Sunday, 03 December 2017 00:00

“ማንን ላግባ?”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

 የመነፅሩ - ብርጭቆ ውፍረትና ጥልቅ አተያዩ፤ ተመራማሪ ምሁር እንጂ የኔን ቀላል ጉዳይ የሚያደምጥ ሰው አልመሥል አለኝ፡፡ በዚያ ላይ ቅላቱና እጆቹ ላይ በተለይ ከክንዱ ወደ ክንዱ ሳየው ፀጉሩ ጥቅጥቅ ያለ ደን መሥሏል፡፡ ክልስ ነገር ይመሥላል፡፡ ያው ጣሊያን፤ አርመን ነገር!
“ዋናው ምክንያትህ ምንድን ነው?” አለኝ፡፡
“ሚስት ማግባት ነዋ?!” አልኩት እንደ መናደድ እየቃጣኝ፡፡
ባይሆን ኖሮ እርሱ ቢሮ ምን ወሰደኝ…? ሌሊት ከቤት ወጥቼ፤ ከአየር ጤና ጉርድ ሾላ፣ ይህን ሁሉ ሀገር አቋርጬ የመጣሁት ላጤነት መሮኝ መሆኑን እንዴት አድርጌ ላሥረዳው!
“ማለቴ ያነሣሣህ ምንድን ነው?”
“ሽንኩርት በከተፍኩ ቁጥር መቃጠል፣ ንፍጥ ማዝረክረክ፣ እንባ ማፍሰስ!... ካልሲ በየሥርቻው እየጣሉ፣ ጡብ መሥራት!”
“አትቀልድ! ቁም ነገር መሠለኝ የያዝነው፡፡… ለምጠይቅህ ጥያቄ በወጉ መልስ ስጠኝ፡፡ እኛ ቢሮ ከፍተን ላይና ታች የምንለው፣ የሀገራችን ማህበራዊ ግንኙነት የተሻለ እንዲሆንና የተሻለ ዜጋ መፍጠር እንዲቻል እንጂ…” ሳይጨርስ አቋረጠ፡፡
ሰውየው ፖሊስ ይሁን-የጋብቻ አገናኝ ደላላ መለየት አቃተኝ፡፡
“ስማ በዚህ በሰለጠነ ዘመን፣ ሚስትህ ካልሲህን እንድታጥብልህ-መጠበቅ የለብህም” ብሎ ገሰፀኝ፡፡
ሳቄ መጣ፡፡ በገዛ እጄ በራሴ ላይ አለቃ ሾሜ… ብዬ በልቤ ፈገግ አልኩ፡፡
“ትምህርት ለዚህ ካልጠቀመ…” አለና ብዕሩን ወረቀት ላይ ሰካው፡፡ “መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ ስጠኝና ፋይሎች ፈትሼ፣ ላንተ ተስማሚ የሆነችውን እመቤት ላገናኝህ” አለና ፊቱ ቦግ አለ፡፡
“መቸም ከዚህ በፊት እንደኛ አይነት ድርጅቶች ጋ አልሄድክም?”
አንገቴን ነቀነቅሁለት፡፡ ዋሽቻለሁ፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ፣ ሠፈሬ-ብቻዬን መውጣት መግባቱ ሲያስጠላኝ በሬድዮ ማስታወቂያ ሰምቼ ሄጄ ነበር፡፡ ግን አልተሣካልኝም፡፡ አቻዬን ያሏትን አገናኝተውኝ እንድነጋገር አንድ ክፍል ሲያሥቀምጡኝ፣ የጠበቅሁት ነገር ሳይሆን ያልጠበቅሁት ሆነ፡፡
“ሥራህ ምንድን ነው?” አለችኝ፡፡
“የኢኮኖሚክስ ባለሞያ ነኝ” አልኳት ኮራ ብዬ፡፡
“በቢሮ ሃላፊነት ማለት ነው?” ብዙም ቁብ አልሰጣት፡፡
“ኤክስፐርት ነኝ!... ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ተመርቄያለሁ፡፡”
“በመጀመሪያ ዲግሪ?”
“አዎ!”
ቅር አላት፡፡
“አሁን የዲግሪ ነገር ብዙም-ብርቅ አይደለም። በፊት ነበር፤ አሁን ሀገሩ ሁሉ ባለ ዲግሪ ነው፡፡… ይልቅ ዋናው ነገር መኖሪያ ቤት አለህ?”
ደነገጥኩ፡፡
“…ኦኦኦ…”
ብድግ አለች፡፡
“ይቅርታ!”… ቤት ሳትሰራ- ሚስት ፍለጋ አትውጣ!... በየኪራይ ቤቱ ልታንከራትተኝ!”
እየሣቀችብኝ - ሄደች፡፡ የዚያን ቀን የተሰማኝን የልብ ሥብራት መቼም አልረሳው፤ እንጀራ ብቻ ሣይሆን - የምጠጣው ለስላሳም አነቀኝ፡፡ ቤቴ ሄጄ እንደ በሽተኛ አልጋ ላይ ዋልኩ፡፡
“ምን እያሰብክ ነው፤ ቶሎ-ቶሎ መረጃ ስጠኝ”
“እሺ” አልኩት፤ የመነፅሩ ነገር አሁንም እየገረመኝ ነበር፡፡… ዓይኖቹ በምርምር ስራ የደከሙ ምሁር ይመስላል፡፡
“መኖሪያ ቤት አለህ?”
ውሃ ሆንኩ፤ ያቺ ፈልፈላ ሴት ትሆን የላከችብኝ..መቸም እስካሁን ታገባለች፡፡ ቤት ያለው ሞልቷል!
እኔ-ሠፈር ያሉ ሴቶች፤ በየኮንደሚኒየሙ በኪራይ አይደል የሚኖሩት፡፡ አንዷ ብቻ ናት ባልዋ ውጭ ያለው፡፡ የራሷ ቤት ይኑራት አይኑራት እንጃ! ታገሠች ነበር ስሟ መሠለኝ፡፡ ጠይም፤ ረዘም ያለች። ታዲያ- ባልዋ አሜሪካ ነው እያሉ እንደ ብርቅ ያንሾካሹካሉ፡፡ እኔ እንደሁ ለዚህ አይነት ነገር ብዙም አልደነቅ! የኔ ታላቅ ወንድም አሜሪካ ከሄደ ስንት ዓመቱ… ግን ሁሌ በስልክ ችግር እንዳወራ ነው፡፡
ይህቺ ጎረቤቴ ግን-እንዳማረባት ነው፡፡ ከጎንና ጎንዋ ያሉት ጧት ወጥተው ማታ ሲገቡ፤ እሷ ተንቀባርራ ትኖራለች-ይላሉ፡፡ የባልዋ አብሯት ያለመኖር ደግሞ ፀባይዋን ያበላሸው ይመሥለኛል። አንዳንዴ እቤት ሥውል ጎሬቤቷ ካለችው ልጅ እግር ሠራተኛ ጋር ሆና የምታወራው ወሬ ለጆሮ ይቀፋል።
ጠዋት-ሱፌን ቂቅ አድርጌ ስወጣ ካዩኝ፣ በኋላ አቃቂር እያወጡ ጥሬ ስጋዬን መብላታቸው አይቀርም፡፡ ያሽሟጥጡብኛል፡፡ ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ ግን ማግባት አለብኝ፡፡
“የመጀመሪያ ዲግሪ ነው ያለህ?” አለኝ፡፡
“አዎ!”
“አይይ…ስንት ዓመት የሥራ ልምድ አለህ?”
“ከ10 ዓመት በላይ!”
“ጥሩ ነው፡፡ ይኸው እኔም የመጀመሪያ ዲግሪ ይዤ ሥራ- ሳጣ፤ ቀበሌ ባመቻቸልኝ-ዕድል ይህንን ሥራ ጀምሬያለሁ፡፡ ካፒታሌም በያመቱ…” አለና፣ ቀልዱንና ቁም ነገሩን ቀላቀለው፡፡
“ግን-በኢኮኖሚክስ ተመርቄያለሁ” ሲል አከለበት፡፡
ትንሽ-ቅር አለኝ፡፡
“ደሞዝህ ምን ያህል ነው?”
“ደሞዜን ባትጠይቀኝ ደስ ይለኛል!”
“የወንድ ደሞዝና-የሴት ልጅ ዕድሜ” በሚለው አባባል ነው፡፡
“ማለቴ - ለርሷ ደሞዜን - የምነግራት፤ አካውንታንት አይደለች!”
“አትቀልድ!... አካውንታንት ብቻ አይደለችም፤ ማኔጀርህም ናት፡፡ ዓለምን ማን እንደሚገዛት አታውቅም እንዴ… ወይስ የግሪኩ ንጉሥ ያለውን ላሥታውሥህ”
“አውቀዋለሁ!”
“ካወቅህ ንገረኝ!”
ላቤ-ፊቴን አጠበው፡፡ ፈራሁ፡፡ አቴንኝ  ዓለምን ትገዛለች፤ እኔ አቴናን እገዛለሁ፤ ሚስቴ እኔን ተገዛለች፡፡ ነበር ያለው፡፡ ያው የዓለም ገዢዎች ሴቶች ናቸው ለማለት ነው፡፡
“በል ፈጠን በል!”
“ስድስት ሺህ ብር!”
“ው-ኡ!” ከንፈሩን ወደታች ጣለው፡፡
“በዚህ ደሞዝ ልታገኝ የምትችለው፤ ሥራ የሌላትን ሴት-ብቻ ነው፡፡ ምናልባት ካፌ ውስጥ አስተናጋጅ ሆና፤ የትዳር ዘመንዋ ያመለጣት!”
ዝግንን አለኝ፡፡
ፈገግ-አለ፡፡
“ወይ ...ትንሽ ሠራራና! ተመልሰህ…”
አይኖቼ እንባ ያቀረሩ-መሠለኝ፡፡
ባንክ ቤት-ትንሽ ገንዘብ ቢጤ አለችኝ፡፡ አንዳንድ ትርፍ ሥራዎች ሠርቼ ያጠራቀምኳትና ታላቅ ወንድሜ ካሜሪካ ሲልክልኝ አንጀቴን አሥሬ ለክፉ ቀን የቋጠርኳት፡፡
“ምን ወሠንክ?” አለኝ በጥድፊያ፤ “ተረኛ ሰው አለ፤ አሁን ሰው ሁሉ ወደ ትዳር ነው፡፡ እንደ ቀድሞው እንዳይመሥልህ፤ ወጣቱ ነቅቷል፡፡ ዘሩን ሣይተካ ማለፍ አይፈልግም፡፡ ሀገርና ትውልድ አንተ ስትኖር ነው?..
ሳላስበው ከአፌ አመለጠኝ፤ ስለ ባንኩ ብር ነገርኩት፡፡ ምን እንደሚጠቅመው ባለውቅም ፊቱ ፈካ፡፡
“በል ጠብቀኝ” አለና-ስልክ ደወለ፡፡ ከዚያ ብዙም አልቆየ፡፡ ወደ ውጭ ወጣ ብሎ፤ “ተነጋገሩ” ሲል - አንዲት ሴት ገባች፡፡
“በቃ ለኔ የነገርከኝን ሁሉ ለእርሷ ንገራት፡፡ ችግር የለም፡፡ ለትዳር የምትሆን ጨዋ ሴት ናት። እርግጠኛ ነኝ ትወዳታለህ፡፡ ስለ ውበቷ መቸም አልነግርህም”
በሩን በላያችን ላይ ዘግቶ ሄደ፡፡ ይሄ ደግሞ የባሰበት ነው፡፡
የኔም የርሷም አንደበት ተያያዘ፡፡
“ይቅርታ” አልኳት፤ የጎረቤት ሴት ናት፡፡ “ባለቤትዋ አሜሪካ-ይኖራል፤ ተብሎ ተነግሮኝ ነበር።” ያ ሁሉ ጉራ፣ ያ ሁሉ ዲስኩር ገደል ገባ ማለት ነው?... ከንፈሬ ደረቀብኝ፡፡
“ታገሠች ነሽ አይደል?”
“አዎ”
“ባለቤት አለሽ አይደል?!”
“ተወኝ ባክህ ልቦለድ ነው፡፡ የሀበሻ ወንድ፤ ‘ባል አላት፣ ፍቅረኛ አላት’ ሲባል ይንገበገባል ብዬ ነው ያሥወራሁት፡፡”
የሚያስደነግጥ ነገር ነው፡፡ እዚህ ሀገር ሀኪም ያልሆነው ሀኪም፣ መሀንዲስ ያልሆነው መሀንዲስ እያለ… ደሞ አሜሪካ መሄድ ያቃታት፣.. ባሌ አሜሪካ ነው ትል ጀመር!
ልቤ- ኩምሽሽ አለብኝ፡፡ በውሸት ላይ የተመሠረተ ህይወት ምንድን ነው?
“አንተ እንኳ ብቸኛ እንደሆንክ አውቃለሁ፤…ግን”
“ግን ምን?...
“መኖሪያ ቤት የሌለው ሰው ማግባት ትንሽ ይቸግረኛል፡፡…”
የእኔን ምላሽ አልጠበቀችም - ሹልክ ብላ ወጣች፡፡
“እሺ ማንን ላግባ?...” ብዬ እንዳጎነበስኩ፤ ሌላ ሴት ገባች፡፡
ዓይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ በህልሜ ይሁን በእውኔ ግር አለኝ፡፡ ታናሽ እህቴ - ባልዋን መፍታቷን አላውቅም ነበር፡፡
ኡኡ… ኡ-ብላ ጮኸች፡፡ ተቃቅፈን መላቀስ ያዝን፡፡

Read 3951 times