Saturday, 09 December 2017 13:43

የmagnesium sulfate… አስፈላጊነት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(0 votes)

magnesium sulfate የተሰኘው መድሀኒት ወደአገር ውስጥ እንዲገባ በዩኒሴፍ ድጋፍ በኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ማህበር ከ6/ አመት በፊት አንድ ፕሮጀክት ተነድፎ በአገር ውስጥ በስራ ላይ ውሎአል። ይህ መድሀኒት በተለይም በእርግዝና ግዜ የደም ግፊት ለሚይዛቸውና በትክክል በሕክምና ካልታገዘ ወደከፋ የህመም ዳርቻ የሚወስደውን preeclampsia እና ከዚያም ሲያልፍ Eclampsia  ወደተባለው አስከፊ  ደረጃ የሚያደ ርሰውን ሕመም ለመከላከል ቀድሞ ከሚሰጠው መድሀኒት በተሸለ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የታመነበት ነው፡፡ይህ በዩኒሴፍ እገዛ ስራ ላይ የዋለው ፕሮጀክት ካበቃ ወደሶስት አመት ይሆነዋል። በጊዜው የኢትዮጵያ የማህጸንና ጸንስ ሕክምና ማህበርን በመወከል ፕሮጀክቱን ሲያስተባብሩ የነበሩት ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ ናቸው፡፡ዶ/ር ብርሀኑ ከፓውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ እንዲሁም ዶ/ር ልንገርህ ተፈራ ከአብራክ የእናቶችና የህጻናት ሆስፒታል እንዲሁም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሌሎች ባለሙያዎችም ተጋባዥ እንግዶች ናቸው፡፡
ባለፈው እትም ስለሕመሙ አንዳንድ እውነታዎችን ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ ስለሕመሙ አንባቢዎችን ለማስታወስ ያህል በመጠኑ እነሆ፡፡
Preeclampsia:- ማለት  በእርግዝና ጊዜ በሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በሰውነት ውስጥ የውሀ መጠራቀም እና በሽንት ውስጥ ፕሮቲን ሲኖር ሕመሙ የሚገለጽበት ስያሜ ነው፡፡
Eclampsia፡- ማለት እርጉዝ የሆነችው ሴት በሰውነትዋ ውስጥ Preeclampsia ከተከሰተ በሁዋላ ወደከፋ ደረጃ ሲደርስ በአእምሮዋ ውስጥ በሚፈጠር መዛባት የተነሳ ሰውነትዋ መንቀጥቀጥና የጡንቻዎች መኮማተር ወይንም ጤናዋ የተረበሸ ሲሆን እንዲሁም እራስን መሳትና መውደቅ የሚያደርስ በከፍተኛ የደም ግፊት ምክንያት የሚከሰት ሕመም ነው፡፡        
Preeclampsia Eclampsia (ፕሪክላምፕስያ እና ኢክላምፕስያ) የተባለው የጤና ጉድለት የሚከሰተው በእርግዝና ጊዜ ያውም ወደ 20ኛው ሳምንት ገደማ ነው፡፡ አንዲት እርጉዝ ሴት ፕሪክላምፕስያ በተባለው የጤና ጉድለት ተገኘች ማለት ከፍተኛ የደም ግፊት እና በሽንትዋም ውስጥ ፕሮቲን ሲገኝ እና በእግር ወይንም በእጅ ወይንም በፊት በመሳሰሉት ላይ የእብጠት ምልክት ሲታይ ነው፡፡ ይህ ሕመም ወደከፍተኛ ደረጃ ሲሸጋገር የከፋ ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህም ማለት በተረገዘው ጽንስም ይሁን በእናትየው ላይ የህይወት መጥፋት አደጋን ሊያስከትል ይችላል፡፡  
ከላይ እንዳነበባችሁት ይህ ሕመም አስከፊ በመሆኑ እና በተሻለ መንገድ ማስታገሻም ስለሚያስ ፈልገው ቀድሞ በአገር ውስጥ ይሰጥ ከነበረው መድሀኒት በተለየ magnesium sulfate የተሰኘው በስራ ላይ እንዲውል ተደርጎ የነበረ ሲሆን ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ ግን ወደ ሶስት አመት ሆኖታል፡፡ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው የሚለውን ለማወቅ በማህጸንና ጽንስ ሕክምና ማህበር በኩል ፕሮጀክቱን ሲያስተባብሩ የነበሩትን ባለሙያ ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ ነበር ያነጋገርነው። እሳቸውም እንደሚከተለው ማብራሪያቸውን ሰጥተውናል፡፡
እርግዝናን ተከትሎ የሚመጣው የደም ግፊት በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ በእናቶች ሞት ምክንያትነት በሁለተኛ ደረጃ የተመዘገበ ነው፡፡ ስለሆነም magnesium sulfate የተሰኘው መድሀኒት ለዚህ የጤና ችግር አይነተኛ መፍትሔ መሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ የተረጋገጠ ስለሆነ ዩኒሴፍ በሰጠው ድጋፍ በኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ማህበር አስፈጻሚነት ወደ አገር ውስጥ ገብቶ በስራ ላይ ለሶስት አመት ያህል ቆይቶአል፡፡ የፕሮጀክቱ ተግባር መድሀኒቱን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎችንም ስለመድሀኒቱ ባህርይ ስልጠና የመስ ጠት ስራንም ያካተተ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ አስቀድሞ በስራ ላይ የዋለው በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲቀረጽ ያላከተተው ቢሆንም በስራ ላይ ግን በተመረጡ የግል ሆስፒታ ሎችም ስራ ላይ እንዲውል ተደርጎአል፡፡ በዚህም ሂደት መድሀኒቱን ወደአገር ውስጥ ማስገ ባት፣ አማካይ ስፍራዎችን በመጠቀም በትክክል ማከፋፈል እና መድሀኒቱ ጥንቃቄን የሚሻ እና አለአግባብ ከተሰጠ አደገኛ ስለሚሆን በመድሀኒቱ አሰጣጥ ላይ ባለሙያዎች በቂ የሆነ እውቀት እንዲኖራቸው ስልጠና መስጠት ትልቁ የፕሮጀክቱ የስራ ድርሻ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ ጊዜውን ሲያጠናቅቅ የስራው ርክክብ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተደርጎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በአስ ፈላጊ የመድሀኒት ዝርዝር ውስጥ ገብቶ ለታካሚዎች የሚቀርብበት ዘዴ እንዲኖር መቀየሱንና ወደስራው መገባቱን አስታውሳለሁ፡፡ ብለዋል ዶ/ር ብርሀኑ፡፡
ዶ/ር ብርሀኑ በማስከተልም magnesium sulfate የተሰኘው መድሀኒት በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ አርባ አመት በላይ የተጠቀሙበት ሲሆን በአገራችን ግን በቅርብ ጊዜ የመጣ ነው፡፡ በኢትዮ ጵያ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው መድሀኒት ከ magnesium sulfate ጋር ሲወዳደር ምናል ባት በውጤታማነቱም ሆነ በሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳት በጣም ደረጃው አነስ ያለ ዲያዜፓ የተባለ እና ሌሎች መድሀኒቶችም ከጥቅም ላይ ይውሉ ነበር፡፡ magnesium sulfate ን በተመለከተ በአለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ትልልቅ የጥናት ማእከሎች ውጤታማነቱና የእናቶችን ሞት ከመቀነስ አንጻር የተሻለ በመሆኑ በምን ሁኔታ ወደአገር ውስጥ ማስገባት ይቻላል የሚለው እሳቤ ሲንከባለል ቆይቶ በስተመጨረሻ በዩኒሴፍ አጋዥነት መድሀኒቱ ወደሀገር ውስጥ ሊገባ ችሎአል፡፡
በአገራችን ለእናቶች ሞት ምክንያት ተብለው ከተመዘገቡት አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ከደም መፍሰስ ቀጥሎ የደም ግፊትን ተከትሎ በሚመጣው ፕሪክላምፕሲያ እና ኢክላምፕሲያ በተባለው  ምክንያት መሆኑ በአገራችን የእናቶች ሞት ምክንያት ጥናት በተደረገበት ወቅት የተረጋገጠ ነው። ነገር ግን ማግኔዥየም ሰልፔት የተሰኘው መድሀኒት ከመጣ በሁዋላ ምን መልክ እንዳለው ለማወቅ ሌላ ጥናት ስለሚያስፈልግ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም በተሻለ ሁኔታ መኖሩ ግን አይካድም። ፕሮጀክቱ በስራ ላይ በነበረበት ወቅትም መድሀኒቱ በስራ ላይ እየተተገበረ ለአስር ወራት ያህል የክትትል ስራ ተሰርቶአል፡፡ በዚያም ወቅት በአገር ደረጃ ባሉት የመከታተያ መንገዶች በመጠቀም ስራው ምን ያህል ተግባር ላይ እንደዋለ መመልከት የተቻለ ሲሆን ከዚያ በሁዋላም ለኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ርክክብ ተፈጽሞአል፡፡ እንደ ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ ማብራሪያ፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ ባለሙያዎችን ስናነጋግር አንዲት በፕሪክላምፕስያ ሕመም ምክንያት ከደሴ ሆስፒታል ወደ ቅዱስ ጳውሎስ የተላከች እናት ከሐኪምዋ ጋር አግኝተን ነበር፡፡
‹‹….እኔ የመጣሁት ከደሴ ሆስፒታል ነው፡፡ የመጣሁበት ምክንያትም የምወልደው ልጅ የሙቀት ወይንም የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ያስፈልገው ስለነበር መሳሪያው የተሻለ ነው በሚል ነው፡፡ ልጄ የጨቅላዎች ሕክምና ክፍል መግባት ያስፈለገው  በደም ግፊት ምክንያት ካለቀኑ እንዲወለድ በመደረጉ ነው፡፡ ይህ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የደም ግፊት ከአሁን ቀደምም አጋጥሞኛል፡፡ እንዲያውም አሁን ቢያንስ ቢያንስ ልጁ ተወልዶአል፡፡ በዚያን ጊዜ ግን ልጄንም አጥቼ ነበር። ልጄ ሞቶአል፡፡ እኔን ግን ሐኪሞቹ ከእግዚሀር ጋር ሆነው ነብሴን አትርፈውልኛል፡፡ አሁንም እንደዚያ ያለው ችግር ገጥመኛል ብዬ ፈርቼ ነበር፡፡ ምክንያቱም በጣም እራሴን ያመኝ ነበር፡፡ ሐኪ ሞቹም አመጋገቤን አኑዋኑዋሬን ሁሉ እንዳስተካክል ይመክሩኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ባደርግ ሕመሙ ሊተወኝ አልቻለም። በስተመጨረሻውም የልጁም ሕይወት ሳያልፍ እኔም ሳልጎዳ ይኼው ተርፈናል፡፡››
ዶ/ር ልንገርህ ተፈራ በማህጸንና ጽንስ ሕክምና ክፍል እስፔሻሊስት ሐኪም ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚሰሩት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በአብራክ የእናቶችና የህጻናት ሕክምና ክፍል እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ዶ/ር ልንገርህ በአዲስ አበባ ስራ ከመጀመራቸው በፊት በአሰላ ሆስፒታልም ይሰሩ ነበር፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ የአሰላውን ልምዳቸውን እንደሚከተለው ገልጠዋልል፡፡
‹‹…በእርግጥ ወደአዲስ አበባ ከመጣሁ ገና ሶስት አመት ቢሆነኝ ነው፡፡ በዚህ ወቅትም በተለያዩ ሆስፒታሎች ስሰራ ነበር፡፡ በአሰላ ሆስፒታል በነበርኩበት ወቅት ያጋጠሙኝ የማህጸንና ጽንስ የጤና ሁኔታዎች አንዱ እና እናቶችንና ልጆቻቸውን ገዳይ የሆነው እና በደም ግፊት ምክንያት የሚከሰተው Eclampsia preeclampsia ነው፡፡ ይህ በሽታ ህክምና ያለው ሲሆን በፍጥነት ካልተቆጣጠሩት ግን ገዳይ መሆኑ በገሀድ እየታየ ያለ ነው፡፡ ይህ በሽታ ወደከፋው ወደ ኢክላምፕሲያ እንዳይሻጋገር እሚያስችሉት እንደ ማግኔዥየም ሰልፔት ያሉ መድሀኒቶች መኖራቸው ግድ ነው፡፡ ነገር ግን የመድሀኒቱ አቅርቦት በቂ የማይሆንበት ሁኔታ ካለ እናቶችን በሚያሳዝን ሁኔታ ማጣት የማይቀር ነገር ነው፡፡ ስለዚህም በአሰላ ሆስፒታልም የተረዳሁት ነገር ታካሚዎች ይጎዱ እንደነበር ነው፡፡
ይቀጥላል

Read 2133 times