Sunday, 10 December 2017 00:00

ኢትዮጵያውያን ነገ በፖለቲካ ችግሮቻቸው ላይ ይመክራሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

 *ታዋቂ ምሁራን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ የኢህአዴግ ተወካዮች፣ የደርግ ባለሥልጣናት፣ ባለሃብቶች፣ ደራሲያን ---- በመድረኩ ላይ ይጠበቃሉ
   
    “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?” በሚል መሪ ቃል፣ በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት በነገው እለት በሚካሄደው ህዝባዊ ውይይት ላይ የሀገሪቱ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ፓርቲው ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ አምባሳደር ሲኒማ  አዳራሽ፣ ለ4 ተከታታይ ሳምንታት ያዘጋጀውን ህዝባዊ ውይይት በነገው ዕለት  እንደሚጀምር  የጠቆሙት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ፤ “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት? በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ምሁራን የሀገሪቱን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች  እንደሚፈትሹና የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም እንደሚያመላክቱ አብራርተዋል፡፡   
በነገው ህዝባዊ ውይይት ላይ ከ1500 በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና በክብር እንግድነትና በተሳታፊነትም የሀገሪቱ ታዋቂ ምሁራንና ግለሰቦች፣ፖለቲከኞች፣አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች  እንዲገኙ ፓርቲው በደብዳቤ ጥሪ ማስተላለፉን አቶ አበበ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
በሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ በጥልቀት ይመክራል ተብሎ በታሰበው በዚህ ህዝባዊ ውይይት ላይ ፕ/ር መድህኔ ታደሰ፣ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት፣ አቶ ክቡር ገና፣ ወ/ት ሰሎሜ ታደሰ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፣ ጋዜጠኛ መአዛ ብሩ፣አቶ ሙሼ ሰሙ፣አቶ አስራት ጣሴ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ ከቀድሞ የደርግ አመራሮችም አቶ ፍቅረስላሴ ወግደረስ፣ ሻምበል ፍሰሃ ደስታ በመድረኩ ላይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሰማያዊ ፓርቲ ጠቁሟል፡፡  
በውይይት መድረኩ ላይ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በማህበራዊ ድረ-ገፆች  ሀሳብ በማንሸራሸር የሚታወቁ ጦማሪያንም እንደሚታደሙ የጠቆሙት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ደራሲ ይስማዕከ ወርቁን የመሳሰሉ ዕውቅ የጥበብ ባለሙያዎችም መጋበዛቸውን አስታውቀዋል፡፡  
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በተለይ በግጭት አፈታት ላይ በርካታ ጥናቶችን የሰሩና ያቀረቡ ምሁራን በደብዳቤ ጥሪ እንደተደረገላቸው የጠቆሙት አቶ አበበ፤ በግጭት አፈታት ላይ የሚሰሩ ተቋማትም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ለአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፡- ለደኢህዴን፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ህወሓት በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ፓርቲው በደብዳቤ ጥሪ ማስተላለፉን ተናግረዋል፡፡
 “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?” በሚል አጀንዳ የሚካሄደው ይህ የውይይት መድረክ፤ በቅንነት የሀገሪቱ ችግሮች ተመርምረው፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎች የሚመላከቱበት እንዲሆን ይፈለጋል ተብሏል፡፡ በመድረኩ ላይ የሰማያዊ ፓርቲ ሚና ከማስተባበር የዘለለ እንደማይሆንና የውይይት መድረኩ ለሁሉም ተሳታፊዎች ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል - አቶ አበበ አካሉ፡፡

Read 10021 times