Sunday, 10 December 2017 00:00

የብሔርተኝነት ፖለቲካና አደጋው!?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

በየቦታው ከብሄርተኝነት ጋር በተያያዘ የሚጠሩ ግጭቶችን ተከትሎ የሰው ክቡር ህይወት መጥፋትን ለጆሮአችን የተለመደ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ መዳረሻ ያጣው ብሄርን መሰረት ያደረገ የእርስ በእርስ መጎዳዳት ወዴት ይወስደን ይሆን? ፅንፍ የወጡ የብሄርተኝነት ስሜቶች ምንጫው ምንድን ነው? የብሄር ፅንፈኝነትንና ኢትዮጵያዊነትን የሀገር አንድነትን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የተለያዩ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎችን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሱ አነጋግሮ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

            “ቋንቋችን ቢደበላለቅም ደማችን አንድ ነው”
               አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ (የኦሮሞ አባገዳዎች ም/ቤት ሰብሳቢ)

    የችግሩ መነሻ ምንድን ነው የሚለውን ጠለቅ ብሎ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ጥናት ለማድረግም በቀጥታ ከህዝቡ ውስጥ መግባትና ፍላጎቱን አመለካከቱን መጠየቅና መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ህዝቡ እርስ በእርስ አይጣላም፤ ተጣልቶም አያውቅም፡፡ ትልቁ ችግር ያለው ፖለቲከኞቹና ህዝቡን እንመራዋለን የሚሉት ጋር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከአያት ቅድመ አያቱም ጋር እርስ በእርስ ሲጋመድ የመጣ ነው፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያ በትክክል የሚያውቀው እናቱን እንጂ አባቱን አይደለም። አባቱ ከየት ወገን ከማን ዘር እንደሆነ አብዛኛው በእርግጠኝነት አያውቅም፡፡ እናቱን ግን ያውቃል፡፡
አሁን የሚታየው የዘርና ብሄር ቆጠራ እንዲሁም ይሄን ቆጠራ ጎራ ለይቶ ለመቆራቆዣ የመጠቀም ጉዳይ፣ በተለይ ወጣቶቹ ሊመረምሩት ይገባል። ባለስልጣናቱም ከሺህ አመታት በፊት ተዋዶና ተከባብሮ የኖረን ህዝብ ወደነበረበት ፍቅርና አንድነት ለመመለስ የሚጠበቅቸውን መስራት አለባቸው። ሌላው የዘር ተኮር ግጭቶች ሊፈጠሩ የሚችሉት የግል ጥቅምን ለማስከበር በሚደረግ ጥረት መሃል ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚህ ደም አፋሳሽ ግጭት የሚገኝ ሀብትና ንብረት ዋጋ የለውም፡፡ የደም ዋጋ ነው፡፡ በግፍ የተገኘ እንደመሆኑ ለልጅ ልጅም እርግማን ነው የሚሆነው፡፡ እግዚአብሔር የገነባውን ሰው፣ እንዴት ሰው ያፈርሰዋል። እግዚአብሔር የገነባውን ክቡር የሰው ልጅ፣ በቋንቋ መለያየት በራስ ስልጣን ማፍረስ የሚያስከፍለው ዋጋ እንዲህ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም፡፡
ህዝብችንም በእንዲህ ያሉ ችግሮች መደናቀፍ የለበትም፡፡ አለም አንድ በሆነችበት ጊዜ በአንዲት ኢትዮጵያ፣ በአንድ ባንዲራ ስር ለዘመናት የኖርን ዜጎች፣ ዛሬ ላይ ደርሰን የመለያየትና የመጠላላት ዲስኩር ማሰማት አይገባንም፡፡ አለም ይፋረደናል። መልካም አይሆንም፡፡ እኛ አሁን ያለነው ለትውልዱ መልካም ነገር ማቆየት አለብን፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው ደግሞ የአንድነት ስሜቱ የሻከረውን ይሄን ህዝብ ወደ አንድነት ማምጣት ነው፡፡ የመንግስት አካላትም በስነ ስርአቱ የህዝቡን አንድነት ፍላጎት መረዳት አለባቸው። በህዝቡ ስሜት መጓዝ አለባቸው፡፡ ከህዝቡ በተቃራኒ የሚቆሙ ከሆነ የተሻለ ነገር ሊመጣ አይችልም፤ የባሰ እንጂ። እኛ አባገዳዎች ህዝቡ መሃል ነው የምንኖረው። ብዙ እሮሮዎችን እንሰማለን፡፡ ህዝቡ ጫናው በዝቶብናል፣ ግድያውና እስሩ በዝቶብናል እያለ ነው፡፡ ይሄን የመንግስት ሰዎች መገንዘብ አለባቸው፡፡ እኔ አሁን አባ ገዳ ነኝ ብዬ ህዝብ ላይ በስልጣኔ የፈለኩትን የማደርግ ከሆነ፣ እኔ ያስቀመጥኩትን ግፍ ነው የኔ ልጅ የሚቀበለው፡፡ ዘመናዊ ስልጣንም ከዚህ አንፃር መታየት አለበት፡፡ ህዝቡን የሚለያዩ ነገሮች መወገድ አለባቸው። ጥቅመኝነት ከህዝብና ከሃገር አይበልጥም፡፡ ጊዜውን ጠብቆ ዋጋ ያስከፍላል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሩ ህዝብ ነው፡፡ ፈጣሪ ነው ይሄን ጥሩነት ያደለው፡፡ ጣሊያንን በጋራ የተፋለምነው በእግዚአብሔር ኃይል በተሰጠን አንድነት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ መሬቴን ወሰድክ በሚል የሚፈጠረው ፀብ ደግሞ ከንቱ ነው። እኛ ሰፊ መሬት ላይ የፈለግነውን ያህል ብንዘል መጨረሻችን ሁለት በሁለት በሆነች ጉድጓድ ውስጥ ነው የሚጠናቀቀው። እኔ መሬትን እንዲህ ነው የምረዳት፡፡ በዚህ ህዝብን ዝም ብለን ማደናቆር የለብንም፡፡
ከሀብትም ከመሬትም በላይ ህዝብ ወንድም፣ እህት፣ አባት፣ አጎት ይበልጣል። ቋንቋችን ቢደበላለቅም ደማችን አንድ ነው፡፡ ሁሉም ለፍቅር ራሱን ካስገዛ ይህቺ ሀገር አንድነቷና ክብሯ ይመለሳል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ አሁን እንደተጀመረው ህዝቡን እርስ በእርሱ ማቀራረብ፣ በተለይ ወጣቶችን በየትምህርት ቤቱ ማወያየት ያስፈልጋል። ስልጣን ላይ ያለው እንደሚመቸው ሳይሆን ህዝቡ እንደሚመቸው ነው ማድረግ ያለብን። ጨዋ ህዝብን ሰላም መንሳት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ህዝባችን ሰላማዊ ነው፡፡

-------

               “የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ መልሶ ለማምጣት ብዙ ድርድር ያስፈልጋል”
                  አቶ ክቡር ገና (የቢዝነስ ባለሙያ)

    ይሄ የብሄር ግጭት ችግር ከተፈጠረ ጀምሮ ነገሮቹ በእጅጉ እያሳሰቡኝ ነበር፡፡ ዋናው ነገር ለዚህ አይነቱ ችግር መጀመሪያውኑ ሁኔታዎች የመመቻቸታቸው ጉዳይ ነው፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ነው የቆየነው፡፡ የመንግስቱ አወቃቀር ገና ሲጀመር የኢትዮጵያ አንድነት ሊረጋገጥ የሚችለው፣ብሄርተኝነትን ማዕከል ባደረገ ስርአት ላይ ነው የሚል መርህ ነው የያዘው፡፡ በእንደዚህ መልኩ በብሄር የተመሰረተ ክልል ከአስቀመጡ በኋላ ብሄርተኝነት እንዲስፋፋ አልፈልግም ማለት ደግሞ ሌላ ተቃርኖ ነው፡፡ በብሄር የተመሰረተ አከላለል ሲቀመጥ በዚያ ውስጥ ተኮትኩተው የሚያድጉ ልሂቃን እየተፈጠሩ ነው የሚሄዱት፡፡ አሁን የተደረሰበት ደረጃ የዚያ ውጤት ነው፡፡ አሁን ወደ ኋላ መመለስና ማስተካከል ይቻላል ወይ የሚለው አስቸጋሪ ነው፡፡ በህዝቡና በልሂቃኑ መካከል ይህ አይነቱ ወደ ኋላ የመመለስ ፍላጎት አለ ወይ ነው ጥያቄው፡፡ እኔ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም እነዚያ ልሂቃን አሁን የራሳቸውን ብሄር ጥቅም ለማስጠበቅ ነው ቅድሚያ የሚሰጡት፡፡ አስቀድመን መታወቂያ ላይ ሳይቀር ብሄር አስቀምጠን ስናስጠናው ነው የዘለቅነው፡፡ ታዲያ ዛሬ እንዴት ነው ወደ ቀድሞ መመለስ የሚቻለው? ወደ ኋላ መመለስ ካስፈለገ፣ አዲስ ስትራቴጂ ማጥናት ነው የሚያስፈልገው፡፡
በፌደራል ስርአቱ የተቋቋሙ ክልሎች አሁን የቀድሞውን ኢትዮጵያዊነት ይፈልጉታል ወይ የሚለውን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ አሸናፊው ወገን በብሄርና በኢትዮጵያ ስም ነው ያቋቋማቸው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ እነዚህ ክልሎች አቅም አግኝተዋል፡፡ በዚያው ልክ የብሄርተኝት ስሜታቸው እየጠነከረ ነው የመጣው፡፡  እኛ የምንላትንና የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ መልሶ ለማምጣት ብዙ ድርድር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያን ጉዳይ ብናነሳ የሃገሪቱ እምብርት ነው፡፡ ዛሬ ከሀገሪቱ የተለየ ጥቅም ያስፈልገናል ካለ፣ያንን ጥቅም መስጠት ሁሉ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በብሄር ብሄረሰብ ያለው አስተዳደር ይቀጥል ከተባለም በየጊዜው በጥናት ማበልፀግ ያስፈልጋል፡፡ ዋናውን ስልጣን ደግሞ ክልል ላይ ሳይሆን ወረዳዎች ላይ ማድረግ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ትልቁ አቅም መፈጠር ያለበት በክልሎቹ ላይ ሳይሆን ከህዝቡ ጋር በሚቆራኙት ወረዳዎች ላይ ነው፡፡ ሥልጣኑን ማውረድ ያለብን ህዝቡ ላይ ነው፡፡ ይሄን ካደረግን ትንሽ ለውጦች ማምጣት ይቻለን ይሆናል፡፡


-------

           “ህዝብ መንግስትን ይፈጥራል እንጂ መንግስት ህዝብን አይፈጥርም”
             ሻምበል ለማ ጉያ (ሰዓሊ)

    እኔ አሁን የ90 ዓመት አዛውንት ነኝ፡፡ የዚህችን ሀገር ብዙ ሂደቶችና ውጣ ውረዶች አይቻለሁ። ከዛሬ 40 እና 50 ዓመት በፊትም ሆነ ዛሬ፣ ከ80 በላይ ብሄሮች በዚህችው በኢትዮጵያ ስር ነው የምንኖረው፡፡ የተለወጠች የተቀየረች ሀገር የለችንም፡፡ የተለወጠው ፖለቲካው ብቻ ነው። ሀገሪቷም ህዝቧም ያው ናቸው፤ አዲስ የመጣ ህዝብ የለም፡፡ ጃንጥላችን ኢትዮጵያችን ነች። ኢትዮጵያ ማለት አንድ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ስንል ሃምሳ ስድስት ግዛት የሚለው ወደ አዕምሯችን ፈጥኖ አይመጣም፡፡ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ጠንካራዋና አንድ የሆነችው አሜሪካ ምስል ነው። በአድዋ ጦርነት ጠላትን አሸንፈን ሃያላንን ያስደነገጥነው በ10 ወይም 11 ግዛቶች ተከፋፍለን አይደለም፤ በአንዲት ኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነን ነው፡፡ ጎሰኝነትና ዘረኝነት፣ ሀያል እንሆናለን ብለው ለተነሱት የጀርመኑ ሂትለርና የጣሊያኑ ሞሶሎኒም አልበጀም፡፡ ሺህ ጦርና ጉልበት ቢኖር አንደበት ፍቅርና አንድነትን ካልሰበከ፣ ተከታዮቹ ሰይጣኖች ስለሚሆኑ የኋላ ኋላ የትም ተጥለው ነው የሚቀሩት። ሂትለርና ሞሶሎኒ መጨረሻቸው ያላማረው አስተሳሰባቸውን የራሳቸው ህዝብ ስለማይወደው ነው፡፡ ስለዚህ አንድነትን መስበክ የፈጣሪ ስራን መስራት ነው፡፡ ያስከብራል እንጂ አያዋርድም፡፡ ዘረኝነት ነው የሚያዋርደው፡፡ የህዝብን አንድነት ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ሁሉ ከሰይጣን በስተቀር ሁሉም ይደግፈዋል፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ለ66 ዓመታት ኢትዮጵያን የከፋፈሉ መሳፍንቶችን አጥፍቶ አንድነትን የሰበከ ሰው ነው፡፡ ዛሬ በርካቶች በስሙ የሚጠሩት ታሪኩ ኩራት ስለሆናቸው ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ 10 ቦታ ነው የተከፋፈለችው፡፡ ይሄ ጥሩ አይደለም። ይሄን ህዝብና ሃገር አንድ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄን የሚያመጣ ሙሴ ያስፈልገናል፡፡ እዚህ ጋ አንድ ታሪክ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ዛሬ የህንድ ውቅያኖስ የሚባለው ጥንተ ስሙ የሶማሌ ውቅያኖስ ነበር፡፡ ሶማሌዎች በጎሳና በዘር በመከፋፈላቸው አንድነታቸውን ማስጠበቅ ተስኗቸው፣ ጥንተ ስማቸውንና ክብራቸውን በንግድ እንቅስቃሴ የዘመኑ ሃያል በነበረችው ህንድ ተነጥቀዋል። ኢትዮጵያም ክብሯ ተጠብቆ የሚኖረው በጎሳ በመከፋፈል ሳይሆን በፅኑ አንድነት ብቻ ነው፡፡
በአድዋ ጦርነት ምኒልክ መሪ ሆኑ እንጂ የተዋጋው ከየአቅጣጫው የተሰባሰበው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ይሄ የህዝቡ አንድነት ደግሞ የሚያኮራ ነው፡፡ እነሱ በአንድነት በአኩሪ ገድል ያስረከቡንን ሀገር ለመበታተን በመጣደፋችን አዝናለሁ፡፡ እኛ ሽማግሌዎች ነን፤ ወጣቶቹ ይህቺን ሀገር ሊበትኗት ሲነሱ ያሳዝነናል፡፡
የት ልንሄድ ነው? እኛ በዚህ እድሜያችን እንሰደዳለን እንዴ? ይሄ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እኛ ታግለን ይህቺን ሀገር አስረክበናል፤ ትውልዱ ግን ራሱን ወዳልሆነ አቅጣጫ እየወሰደ ነው፡፡ መልዕክቴ፡- ኢትዮጵያን አትንኩ ነው፡፡ ኢትዮጵያን መንካት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ቀድሞ ጊዜ ጥሪ አሳልፈናል፤ አሁን የሚታየው ግን በዚህ እድሜዬ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡ ህዝብ ነው መንግስትን የሚፈጥረው እንጂ መንግስት ህዝብን አይፈጥርም፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡


-------

            “ኢትዮጵያዊነት በህገ መንግስቱ ድጋፍ የለውም”
              አርቲስት አያልነህ ሙላት

    ብሄርተኝነት በአንዱ ገፅታ ሲታይ ሀገር ማለት ነው። ሀገርን መውደድ በሀገር ስሜት መስጠም ማለት ነው፡፡ እነዚህን ጥሩ ገፅታዎች ስንመለከት፣ብሄርተኝነት መጥፎ ነው ለማለት አያስችለንም፡፡ ሰዎች ስለ አካባቢያቸው መቆርቆራቸውና አካባቢያቸውን መውደዳቸው መጥፎ አይደለም፡፡ ትልቁ ጥያቄ፣ የኔ ብሄር ከሌላው ይበልጣል። የኔ ብሄር ባህል፣ አኗኗር ከሌላው ይበልጣል ወይም ይሄ ብሄር በዚህ ብሄር ላይ አመራሩ በደል አድርሷል የሚሉና የመሳሰሉ ከፋፋይ ሃሳቦች ሲገቡበት ነው፡፡ ያኔ ብሄርተኝነት ገፅታው ይለወጣል፡፡ እንዲህ አይነቱ ነገር ነው ሃገር የሚያጠፋው፡፡ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋዎች ያሉባትና በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖሩባት እየተባለ ነው የሚነገረው፡፡ እኔ ደግሞ ኢትዮጵያ በአንድ መደብ ላይ የተለያዩ አበቦች የበቀሉባት ነች ነው የምለው፡፡ አበቦቹ የየራሳቸው ውበት አላቸው። አንድ ላይ ሆነው የለመለሙበትን መደብ ይዘው ሲገኙ ያምራሉ፡፡ ይሄ ነው የኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና መሆን ያለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን ያለው ኢትዮጵያዊነት እንደዚህ ነውን? ይሄ ለሁሉም መቅረብ ያለበት ጥያቄ ነው። አሁን መልኩ ጠፍቷል፣ እያንዳንዱ በራሱ ዛቢያ ብቻ የሚሽከረከር ሆኗል፤ ስለ ጠቅላላዋ አንዲቷ ብሄር - ኢትዮጵያ ማሰብ ቀርቷል፡፡ ይሄም የሆነበት ምክንያት ደግሞ ከራሱ ከመንግስቱ አወቃቀር እንዲሁም ከህገ መንግስቱ አቀራረፅ የተነሳ ነው። ኢትዮጵያዊነት በህገ መንግስቱ ድጋፍ የለውም። በህገ መንግስቱ እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ነው ድጋፍ ያለው፡፡ እያንዳንዱ ብሄር የራሱን እድል በራሱ ወስኖ የመገንጠል መብት ሁሉ አለው ይላል፤ህገ መንግስቱ፡፡ ይሄ የፈጠረው ጠባብነት ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮች ምንጭ፣ ህገ መንግስቱ የፈጠረው ነው፡፡  
ሌላው የዚህ ሀገራዊ ቀውስ ችግር መንስኤ፣ የትምህርት ስርአታችን አቀራረፅ ነው፡፡ ነባሩን ሀገራዊ እውቀት፣ ባህል፣ አስተሳሰብ ወደ ኋላ ገፍተን ባዶ ሜዳ ላይ ነው ስርአተ ትምህርቱን የቀረፅነው፡፡ በሃይማኖትና ባህል አስታከን ነው፣ በውስጡ ጥልቅ ሳይንሳዊ ፍልስፍና (ስነ ከዋክብት ብንል፣ ስነ ፍጥረት ብንል፣ የቀን አቆጣጠር ብንል፣ ህክምና ብንል) የያዘውን ሀገር በቀል እውቀት አሽቀንጥረን ጥለን የውጭውን የተከተልነው። ሀገር በቀል እውቀቶቻችንን፡- ስነ ጥበብን፣ ስነ ስዕልን፣ ስነ ሙዚቃን (ያሬድ) ጥለን ነው የማናውቀውን የተቀበልነው፡፡ ምክንያቱም የፈረንጅ በመሆኑ ብቻ ተቀበልነው፡፡ ይሄ ደግሞ በቀጥታ የተማረውን ማንነቱን አስተፍቶ ነው የሌላውን የያዘው፡፡ እኛን ሀገር በቀል እውቀታችንን ካስተፉን በኋላ እነሱ ተመልሰው ወስደው በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ያስተምሩታል፡፡ ግዕዝን ማንሳት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ለሀገራችን የነበረንን ፍቅር፣ ክብርና አንድነት ካላሉት መካከል አንዱ፣ ከውጭ ዝም ብለን የተቀበልነው ዘመናዊ ትምህርት ነው፡፡
ሌላው ብሄርተኝነትን የሚፈጥረው ድህነት ነው፡፡ ድህነትን መሻገር ያልቻልነው ደግሞ ችግር ፈቺ ስርአተ ትምህርት ባለመቅረጻችን ነው፡፡ አሁን የፈረንጅ ቧንቧ ነው የሆንነው፡፡
እኔ አሁንም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ትልቅ እምነት አለኝ፡፡ በደምና በአጥንት የተገነባ የአንድነት ግንብ እንዲህ በቀላሉ መፍረስ አይችልም፡፡ ህዝብ ለህዝብ እየተገናኘ አሁንም አንድነቱን ለማጠናከር እየታተረ ነው፡፡
አሁንም ይሄን አንድነት ማምጣት የሚቻለው መሪዎች ህዝቡን መስለው ስለ ሀገር አንድነት መስበክ ሲችሉ ነው፡፡ መንግስት የህዝቡን ምክር መስማት አለበት፡፡ ህዝብ አንድነቱን ዛሬም እንደሚፈልገው እያሳየ ነው፡፡ መንግስት ከዚህ የህዝብ ቋንቋ ከተለየ ራሱን ማረም አለበት፡፡ በህዝቡ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ አለበት። እውቀቶች በሙሉ በህዝቡ ባህል ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው። ኢትዮጵያዊነት ስንል ይሄን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ዘመናዊነትን በራሳችን ባህል ላይ መገንባት አለብን።

Read 4052 times