Saturday, 09 December 2017 12:55

ኤድናሞል የመዝናኛና የጨዋታ ዞን 10ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

“በጣም የሚያስደስተኝ፣ ግን ደግሞ አነስተኛ ገቢ የሚያመጣው ኤድናሞል ነው” - አቶ ተክለብርሃን አምባዬ
       
   በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ማግስት የመዝናኛ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው ኤድናሞል የመዝናኛና የመጫወቻ ዞን፤ የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት በዓል፣ ከትናንትና አንስቶ በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው። በዓሉ ለቀጣዮቹ 10 ቀናት እየተከበረ እንደሚቀጥል የድርጅቱ ኃላፊዎች ባለፈው ማክሰኞ በኤድናሞል ማቲ መልቲ ፕሌክስ ሲኒማ ሶስት አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት በ5 ሚ. ብርና በ200 ሰራተኞች ስራ የጀመረው ኤድናሞል ሶስት፤ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሲኒማ ቤቶች፣ የጨዋታ ዞኖችና ከ80 በላይ የጨዋታ አማራጭ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ከሆሊውድ በቀጥታ የሚመጡ 3ዲ ተወዳጅ ፊልሞችን ከሌላው አለም እኩል በማሳየት፣ በአገራችን የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ግንባር ቀደም መሆኑን ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡
የ10 ዓመት ጉዞውን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በቀረበ ዘጋቢ ፊልም ላይ የኤድናሞል ባለቤት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ ሲናገሩ፤ “ካሉኝ ስድስት ኩባንያዎች በጣም የሚያስደስተኝም ዝቅተኛ ገቢ የሚያመጣውም ኤድናሞል ነው፤ ምንም ገቢው ዝቅተኛ ቢሆንምና ከሌሎች እህት ኩባንያዎች በሚደረግለት ድጎማ ቢንቀሳቀስም የህሊና ሰላም ይሰጠኛል” ብለዋል፡፡
በአሥሩም ቀናት የተለያዩ የመዝናኛና የመጫወቻ ፕሮግራሞች የተሰናዱ መሆናቸውን የገለፁት ኃላፊዎቹ፤ ከነዚህም መካከል በ10 ዓመት ውስጥ ከታዩት የሆሊውድ ፊልሞች “ምርጥ አስሩ” በየቀኑ በነፃ ለእይታ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል። በዓሉን አስመልክቶም፤ ከተመረጡ ስድስት ት/ቤቶችና የበጎ አድራጎት ድርጅቶ ለሚመጡ ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎች፤ ነፃ የመጫወቻ፣ የምሳና የለስላሳ መጠጥ አቅርቦት የተዘጋጀ ሲሆን ለዚህም ከግማሽ ሚ. ብር በላይ መመደቡን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በ10ሩ የበዓሉ ቀናት ወደ መዝናኛ ማዕከሉ ለሚመጡ ህፃናትም የመጫወቻ ዋጋ ቅናሽ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ በመዝናኛ ኢንዱስትሪው ተግዳሮቶች፣ በባህል አጠባበቅና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የፓናል ውይይት እንደሚደረግም ታውቋል፡፡
ኤድናሞል ሰራተኞቹንም አልረሳም፡፡ ከህንፃ ግንባታው ጀምሮ እስካሁን በፅናት ያገለገሉትን ሰራተኞች የመሸለምና እውቅና የመስጠት ፕሮግራምም አለው ተብሏል፡፡ ኤድናሞል የመዝናኛ ኢንዱስትሪውን ለማዘመንና ልዩነት ለመፍጠር የውሃ መዝናኛ “water park” የማስገንባት እቅድ የያዘ ሲሆን ኤድናሞልን በየክልሉ የማስፋፋትና አውት ዶር አሚዩዝመንት ላይ ለመስራት በርካታ እቅዶች እንዳሉት ተገልጿል፡፡
ለመዝናኛ አገልግሎት የሚከፈለው ዋጋ ውድ በመሆኑ የሚያገለግለው በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉትን የህረተሰብ ክፍሎች ነው ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ፣ ኃላፊዎቹ ሲመልሱ፤ ኤድናሞል የመጫወቻ እቃዎችን ሲያስገባ ከፍተኛ ቀረጥ እንደሚጣልበት፣ የሆሊውድ ፊልሞችን ሲያስገባ ሌላው አገር በሚወስድበት እኩል ዋጋ በዶላር እንደሚገዛ፣ የሚመጡት የመጫዎቻ እቃዎች ሲበላሹ የጥገና አገልግሎት ማጣት ችግር እንዳለበት ጠቁመው፣ ይሄም ሁሉ ሆኖ ግን ህብረተሰቡ ላይ የሚጣለው ክፍያ በጣም አነስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተለይ የሆሊውድ ፊልሞች በኪሳራ እንደሚያሳዩና ኤድናሞል ከሌሎች ቢዝነሶች እየተደጎመ እንደሚሰራ የገለፁት ኃላፊዎቹ፤ የመዝናኛ ኢንዱስትሪው የፖሊሲ ድጋፍ ስለሌለው ስራውን ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል፡፡   

Read 2423 times