Saturday, 02 December 2017 08:44

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(6 votes)

 Preeclampsia:- ማለት  በእርግዝና ጊዜ በሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በሰውነት ውስጥ የውሀ መጠራቀም እና በሽንት ውስጥ ፕሮቲን ሲኖር ሕመሙ የሚገለጽበት ስያሜ ነው፡፡
Eclampsia፡- ማለት እርጉዝ የሆነችው ሴት በሰውነትዋ ውስጥ Preeclampsia ከተከሰተ በሁዋላ ወደከፋ ደረጃ ሲደርስ በአእምሮዋ ውስጥ በሚፈጠር መዛባት የተነሳ ሰውነትዋ መንቀጥቀጥና የጡንቻዎች መኮማተር ወይንም ጤናዋ የተረበሸ ሲሆን እንዲሁም እራስን መሳትና መውደቅ የሚያደርስ በከፍተኛ የደም ግፊት ምክንያት የሚከሰት ሕመም ነው፡፡        
Preeclampsia Eclampsia (ፕሪክላምፕስያ እና ኢክላምፕስያ) የተባለው የጤና ጉድለት የሚከሰተው በእርግዝና ጊዜ ያውም ወደ 20ኛው ሳምንት ገደማ ነው፡፡ አንዲት እርጉዝ ሴት ፕሪክላምፕስያ በተባለው የጤና ጉድለት ተገኘች ማለት ከፍተኛ የደም ግፊት እና በሽንትዋም ውስጥ ፕሮቲን ሲገኝ እና በእግር ወይንም በእጅ ወይንም በፊት በመሳሰሉት ላይ የእብጠት ምልክት ሲታይ ነው፡፡ ይህ ሕመም ወደከፍተኛ ደረጃ ሲሸጋገር የከፋ ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህም ማለት በተረገዘው ጽንስም ይሁን በእናትየው ላይ የህይወት መጥፋት አደጋን ሊያስከትል ይችላል፡፡  
አንዲት ሴት በምታረግዝበት ወቅት ለሚከሰተው ፕሪክላምስያ እና ኢክላምፕስያ በትክክል ምክንያቱ ይህ ነው ለማለት ባይቻልም በቅርቡ ግን አንዳንድ ጥናቶች የጠቆሙት ነገር አለ፡፡ ይኼውም በእርግዝና የመጀመሪያው ተርም ማለትም እስከሶስት ወር ድረስ ባለው ወቅት የእንግዴ ልጅ እራሱን በሚጠበቀው ደረጃ ከማህጸን ግድግዳ ጋር እንዲተዋወቅ አለማድረጉ ይሆናል የሚል ነው፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የተቀመጠ ግልጽ የሆነ ነገር ባይኖርም ምናልባት በሴትየዋ ወይንም በባልየው ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ወይንም በሌላ ሕመም ምክንያት ማለትም በስኩዋር ወይንም በደም ግፊት ምክንያት በሚወሰዱ መድሀኒቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ በግልጽ ከሚገመተው ምክንያት ውጭ ከመጀመሪያውኑ የፕላዜንታ በትክክለኛው መንገድ አለመፈጠር ወደፊት የደም ግፊት እንዲመጣ ወይንም የደም ስሮች ወይንም ሌላ የውስጥ አከላት አንዲጎዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አርተሪ የተባለው ደምን ከልብ ወደሌላው የሰውነት ክፍል የሚያደርሰው የደም ስር ከመጠን በላይ በሚሆነው የደም ግፊት የመጨናነቅ ወይንም የመጣበብ ችግር ሊደርስበት ይችላል፡፡ በዚህም ሳቢያ ደም ወደማህጸን እና ፕላዜንታ እንዲሁም ለሴትየዋ ኩላሊቶች ፣ጉበት ፣አይንና አእምሮ እንዲሁም ወደቀሩት የሰውነት ክፍ ሎች በተገቢው ሁኔታ ላይሰራጭ ይችላል።
በአለማችን በተለይም ሕክምናው ውስን የሆነ አቅም ባለባቸው አገራት ሴቶች በእርግዝና ወቅት በሚገጥማቸው Preeclampsia Eclampsia (ፕሪክላምፕሲያና ኢክላምፕሲያ) ለሞት የሚዳረጉ ሲሆን በኢትዮጵያም በእናቶች ሞት ምክንያትነት በሁለተኛ ደረጃ የተመዘገበ አስከፊ ሕመም ነው፡፡ በእርግጥ ሕክምናውን  በጊዜው እና በተገቢው የሚያገኙ እናቶች እንደሚፈወሱም የተረጋገጠ ነው፡፡
በእርግዝና ጊዜ ለሚከሰተው ፕሪክላምፕሲያ ሊያጋልጡ ወይንም አጋጣሚውን ሊፈጥሩ ይችላሉ ከተባሉት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት፣
ከፍተኛ ውፍረት፣
የስኩዋር ሕመም፣
የኩላሊት ሕመም፣
ቀደም ባለ እርግዝና ጊዜ ከባድ ፕሪክላምፕሲያ ተከስቶ ከነበረ፣
መንትያ ወይንም ከዚያ በላይ እርግዝና (ከአንድ በላይ ፕላዜንታ ስለሚኖር ምናልባት አጋጣሚው እንዲሰፋ ሊያደርግ ይችላል ከሚል ግምት ነው።)
በቅርብ ቤተሰብ …ማለትም በእናት፣ በእህት በመሳሰሉት የቅርብ ዘመዶች ላይ የሚከሰት ከሆነ…ወዘተ
ለሕመሙ መከሰት ምልክቶች፡-
አንዲት እርጉዝ ሴት መጠነኛ የሆነ ፕሪክላምፕሲያ ቢኖራት ምናልባትም በእግርዝናው ወቅት እጅ ላይ እብጠት ወይንም የሰውነት መጠን መተለቅ ከማጋጠሙ በስተቀር ሌላ የጤና መጉዋ ደል ስሜት ላይሰማት ይችላል፡፡ በእርግጥ አብዛኛዎች እርጉዝ ሴቶች በፕሪክላምፕሲያ ምክን ያት ሳይሆን ዝም ብሎ ሰውነታቸው ሊያብጥ ይችላል፡፡ ስለዚህም እብጠት ተከሰተ ማለት ፕሪክላምፕሲያ ተከሰተ ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
የእራስ ምታት ሕመም፣
የእይታ መለወጥ፣
ማቅለሽለሽ ፣የሆድ ሕመም የመሳሰሉት ስሜቶች፣
የአተነፋፈስ ችግር ሕመሙ ለመከሰቱ እንደ ጠቋሚ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላል፡፡
ፕሪክላምፕሲያ በሚከሰትበት ጊዜ የሰውነት በተለይም የእጅና እግር መንቀጥቀጥ፣ መጣል፣ እራስን መሳት የመሳሰሉት ክስተቶች ይታያሉ፡፡
ፕሪክላምፕሲያ አንዳንድ ጊዜ በተለይም የደም ግፊቱ መለስተኛ ከሆነ ስሜቱ ላይታወቅ ስለሚችል እርጉዝ ሴቶች በትክክለኛው መንገድ ወደ ሕክምና በመሄድ ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ከተደረገ ሕመሙ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት መፍትሔ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህ ሕመም አስቸጋሪ የሚሆነው በተለይም ሴቶች ከእርግዝና በፊት ከፍተኛ የደም ግፊት ታማሚ ከሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የደም ግፊት ከነበረባቸው አራት ሴቶች አንድዋ ፕሪክላምፕሲያ ወደተባለው የከፋ ሕመም ልትገባ ትችላች፡፡ በተለይም እንደዚህ ያለ የጤና ችግር ያለባቸው ሴቶች በእርግዝና ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የከፋ የጤና ችግር አስቀድመው በመገመት የደም ግፊት ሁኔታን ለማስተካከልና በሽንት ውስጥ የሚኖረውን ፕሮቲን ለማስተካከል የህክምና የቅርብ ክትትል እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡
ፕሪክላምፕሲያ አስከፊ የማይሆንበት፡-
የእርጉዝ ሴት የደም ግፊቱ 140/90 ወይንም ከፍ ሲል፣
የእርጉዝ ሴት እጅ፣ እግር ወይንም ፊት ላይ እብጠት ሲታይ፣ በሽንት ውስጥ ፕሮቲን ሲታይ፣
ከላይ የተዘረዘሩት የህክምና ውጤቶች በከፍተኛ ሁኔታ እስካልተመዘገቡ ድረስ መጠነኛ በሚል ክፍል የሚመደቡ ስለሆነ እርጉዝ ሴቶችም የህመም ስሜት ላይሰማቸው ይችላል፡፡
ፕሪክላምፕሲያ አስከፊ የሚሆንበት፡-
የእርጉዝ ሴት የደም ግፊት 160/110 ወይንም ከዚያ በላይ በመሆን ለ6/ ሰአታት ከቆየ፣
የእርጉዝ ሴት ለ24/ሰአት በመሽናት የተጠራቀመው ሽንት ከ5/ግራም በላይ ፕሮቲን ካለው፣
የከፋ እራስ ምታት፣ የማየት ችግር፣ ሽንት መሽናት ሲቀንስ፣ የሆድ ሕመም፣ በሳንባ ውስጥ ፈሳሽ መኖር ወይንም የጀርባ ሕመም መሰማት፣
በሳንባ፣ በደም ውስጥ ያሉ እንዲሁም ደም እንዲረጋ የሚያስችሉ ሴሎች መጎዳት፡- (ይህ በ10/በመቶ ታማሚዎች ላይ ይከሰታል)
የመሳሰሉት ሕመሞች ሲያጋጥሙ አስቸኳይ መፍትሔ ይሻሉ፡፡
ፕሪክላምፕሲያ ወደከፋ ደረጃ ሲደርስ ሕመሙ ያጋጠማቸው ሴቶች የሰውነት መንቀጥቀጥ የመሳሰሉት ሕመሞች መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ በእርግጥ ኢክላምፕሲያ በእርግዝና ወቅት ብቻ ሳይሆን ሴቶች እንደወለዱ ሊከሰትም ይችላል፡፡ ኢክላምፕሲያ ከያዛቸው ከ30-50/በመቶ የሚሆኑ ሕመምተኞች በሳንባ ፣በደም ውስጥ ያሉ እንዲሁም ደም እንዲረጋ የሚያስችሉ ሴሎች መጎዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡
ሴቶች ፕሪክላምፕሲያ አጋጥሞአቸው የሚያውቅ ከሆነ በቀጣዩ የህይወት ዘመናቸው ለከፍተኛ የደም ግፊትና ለልብ ሕመም ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ምክንያት ብቻም ሳይሆን በሌላም ምክንያት ለሕክምና በሚቀርቡበት ጊዜ ታሪካቸውን ለሕክምና ባለሙያ መናገር ይጠበቅባቸዋል። ምንም እንኩዋን ከእርግዝና ወይንም ከወሊድ በሁዋላ የተለዩና የሚሰጡ የህክምና ክትትሎች ባይኖሩም ሴቶቹ በወደፊት ሕይወታቸው ግን ችግር እንዳይገ ጥማቸው ሲባል የሚመከሩ ነገሮች አሉ፡፡
ጤናማ የሆነ የሰውነት ክብደት እንዲኖራቸው፣
የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በዘወትር ኑሮአቸው ማካተት፣
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣
ሲጋራ አለማጤስ፣
አልኮሆልን በመጠኑ መጠቀም፣
ይህ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት Preeclampsia Eclampsia በተለይም በኢትዮጵያ በገዳይነቱ በ2/ኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን የህክምና አተገባበሩ ምን ይመስላል?
ምንጭ ፡- Drugs.com -  ይቀጥላል፡-

Read 15917 times