Sunday, 03 December 2017 00:00

“የተገፋ እውነት እና ሌሎች ታሪኮች” ለገበያ ቀረበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 በደራሲ ብዙነህ ወልደዮሐንስ የተደረሱ አጫጭር ልብወለዶችን የያዘው “የተገፋ እውነት እና ሌሎች ታሪኮች” መፅሐፍ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቧል፡፡
በአጫጭር ልብወለዶቹ መጨረሻ ላይ “ማመልከቻ፤ እንደ መውጫ” በሚል ርዕስ አሰፋ መኮንን ባሰፈሩት አስተያየት፤ “ታሪኮቹ እንደ ጥቅምት እሸት የማይጠገቡ፣ ትኩስነት ባላቸውና የምዕራባዊያን ባህላዊ ዘይቤ ባልተጫነው የቋንቋ ለዛ የበለፀጉ ናቸው ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ለዚህ ትዝብቴም “ሜይሩ” እና “ብርቱካን” ቀዳሚ ዋቢዎቼ ናቸው” ብለዋል፡፡
በ203 ገፆች የተመጠነው መድበሉ፤ ስምንት አጫጭር ልቦለድ ታሪኮችን የያዘ ሲሆን ለአገር ውስጥ በ65 ብር፣ ለውጭ አገራት በ12 ዶላር ለገበያ እንደቀረበ ታውቋል፡፡
“ግድግዳውን አይተኸዋል?”
የዘመመ፣ ምናልባትም በቅርብ ጊዜ ውስጥ መውደቁ የማይቀር የቤት ግድግዳ እየቀባ ሳየው፤ “እና እኔ ምን አገባኝ” አለኝ፡፡ እኔን ሳይሆን ጥያቄዬን ንቋት። ያቆመ ሥራውን ቀጠለ፡፡ አሁን በግማሽ ልቡ ነው እሚያዋራኝ፡፡
“እንደሚፈርስ እያወክ?”
“የኔ ጉዳይ አይደለም፡፡ እኔ ቀባ ስባል መቀባት ብቻ ነው”
“ለምን አትነግራቸውም?”
“ምኑን?” አለኝ፤ እያወቀው፡፡ ለጥያቄዬ መልስ ሳይጠብቅ… “መጣመሙን?”
“እህሳ”
“መች አጡት”
“ስህተቱን አርሞ በትክክል ማቆሙ አይቀድምም?”
“ግድ ስለማይሰጣቸው ነዋ!”
“ሲወድቅስ?”
የሱ አባባል እንዳልሆነ በሚነግር አሽዋፊ ዜማ፤ “ጠላቶች ጣሉት እንላለና” አለኝ፡፡
….እያለ ይቀጥላል… “የተገፋ እውነት” የሚለው አጭር ተረክ (ከገፅ 128-129)፡፡

Read 2518 times