Tuesday, 05 December 2017 00:00

‘ሪያሊቲ ሾው’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)


             “--‘ነገር’ በአለቆች ፉከራ መልክ ይመጣል፡፡ ስንት ወር ሙሉ በራሱ ድክመት ያልሰበሰበውን
ሂሳብ “በሁለት ቀን ውስጥ ባትከፍሉ እናንተን አያድርገኝ!” አይነት ቃና ያለው ፉከራ፡፡ ‘ነገር’ ሆነ
ተብሎ የተሳሳተ መረጃ በማስተላለፍ መልክ ይመጣል፡፡ “የአካባቢው ሰዎች በአገልግሎት አሰጣጡ
መደሰታቸውን ለሪፖርተራችን ገለጸውለታል” አይነት ነገር፡፡---”
    ኤፍሬም እንዳለ

    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በቀደም የገና ጾም መግቢያ ቅበላ ነበር። ለጿሚዎች አንድ ‘ሪያሊቲ ቲቪ ሾው’ ምናምን አይነት ነገር ሳይሆን የእውነት ከልብ የሆነ የጾም ወቅት ያድርግላቸውማ፡፡
እኔ የምለው…በቀደም እንደ ዶሮ ማነቂያ የመሳሰሉት ሉካንዳ ቤቶች ያሉባቸው አካባቢዎች የነበረው ግፊያ ላይ ሰው አይገርምም? በተወደደ ሥጋ፣ ‘ዋንስ አፖን ኤ ታይም’ (ከእለታት አንድ ቀን እንደማለት) ከተገኘም እሰየው ለሚባልለት ሥጋ፣ ይሄ ሁሉ በአናት ላይ አናት የሆነ ግፊያ! (በነገራችን ላይ ባለሉካንዳ ቤቶች በቅበላና በመሳሰሉት ጊዜያት... አለ አይደል…ተራ አስከባሪዎች ምናምን ሳያስፈልጋቸው አይቀርም! ወይም “ለቅበላ ሥጋ ገዝቶ ለመውሰድና እዛው ለመመገብ ለሚፈልጉ ሁሉ፣ የቦታ ማስከበሪያ መቶ ብር በመክፈል ከእለቱ ከሦስት ቀን በፊት ወረፋ ማስያዝ አለባቸው” ምናምን የሚል ማስታወቂያ የሚያስነግሩበት ጊዜ አይመጣም አይባልም!)
ታዲያላችሁ…እንዲህ እየሆንን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ምናምን የሚያሰሉት ሰዎች ግራ ሳይገባቸው አይቀርም፡፡ ምንም ቁጥር፣ ‘ዳታ’ ቅብጥርሶ ሳያስፈልግ፣ የሥጋ ቤቱን ግፊያ ብቻ በማየት… “በቃ የሰውን የነፍስ ወከፍ ገቢውን አምስት ሺህ ዶላር ብለህ ሙላው” ባይባባሉ ነው!
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ጓደኛሞች ሰብሰብ ብለው እያወሩ ነው፤ሁሉም ቅበላን እንዴት እንዳሳለፉ የየራሳቸውን ‘ገጠመኝ’ ይተርካሉ፡፡ ይሄን ሁሉ ጊዜ አንደኛው ዝም ብሏል፡፡
“አጅሬው ምነው ዝም አልክ! ጾም አልተቀበልክም፣ ትንሽ ቁርጥ ምናምን አላልክም እንዴ?” ይሉታል፡፡ ምን ቢል ጥሩ ነው፣
“እኔ ገና መቼ ያለፈውን ጾም ጨረስኩና! አሁንም ገና እየጾምኩ ነው” አለና አረፈው፡፡ የገነት መግባት ጉዳይ ሳይሆን ኑሮ እንዲጾም አስገድዶታል። እናም በኑሮ ተገደን የምንጾማቸውና ልንፈታቸው ያልቻልናቸው ነገሮች መአት ናቸው፡፡ በሁሉም ነገር ‘ጾሙ’ በቀን ሀያ አራት ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀን የሆነባቸው ብዙ ናቸው፡፡
“ምን ተሞክሮ አለዎት?”
“ተሞክሮ ማለት…”
“ማለት እንደው በዚህ ሁሉ ዘመን ከቅበላ ጋር በተያያዘ ፈገግ የሚያደርጉ፣ የሚያዝናኑ ነገሮች ሳይገጥምዎት አልቀሩም፡፡”
“በእርግጥ በርካታ ፈገግ የሚያደርጉና የሚያስደንቁ ነገሮች ገጥመውኛል፡፡ ግን ለመጨረሻ ጊዜ ጾም በቁርጥ የተቀበልኩት ማራዶና እንግሊዝ ላይ በእጁ ያገባ ሰሞን በመሆኑ ገጠመኞቼን ሁሉ ረስቻቸዋለሁ፡፡”
እንዲህ ነው… ጊዜ እየረዘመ ሲሄድ “ስማ፣ አንዱን ኪሎ ጥብስ፣ ሁለቱን ጥሬ አድርገው” እየተባባልን ስንጮህ የነበርነው ሁሉ ወደ አፈ ታሪክነት ይጠጋል።
በነገራችን ላይ መጾም በእምነት ደረጃም ሆነ በሳይንሱም አሪፍ ነው፡፡ ግን በእምነት ደረጃ የምንጾመውን የሆነ ‘ሲቹኤሽን ኮሜዲ’ አይነት ስናስመስለው አሪፍ አይደለም፡፡ “ከማን ጋር ነው ድብብቆሹ!” ያሰኛል፡፡
“ስማ ቁርስ እንብላ፣ የእኔ ግብዣ ነው፡፡”
“አይ ይቅርብኝ…
“ለምን! ዘንድሮ ያውም ጋባዥ ተግኝቶ መግደርደር አለ እንዴ!”
“እንደ እሱ ሳይሆን፣ እስከ ስድስት ሰዓት ስለምጾም ነው፡፡”
ስለዚህ የቁርሱ ግብዣ ወደ ምሳ ይሸጋገራል፡፡ ምሳ ሰዓት…
“ጥሩ የጾም ምግብ ያለው የት ነው? ምርጫ ከአንተ፣ ግብዣ ከእኔ…”
“እዚህ ሳር ቤት አካባቢ እንትን የሚባል ሬስቱራንት…”   
እተባለው ስፍራ ይኬዳል፡፡ አለ አይደል…ልክ የቅበላው ጊዜ ሉካንዳ ቤቶች ሲጋፋ የነበረው ህዝብ ወደዚሀ የተገለበጠ ነው የሚመስለው፡፡ ሰዉ ተኮልኩሏል፤ ቤቷ ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሏል፡፡ “እዚህ ሁለት በየአይነቱ አምጪልን…”
ምግቡ ሲመጣ ወጣወጡ፣ ጎመና ጎመኑ፣ ቅጠላ ቅጠሉ በጣባ፣ በጣባ ተደርድሮ ይመጣል… ወደ አስራ አምስትና አስራ ስምንት አይነት ምግብ!
እንዴ ቆይማ… ጾም አይደለም እንዴ! ጾም ማለት አካልን ትንሽ እየጎዱ ፈጣሪን ማሰብ አይደለም እንዴ! ታዲይ የሀብታም ሰርግ ይመስል ይሄ ሁሉ ‘የምግብ ኤግዚቢሽን’ የሚመስል ነገር ምንድነው! የምር ግን…ብዙ ሰው እኮ እነዚህ አስራ ምናምን አይነት  ምግቦች እንኳ በአንድ ምሳ ላይ ሊመገብ ቀርቶ አጠገብ፣ ለአጠገብ ተደርድረው አይቷቸው አያውቅም!
“ስማኝ ያቺ በቢጫ ሳህን ያለውን ምግብ የበላሁት ትዝ ይለኛል፤ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ የዘመድ ግብዣ ሄጄ…”
“እኔ ደግሞ ያቺኛዋን በሰማያዊ ሳህን ያለውን ምግብ  ያ ማነው…ኢንጂነር የሚሉት ጎረቤታችን ያገባ ጊዜ…”
“እሱ እኮ ወደ ሰባት ዓመት ገደማ ሆኖት የለም እንዴ!”
“እሱን አይደል የምልህ! የዛሬ ሰባት ዓመት ነው የበላሁት፡፡”
“ለነገሩ ቅርብ ጊዜ ነው፣ እድሜ ልክህን እንኳን ልትቀምሰው ሸቶህ እንኳን የማያውቅ መአት የአገር ውስጥ ምግብ አለ አይደል እንዴ!”
እናማ…አንዳንዶቻችን የጾማችን ነገር እንዲህ ያደርገናል…እንኳን ቀምስን ልናጣጥመው እድሜ ልካችንን ሸቶን የማያውቅ ምግብ በመጾሚያችን ጊዜ ይደረድርልናል፡፡ እንደ እውነቱ የተመጣጠነ ምግብ ለሚባለው የቀረበ አመጋገብ የምንመገበው በጾም ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፡፡”
እና ጾም ሊገባ ነው ብለን በየሉካንዳው በራፍ እየተጋፋን ከገባን በኋላ የጾም ምግብ በሰልፍ የሚደረደርበት ምግብ ቤት እንኮለኮላለን፡፡ አስራ ምናምን ጣባ የተደረደረበት ትሪ ፍለጋ ወንበር እስኪለቀቅ ተራ እንጠብቃለን፡፡ ጧት ላይ ግን “እስከ ስድስት ሰዓት እጾማለሁ” ብለን ዳቦ በሻይን “ልክሽን እወቂ!” በሚል የክፉ ቀን ባለውለታነቷ ላይ ውሀ እንቸልስበታለን፡፡
የምር ግን የሆነ የተሳሳተ፣ ወይም ‘አሜንድመንት’ ምናምን ተደርጎበት እኛ ገና ያልገባን ነገር መኖር አለበት…ይበልጥ የተመጣጠነ ምግብ የምናገኝበት ወቅት በፍስኩ ጊዜ ሳይሆን ‘ለነፍሳችን በምናድርበት’ የጾም ጊዜ ሲሆን ምናልባት ‘ከዘመን ወደ ኋላ ቀርተን’ ይሆን ይሆናል፡፡ ወይንም እየተዋወቅን ድራማው ላይ ተሳታፊዎች ነን፡፡
ሁሉ ነገር ‘ሪያሊቲ ሾው’ ምናምን አይነት ሲመስል ብዙም አያስኬድም፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ የጾም ነገር ከተነሳ እያጋፉ ሰው ዓይን የማይከቱ፣ ወንበር እስኪለቀቅ የማያስገትሩ፣  “እስከ ስድስት ሰዓት፣ እስከ ምናምን ሰዓት እጾማለሁ፣” የማያስብሉ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጥቂት ሳምንታት እንኳን እኛም፣ አሳዳሪዎቻችንም ከ‘ነገር’ ብንጾም አሪፍ ይሆን ነበር፡፡ ዘንድሮ አገር እያመሰ ያለው መልኩን እየለዋወጠ የሚመጣ ‘ነገር ነው፡፡ በተለይ ዘንድሮ ብዙው  ጉዳይ ‘ነገር!  ነገር!  ነገር!’ ሆኖ፣ ያለንበትንም፣ የምንሄድበትንም እያጠፋብን ነው፡፡
‘ነገር’ በአለቆች ፉከራ መልክ ይመጣል፡፡ ስንት ወር ሙሉ በራሱ ድክመት ያልሰበሰበውን ሂሳብ “በሁለት ቀን ውስጥ ባትከፍሉ እናንተን አያድርገኝ!” አይነት ቃና ያለው ፉከራ፡፡ ‘ነገር’ ሆነ ተብሎ የተሳሳተ መረጃ በማስተላለፍ መልክ ይመጣል፡፡
“የአካባቢው ሰዎች በአገልግሎት አሰጣጡ መደሰታቸውን ለሪፖርተራችን ገለጸውለታል” አይነት ነገር፡፡  የአካባቢው ሰዎች እኮ “ሰልፍ እንውጣ ብንል ጥርስ ይነከስብናል ብለው በሆዳቸው እየተብከነከኑ ነው፡፡ ‘ነገር’… “እባክህ እሱ ይሄን ሁሉ ገንዘብ ያገኘው ተንኮል ቢኖረው ነው በሚል ‘የምቁነት ነፋስ ነካ ባደረገው’ ወዳጅ መልክ ይመጣል፣ ሰውየው እኮ ገንዘቡን ያገኘው ለሰዉ በግልጽ የሚታይ ሥራ እየሠራ ነው! ‘ነገር’ በፊት ለፊት እያቀፈና እየሳመ፣ ከጀርባ ጉድጓድ በሚቆፍር ሰው መልክ ይመጣል፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ጀርባ ደግሞ ያለው የተለየ፣ ከሌላ ዓለም የመጣ ፍጡር ሳይሆን እኛው “ጾም ሊገባ ነው” ብለን ሉካንዳ ደጃፍ የምንጋፋ፣ “ጾም ገባ” ብለን አሥራ ምናምን አይነት ለመመገብ የምግብ ቤት አድራሻ እየጠየቅን፣ ከከተማ ጫፍ ከተማ ጫፍ የምንጓዘው ነን፡፡
ለምንጾመው፣ ጾሙን የአንደበትና የ‘ሪያሊቲ ሾው’ ነገር ሳይሆን ከልብ የሆነ፣ ደግ የምናስብበትና ደግ የምንሠራበት ያድርግልን፡፡
ጾም ለማይመለከተን ጊዜውን ጉድጓዱ ስር ያለውን ጨለማ ሳይሆን፣ ዋሻው ጫፍ ያለውን ብርሀን የምናይበትና ብርሀኑም ለሁሉም እንዲዳረስ የምንመኝበት ያድርግልን፡፡  (ደግሞ ሌላ ‘የስብከት’ ቻነል ለመክፈት ዝግጅት ላይ ያለሁ አስመሰለብኝ እንዴ!”)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3289 times