Sunday, 10 December 2017 00:00

ግልፅ ደብዳቤ ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መሪዎች - (ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)

Written by 
Rate this item
(15 votes)

 “ከእንግዲህ ወዲህ አርማችሁንም ኢትዮጵያዊነትን አድርጉ!”
ይህን ደብዳቤ የምፅፍላችሁ እንደ አንድ ለሃገሩ ተቆርቋሪ ግለሰብ ሆኜ፣እናንተ አሁን በምትመሯት ኢትዮጵያ ላይ ፍቅር፣ አንድነት፣ ሰላም፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ ይሰፍኑ ዘንድ ይረዳ ይሆናል በማለት ነው። ቀጥሎም፣ በኢህአዴግ ውስጥ የተደራጁት የእናንተ አባላት ለሆኑት ለኦሮሞና አማራ ክልሎች ፕሬዚዳንቶች ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸው፤ ኢትዮጵያዊነትን እንዲያራምዱ በመከርኳቸው መሰረት፣ ሃሳቤን ብትጥሉትም ብታፀድቁትም የበኩሌን እንደ መርህ እናንተንም ለመምከር ነው። ከዚህም በተጨማሪ፣ ህሊናዬ ይህን ደብዳቤ ፃፍላቸው ስለ አለኝ፣ ለህሊናዬ ታዛዥ ሆኜ ነው።
ተጋሩን፣ ጉራጌን፣ አማራን፣ አፋርን፣ ኦሮሞን፣  ከምባታን፣ ሀዲያን፣ ሲዳማን፣ ሱማሌንና ሌሎቻችንን በኢትዮጵያም ሆነ በውጪ ሀገር የምንኖረውን ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያዛምደን፣ ኢትዮጵያን በስሙ ያስጠራት የንጉሦች ንጉሥ፣ የካህኖች ካህን የነበረው አባታችን ኢትዮጵ ነው። ኢትዮጵ የኖረው በጣና ደሴቶች ላይ ሲሆን ዘመኑም ከ4000 ዐመታት በፊት ነው። እሱም 10 ወንዶችና 3 ሴቶች ልጆች ወልዶ ነበር። 10ሩ ወንዶች ልጆች 10 ነገዶች ሆነው፣ ለ4000 ዐመታት በመባዛት እኛን የዛሬዎቹን ኢትዮጵያውያንን አስገኝተዋል። የኢትዮጵ አስሩ ወንዶች ልጆች ስሞችም፡- አቲባ፣ ቢዖር፣ ተምና፣ አቴር፣ አሻን፣ አክዚብ፣ በሪሳ፣ ቴስቢ፣ ቶላ፣ እና አዜብ ነበሩ።  ከሶስት ሴት ልጆቹ አንድዋ ሱባ ትባል ነበር። የዛሬ 4000 ዐመት ከወጡት ከእነዚህ ስሞች ውስጥ አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ለምሳሌ አዜብ፣ በሪሳ፣ ቶላ፣ አሻን እና ሱባ የተባሉት። ከአባታችን ከኢትዮጵ በኋላ የተከተሉት ነገሥታት ልጆቹ፣ የኢትዮጵያን ስልጣኔ በመላው አፍሪካ አሰራጭተው፣ ዛሬ አፍሪካ የሚባለው ሰፊ ምድር እስከ ዛሬ ሁለት መቶ ዐመታት ድረስ ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራ ነበር። LOWER እና UPPER ETHIOPIA ብለው ከፍለውት ነበር።  ከእዚህም በላይ የህንድ ውቅያኖስና ከምእራብ አፍሪካ ብብት ስር ያሉት ውቅያኖሶች ሁሉ የኢትዮጵያ ውቅያኖሶች ይባሉ ነበር።  አሁንም ቢሆን አፍሪካ፣ አፍሪካ የተባለችው በእኛው በአፋሮች ስለሆነ ደስ ይለናል እንጂ አንቆጭም። እስያም እስያ የተባለችው ንግሥተ ሳባ ዙፋኑን በተካችው በዐፄ እስያኤል ስለሆነ በዚህም እንታበያለን። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉሙ  “የተቃጠለ ፊት” ሳይሆን “ቢጫ ወርቅ” ስጦታ ለእግዚእብሄር ነው። ቅዱስ ስሟን ለመፋቅ ወይም ለመቀየር የተመኙ ሁሉ የኢትዮጵያ ስም ከእግዚአብሄር ጋራ የተያያዘ በመሆኑ ምኞታቸው ከሽፎ፣ የእግዚአብሄር ዐይኖች ኢትዮጵያ ላይ ተተክለዋል። በቅዱስ መፅሃፉ ውስጥ እግዚእብሄር ኢትዮጵያን ደጋግሞ የሚጠራት ያለ ምክንያት አይደለም። ከማንም ይልቅ ኢትዮጵያን ስለሚወዳት ነው። በነቢዩ አሞፅ አፍ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡-
“እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፤ እናንተ ለኔ እንደ ኢትዮጵያውያን ልጆቼ አይደላችሁምን?”  (አሞፅ 9: 7) ከእዚህ ጥቅስ የምንማረው እኛን ኢትዮጵያውያንን እግዚአብሄር ከእስራኤላውያን ይበልጥ ወይም እኩል እንደሚወደን እና ልቡ ውስጥ እንደአለን ነው። ስለዚህ እሱ ጥሎ አይጥለንም።
የንግሥት ሳባ የልጅ፣ ልጅ፣ ልጅ የነበረው አፄ አክሱማይ በገነባትና በስሙ በሰየማት በአክሱም ከተማ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ስልጣኔ፣ ለበርካታ ምዕተ ዐመታት ገንኖ፣ ኢትዮጵያን አስከብሯት ነበር። ብልሁና ፍትሃዊው አፄ አክሱማይ፣ ከኢትዮጵያ ዳር ድንበር አልፎ፣ ኢትዮጵያ በዛን ጊዜ ታስተዳድራቸው በነበሩት የግብፅ፣ የሊብያና የኑብያ እንዲሁም የባቢሎን ህዝቦች ሳይቀሩ ንጉሦቻቸው ሲበድሉአቸው ለአቤቱታ ወደ እሱ ይጎርፉ ነበር። በእዚህ ምክንያት የነገሥታት እራስ፣ የዐለም አባት ተብሎ ይጠራ ነበር።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዐላማ እያውለበለቡ፣ ከአክሱማይ ልጅ ከአፄ አውሳብዮስ ጀምሮና ከሱም በኋላ የነገሡት ነገሥታትም፣ ንግሥት ዮዲት (እሳቶ የሚል የቅፅል ስም ጠላቶቿ የሰየሙላት) እስከ አሳደደችው እስከ አንበሳ-ሰገድ ድረስ ለ850 ዐመታት አክሱምን መናገሻ ከተማቸውና ማእከል በማድረግ ለ850 ዐመታት ያህል በኢትዮጵያ ላይ ነግሠዋል። ከቀዳማዊ ምንይልክ ዘመን ከጀመርን ደግሞ በአክሱም ላይ የነበረው የንግሥና ዘመን ወደ 950 ዐመታት ገደማ ይሆናል። በላስታ ላሊበላ ለ343 ዐመታት ያህል የነገሡት የዛግዌ ስርወ-መንግሥት አባላትና ከአፄ ዩኩኖአምላክ ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኅይለሥላሤ ድረስ በሸዋ በቀዳማዊ ምንይልክ ዙፋን ላይ የነሡትም ነገሥታት ምንጫቸው ከአክሱም እንደ ነበር በኩራት ይናገሩ ነበር። በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵ ዘር ነን ብለው በኢትዮጵያዊነታቸው ይታበዩና ይጀነኑ ነበር። ሁልጊዜም የገናናው የኢትዮጵ ዘር፣ ኢትዮጵያውያን ነን ይሉ ነበር። በቅርቡ ከአፄ ቴዎድሮስ ቀጥለው በኢትዮጵያ ላይ የነገሡት የትግራዩ ተወላጅ አፄ ዮሐንስም በኢትዮጵያዊነታቸው ከመኩራት አልፈው ተርፈው አፄ ቴዎድሮስ የጀመሩትን የኢትዮጵያ አንድነት ቀጥለውበት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እያስፋፉና እየጠበቁ ህይወታቸውን አሳልፈዋል። አፄ ዮሐንስ የቆሙት ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ለመላዋ ኢትዮጵያ ነበር። እሳቸው ለአንዲት ካልኢትም እንኳን ኢትዮጵያዊነታቸውን ጥያቄ ውስጥ አስገብተው አያውቁም። ጣልያንን በዶግአሊና በአድዋ ያርበደበዱት የሳቸው የጦር አበጋዝ ጅግናው ራስ አሉላ አባ ነጋም ተጋሩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እስከ አጥንታቸው ጥልቀት ድረስ የጠሩና የነጠሩ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። በኢትዮጵያዊነታቸው ለአፍታም ያህል ከጣልያኖች ጋር ያልተደራደሩት  ተጋሩው ባሻ አውአሎም እንኳን ለአድዋ ድል ወሳኝ የሆነውን መረጃ ለጌታቸው ለአፄ ምንይልክ ያቀበሉት በዚያው በኢትዮጵያዊነት ፍቅራቸው ተቃጥለው አልነበረምን? እንግዲህ የእናንተስ የትግራዋይ ተወላጆቹ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይገባልን? እናንተስ የእነዚህ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ዝርያ አይደላችሁምን? እባካችሁ የእነሱ ዝርያ መሆናችሁን አስታውሳችሁ፤ ኢትዮጵያዊነትን አጥብቃችሁ ያዙ። ለሌሎችም አርአያ ሁኑ። ተራዎቹንና ብርቱ ክርስትያን የሆኑትን ክቡራኑን የትግራዋይ እባቶቻችሁንና እናቶቻችሁን እስቲ ተመልከቱአቸው። በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው አስከሬናቸው በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተጠቅልሎ አይደለምን የሚቀበሩት? እናንተስ ከእነሱ አብራክ የወጣችሁ አይደላችሁምን? አሁንም ኢትዮጵያን ካለችበት ማጥ የሚያወጣት ኢትዮጵያዊነት ብቻ እንጂ በቋንቋ ላይ የተገነባው፣ በልማድ ብሄር ብሄረሰቦች የሚባለው በትክክለኛ አጠራሩ ግን ጎሳና ነገድ በሆነው ክልለኝነት አይደለም። ይህ ጎሰኝነትና ክልለኝነት፣ የጎሳንና የነገድን የብሄር ብሄረሰብን መብት አስከብራለሁ ቢልና መብቱ ተገቢ ቢሆንም ድንበር እየሳተ፣ እውስጡ ያሉትን የአናሳዎች መብት እየገፈፈ፣ አያሌ ቀውስ እንዳስከተለ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም።  ለ26 ዐመታት ተሞክሮም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አይሏል።
በእውነትም አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ችግር መፍትሄው፣ኢትዮጵያዊነት እንጂ በቋንቋ ላይ የተገነባ ጎሰኝነት አይደለም። ጎሳ ማለት ቋንቋ ማለት ነው፤ “ጎሰአ”፣ ማለትም  ተናገረ  ከሚለው የግዕዝ ቃል የፈለቀ ነው። ስለዚህ ቋንቋ ማለት ጎሳ ነው። ጎሳ ማለትም ቋንቋ ነው።  በሌላ አነጋገር፣ ጎሳ የቋንቋ ክፍል እንጂ የደም ወይም የዘር ዘርፍ አይደለም። አንድ ዐይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በሞላ በዛ ቋንቋ አፍ ከፈቱ የዛ ቋንቋ  ወይም ጎሳ አባላት ይሆናሉ። ይህን ሁልጊዜ በምጠቅሰው ምሳሌ ላሳይ። እኔ በፈረንሳይ፣ በጀርመንና እንግሊዝ ሃገሮች ኖሬ፣ ሶስት ልጆች ብወልድና እነሱ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛና እንግሊዝኛ ቢናገሩ፣ የእኔ አፍ መፍቻ ደግሞ ኦሮምኛ ቢሆን ልጆቼ ሶስት የተለያዩ ቋንቋዎች በመናገራቸው ጎሳቸው ፈረንሳይ፣ ጀርመንና እንግሊዝ ቢሆንም የእርስበርስ ዝምድናቸው አይፋቅም።  እኔም ኦሮምኛ ስለተናገርኩ ጎሳዬ ኦሮሞ ቢሆንም አባትነቴ አይሰረዝም። እኛን የሚያዛምደን የኔ ደም ወይም ዘር እንጂ ቋንቋ ወይም ጎሳ አይደለምና። ስለዚህ ሰዎችን በስጋ የሚያዛምድ ደም ወይም ዘር ነው እንጂ ቋንቋ ወይም ጎሳ አይደለም።  ደሞ ቋንቋ ሊረሳም ሊለዋወጥም ስለሚችል አስተማማኝ የማንነት መለያ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ 82 ቋንቋዎችና ዳያሌክቶች እንደ አሉ ይነገራል። ቋንቋ ማለት ጎሳ ማለት ስለሆነ በዚህ ቁጥር መሰረት 82 ጎሳዎች አሉ ማለት ነው። በልጆቼ ምሳሌ እንደምናየው፤ ደም እንጂ ቋንቋ አያዛምድም።  እነዚህ ሁሉ የቋንቋ ተናጋሪዎች በደም ወይም በዘር የሚዛመዱት ሁሉም ከኢትዮጵ ወይም ከእሱ 10 ልጆች አብራክ ስለፈለቁ ብቻ ነው። በተጨማሪ ደግሞ በጋብቻ ደም ስለተደበላለቁና በኢትዮጵያ ግዛት ለሺዎች ዐመታት አብረው ኖረው በባህል፣ በልቦና እና እምነት ስለተሳሳቡ እና ስለተወሳሰቡ እንዲሁም የጋራ የማንነት እሴቶችን ስለአካበቱ  ነው።  እንግዲህ እናንተንም የኢትዮጵያን ህዝቦች የሚያዛምዳችሁና አንድ የሚያደርጋችሁ፣ ከዛም አልፎ የሚያኗኑራችሁ፣ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ጎሰኝነት ወይም በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ክልል አለመሆኑን ተረድታችሁ፣ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ተጋሩነታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ላይ አተኩሩ።
ኢትዮጵያዊነት ላይ አትኩራችሁም የአመራር ሚና እየተጫወታችሁ፣ ሌሎቹንም ኢትዮጵያውያንንም፣ ማለትም ብዙሃኑን የኦሮሞን፣ የአማራን፣ የአፋርን፣ የተጋሩንም ጭምር፣ የሲዳማን፣ የጉራጌን፣ የሃዲያን፣ የከምባታን፣ የሱማሌን፣ የከፋንና ሌሎቹን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ተወካይዎች ጋብዛችሁ ተመካክራችሁ፣  ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ርትእ፣ የሰብአዊና የሃብት እኩልነትን አስከብሩ። የንግግርና የፅሁፍ ነፃነት፣ በድፍን ኢትዮጵያ የመንቀሳቀስና የመኖር መብትን አስከብሩ። በጎሰኝነት ጦስ በከንቱ የሚፈሰውን ደም አስቁሙ። የፖለቲካ እስረኞችን ሁሉ በአስቸኳይ ፍቱ። ኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጪ የአሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህብረተሰባዊ ማህበራትን ሳትንቁ በማሰባሰብ፣ እነሱም የሃገራቸውን ወደፊት እንዲወስኑ ዕድል ስጡአቸው። ከእንግዲህ ወዲህ አርማችሁንም እስከ መጨረሻው ድረስ ኢትዮጵያዊነትን አድርጉ። አሁን በሃረር የሶማልያ ክልል፣ በእብሪተኞች መሰሪነት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ኦሮሞዎችና ከነሱ ጋር በሰላም ለዘመናት የኖሩት ሶማሌዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ ጣሩ። የጎንደር ህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ የተቻላችሁን ፈፅሙ። ይህን ሁሉ ብትፈፅሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ እኩልነት፣ የንግግርና የፅሁፍ ነፃነት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የሰብአዊ መብት፣ ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ይሰፍናሉ። ኢትዮጵያም በነፃነቷ ለዘላለም ትኖራለች።
እነዚህን አንገብጋቢ ጉዳይዎች በመፈፀም ፈንታ እንደ ቀድሞው ለብቻችን ስልጣኑን ጨብጠን፣ እንደ በፊቱ በጦር ኅይል ብቻ ችግሩን እንፈታዋለን ካላችሁ፣ ውጤቱ ይብስ እልቂት፣ ይብስ ሰቆቃ ይሆናል። አመፅ አመፅን ይወልዳልና የአመፅ ክበት እየተሽከረከረ ሁሉንም ያወድማል። አሁን ሁሉም ሰው በፖለቲካ ስለበሰለና መብቱንና ማንነቱን ስለአወቀ፣ ፍርሃቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ ለመብቱና ነፃነቱ ሲዋደቅ እየታየ ነውና። ደሞም የአሁኗ ኢትዮጵያ፣ የዛሬ 26 ዐመትዋ አይደለችምና። ስለዚህ ቡናው ፈልቶ መንተክተኩን ማሽተት ይገባችኋል። እናንተ ባላችሁበት የስልጣን ማማ ላይ ሆናችሁ፣ ሰፊውን የትግራይን ህዝብ ጨምሮ ለመላው የኢትዮጵያ ዜጎች ህይወት መጠበቅና ደህንነት ሃላፊነት አለባችሁ። ለራሳችሁም ደህንነት እንዲሁ። እምብዛም ብልሃት ያደርሳል ከሞት፣ እምብዛም ስለት ይቀዳል አፎት ተብሏልና። ደሞም ኅያል ሁልጊዜ በጦሩ ብዛት አያሸንፍምና። አዱኛና ጊዜም ከዳተኛ ናቸውና። በዚህ ዐለም ላይ ለዘላለም ፀንቶ የሚኖር ምንም ነገር የለምና። ሁሉም ነገር ማብቂያ ወቅት አለውና። የእናንተም ጉልበት እንደ ድሮው አይደለም። በዱር በገደሉ 17 ዐመታት፣ በከተማዎች 26 ዐመታት፣ በጠቅላላው ቢያንስ ለ43 ዐመታት ታግላችሁ እረፍት አግኝታችሁም አታውቁም። ለመሆኑ ጡረታ ወጥታችሁ እፎይ ብላችሁ የምትተርፋችሁን አጭር እድሜ የምትዝናኑባት መቼ ነው? ከእናንተ በዕድሜ ለሚያንሱት፣ ጉልበትና አዲስ ሃሳብ አዲስ እውነታ ለሚያፈልቁት ወጣት ኢትዮጵያውያን ስልጣን አስተላልፋችሁ፣ እናንተ የታፈራችሁ እንዲሁም የተከበራችሁና እንደ አርአያ የምትታዩ አረጋውያን ዜጎች የምትሆኑበት ወቅትስ መቼ ይሆን?  እባካችሁ ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ በመልቀቅ፣ለወጣቱ ትውልድ እንዲሁም ለአፍሪካ አምባገነን መሪዎች አርአያ ሁኑ፡፡ እናንተም በአገራችሁ ከሥልጣን በኋላ እፎይ ብላችሁ ኑሩ፡፡ ለኢትዮጵያም እፎይታ ስጡአት፡፡ ይበልጥ ክብርና ድል እንጂ ሽንፈትና ውርደት አይሆንባችሁም። ሥልጣናችሁን በክብር እንጂ በውርደት እንደማትቋጩት አምናለሁ፤ እመኛለሁም። ስለዚህ የኔን ትንሿን ምክሬን ሳትንቋት እንደምትተገብሯት እምነቴ የፀና ነው።
የኢትዮጵያ ታሪክ የ100 ዐመት ሳይሆን በሺህዎች የሚቆጠር መሆኑን የአክሱም ታሪክ ብቻ እማኝ ነው። መላው አፍሪካ ድሮ ኢትዮጵያ ይባል እንደነበር የሚመሰክር ጥንታዊ ካርታ እታች ሰፍሮአል። ያኔ አፍሪካ የታችውና የላይኛው አፍሪካ ተብሎ ነበር የተከፈለው። ዝቅ ብላችሁ እሱን ከማየት አትዘናጉ።
 በሚቀጥለው ገፅ የአለው ካርታ ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካ ብብት በታች ያለው ውሃ ሁሉ የእትዮጵያ ውቅያኖስ ይባል አንደ ነበር ያሳብቃል። ዛሬ የህንድ ውቅያኖስ የሚባለውም ጥንት የኢትዮጵያ ውቅያኖስ ይባል እንደነበር የሚያሳይ ካርታም ዐይቻለሁ።
ምእራብ አፍሪካ ብብት ስር በእንግሊዝኛ የኢትዮጵያ ውቅያኖስ የሚለውን ፅሁፍ አስተውሉ።

Read 8456 times