Sunday, 10 December 2017 00:00

“መንገኝነት ማንንም የትም አያደርስም” - የህንዶች አባባል

Written by 
Rate this item
(8 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ዕውቅ የአገር ፈላስፋ፣ አንድ ወንዝ ዳር እየተቀመጡ ምርምር፣ ምህላና ጥልቅ - ፀሎት ያደርጉ ነበር ይባላል፡፡ ወንዙ በፀጥታ መጥቶ፣ በፀጥታ በአዛውንቱ ፈላስፋ አጠገብ ያልፍና ቁልቁል በተዳፋቱ ይወርዳል፡፡ ይሄ ፀጥ ብሎ የሄደ ወንዝ፤ የአዛውንቱን ተመስጦ አልፎ በጨዋ ደንብ ያለ አንዳች ድምፅ ይወርድና አንድ የሚገርም ጩኸት ያሰማል፡፡ አዛውንቱ ፈላስፋ በወንዙ ቅላፄና ጠባይ ለብዙ ዓመታት ሲገረሙ ኖረዋል፡፡
አንድ ቀን አንድ እረኛ ከብቶቹን ውሃ ሊያጠጣ ወደ ወንዙ መጥቶ አዛውንቱን ያገኛቸዋል።
“እንደምን ዋሉ አባቴ?” ይላል፤ በአገሩ ደንብ እጅ እየነሳ፡፡
“ደህና፤ እግዚአብሔር ይመስገን” ይሉታል፤ በአክብሮት፡፡
“ምን እያደረጉ ነው?”
“የተመስጦ ፀሎት እያደረስኩና ይሄ ወንዝ የእኔን ምህላ ሳይረብሽ፣ በፀጥታ ማለፉ እየገረመኝ ተፈጥሮን እያደነቅሁኝ ነው”
“ይሄ እንዴት ያስደንቅዎታል? ከእርሶ ከተለየ በኋላኮ ወንዙ መጮሁ አይቀርም”
“ከእኔ በኋላ ምን ያስጮኸዋል?”
“ከእርሶ በኋላ ቁልቁለቱን ሲወርድ አንድ ትልቅ ቋጥኝ ድንጋይ አለ፡፡ ያንን ድንጋይ ውሃው ይገጨዋል፡፡ ከፍተኛ ድምፅ ይፈጥራል፡፡ ውሃው ያንን ቋጥኝ ሲመታው ታላቅ ጩኸት ይጮሃል፡፡ ‹ውሃውን ምን ያስጮኸዋል? ድንጋይ› የሚባለው አነጋር የመጣው ከዚህ ነው”
አዛውንቱ ተገረሙና፤
“ዕድሜ ልኬን እዚህ ስኖር፣ ወደዚህ ወንዝ የምመጣው የእኔን ፀሎት አክብሮ በፀጥታ ማለፉን ለማየት ብቻ ነበር፡፡ እኔን ካለፈ ወዲያ የሚጮኸው በአምላክ ትዕዛዝ ነው እል ነበር፡፡ ለካ እንዳንተ የተፈጥሮን ተዓምር የሚያይ ሰው ከጎኔ እንዲኖር ያስፈልግ ኖሯል”
እረኛውም፤
“አባቴ፤ እኔ የነገርኩዎት ማንም የሚያየውንና የሚያውቀውን ነገር ነው፡፡ ይልቁንስ የሚያስገርመው ለዓመታት ውሃው ውስጥ የተቀመጠው ቋጥኝ ድንጋይ የሚያስበው ነገር ነው፡፡ ሁልጊዜ የሚኮፈሰው ‹በዋና ከእኔ የሚበልጥ ማንም የለም› እያለ መሆኑ ነው፡፡”
“ይገርማል” አሉ አዛውንቱ፤ “የቆመው ሁሉ የሄደ፣ ውሃው የገጨው ሁሉ የዋኘ፣ ከመሰለው እንቅስቃሴ ከንቱ ቀረ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን!” አሉ፡፡
*       *      *
አካባቢያችንን በቅጡ ካላየንና በሚገባ ካልመረመርን፣ እያሰብን ሳይሆን እየተኛን ነው! ከተኛን ደግሞ የተመኘነው ለውጥ አይመጣም፡፡ በሀገራችን የምንናገረውን የሚያዳምጥ፣ ያዳመጠውንም የሚያውጠነጥን ዜጋ ከሌለ የለውጥና የተሀድሶ ተስፋ ይጨልማል፡፡ ማንም የምንሰጠውን አስተያየት ከጉዳይ ካልጣፈ መግባባት ድራሹ ይጠፋል፡፡ የመናገርና ሀሳብን የመግለፅ ዲሞክራሲያዊ ነፃነት አለ የምንለው፣ የምንናገረውን እህ ብሎ የሚሰማ፣ ሰምቶም እራሱን የሚመረምርና የሚለውጥ የበላይ አካል ሲኖር ነው! ይሄ ከሌለ በድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ ነው ትርፋችን፡፡ ለውጥ አይኖርም፡፡ እንቅስቃሴ አይኖርም፡፡ የኑሮ መልክ እየተጎሳቆለ ይመጣል፡፡ የሰማው ያላንዳች ፋይዳ ያልፋል፡፡ ያልሰማው እንደ አዲስ ኃይል መጥቶ ያደነቁረናል፡፡ ገጣሚና ተርጓሚ ከበደ ሚካኤል፤ “አዝማሪና ውሃ ሙላትን” የፃፉት ያለነገር አይደለም፡፡ እነሆ፡-
“አንድ ቀን፣ አንድ ሰው፣ ሲሄድ በመንገድ
የወንዝ ውሃ ሞልቶ፣ ደፍርሶ ሲወርድ
 እዚያው እወንዙ ዳር፣ እያለ ጎርደድ
አንድ አዝማሪ አገኘ፣ ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ፣ ድምፁን አሳምሮ
“ምነው አቶ አዝማሪ፣ ምን ትሠራለህ?”
ብሎ ቢጠይቅ፤
“ምን ሁን ትላለህ?”
“መንገዴን ዘግቶብኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት፣ በግጥም ብዛት
ሆዱን አራርቶልኝ፤ ቢያሻግረኝ ብዬ”
“አሁን ገና ሞኝ ሆንክ፣ ምነዋ ሰውዬ
 ነገሩስ ባልከፋ፣ ውሃውን ማወደስ
 ግን እንደዚህ ፈጥኖ፣ በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ፣ ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን እያሽካካ፣ መገስገሱን ትቶ
 እስኪ ተመልከተው፣ ይህ አወራረድ
 ያልሰማው ሲመጣ፣ የሰማው ሲሄድ
 ተግሳፅም ለጠባይ፣ ካልሆነው አራሚ
 መናገር ከንቱ ነው፣ ካልተገኘ ሰሚ!”
የሚሰማ ሳይኖር መናገር፣ አገርን አያበለፅግም፡፡ አስቦ የሚናገር ከሌለ፣ መደነቋቆር አይቀሬ ነው፡፡ ለሀገር የሚያስብ ሰው ምን ጊዜም አስፈላጊ ነው፡፡ የሚያስብን ሰው የሚያከብር ትውልድ መኖር አለበት፡፡ ተኪው የተተኪው ዱካ በመልክ በመልኩ ለክቶ ይያዝ እንጂ በጭፍን አይከተል፡፡ “መንገኝነት ማንንም የትም አያደርስም” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡

Read 5967 times