Saturday, 09 December 2017 12:59

በደብር አለቃው ቢሮ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ተገኘ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “በፍተሻው ወቅት ወደ ቢሯቸው ፈጥነው ገብተው ሽጉጡን ለመሰወር ሞክረዋል”

     በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ነፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ፣ የሳሪስ ፈለገ ብርሃን ቅ/ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ደብር፣ ተመዝብሯል ስለተባለ ገንዘብ ለማጣራት፣ የሀገረ ስብከቱ ልኡካንና የሰበካ ጉባኤ አባላት ፍተሻ በሚያደርጉበት ወቅት፤ በደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ልዑል አማረ ታዬ የቢሮ ጠረጴዛ መሳቢያ ውስጥ ሕገ ወጥ ሽጉጥ መገኘቱ አነጋጋሪ ሆነ፡፡
የደብሩን አስተዳዳሪና የጽ/ቤቱን ሓላፊዎች፣ ከሰበካ ጉባኤ አባላት እና ከምእመናን ጋር ውዝግብ ውስጥ የከተታቸው ጉዳይ፤ በወር 105ሺ ብር ያህል ገንዘብ የሚያስገኙ የወፍጮ ቤትና የሱቅ ገቢዎች፣ ላለፉት ስድስት ወራት የደረሰበት ባለመታወቁ እንደሆነ የጠቆሙት ምንጮች፤ የደብሩ አስተዳዳሪ፣ ት/ቤት አሠራለሁ በማለት ላለፉት 3 ዓመታት ከምእመናን መጠኑ የማይታወቅ ገንዘብ ማሰባሰባቸውንና ገንዘቡ የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ይገልጻሉ፡፡
ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ በሚል ያለጥናት ቦታ መመረጡንና በቁፋሮ የወጣው ገረጋንቲ ድንጋይ፣ በአንድ በጎ አድራጊ ትብብር በነጻ ከስፍራው ቢነሣም፣ በክፍያ ነው ብለው በግል መጠቀማቸውን ምንጮቹ አክለው ያስረዳሉ፡፡ በእነዚህ ውዝግቦች የጀመረው አለመግባባት፣ የአካባቢው ወጣቶችና ምዕመናን፣ የደብሩን አስተዳዳሪ ቢሮ በኃይል በይደው እስከ ማሸግ አድርሷቸዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተላኩ የአጣሪ ኮሚቴ አባላትና የፀጥታ አካላት፣ ማክሰኞ ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት ገደማ፣ በታሸጉት የጽ/ቤቱ ቢሮዎች ላይ ፍተሻ ለማካሔድ በሚከፍቱበት ወቅት፣ ከደብሩ አስተዳዳሪ ቢሮ ጠረጴዛ መሳቢያ ውስጥ ሽጉጡ መገኘቱን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ አስተዳዳሪው ቢሯቸው በሚከፈትበት ወቅት፣ ፈጥነው ወደ ውስጥ በመዝለቅ፣ ከመሳቢያ ውስጥ ሽጉጡን አውጥተው ወደ መታጠቂያቸው ለመደበቅ ሲሞክሩ፣ በሰበካ ጉባኤው አባላት እጅ ከፍንጅ መያዛቸውንና ወደ ክፍለ ከተማው ፖሊስ ጣቢያም ተወስደው ምርመራ ሲካሔድ፣ መሣሪያው ሕገ ወጥ ኾኖ መገኘቱ ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪው አስተዳዳሪ፣ በበነጋው ረቡዕ ኅዳር 27 ቀን በዋስትና ቢለቀቁም፣ ቀደም ብሎ በማኅበረ ምእመናኑ ማስጠንቀቂያ ወደ ደብሩ እንዳይገቡ ከሌሎች የጽ/ቤት ሓላፊዎች ጋር የተላለፈባቸው እገዳ፣ አሁንም ጸንቶ እንደሚገኝ ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
ምእመናኑና የሰበካ ጉባኤ አባላቱም፣ አስተዳዳሪው፣ የሒሳብ ሹሙ፣ ተቆጣጣሪው፣ ገንዘብ ያዡና የስብከተ ወንጌል ሓላፊው በሕግ እንዲጠየቁላቸው፤ በምትካቸውም “ለሃይማኖቱ ቀናዒ የኾነና የተመሰከረ የሥነ ምግባር ግለ ማኅደር ያለው የሃይማኖት አባት” እንዲመደብላቸው ባለፈው ሰኞ ከሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር ባደረጉት ውይይት ጠይቀዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ መምህር ጎይቶም ያይኑ በበኩላቸው፣ ለምእመናኑ ጥያቄ በአፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሰጡ ማረጋገጣቸው ታውቋል፡፡  

Read 5962 times