሩጫ፤ የአውሮፓ ቀን የልጆች ሩጫ፤ እያስተዳደርን ያለው የኮፓ ኮካ ኮላ ውድድር እንዲሁም የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን  ከዋናው የ10 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ባሻገር በመላው አገሪቱ የስፖርቱን ባህል ለማስፋፋት የምናካሂዳቸው ውድድሮች ናቸው፡፡ ባለፉት 17 ዓመታት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያካሄድናቸው ውድድሮች ብዛት ከ100 በላይ ሲሆን በእነዚህ ውድድሮች ከ550ሺ በላይ  ስፖርተኞች መሳተፋቸውን ስትገምት ምን ያህል በአገሪቱ ህዝብ የስፖርት ባህልን የምናስፋፋበት ተቋም ላይ እየሰራን እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡ ውድድሮችን በክልል ከተሞች እያስፋፉ መቀጠልን ስንሰራበት የቆየንብት ነው፡፡ በሃዋሳ ከተማ ዓመታዊውን የግማሽ ማራቶን ለ7 ጊዜ ዘንድሮ እንካሂዳለን፡፡ ከዚያም በቅደም ተከተል ለውድድር መስተንግዶ የሚሆኑ ከተሞችን እየመረጥን ለመስራት እንፈልጋለን፡፡ በባህርዳር፤ መቀሌ ግዙፉን የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ለመጀመር በከተሞቹ አስተዳደርም በእኛ በኩል ፍላጎት አለ። ዘንድሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 75ኛ ዓመቱን ለማክበር ሲወስን  ከታላቁ ሩጫ  በኢትዮጵያ ጋር በአምስት የክልል ከተሞች በአጋርነት ለመስራት እና የአልማዝ እዮቤልዩ ክብረበዓሉ አካል እንዲሆን ማድረጉንም መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ በሃዋሳ፤ ባህርዳር፤ መቀሌ ፤ አዳማ እና አዲስ አበባ  እነዚህን ውድድሮች የሚያስተናግዱ ከተሞች ናቸው፡፡ እና እነዚህን ውድድሮች ከጨረስን በኋላ የ10 ኪ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫውን ከአዲስ አበባ ከተማ ባሻገር በተለይ በባህርዳር ወይም በመቀሌ ከተሞች ለመጀመር አቅደናል፡፡ የጎዳና ላይ ሩጫውን በክልል ከተሞች እንደአዲስ ለመጀመር የከተሞቹን የመስተንግዶ አቅም፤ የጎዳናዎች አመቺነት፤ በአጋርነት አብረውን የሚሰሩ ስፖንሰሮችና ሌሎች ሁኔታዎችን በጥናት እየመረመርን ነው፡፡ በአንዱ ከተማ ጀምረን ለሁለት እና ለሶስት ዓመታት አጠናክረን ከሰራን በኋላ በሌላ አዲስ ከተማ በተመሳሳይ እየጀመርን እንቀጥላለን፡፡ ወደፊት ይህን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስፖርት ባህል  በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ለማስፋፋትም እንፈልጋለን፡፡  በተለያዩ አቅጣጫዎች ይህን እቅዳችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራን ሲሆን ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ልንጀምር ያሰብነው በጅቡቲ ነው፡፡ ከጅቡቲ ጋር ከወደብ  ትራንስፖርት ጋር ያለውን ቅርበት በመጠቀም ዓመታዊ ውድድር በቅርቡ ለማዘጋጀት ወስነናል፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ውድድር ሳይስተጓጎል ዓመቱን እየጠበቀ፤ በአዳዲስ አሰራሮች እየተጠናከረ፤ በውድድር ድምቀቱ እና ድባቡ እየገዘፈ ቀጥሏል፡፡ በአገሪቱ ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ የሚጫወትም ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ በፕሮፌሽናል አደረጃጀት እየተመራ የሚካሄድ ደረጃውን የጠበቀ የጎዳና ላይ ሩጫ ሆኗል፡፡ የተቋሙ እንቅስቃሴ በአገሪቱ ልዩ የስፖርት ባህልም እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል? በውድድር አዘገጃጀት ምን አይነት ስኬቶችስ ተገኝተዋል?
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአገራችን ስፖርት አዎ ትልቅ ባህል እየሆነ የመጣ ነው፡፡ በየዓመቱ ከውድድር የማይቀሩ ደንበኞችን አፍርቷል፡፡  በግሉ፤ ከቤተሰብ ጋር ከሙያ ባልደረቦቹ እና ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ውድድሩን በናፍቆት እየጠበቀ በየዓመቱ የሚሳተፍ ሁሉም ነው፡፡ በየዓመቱ ያለማቋረጥ የሚሳተፉ ደንበኞቻችን ከ30ሺ በላይ ይሆናሉ፡፡ ታላቁ ሩጫን ባህላቸው ያደረጉ ደንበኞቻችን በሶስት መደብ ልንከፍላቸው ይቻላል፡፡ የመጀመርያዎቹ ስራቸው ፕሮፌሽናል የሆኑ ሯጮች ናቸው፡፡ በክለብ የሚሰሩ እና ያለ ክፍያ በነፃ ውድድሩን ለመሳተፍ በኮታ የምንመዘግባቸው ናቸው። ለግል ተወዳዳሪዎች እጣ እያወጣን የተሳትፎ እድል እንሰጣለን። በውድድሩ ላይ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ትልልቅ አትሌቶች የሚሳተፉበት ሁኔታ እንደባህል እያደገ መጥቷል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች የምንሰጠውን ሽልማት ወደ 100ሺ ብር ማሳደጋችን ይህን የፕሮፌሽናል አትሌቶች የተሳትፎ ጉጉት እና ባህል የሚጨምረው ነው፡፡ በተጨማሪም እውቅ አትሌቶች በእኛ ውድድር ተሳትፈው በውጭ በተለያዩ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ለሚሳተፉ የገቡበትን ሰዓት አጣቅሰን የድጋፍ ደብዳቤ እየሰጠን ትኩረት እንዲሰጡት አድርጎናል፡፡
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከ10 በላይ የኦሎምፒክ ወይም የዓለም ሻምፒዮን የሆኑ አትሌቶች እየወጡ መሆናቸውም ሌላው የውድድራችን ትልቅ ደረጃ እና ስኬት ነው፡፡ በዋናው የአትሌቶች ውድድር በወንዶች ምድብ የመጀመርያው አሸናፊ የውድድሩ የበላይ ጠባቂና መስራች ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን በሴቶች ምድብ ብርሃኔ አደሬ ነበረች፡፡ በ2ኛው በወንዶች ምድብ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም በሴቶች ወርቅነሽ ኪዳኔ፤ በ3ኛው በወንዶች ምድብ ስለሺ ስህን በሴቶች ምድብ  ጥሩነሽ ዲባባ፤ በ7ኛው ማራቶኒስቱ ፀጋዬ ከበደ ከውድድሩ አሸናፊ ታላላቅ አትሌቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ምርጥ የማራቶን ሯጮች መካከል በሴቶች አበሩ ከበደ፤ ድሬ ቱኔ እና ጠይባ ኢርኬሶ እንዲሁም በወንዶች ቻላ ደቻሳ እና ጌቱ ፈለቀ  እንዲሁም የዳመንድ ሊጉ አሸናፊ ሃጎስ ገብረህይወት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተሳትፎ ታሪካቸው ወደ ስኬት ለመውጣት ከቻሉት አትሌቶች ይገኙበታል። ከ10 በላይ ታዋቂ የዓለም አትሌቲክስ ማናጀሮች በ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ እየተገኙ አትሌቶች ለመመልመል የሚጠቀሙበት አመቺ መድረክ እየሆነ መምጣቱም ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ግምት የሚሰጠው እና በውድድሩ ጥሩ ደረጃ ያገኘ አትሌት በሌላ ዓለም አቀፍ ውድድር የመሳተፍ እድሉ ሰፊ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ዛሬ የጎዳና ላይ ሩጫው በአሁኑ ወቅት በዓለማችን መሮጥ አለባቸው ከተባሉ 10 የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች አንዱ ነው። የአፍሪካ ግዙፉ የጎዳና ላይ ሩጫ ተብሎ ከመጠቀሱም በላይ አንድ ቀለም ቲሸርት በሚለብሱ ተሳታፊዎቹ የአፍሪካ አስደናቂው የአትሌቲክስ መድረክም ተብሏል፡፡ በ2005 እኤአ ላይ የዓለም አቀፉ የማራቶንና የረጅም ርቀት ሩጫዎች ማህበር AIMS   አባል እንደሆንን የሚታወቅ ሲሆን ማህበሩ በ90 አገራት 300 መሰል የሩጫ ውድድሮችን ያሰባሰበ በመሆኑ የተቋሙን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ያጠናከረ ነው፡፡
ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ የብሮድካስት ኩባንያ ዲኤስቲቪ፤ ፋና ብሮድካቲንግ ኮርፖሬሽን፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፤ ሌሎች በሩጫ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ተቋማት፤ ህትመቶች እና የሚዲያ አጋሮች በየዓመቱ የሚሰጡትም ትኩረት ከጠንካራ ተመክሮዎቹ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ለ10 ኪ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው የዲኤስቲቪው ሱፕር ስፖርት የ52 ደቂቃዎች ስርጭት እንደሚሰራ የሚታወቅ ሲሆን በኢቢሲም በኩልም በየዓመቱ በየውድድሩ ቀን የሚኖረው የ2 ሰዓታት የቀጥታ ስርጭት የሚኖረውን የገፅታ ግንባታ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በቱሪዝም ገቢ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለውም የሚታወቅ ነው፡፡ ዘንድሮ ከ26 የተለያዩ አገራት በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ እንደመጡ ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ ውድድሩ ላይ እስከ 500 የውጭ አገር ዜጎች በአማካይ በሚሳተፉበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በየጊዜው ታላላቅ የክብር እንግዶችን ከውጭ እና ከአገር ውስጥ በማሳተፍም የጎዳና ላይ ሩጫው ስኬታማ  መሆኑንም ማንሳት ይቻላል፡፡  ዘንድሮ ሁለቱ የኬንያ አትሌቶች ቪቪያን ቼሮይት እና ሎራንህ ኪፕላጋት መጥተዋል፡፡ ከዓመት በፊት በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ በ3ሺ መሰናክል የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው  አትሌት ዢን ዋን እና ታዋቂው የረጅም ርቀት፤ የማራቶን ሯጭ የሆነው ሄንድሪክ ራማላ ከደቡብ አፍሪካው በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ ፖል ቴርጋት፤ ገብሬላ ዛቦ፤ ካሮሊና ክሉፍት፤ ዴቭ ሞርክሩፍት፤ ፓውላ ራድክሊፍ፤ የኒውዮርክ ማራቶን ዲያሬክተር ሜሪ ዊተንበርግ፤ የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት፤ እንዲሁም የኬንያዎቹ አትሌቶች  ካተሪን ንድሬባ፤ ኤሊውድ ኪፕቾጌ፤ በጎዳና ላይ ሩጫው በክብር እንግድነት ከተገኙና ውድድሩን ካስጀመሩ የዓለማችን ምርጥ ታላላቅ አትሌቶች ይጠቀሳሉ፡፡  
በሌላ በኩል ተቋማችን ከአጋር ስፖንሰሮችና ከባለድርሻ አካላትም ጋር አርዓያ በሆነ መንገድ በሚሰራበትም ባህል ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡በተለይ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው  በየዓመቱ ከ10 በላይ የተለያዩ ስፖንሰሮችን የሚያሰባብምና በተሳካ ሁኔታ የሚካሄድ ውድድር ሆኗል፡፡  እንደቶታል፤ ቶዮታ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፤ ኮካ ኮላ እና ሌሎች ትልልቅ ድርጅቶች በአብይ ስፖንሰር ከተቋማችን ጋር ለመስራት ያላቸው ፍላጎት በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ለሌሎችም ኩባንያዎች በተምሳሌትነት ሊጠቀስ የሚያችል ነው፡፡ በተለያዩ የውድድር መሳርያዎች፤ ቁሳቁሶችና ልዩ ልዩ ግብዓቶች  አቅርቦት፤ በተሳታፊዎች የተለያዩ የመስተንግዶ ስራዎችና ሌሎች ተግባራት ዙርያ አብረውን የሚሰሩት ከ50 በላይ ድርጅቶች እንደሆኑም ይታወቃል፡፡
በ2013 እኤአ ላይ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሚያዘጋጃችው ውድድሮች የሚሊኒዬሙን የልማት ግቦች ለማሳካት ባደረገው አስተዋፅኦ ግምት ውስጥ ገብቶ የAIMS የማህበረሰብ አገልግሎት ልዩ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ ከዋናው የጎዳና ላይ ሩጫ ጋር ተያይዞ  በሚያነግባቸው መርሆችም በሚሰራበት የስራ ሂደቱና  ባህሉ ተሳክቶለታል፡፡ በገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴም ዘንድሮን ጨምሮ ባለፉት ሰባት አመታት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ እሰከ 24 የግብረሰናይ ድርጅቶችን በሚደግፍ በጎ አድራጎት ዘመቻ የሚሰራ ሆኗል፡፡
በመጨረሻም የምጠቅሰው የዓመቱ አዳዲስ ነገሮችን አካታቶ መስራትን ባህሉ ያደረገው ተቋማችን ከ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫውጋር በማያያዝ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የታላቁ ኢትዮጵያ ኮንሰርት አካሂዷል፡፡ ከ3ሺ በላይ ተሳታፊዎች ባገኘው ይህ ኮንሰርት ከውጭ ሉችያኖ፤ ካሊ ፒ፤ቲዎኒ ፤ ታሻ ቲና ማይ ፍሌክስ ባንድ ከአገር ውስጥ እውቆቹ ድምፃውያን ንዋይ ደበበ፤ ማዲንጎ አፈወርቅ፤ ብራዘርስ ባንድ እና ኮሜዲያን ቶማስ ተሳትፈውበታል፡፡  ታላቁ ሩጫን ከሙዚቃ ጋር በማስተሳሰር በየዓመቱ አጠናክረን ስኬታማ ልናደርገው የምንፈልገው ነው፡፡

Read 1525 times