Saturday, 09 December 2017 14:04

ትራምፕ በእየሩሳሌም ጉዳይ ከመላው አለም ውግዘት ገጥሟቸዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ “እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን እውቅና ሰጥቻለሁ፤ በእስራኤል የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲም ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም አዘዋውራለሁ” ማለታቸውን ተከትሎ፣ መካከለኛው ምስራቅን ጨምሮ ከመላው አለም እጅግ ከፍተኛ ውግዘት እየገጠማቸው ይገኛል፡፡
የእየሩሳሌም ጉዳይ በሁለቱ ወገኖች መግባባትና ድርድር ይፈታ የሚለውንና አሜሪካ ለአስርት አመታት ስታራምደው የቆየቺውን አቋም፣ ጊዜው ያለፈበትና የማያዋጣ ብሎ በድንገት በናደውና አለምን ባነጋገረው የትራምፕ ንግግር ክፉኛ የተቆጡ ፍልስጤማውያን ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን ጉዳዩን የሚያወግዙ መንግስታት ቁጥርም እያደገ ነው፡፡
የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት መሃሙድ አባስ፤”አሜሪካ ከአሁን በኋላ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የአደራዳሪነትና የሸምጋይነት ቦታ የላትም” ያሉ ሲሆን፣ ይህ አደገኛ ውሳኔ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሰላም መንገድ እንዲሁም የአካባቢውን ብሎም የመላውን አለም ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ የትራምፕን ንግግር ነቅፈዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታኒያሁ በበኩላቸው፤ “ለዚህ ታሪካዊ ውሳኔዎት እጅግ አመሰግንዎታለሁ፤ አይሁዳውያንና የአይሁዳውያን አገር ሁሌም ሲያመሰግኑዎት ይኖራሉ” በማለት ትራምፕን ማመስገናቸውን ሲኤንቢሲ ዘግቧል፡፡
የሃማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒ በበኩላቸው፤ ከጋዛ ሰርጥ ባስተላለፈው መልዕክት፣ “ትራምፕ በፍልስጤማውያን ላይ ጦርነት አውጇልና፣ ሴት ወንድ ህጻን አዛውንት ሳትሉ ታጥቃችሁ ተነሱ፤ ከእስራኤል ጋር ለምንፋለምበት አዲሱ ኢንቲፋዳ ተዘጋጁ” ሲሉ ለፍልስጤማውያን በይፋ የክተት አዋጅ ጥሪውን አስተላልፈዋል፡፡ ይህን ተከትሎም፣ በርካታ ፍልስጤማውያን ከትናንት በስቲያ መደበኛ እንቅስቃሴያቸውን አቋርጠው፣ ወደ ጋዛ ጎዳናዎች በመጉረፍ፣ በቁጣ እየነደዱ የትራምፕን ፎቶግራፍና የአሜሪካን ባንዲራ አቃጥለዋል፡፡
“ሰውዬው መካከለኛው ምስራቅ ላይ የማይጠፋ እሳት ለኮሰ!” ሲሉ የትራምፕን ንግግር አደገኛነት የገለጹት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጠይብ ኤርዶጋን ሲሆኑ፣ የግብጹ አቻቸው አብዱል ፋታህ አልሲሲ በበኩላቸው፤ የትራምፕ አካሄድ የሰላም ዕድሎችን የሚዘጋ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ኢራን፣ ሊባኖስና ኳታር የትራምፕን ውሳኔ በአደባባይ የነቀፉ ሲሆን ወገንተኝነቷ ለአሜሪካ ነው የምትባለው ሳዑዲ አረቢያ ሳትቀር፣ የትራምፕን ውሳኔ ተገቢነት የሌለውና ሃላፊነት ከማይሰማው ሰው የሚጠበቅ ስትል ነቅፋዋለች፡፡ የአሜሪካ ወዳጅ የምትባለው ዮርዳኖስም በተመሳሳይ ሁኔታ የትራምፕን ንግግር በአደባባይ አውግዛለች፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትራምፕ ውሳኔ ለእስራኤላውያንና ለፍልስጤማውያን የማይበጅ፣ የሰላም ጥረትን የሚያጨናግፍ አደገኛ አካሄድ ነው ማለታቸውን የዘገበው ቢቢሲ፤ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ፈረንሳይን ጨምሮ ስምንት የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት ያቀረቡትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ፣ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ትናንት ቀጠሮ መያዙንም አመልክቷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ትርጉም ያለው የሰላም ሂደት እንደገና እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረበ ሲሆን የእንግሊዝ መንግስት የትራምፕን ውሳኔ “የማያተርፍ” ሲል በይፋ ነቅፎታል፤ ስዊድን፣ ፈረንሳይና ጀርመንም “ጉዳዩ በሁለቱ አገራት የጋራ ስምምነት እልባት ማግኘት ሲገባው ትራምፕ ጣልቃ ገብተው አደገኛ ነገር መናገራቸውን አልወደድነውም” የሚል ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቀዋል፡፡
አለም በአንድ ድምጽ ውግዘቱን የሚያወርድባቸው ትራምፕ ግን፣ “ጉዳዩ የምታጋንኑትን ያህል አይደለም፤ ለእውነታ እውቅና መስጠት ነው” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ እና በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ኢምባሲዎች በበኩላቸው፤ ሊቀሰቀሱ ከሚችሉ ተቃውሞዎች፣ አመጾችና ብጥብጦች ራሳችሁን ጠብቁ ሲሉ ዜጎቻቸውን አስጠንቅቀዋል፡፡
አደገኛ ጥፋትን የሚያስከትል አጉል ውሳኔ ሲል የትራምፕን አካሄድ ያወገዘው የአረብ ሊግ አባል አገራት፤ ዛሬ በቱርክ ተሰብስበው በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ቀጠሮ መያዛቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Read 2368 times