Sunday, 10 December 2017 00:00

ኢዴፓ የአመራር ለውጥ አደረግሁ እንጂ አልተከፋፈልኩም አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

· “መፈንቅለ ስልጣን ተፈፅሞብናል” ዶ/ር ባንትይገኝ ታምራት
                · አዲሱ አመራር ራሱን ከድርድሩ ሂደት አግልሏል
                 
    በፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ተመርጠን ወደ ስልጣን መጥተናል ያሉት አቶ አዳነ ታደሰ፤ኢዴፓ አለመከፋፈሉንና ፕሬዚዳንት በነበሩት ዶ/ር ጫኔ ከበደና 3 አመራሮች ላይ ብቻ እርምጃ መውሰዱን የገለፁ ሲሆን የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ባንትይገኝ ታምራት በበኩላቸው፤”መፈንቅለ ስልጣን ነው የተፈፀመብን፤ ጉዳዩንም ወደ ፍ/ቤት ወስደነዋል” ብለዋል፡፡
ከኢህአዴግ ጋር በሚደረገው ድርድር ከፍተኛ የዲሲፕሊን ግድፈት በፈፀሙ ሶስት አመራሮች ላይ የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ከኃላፊነት ዝቅ የማድረግ እርምጃ መውሰዱን የጠቀሱት አቶ አዳነ፤ በዚህ ምክንያት በአንዳንድ ወገኖች ኢዴፓ እንደተከፋፈለ ተደርጎ መነገሩ ስህተት ነው ብለዋል፡፡
በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት እርምጃ የተወሰደባቸው የቀድሞ አመራሮች ውሳኔውን ለመቀበል ባለመፈለጋቸው ችግር መፍጠራቸውን፣ ነገር ግን መላው የፓርቲው አባላት አንድነታቸውን ጠብቀው ፓርቲውን እያገለገሉ መሆኑን አቶ አዳነ ከትላንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡  
ለመሆኑ እናንተን ምርጫ ቦርድ ያውቃችኋል ወይ? የሚል ጥያቄ ከአዲስ አድማስ የቀረበላቸው አቶ አዳነ በሰጡት ምላሽ፤ “ለቦርዱ የአመራር ለውጡን በተመለከተ በደብዳቤ አሳውቀናል፤የፓርቲውን ደንብ ተመልክቶ ውሳኔ ያሳልፋል ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፓርቲው የአመራር ለውጥ ማድረጉንና ተደራዳሪዎቹን መቀየሩን በተደጋጋሚ ለፓርቲዎች ድርድር ኮሚቴ ቢያሳውቅም ቀና ምላሽ ባለማግኘቱ፣ ከድርድሩ ራሱን ማግለሉን አቶ አዳነ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ባንትይገኝ ታምራት ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ጉዳዩ በህግ ተይዟል፤ ነገር ግን የተፈፀመብን መፈንቅለ ስልጣን ነው፤ አሁንም ህጋዊ አመራሮቹ እኛ ነን” ብለዋል፡፡

Read 5257 times