Sunday, 10 December 2017 00:00

በጣሊያን ኤምባሲ የተጠለሉ 2 ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣናት “አስታዋሽ አጣን” አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(47 votes)

 • “ለ26 ዓመታት በቁም እስር ላይ ነን፤ ወዳጅ ዘመድ አያየንም፤ በቂ ህክምናም አናገኝም”
           • “ሸማግሌዎች ከኤምባሲ አስወጥተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ጥረት ያድርጉ”
               
   የደርግ ውድቀትን ተከትሎ በኢህአዴግ እጅ ሥር እንዳይወድቁ በአዲስ አበባ የጣሊያን ኤምባሲ ከለላ ጠይቀው የገቡ 2 የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ ላለፉት 26 ዓመታት በቁም እስረኝነት እንደሚገኙ ገልፀው፤ “አስታዋሽ አጥተናል፣ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳያችንን ይመልከትልን” ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ፡፡
ሁለቱ ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት በቅርብ ወዳጆቻቸው አማካይነት ለአዲስ አድማስ በላኩት ደብዳቤ፤ ሀገራቸውን በተለያዩ ኃላፊነቶች ማገልገላቸውን በመጥቀስ፣ ላለፉት 26 ዓመታት በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ከዘመድ ወዳጆቻቸው ተነጥለው የሰቆቃ ጊዜ እያሳለፉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ምንም እንኳ ኤምባሲው ከለላ ሆኗቸው የቆየ ቢሆንም ወዳጅ ዘመድ  እንደማይጠይቃቸውና በቂ ህክምናም እንደማያገኙ የገለፁት ባለስልጣናቱ፤ በዚህም የተነሳ ለከፍተኛ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት መዳረጋቸውን በፃፉት ደብዳቤ ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ከሁለቱ ባለስልጣናት በላይ የመንግስት ስልጣን የነበራቸውን ሳይቀር ከ6 ዓመታት በፊት በይቅርታ መፍታቱን ያወደሱት ወዳጆቻቸው፤ የእነዚህ ባለስልጣናትንም ጉዳይ እንዲመለከተው በተለያየ ጊዜ አቤቱታ ቢቀርብም እስከ ዛሬ ቀና ምላሽ አለመገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻዎቹ የደርግ የስልጣን ዓመታት፣ የመንግስት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት (አሁን  የ82 አመት አዛውንት) ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የነበሩት (አሁን የ74 ዓመት አዛውንት) ሌ/ጀነራል አዲስ ተድላ አየለ፤ ሀገራቸውን በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ መንግስት ጉዳያቸውን በአንክሮ እንዲመለከተው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቀደም ሲል ሁለቱን ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት ከጣሊያን ኤምባሲ የቁም እስር ለማስወጣት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በሽምግልና ጥምር ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው እንደቀረ ይነገራል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንትም፣ እውነቱን አረጋግጠዋል፡፡ በእርግጥም ባለስልጣናቱ እንዲወጡ ሙከራ አድርገው እንደነበር ያወሱት አቶ ግርማ፤ ጉዳዩ ከዳር ሳይደርስ በተለያዩ ምክንያቶች ተሰናክሎ ቀርቷል ብለዋል፡፡ “አሁንም ጊዜው አልረፈደም” የሚሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ለጉዳዩ ቀና አተያይ ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎች፤ ግለሰቦቹን ከጣሊያን ኤምባሲ አስወጥተው፣ በሰላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ጥረት ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል- የቀድሞ ባለሥልጣናቱ ያሉበት ሁኔታ በእጅጉ የሚያሳዝን መሆኑን በመግለጽ፡፡
የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት ሌ/ኮ ብርሃኑ ባይህ እና ሌ/ጄ አዲስ ተድላ፤ የትውልድ፣የትምህርትና የሥራ ሃላፊነታቸውን በዝርዝር የሚገልጽ መረጃ ለአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል የላኩ ሲሆን ለግንዛቤ ያህል ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡

Read 18136 times