Saturday, 09 December 2017 13:18

“ተቃዋሚዎች በድርድሩ ያገኙት ውጤት የለም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 · ኢህአዴግ የሚሰጠን ድጎማ ይቅርብን ብለን ከጋራ ም/ቤት ወጥተናል
      · የፀረ-ሽብር አዋጁ በድርድሩ ያለን ቆይታ የሚወሰንበት ነው
      · ኢህአዴግ የደርግን ስህተት እየደገመው ያለ ይመስላል
      · ዓላማችን አራት ኪሎ ቤተ መንግሥትን መቆጣጠር ነው
           አቶ ተሻለ ሰብሮ (የኢራፓ ፕሬዚዳንት)

    የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ እንደሚሉት፤ፓርቲያቸው ለ6 ዓመት በአባልነት ከቆየበት የኢህአዴግና ተቃዋሚዎች የጋራ ም/ቤት ራሱን አግልሏል፡፡ ለምን ይሆን? እስካሁን ተቃዋሚዎች ውጤት አላገኙበትም ከሚሉት የኢህአዴግና የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር ሂደት ያላቸው ቆይታ የሚወሰነውም በቀጣዩ የጸረ ሽብር አዋጅ አጀንዳ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመትና እንቅፋቶች የሚሏቸውንም  አብራርተዋል፡፡ እነዚህን ጨምሮ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንዲህ ተጠናቅሯል፡-


    በሀገሪቱ ለተፈጠሩ የፖለቲካዊ ቀውሶች መንግስት እየሰጣቸው ያሉትን ምላሾች ኢራፓ እንዴት ይመለከተዋል?
ያለመታደል ሆኖ ሀገራችን መጠነ ሰፊና የተወሳሰቡ ችግሮች ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከሁሉም አሳሳቢው ደግሞ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ተብለው የሚወሰዱ እርምጃዎችና የሚወጡ መመሪያዎች፣ ችግሮቹን ከድጡ ወደ ማጡ መውሰዳቸው ነው። ይሄ ፓርቲያችንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ እርግጥ ነው የፖለቲካ ችግሮች በየትኛውም ሀገር ውስጥ ይኖራሉ። ትልቁ ልዩነት ችግሮች የሚፈጠሩበት አቅጣጫ ላይ ነው፡፡ እኛ ዘንድ ጥቃቅን የእሳት ፍንጣሪዎች፣ ሰደድ እሳት እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ሲደረግ አይታይም፡፡ ሰደድ እሳት ከተፈጠረ በኋላ ነው እሳቱን ለማጥፋት ጥረት የሚደረገው፡፡ ይሄ አሳዛኙ የፖለቲካ አካሄዳችን ነው። ችግሮችን ለመፍታት የሚሞከረው በጉልበትና በኃይል ነው፡፡ ዘዴና ብልሃት እንጂ ኃይልና ጉልበት እሳት አያጠፋም። እንዲያውም ፍንጣሪዎቹን ያበዛና ወደ ጤነኛው ያዛምታል፡፡ እኛ ሀገር ቅንነት የለም፣ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የለም፡፡ እነዚህ በሌሉበት ሁኔታ ለዚህች ሀገር ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ ማምጣት አይቻልም። በመንግስትና በገዥው ፓርቲ እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሄ እርምጃዎች ለዚህች ሀገር የሚመጥኑና በቂ አይደሉም፡፡ ተስፋ ሰጪዎችም አይደሉም፡፡ ሁሉም ወገን በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያስብበት ይገባል፡፡
የሀገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
ጥያቄው ምሁራዊ ትንታኔ የሚያስፈልገው ነው። ሀገሪቱ አሁን ምን ላይ ትገኛለች ሲባል መጀመሪያ ምን ሲሰራ ነበር? አሁን ምን ተሰራ? በቀጣይስ ምን ሊሰራ ታቅዷል? የሚሉትን ጥያቄዎች የሚያካትት ነው፡፡ መንግስት “አሁንም ደህና ነኝ፣ ጥልቅ ተሃድሶ እያደረግሁ ነው፣ ቤቴን እየፈተሽኩ ነው፣ ጉልቻዎቹን እየቀየርኩ ነው” በሚልበት በዚህን ወቅት፣ መሬት ላይ የሚታየው ሃቅ ግን መንግስትን በቀጥታ የመቃወም እንቅስቃሴ ነው፡፡ ተቃውሞውም መፍትሄ ሲያጣና ጆሮ ዳባ ልበስ ሲባል ወደ ብሄር ግጭቶችና አለመረጋጋቶች እየተቀየረ ነው። ሰዎች እየሞቱና እየተፈናቀሉ፣ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እየፈጠረ ነው፡፡ ሀገሪቱ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነች ከተባለ፣ ሊገልፀው የሚችለው፣መንግስት ህገ መንግስቱን ከማስፈፀምና የሀገሪቱን ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር የተዳከመበት፣ ከማጥቃት ይልቅ ቆሞ ወደ መከላከል ብቻ የወረደበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡ ራሱን ማዳንና መከላከል ላይ ብቻ ነው ያተኮረው፡፡
የኢትዮጵያ ሁኔታ ወደ 1983 የሽግግር ወቅት እየተመለሰ ነው፡፡ ከሽግግሩ ወቅት ቀደም ብሎ በረሃ ያሉት “እንደራደር” ሲሉ፣ ቤተ መንግስት ያለው “ተራ ወንበዴዎች ናቸው” ብሎ እየናቀ ቆይቶ ነበር፡፡ የማታ ማታ የኃይል ሚዛኑ ወደ በረሃ ታጋዮች ሲያደላ፣ ቤተ መንግስት ያለው ለእርቅና ለሰላም ቢሯሯጥም ሰአቱ አልፎበት፣ ውድቀቱ ሲፋጠን በአይናችን ተመልክተናል። ይሄን የደርግ ስህተት አሁን ያሉትም እየደገሙት ይመስላል። ኃይል መፍትሄ አይሆንም፡፡ እርቀ ሰላምና ድርድርን ከወዲሁ ማሰብ አለባቸው፡፡ የንፋሱ አቅጣጫ የሚያመላክተው የ1983 ሁኔታን ነው። አሁን ሀገሪቱ ወደ መስቀለኛ መንገድም እየገባች ነው። ህዝብ የትኛውን አቅጣጫ መያዝ እንዳለበት መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሞ እያሰላሰለ ነው፡፡
ኢህአዴግ በግምገማ የተሻለ ሥርዓት እፈጥራለሁ እያለ ነው፡፡ ይሄ ምን ያህል ያዋጣል?
ራሴን በራሴ እገመግማለሁ፣ የአመራር ምንጠራ አደርጋለሁ ማለቱ የሚያዋጣ አካሄድ አይደለም። ከጎኑ ጠንካራ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲፈጠሩና ህዝቡ በእነሱ ስር እንዲደራጅ መንገዱን ቢከፍት ነው የሚሻለው፡፡ እሱም የሚጠናከረውና በሳል የሚሆነው ከጎኑ ጠንካራ ተቃዋሚ ሲኖር ነው፡፡ ያ አለመደረጉ የዚህ መንግስት አንዱ ድክመት ነው። ራስን በራስ ማደስ የሚለው የትም አያደርስም። ኢህአዴግ እባብ ነው ማለቴ ባይሆንም እባብ ቆዳውን በየጊዜው ይቀይራል ያድሳል ግን እባብነቱ አይቀየርም፤ ያው እባብ ነው፡፡ ቆዳ ቢቀየር ማንነትን አይለውጥም፡፡ ተሃድሶውም ይኼው ነው፡፡ ኢህአዴግ መልሶ ክብርና ሞገሱን ለማግኘት ከፈለገ ያለው አንድ አማራጭ  ብቻ ነው። እሱም ያለ ማወላወልና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ፣ ሁሉንም ለሀገሩ የሚቆረቆር ዜጋ፣ ያለ አንዳች ፍረጃ የሚያሳትፍ፣ ብሄራዊ የመግባባት መድረክ መፍጠር ነው፡፡ እስከ ስልጣን ማጋራት ድረስ ገፍቶ የመሄድ ቅን አስተሳሰብ ካለው፣ ክብርና ሞገሱን መልሶ ሊቀዳጅ ይችላል፡፡ ግን ይሄን የሚያደርግ አይመስለኝም። ደርግም ይሄን አድርግ ተብሎ በምሁራን፣ በሀገር ሽማግሌዎች ቢመከር ቢዘከር አልሰማም ብሎ ነበር፤ ታሪክ ራሱን ይደግማል ነው ነገሩ፡፡ ኢህአዴግ የጀመረው ጥገናዊ ለውጥም አይሰራም፡፡ ጥገናዊ ለውጥ ሊሰራ ይችል የነበረው ከ2007 ምርጫ በፊት ነበር፡፡
የእርስዎ ፓርቲን ጨምሮ ተቃዋሚዎችስ የህዝቡን ጥያቄዎች በትክክል የተረዱ ይመስልዎታል? በህዝቡና በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ይገልፁታል?
የሚያሳዝነው እኛም የሚጠበቅብንን ያህል አልሰራንም፡፡ ከህዝቡ ጎንም አልቆምንም፡፡ ተቃዋሚዎች በወቅቱ የህዝቡን ጥያቄ ተቀብለው እንዳያስፈፅሙ፣ መንግስት አጋጣሚውን ተጠቅሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው የደነገገው፡፡ በዚህ አዋጅ ውስጥ ለ10 ወር ያህል ምንም የፖለቲካ ስራ መስራት አልተቻለም ነበር፡፡ ሁሉንም ነገር ሽባ ያደረገው አዋጁ ነው፡፡ ሰርተፊኬታችንን ወይም ህልውናችንን ጠብቀን ማቆየታችን በራሱ ተአምር ነው፡፡
ተቃዋሚዎች ርዕዮተ አለም፣ ስትራቴጂና ሁነኛ የፖለቲካ ፕሮግራም የላቸውም የሚሉ ትችቶች ይደመጣሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
እንደ ኢራፓ ነው ጉዳዩን ማየት የምፈልገው። እኛ በተለይ ህዝባዊ መሰረታችን የጠነከረ፣ አመራሩ በምሁራንና በወጣት ምሁራን የተገነባ ነው፡፡ ህዝባዊ አጀንዳም አለን፣ ምርጫ ቦርድ መቼም ግልፅ አጀንዳና ፕሮግራም የሌለውን ፓርቲ አይመዘግብም፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች ስትራቴጂክ ፕሮግራም የላቸውም የሚለው የኢህአዴግ የማዳከሚያና የማጥላያ ዘዴ ነው፡፡ የራሱን ምርጫ ቦርድ እየሰደበ መሆኑንም ማወቅ አለበት፡፡ ፓርቲ መርምሮ መመዝገብ አይችልም እያለ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ እኛ እንደ ፓርቲ የራሳችን ግብ አለን፡፡ ግባችንም ስልጣን መቆናጠጥ ነው፡፡ አራት ኪሎ ታላቁ ቤተ መንግስትን ነው መቆጣጠር የምንፈልገው፡፡ ይህንንም የምናደርገው ህዝቡን ይዘን፣ በሰላማዊ የምርጫ ስርአት ነው፡፡ ለዚህ ነው የተቋቋምነው፡፡ የራሳችን ዝርዝር ፖሊሲም አለን። ከፖሊሲ አልፎ የምርጫ ማኒፌስቶም እያዘጋጀን ነው። ብሔራዊ እርቅና ብሄራዊ መግባባት ደግሞ ዋነኛ ፖሊሲያችን ነው፡፡ አካሄዳችንም ስትራቴጂን የተከተለ ነው። ስትራቴጂያችንም እኛ ከየትኛውም የፖለቲካ ንግግር መድረክ ያለበቂ ምክንያት አናፈገፍግም። የኢህአዴግና ተቃዋሚዎች የጋራ ምክር ቤት የገባነውም በዚህ መርህ ነበር፡፡ ለ6 ዓመት ተኩል በም/ቤቱ ከቆየን በኋላ ከስትራቴጂያችን ጋር አብሮ የሚሄድ ነገር ባለማግኘታችን ለቀን ወጥተናል። ኢህአዴግ የሚሰጠን ድጎማ ይቅርብን፣ የህዝብ አጀንዳ ይበልጣል ብለን ነው ለቀን የወጣነው። በተጀመረው ድርድርም ያቀረብናቸው ሃሳቦች የተቀባይነት መጠናቸውን ከገመገምን በኋላ ካላዋጣን ለቀን ለመውጣት አናመነታም፡፡ ርዕዮተ አለማችንም ሊበራል ዲሞክራሲ ነው፡፡
የሀገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ሰፊ የህዝብ ተቀባይነት ማግኘት ያልቻሉት ለምን ይመስልዎታል?     
ስለ ሌሎቹ ብዙ መናገር አልችልም፡፡ ህብረተሰቡ ሲናገር፣ ተቃዋሚዎች አንድነት የላቸውም ይላል። ይሄ እውነት ነው፡፡ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ አዳዲስ መስመሮችን ይፈልጋል፡፡ ሙጋቤ ከስልጣን የተወገዱት ምን አጉድለው ነው? ጋዳፊ የተወገዱት ለምንድን  ነው? ትልቁ የለውጡ አስኳል ግን ህዝብ አዲስ እይታ፣ አዲስ አቅጣጫ የመፈለግ ተፈጥሮአዊ ባህሪው ነው፡፡ እኛ ሀገርም ህዝብ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር የሚሄድ ስራ የሚሰሩ ተቃዋሚዎች የሉም የሚለው ያስማማናል፡፡ እኛ እንኳ 2002 ላይ ከምርጫ ቦርድ እውቅና ሲሰጠን፣ 92ኛ አገር አቀፍ ፓርቲ ሆነን ነው የተመዘገብነው፡፡ አሁን 92ቱ ፓርቲዎች የት አሉ? የመንግስትም ትልቁ የመድብለ ፓርቲ ግቡ፣ ቁጥራቸው መበራከቱ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ልንቀሳቀስ ቢሉ መፈናፈኛ አይሰጣቸውም። አሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስማችን ብቻ ነው ያለው። ከህዝባችን ጋር መገናኘት አንችልም፡፡ ከግል ሚዲያዎች በስተቀር ማንም ሃሳባችንን ለህዝብ አያስተላልፍም፡፡
በአጠቃላይ እኛ ተቃዋሚዎች አሁን ባለው ሁኔታ የቁም እስረኞች ነን፡፡ ስማችንንና ሰርተፍኬታችንን ብቻ ይዘን ነው የተቀመጥነው። በዚህ መሃል ህዝብ እንደ ደካማ ቢቆጥረን አይገርምም፡፡ እኛ እንደ ኢራፓ፣ በጠበበችው መንገድም ቢሆን የህዝብን አጀንዳ ለማሰማት ብርቱ ጥረት እናደርጋለን፡፡ እያደረግንም ነው፡፡
ከኢህአዴግ ጋር በምታደርጉት ድርድር እስካሁን ምን ውጤት አገኛችሁ?
እስካሁን ተቃዋሚዎች አቅርበውት በድርድሩ ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ የለም፡፡ አሁን የቋጨነው በምርጫ ስርአቱ፣ የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣ የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጆች ናቸው። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ፓርቲያችን ምንም ውጤት አላገኘበትም፡፡ የምንፈልገውንም አላገኘንም፡፡ በአጠቃላይ ለድርድሩ 34 ጉዳዮችን ብናቀርብም የተቀበሉት አስራ አንድ ያህሉን ብቻ ነው። እነሱም ገና ድርድር ይካሄድባቸዋል፡፡ እኛ ደፈር ብለን ህዝቡ የ2007 ምርጫ ውጤትን በህዝበ ውሳኔ ያረጋግጥ ብለናል፡፡ መንግስት በራሱ ፍቃድ ስልጣኑን ይልቀቅ ብለንም ጠይቀናል፡፡ ይሄም ወቀሳ ነው ያስከተለብን። በአጠቃላይ በዚህ ድርድር ኢህአዴግ የሚፈልገው ብቻ ነው እየሆነ ያለው፡፡
እስካሁን በድርድሩ የምትፈልጉትን ውጤት ካላመጣችሁ ከእንግዲህ በኋላ ምንድን ነው ተስፋችሁ?
የምርጫ ጉዳይን በተመለከተ የትኛውም ፓርቲ ውጤት ያላመጣበት፣ ኢህአዴግ የሚፈልገውን ያደረገበት ድርድር ነው የተካሄደው፡፡ ፓርቲያችን ቀጣዮቹ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ያስባል፡፡ እኛ መደራደርን አንፈራም፤ በደካማ ጎን መደራደርን ነው የምንፈራው። ተደራድረን መሄድ ያለብን ደረጃ ድረስ ሄደን ውጤት ካላመጣን፣ ሂደቱን አጋልጠን ነው፣ ከሂደቱ የምንወጣው፡፡ አሁን ቀጣዩ አጀንዳ የፀረ ሽብር አዋጁ ጉዳይ ነው። ይሄ በአጀንዳነት ከተያዙልን አንዱ ጉዳይ ነው። ይሄ እንግዲህ የምንፈተንበትና በድርድሩ ያለን ቆይታ የሚወሰንበት ነው የሚሆነው፡፡ በአዋጁ ላይ አንቀፅ የአንቀፅ ማሻሻያ፣ ስረዛና ተጨማሪ ነጥቦች አቅርበናል፡፡ በዚህ ላይ የምናገኘው ውጤት ለቀጣይነታችን ወሳኝ ነው፡፡
በድርድሩ ሂደት የኢህአዴግ ተፅዕኖ የበረታው ለምንድን ነው?
መድረኩ በራሱ የተከፋፈለ ነው፡፡ የጋራ ምክር ቤት አባላት ያልሆነው በአንድ ጎራ፣ የምክር ቤቱ አባላት በሌላ ጎራ ነው ያለነው፡፡ የጋራ ም/ቤት አባላት ከራሱ ከኢህአዴግ የድጎማ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ድጎማውን በማግኘታቸው የተነሳ የራሳቸውን አቋም ለመግለፅ ካልደፈሩ ግን ድርድሩ ዋጋ የለውም፡፡ የድርድሩ ገፅታ ይሄን ነው የሚመስለው፡፡

Read 2607 times