Print this page
Sunday, 10 December 2017 00:00

እንኳን አማቶች ተጨምረውበት…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

 አዲሶቹ ሙሽሮች የቄሱን ቡራኬ ለመቀበል ፊታቸው ናቸው፡፡ ቄሱ እስኪባርኩ ድረስ እርስ በእርስ መንቆለጳጰስ
ይዘዋል፡፡ ሙሽራው፡- “የእኔ እንጆሪ፣ የእኔ ብርቱካኔ!” ምናምን ነገር ይላታል፡፡ ሙሽሪት ደግሞ በበኩሏ… “የእኔ መንደሪን፣ የእኔ የወይን ዘለላ!” ምናምን ትለዋለች፡፡ ይሄኔ ቄሱ፡- “ባልና ሚስት ብያችኋለሁ” ከማለት ይልቅ ምን ቢሉ ጥሩ ነው… “አትክልትና ፍራፍሬ ብያችኋለሁ!” ---
    
   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እሱ ለእናቱ  “ሚስቴ ትቼህ እሄዳለሁ እያለች ታስፈራራኛለች፣” ይላቸዋል፡፡ እናት፣ የልጅቱ አማት ማለት ነው፣ ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“ማስፈራራቱን ተይና እሄዳለሁ ስትይ ቃል ግቢልኝ በላት” አሉትና አረፉት፡፡
አሪፍ የሚባል ትዳር ነበር፡፡ ምንም አይነት ሀይል ሰብሮ የማይገባው የሚባል አይነት፡፡ “እነሱን አታዩዋቸውም!” የሚባል አይነት ጥምረት፡፡ ግን ሁሉም አይነት ግንብ ሲውል ሲያድር እንደሚሰበር ሁሉ ይህኛውም የበርሊን ግምብ ተሰበረ…በአማትዬው፡፡ በሰውየው እናት፡፡
እኔ የምለው… በአማቶች የተነሳ መጣላት የቀረ መስሎን ነበር እኮ! አሀ…ዘንድሮ ደግሞ ለመጋጨትና ለመተናነቅ ምን ‘ነገረኛ አማት’፣ ምን ‘የሩቅ አክስት’ ያስፈልጋል!
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ምን የመሰለ ባህሪይ የነበራት ሴት… ማንም ይሁን ማንም ደንቀፍ ሲያደርግው “እኔን ይድፋኝ” ትል የነበረች ሴት… አማት በምትሆንበት ጊዜ ገድገድ ያደረገውን ሁሉ “ኸረ የእናት አባቴ አምላክ ይድፋህ!” የሚያሰኛት ለምንድነው? …የአማትነት ዲ.ኤን.ኤ የተለየ ነው እንዴ! አማት የሚለው ስም ይዞ የሚመጣው የሆነ የተከለከለ ንጥረ ነገር አለ እንዴ! የፍቺው መጠን ወደ 50% እየተጠጋ ባለበት ጊዜ ወደፊት ሰማንያ ሲፈራረሙ፣ አማቶችን በተመለከተ አባሪ ሰነድ ነገር መግባት ሳይኖርበት አይቀርም፡፡
አንደኛ፣ አማቶች ሰተት ብለው ማብሰያ ቤት የሚገቡበት ነገር፣ በህግና በመመሪያ ይወሰን፡፡ “እናትህ እዚህ ቤት በሚመጡበት ጊዜ ኩችና ዝር እንዳይሉ፣ የቀረበላቸው ምግብ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ሳይሰጡ ከፈለጉ መብላት፣ ካልፈለጉ መተው ነው፡፡” እንዲህ የሚያስሩ አንቀጾች ከሌሉ አስቸጋሪ ነዋ!
“ስሚ ደግሞ ጨዉን ሞጅረሽ ልጄን ለደም ብዛት እንዳትዳርጊው!” የተባለች ሚስት የሚሰማትን አስቡት፡፡ ምናልባት እኮ እንኳን ጨው ሊበዛበት ውሀ፣ ውሀ የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አማቶች አስተያየት መስጠት አለባቸዋ! የልጃቸው ተከላካይ ጠበቃ አይነት ነገር መሆን አለባቸዋ! አማትየው እኮ ልጃቸውን ያሳደጉት… አለ አይደል… “ሽንኩርት ኖረው አልኖረው ምን አባክ አገባህ! ትበላ እንደሁ አርፈህ ብላ!” እያሉ፣ በ‘ሹሮ ጁስ ነገር’ ሲጠቀጥቁት ኖረው ሊሆን ይችላል!
እናማ…እንኳን አማቶች ተጨምረውበት ዘንድሮ ስንት የሚያጋጭ ነገር ሞልቷል፡፡
“ልጄን ለባል ሰጠሁ ብዬ፣ ለካስ በርሜል ነው ያገባችው!” የተባለ ባል የሚሰማውን አስቡት፡፡ አማትየው እንዳሉት አጠጣጡ ስሙ ከበርሜል ጋር በአንድ አረፍተ ነገር ውስጥ እንዲነሳ የሚያደርገው ሳይሆን ከሥራ በኋላ ሁለቷንም፣ ሦስቷንም ቀመስ አድርጎ ስለሚመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አማቶች አስተያየት መስጠት አለባቸዋ! የልጃቸው ተከላካይ ጠበቃ አይነት ነገር መሆን አለባቸዋ!
ስሙኝማ… አማቶች እኮ ምንጊዜም ልጆቻቸው ክንፍ ጎደላቸው እንጂ መላእክት ናቸው፡፡ “የእኔ ልጅ እኮ በጨዋነት ነው ያደገችው፡፡ ለራሷ ሰው ቀና ብላ አታይ! ሁልጊዜ አንገቷን እንደደፋች…” እያሉ እናት ልጃቸውን ዙፋን ላይ ያስቀምጧታል፡፡ እሷ እኮ የሆነ ሰው ላይ የእርግማን መአቱን ማውረድ ከጀመረች አንድ ሰው ብቻ የሚናገር ሳይሆን ሙሉ የእግር ኳስ ቡድን የሚጮህ ነው የሚመስለው። “ይኸው፣ የሆነ ነገር አቅምሰውብኝ…” ምናምን ይባላል፡፡
“እሱ እንኳን መጠጥ ሊቀምስ በቡና ቤት በራፍ እንኳን አልፎ አያውቅም፡፡ ለበዓል የተጠመቀ ጠላ ሲሸተው አፍና አፈንጫውን በልብስ ይሸፍን ነበር፡፡ አረንቻታ ስሰጠው እንኳን እማዬ ይሄ ነገር ያሰክረኛል ይል ነበር፤ አሁን የሆነ ነገር አስነክተውብኝ…” ምናምን ይባላል፡፡
እኔ የምለው …ይሄ “እንዲህ አይነት ነገር አቅምሰውት ነው…”፣ “እንዲህ አይነት ነገር አስነክተውት ነው…” የሚባለው ነገር…አለ አይደል…ያልቀመሰና ያልተነካ ሰው የለም ማለት ነው!
እናማ…እንኳን አማቶች ተጨምረውበት ዘንድሮ ስንት የሚያጋጭ ነገር ሞልቷል፡፡
አማቶች ስለ ሚስት ሙያ፣ ስለ ባል ቢራ መውደድ ምንም አይነት አስተያየት እንዳይሰጡ ማእቀብ መጣል አለብን እንዴ! በነገራችን ላይ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በሆነ ምክንያት የሆነ ጡንቸኛ ማእቀብ ቢጣልብን ምን ሊሆን እንደሚችል አስባችሁት ታውቃላችሁ? ጥሬ ሥጋ! “ከእንግዲህ ነዳጅ አይገባም፣ ባለስልጣኖቻችሁ ደግሞ የትም አገር ዝር አይሏትም!” ምናምን የሚል ሳይሆን “ለሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት ጥሬ ስጋ መመገብ የተከለከለ ነው!” ቢባልስ!
ህዝቤ ጠቅላላ ጉግል እየገባ በዓለም ታሪክ በጥሬ ስጋ ምክንያት አብዮት የተነሳባቸውን ምክንያቶች ባያጠና ነው! ከዚህ በፊት ከሌለም የእኛ ‘በጥሬ ስጋ መከልከል የተነሳ የተቀሰቀሰ የመጀመሪያው አብዮት’ ምናምን ይሆናል፡፡ የምንወዳት ነገር፤ ይቺ ከአፍሪካ ምናምነኛ፣ ከዓለም ምናምነኛ የሚሏት ነገር!
ደግሞስ…አለ አይደል…“ኢትዮዽያ የአፍሪካን ዋንጫ ደግማ እስካልወሰደች ድረስ እነሆ በረከት ተከልክሏል” ቢባል ሰዋችን ምን እንደሚሆን አንድዬ ይወቀው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ይሄ የ‘እነሆ በረከት’ ነገር እንደ ‘ሆቢ’ ነገርም ይሆናል እንዴ! ግራ ስለገባን እኮ ነው! እንዴ፣ ልክ ማዶ ካፌ “ሻይ ቀምሼ ልምጣ” እንደሚባለው እሱ ነገርዬ እንዲህ ቀለለ!
ቂማ ላይማ፣ አይደለም ማእቀብ መጣል ማሰቡ እንኳን እውነተኛ ሱናሚ ምን አይነት እንደሆነ ለዓለም ማሳያ ይሆናል፡፡ ከፈለጉ ከዓለም አንደኛና ሦስተኛ የሆንባቸውንና ወደፊት የምንሆንባቸው ነገሮች በሙሉ ይውሰዷቸው እንጂ በቂማ ቀልድ የለም፡፡
ባልና ሚስትን የማጣላት የአማቶች ታሪካዊ ሚና በሌላ የተወሰደ መስሎን ነበር፡፡
ለነገሩ እንደ ነገረኛ አማቶች በየቦታው ጥልቅ እያልን የቆመውን የምናንጋድድ መአት ነን፡፡
“ካላጣሽው ሰው እሱን ጓደኛ ታደርጊያለሽ!”
“አንቺ ምነው ይሄን ያህል ጠመድሽው!”
“ብቻ ነገርኩሽ…”
“ብቻ ነገርኩሽ ብሎ ነገር ምንድነው?”
“እንጃ በቃ ሳየው ደስ አይለኝም፡፡”
አስቸጋሪ ነው…እንደ አማካሪ፣ መካሪ ምናምን መስለን ግን እንደ ‘ነገረኛ አማት’ የሚያደርገን ብዙ ነን፡፡ ጥብቅ በሆነና ‘የሚያስቀና’ የሚባል ወዳጅነት መሀል እንገባለን፡፡ ተመራርጠው ጓደኛ በሆኑት ሰዎች መካከል ገብተን “ደግሞ ጨዉን ሞጅረሽ በደም ብዛት እንዳትገዪው!” የሚመስል ነገር እንላለን፡፡
“ስማ፣ እሱ ለአንተ ጓደኝነት አይመጥንም፡፡”
“አይመጥንም ማለት ምን ማለት ነው?”
“ሳየው ተንኮለኛ ይመስላል፡፡ ከአንተ የሆነ የፈለገው ነገር መኖር አለበት፡፡”
“የምታውቀው ነገር ካለ ለምን አትነግረኝም!”
ስሙኝማ …ጨዋታም አይደል… በየፊልሙ እንደምናየው፣ ቄሶቹ መጨረሻ ላይ ሙሽሮቹን “አሁን ባልና ሚስት ብያችኋለሁ” አይነት ነገር ይሏቸውና ግንባርም ሆነ ምን ተሳስመው ጋብቻው ይጸናል፡፡ አዲሶቹ ሙሽሮች የቄሱን ቡራኬ ለመቀበል ፊታቸው ናቸው፡፡ ቄሱ እስኪባርኩ ድረስ እርስ በእርስ መንቆለጳጰስ ይዘዋል፡፡ ሙሽራው፡-
“የእኔ እንጆሪ፣ የእኔ ብርቱካኔ!” ምናምን ነገር ይላታል፡፡
ሙሽሪት ደግሞ በበኩሏ… “የእኔ መንደሪን፣ የእኔ የወይን ዘለላ!” ምናምን ትለዋለች፡፡ ይሄኔ ቄሱ “ባልና ሚስት ብያችኋለሁ” ከማለት ይልቅ ምን ቢሉ ጥሩ ነው… “አትክልትና ፍራፍሬ ብያችኋለሁ!” ብለዋቸው አረፉት፡፡
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ባል ከጓደኛው ጋር እያወራ ነው፡፡
“ሚስቴ፤ እናቴ ዘንድ እሄዳለሁ እያለች ነው፡፡ እኔም ዛቻ ነው ወይስ ቃል እየገባሽ ነው አልኳት፡፡”
“ምን ልዩነት አለው?”
“ወደ እናቴ መሄዴ ነው ማለቷ ከሆነ ቃል መግባት ነው፡፡ እናቴን እቤት አመጣታለሁ ማለት ከሆነ ግን ዛቻ ይሆናል፡፡”
እናማ…እንኳን አማቶች ተጨምረውበት፣ ዘንድሮ ስንት የሚያጋጭ ነገር ሞልቷል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4372 times