Print this page
Sunday, 10 December 2017 00:00

ሸረሪቷ!

Written by  ደራሲ፡- ኦርጅነስ ሌሳ ትርጉም፡- ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(3 votes)

ማስታወሻ
በጁላይ 1903 በብራዚል ሳኦፖሎ የተወለደው ኦርጂነስ ሌሳ፤ በጋዜጠኝነቱ እንዲሁም በአጭርና ረዥም ልብ ወለድ ደራሲነቱ ይታወቃል፡፡ ይህ “ሸረሪቷ” በሚል ርዕስ የቀረበው አጭር ልብወለድ፤ በ1946 ዓ.ም ከታተመው “Omelet in Mobai” ከሚል የአጭር ልብወለድ ስብስብ ስራዎቹ የተወሰደ ነው፡፡
------------
“ለድርሰትህ መነሻ የሚሆን ታሪክ ትፈልጋለህ?”
አኒስ ከመተላለፊያው ኮሪደር ጠርዝ ስንገናኝ ያቀረበልኝ ጥያቄ ነበር፡፡
“አመሰግናለሁ፤ አያስፈልገኝም”
“ለየት ያለ፣ እውነተኛና  የሚስብ…”
“አሁን አያስፈልገኝም ሌላ ጊዜ”
“ትቸኩላለህ መሰለኝ?”
“በጣም!”
“መልካም፤ ሌላ ጊዜ አጫወትሃለሁ። በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው፤ የሚያስፈልገው መጠነኛ ሥነ ጽሁፋዊ ለዘና ውበት በማላበስ የጥበብ እስትንፋስ መዝራት…”
“ሌላ ጊዜ ታጫውተኛለህ አልኩህ’ኮ… አሳንሰር እየጠበቅኩኝ  ስለሆነ….” ብዬ ልለየው ስል፣ ሌላ ሰው መሀላችን ገባ፡፡
“ምን አዲስ ነገር አለ?” ሰውዬው አኒስን ጠየቀው፡፡
አኒስም፤ “ወግ ይዘናል፤ ምርጥ ታሪክ የሚወጣው አንድ ድርሰት--- ከተስማማው ክፍያ ልነግረው ነበር፡፡ እኔው ራሴ የታሪኩን ሴራ….እእ..ትልም መጻፍ ጀምሬ ነበር፤የፈጠራ ድርሰት የመፃፍ ተስጥኦው ስለሌለኝ አልተሳካልኝም…..
“ስለ ምንድን ነው?” ሰውየው ጠየቀ፡፡
“…ቆየት ያለ ታሪክ ነው፤ ሜሉን ታውቀዋለህ? እዚህ ሳኦፖሎ ውስጥ የሥጋ ተዋፅኦ ማቀነባበሪያ….. በየገጠሩ አያሌ ማሳዎች ያሉት ሰው ነው--- አወቅኸው?”
ጥያቄው የተሰነዘረው ለኔ በመሆኑ “አዎ” ከማለት ሌላ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ሜሉን አውቀዋለሁና … “የጠየኩህ ለምን መሰለህ?… ታሪኩ ከሜሉ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው… ታሪኩንም የነገረኝ ራሱ ነው…ያልተበረዘና ያልተከለሰ … ያለ አንዳች ኩሸት እውነተኛ ገጠመኙን ነው የተረከልኝ፣ በፈጠራ ኪናዊ ቅመም  ሳይኳኳል በጥሬው በግርድፉ የቀረበ ነው…  ከአንተ የሚጠበቀው የነጠረ ሥነ ፅሁፋዊ ለዛ በማላበስ፣ ተራ ቃላትን ወደ እንቁነት ለውጠህ፣ እንደ ንሥር በተደራሲው ምናብ መጥቀው እንዲበሩ የማብቃት---የመከሸን  ክህሎት ብቻ ነው--
“አንድ ምሽት በአዛውንቱ ቤት ከሜሉ ጋር በአጋጣሚ ተገናኝተን ነው ታሪኩን ያጫወተኝ …..ሜሉ የታወቀ ጊታር ተጫዋች ስለመሆኑ የምታውቁ አይመስለኝም፤ ወደ መድረክ የወጣባቸው አጋጣሚዎች ውስን ናቸው… ፖሊሰታ ውስጥ የእርሻ መሬት ነበረው፤ ጊዜውን የሚያሳልፍበት የገጠር ቤቱ ፀጥ እረጭ ያለ ኦና ቤት! ለሜሉ ያለው መዝናኛ አሮጌ ጊታሩ ብቻ ነው፡፡ ሥራውን አጠናቆ ከጊታሩ ጋር ያመሻል … በህሊና ውስጥ ሰርፆ፣ ልብን የሚያባባ የትካዜና የትዝታ ዜማው ታዳሚን በእንባ የሚያራጭ ነበር …. አንዳንዴ ከተለመዱ የዜማ ስልቶች ወጣ ብሎ ዘመን ተሻጋሪ ክላሲክ ሙዚቃዎችንም ይጫወታል ---- የሾፐን፣ የቤትሆቭን …….. ጊታሩን እንደ ሰው ያናግረዋል ማለቱ ይቀላል … እኔው ራሴ ታዳሚ ሆኜ፣ ዜማዎቹን አዳምጫቸዋለሁ…. ለሙዚቃ የተፈጠረ ንጥረ ነፍስ…!
ከአስረኛ ፎቅ በገቡ ሰዎች አሣንሠሩ ጢም ብሎ ሞልቷል፤ መግባት አልቻልኩም! በቀጣዩ አሣንሠር ለመሄድ ደወሉን በተደጋጋሚ ተጫንኩት…የማጫውታችሁን ወግ የነገረኝ ራሱ ነው…. የኔ ፈጠራ አይደለም፡፡ የምትረክላችሁ ልክ እኔ በሰማሁት መንገድ ነው፡፡
“--በአንድ የጨረቃ ምሽት ሜሉ የሚመስጥ ዜማ እየተጫወተ ነበር … የሥነ ፅሁፍ ውበት የሚጨለፈው ከዚህ መሰል ድባብ ይመስለኛል….. ምትሀታዊ የጨረቃ ውበት! በዘንባባ ዛፎች መሀል የሚያልፍ የነፋስ ሽውታ፣ የታሪኩን ፍሰት ኮለል ብሎ እንዲወርድ ያደርገዋል፡፡…..”
ሁለት ሰዎች ቀድመውኝ ወደ አሣንሠሩ ዘው ብለው ገቡ! ሊፍቱ ሞልቷል! የአኒስን የተንዛዛ ትረካ ማዳመጥ ግደታዬ ሆነ፡፡
“.…ሜሉ በፍጹም መመሰጥ ጊታሩን እየተጫወተ ሳለ፣ ድንገት ወለሉ ላይ  ግዙፍ በፀጉር የተሸፈነች ሸረሪት ተመለከተ--- ዘግናኝ ፍጥረት! ስቅጥጥ አለው፡፡ መጫወቱን አቆመ፤ ሸረሪቷ በወለሉ ንቃቃት ገብታ ተሰወረች፤ ሜሉ በፍርሃት ነጭ ላብ አሰመጠው፤ይህቺን መሰል ግዙፍ ዘግናኝ ሸረሪት አይቶ አያውቅም፡፡ ጊታሩን አስቀመጠ …. ለ15 ደቂቃ ዓይኑን ከወለሉ ንቃቃት ላይ ሳይነቅል ቢያፈጥም ሸረሪቷ ብቅ አላለችም፡፡ ወደ ጊታር ጨዋታው ተመለሰ፡፡ የትካዜ ከርቤ --- የሰቀቀን ዋይታ--- ድምፀት ያለው ዜማ መጫወት ጀመረ፡፡ ብዙም ሳይቆይ በፀጉር የተሸፈነው የሸረሪቷ እግር ከወለሉ ስንጣቂ ብቅ አለ ……”
አሣንሰሩ ተከፈተ፡፡ ሦስት ሰዎች እንደ ወረዱ፣ ወዲያውኑ ተዘግቶ ጉዞውን ቀጠለ….
አኒስም ትረካውን…
“--አስፈሪዋ ፍጡር በዝግታ እየተቃረበችው ስትመጣ ጊታር መጫወቱን አቆመ፤ ሸረሪቷ መለስ ብላ ወደ ወለሉ ስንጥቅ ገብታ ተሰወረች፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሜሉ በሁኔታው ተደመመ፡፡ ከደቂዎች በኋላ መጫወቱን ቀጠለ…. ትዕይንቱ ተደገመ…. ሸረሪቷ ከወለሉ ንቃቃት ወጣች፤ በቀስታ ወደ ሜሉ ተጠጋች….ግዙፍ አካሏ በፀጉር ከመሸፈኑ በቀር አቀራረቧ ፍጹም ወዳጅነት የተላበሰ ነበር….ሙዚቃው ይሆን? ሲል አውጠነጠነ…ጊታሩን መጫወቱን አቆመ፡፡ ሸረሪቷ ሁለት ጋት ያህል ወደ ኋላ አፈገፈገች…”
አሣንሰሩ ቢከፈትም የመሄድ ዕቅዴን ለጊዜው ተውኩት…. የአኒስን ትረካ ማድመጤን ቀጠልኩ….
“-- ከወለሉ ስንጥቅ ገብታ ተሰወረች፡፡  ጊታሩን መጫወት ጀመረ፤ ሸረሪቷ ወጣች…..ይህ ድንቅ ትዕይንት ከሦስት ጊዜ በላይ ተደጋገመ….ሜሉ ቤቱ ውስጥ መርዛማ ፍጡር መኖሯን እያወቀ ወደ መኝታው ገብቶ አንቀላፋ…. በማግስቱ ቀኑን ሙሉ ስለ ሸረሪቷ እያሰላሰለ ሲገረም ዋለ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው የታሪኩ ክፍል ይበልጥ ግርምት የሚጭር ነው…. ሸረሪቷ ትመለሳለች? ወይስ ክስተቱ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው? ሜሉ ቀኑን ሙሉ ፋታ አላገኘም፡፡ ማሳው ላይ ሲማስን ውሎ አመሻሽ ወደ ቤቱ ገባ፡፡ መድረክ ላይ ዝግጅቱን ለታዳሚው እንደሚያቀርብ አርቲስት ጊታሩን ማናገር ጀመረ…. የልብ ትርታው ጨመረ….. ዓይኑን ከወለሉ ንቃቃት ላይ ሳይነቅል መጫወቱን ቀጠለ….. ከአስራ አምስት ደቂቃ በኋላ ሸረሪቷ ብቅ አለች…. ፀጉራማ እግሯ በደብዛዛ ብርሃን ጥቅርሻ መስሏል…. ላይ! ታች! መለስ ቀለስ…. በፈራ ተባ እንቅስቃሴ ወለሉ መሀል ቆማ፣ የጊታሩን ቅኝት ማዳመጥ ጀመረች፡፡ ሜሉ ሙከራውን በተጨባጭ ለማረጋገጥ የጊታሩን ምት አቆመ! ፀጥታው ሲረዝም ሸረሪቷ ወደ ኋላ አፈግፍጋ በወለሉ ስንጥቅ ገብታ ተሰወረች፡፡ ጊታሩን ሲጫወት ደግማ ብቅ! አለች፡፡ ይህ ትዕይንት ከአንዴም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፡፡….
“ሜሉ ታሪኩን ለሰፈርተኛው አደረሰው፤ ሸረሪቷ ታዋቂነትን አተረፈች፡፡ ሙዚቃ አፍቃሪዋን ትንግርተኛ ሸረሪት ለማየት የሜሉ ቤት በእንግዶች ጢም ማለት ጀመረ፡፡ …. አንድ የሾፐን ሙዚቃ…. የትኛው እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም…. ሸረሪቷ ይህንን ዜማ ሰምታ ካለቀ በኋላ እንኳን አትንቀሳቀስም፤ የሙዚቃው ሀያል ጉልበት ተቆጣጥሯት ፍዝዝ ድንግዝ ያደርጋት ነበር…. ሌላው አስገራሚው ጉዳይ! የሜሉ በሸረሪቷ ፍቅር የመያዙ ነገር ነው…. እንደ እንስት ቆጥሯታል---ያውም ንግስት፡፡ ማን እንዳላት አላስታውሰም እንጂ ስም ቢጤ አውጥቶላታል …. ሁለቱም ከመጠን በላይ መግባባት ደረጃ ደረሱ፤ የትኛውን ዜማ በጥልቅ ተመስጦ እንደምታዳምጥ ተረድቷታል፡፡ የሸረሪቷን የሙዚቃ ጥማት ለማርካት ያለ አንዳች ስስት ሲጫወትላት ያመሻል፡፡ ሜሉ ከሁለት ወራት በኋላ ወደ ሳኦፖሎ ስለመመለሱ ባሰበ ቁጥር ጭንቀቱ በረታ፡፡ ሸረሪቷ ሙዚቃውን ሲያቋርጥባት--- ሕይወቷ እንዴት ይሆን? ሸረሪቷን ወደ ሳኦፖሎ መውሰድ ደሞ የሚታሰብ አይደለም….
“--አንድ ምሽት የቅርብ ጓደኛው ራቅ ካለ ቦታ መጣ፤ ሰውየው ለረዥም ጊዜ ስለ ከተማው አሉባልታ--- እንቶፈንቶ ደሰኮረለት፡፡ ሜሉ በመሐል ሸረሪቷን አስታውሶ፣ ጊታሩን አንስቶ መጫወት ጀመረ… እዚህ ላይ በአጽንኦት የምነግራችሁ ስለ ሸረሪቷ ለእንግዳው አንዳችም ነገር አልነገረውም…. ዜማው ሞቅ ደመቅ እያለ ሲመጣ፣ እንደ ወትሮው ሸረሪቷ ከወለሉ ንቃቃት ብቅ አለች፤ እንግዳው አይኖቹ ሸረሪቷ ላይ ባረፈበት ቅጽበት! በደመነፍስ ተስፈንጥሮ በመነሳት፣ በጭቃ በተለወሰው ጫማው ደፈጠጣት!! ሜሉ ሰቀቀናዊ የጣር ጨኸቱን ለቀቀው…. እንግዳው ግር ብሎት አፈጠጠበት…ምንም አልገባውም …. ሜሉም በድንጋጤ በድን ሆኖ፣ ፊቱ ገርጥቶ እንባውን እያፈሰሰ…. <አሁን-- አሁን-- የተጫወትኩትን ዜማ በልዩ ፍቅር ትወደው ነበር..ምስኪን ፍጡር!>
“ምንድን ነው አልገባኝም?”
እንግዳው፤ አሁን የነገርኳችሁን የሸረሪቷን ሙሉ ታሪክ ሲሰማ፣ የሚያድርበትን የሕሊና ፀፀት አስቡት!…

Read 3095 times