Saturday, 02 December 2017 08:40

በድንገተኛ ህልፈቱ በእጅጉ አዝነናል!!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ዮናስ ነ.ማርያም የአዲስ አድማስ ፅሁፍ አቅራቢ ነው (Contributor) የአዲስ አድማስ ቤተሰብ የሚለው የበለጠ ይገልፀዋል፡፡ አዲስ አድማስን እንደ ራሱ ጋዜጣ ነው የሚያየው- ለሱ ተብሎ ብቻ እንደሚታተምለት የግል ጋዜጣው። በጣም ይሳሳላታል፡፡ ከልቡ ነው የሚወዳት! ላለፉት በርካታ ዓመታት፣ በርካታ ምርጥ አጫጭር ልብወለዶቹን ለአድማስ አንባቢያን አስነብቧል። ተወዳጅም ነበሩ- ሥራዎቹ! ከድንገተኛ ህልፈቱ አንድ ቀን በፊትም “ሸረሪቷ” የተሰኘ ትርጉም አጭር ልብ ወለድ ቢሮ ድረስ መጥቶ ለፀሃፊዎች ሰጥቶ ነበር የሄደው- እንደተለመደው
በእውነቱ ህልፈቱ ድንገተኛ፣ አሰቃቂና አሳዛኝ ነው፡፡ ሐሙስ ዕለት ጠዋት ፍልውሃ ወድቆ መገኘቱን ከፖሊስ በስልክ ሰማን። ዘውዲቱ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር፡፡ ግን ህይወቱ አልተረፈም፡፡ በእጅጉ ያሳዝናል!! ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያኑረው!
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልና ማኔጅመንት፤ በዮናስ ነ.ማርያም ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ፤ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹና ለሥራ ባልደረጎቹ ሁሉ መፅናናትን ይመኛል!
የዮናስ ነ.ማርያም የድሮ ተማሪዎች በፌስ ቡክ
የኔ መምህሬ ነበር፤ አስተማሪዬ ሆኖ የልቡን ይነግረኝ ነበር፡፡ የኳስና የቡና ፍቅር ነበረው። ለምንም የማይደንቀው ነበር፡፡ አዝኛለሁ። አንድ ነገር ላሥቸግርህ ፎቶውን ላክልኝ፡፡ ቢያንስ በሱ ልፅናና፡፡
ናርሲሲ እና ጎልድመንድ
ዮናስ 10ኛ ክፍል ሆኜ አማርኛ አሥተምሮኛል፤ የክፍል ሃላፊዬ ሆኖ መካሪዬ ነበር፡፡ አሁን ዳኛ ነኝ፡፡ አንድ ቀን ከሩቅ ጠርቶ መንገድ ላይ የመከረኝን አልረሳውም፡፡  እዚህ ለመድረሴ የእነሱ እጁ አለበት፡፡ ሁሌ ባገኘው እመኝ ነበር። ጌታ ያለው ሆነ፡፡ በጣምምምም ያሣዝናል።
ሮዝ የሉላ
ዮኒ መምህሬ ነበር፡፡ ጓደኛዬም ነው፡፡ ኳስ አብረን እንጫወት ነበር፡፡ መንፈሳዊ-ማንነቴንም ቀርፆታል፡፡ ባገኘሁ እያልኩ ሁሉ እጓጓ ነበር። የክፍላችን ተማሪዎች በቁጥር ሃምሳ ነበርን፡፡ ሃምሳችንም እንወደው ነበር ብልህ ታምናለህ!!
በሚያስተምርበት ክፍለ ጊዜ-ሃያ ደቂቃ ያህል ቀድሞ የሚገኝበት ጊዜ ነበር፡፡ በጣም ብዙ ነገር ያሣውቅሃል፡፡ ብዙ ነገር ትማራለህ፡፡ ስለ ዮኒ ምን ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ በቃ…በቃ
ዘላለም ከሚዛን ተፈሪ (በስልክ)
ከልቅሶ ጋር፡-
ጥበብ እና አዲስ አድማስ አንድ ውድ ልጅ አጡ!
በተስፋዬ አለነ
ዜና እረፍቱን ያነበብኩት ከደረጀ በላይነህ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ነበር። ዓይኖቼን ማመን አልቻልኩም፡፡
ቸው ወዳለኝ አንዳንድ ጋዜጠኞች ዘንድ ደዋወልኩ፡፡ ገሚሶቹ መርዶ አርጂ ሆንኩባቸው። ከዚያ ወደ አዲስ አድማሷ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ እና አንተነህ ይግዛው ዘንድ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ሰደድኩ፡፡ናፍቆት ፈጥና መልስ ሰጠችኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡  ‹‹ውይ! ግን እውነት ባልሆነ›› አልኳት፡፡
የመረጃ ምንጬ ደራሲና ጋዜጠኛ ደረጀ በላይነህ ነውና፤ እውነቱን እንዲያረጋግጥልኝ ጠየቅኩት፡፡የደራሲና ጋዜጠኛ ዮናስ ነማርያምን ህልፈት አረጋገጠልኝ፡፡ እውነት እስካሁን ማመን ከብዶኛል፡፡ በሳል ጸሐፊ እንደነበር ብዙዎች ያምኑበታል፡፡ ለሕትመት የተዘጋጁ ከ50 በላይ የአጭር ልብ ወለድ ድርሰቶች እጁ ላይ እንዳሉ ገልፆልኝ ነበር፡፡ (ይህ የቁጥር መረጃ በወርሃ ሐምሌ በራሱ አንደበት የሰጠኝነው) የዮኒ ሥራዎች ምርጥ ናቸው። አዲስ አድማስን የሚያነብ ሰው፣ የዮኒ ሥራ ምን ሊሆን እንደሚችል ያውቃል። ለመጻፍ እንጂ ለማሳተም የማይጓጓ ሰው ነበር፡፡ እባክህ ‹‹ጠርዝና መጽሐፍ አድርገህ ሥጠን!›› ብዬው ‹‹ሁሉንም ከጊዜ ጋር እናየዋለን››! ብሎኝ ነበር፡፡ እነሆ ጊዜ የፈቀደውን አደረገ፡፡
በቅርቡ የወጣውን መጽሐፌን በተመለከተደውሎ ሲያወራኝ፣ ለኔ ስኬት ፍጹም ተደሳቹ እሱ ነበር። በልጅነት ታሪኮቻችን ዙርያ የሚያትተውን  ‹‹የመንጌ ውሽሚት›› የተሰኘውን መጽሐፌን፣ ወደ ሩሲያ ቋንቋ እንዲተረጎም እንደሚፈልግና ለዚህም አንድ ስመ-ጥር የሀገራችንን ተርጓሚ እያናገረ እንደሆነ ገልፆልኝ ነበር። ‹‹ነበር›› እያልኩ ሳወራ አፌን መረረኝ። ወዳጅ ዘመዶቹን ሁሉ እግዚአብሔር ያፅናችሁ!!፡፡
ነፍስህን በገነት ያኑረው ወንድሜ። ሁሌም በልቤ ውስጥ ትኖራለህ ዮኒዬ! በሰላም እረፍ!

Read 8606 times