Sunday, 03 December 2017 00:00

በኦሮሚያ-ሶማሌ አዋሳኞች ባገረሹ ግጭቶች 18 ሰዎች ተገድለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(35 votes)

      ከሠሞኑ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሣኞች ባገረሹ ግጭቶች፣ በ6 ቀናት ውስጥ ብቻ 18 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ህዳር 20፣ በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢ በምትገኘው የጉሡም ወረዳ በተፈጠረ ግጭት የ4 ሰዎች ህይወት በፀጥታ ሃይሎች ጥይት ማለፉንና 18 ሰዎች መቁሰላቸውን ከወረዳው ኮሚኒኬሽን ሃላፊ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በወረዳዋ ለተፈጠረው ግጭት በዋናነት “አንድ የቀበሌ አስተዳዳሪ በሶማሌ ልዩ ሃይል በጥይት ተመቷል” በሚል የአካባቢው ወጣቶች ተቃውሞ ማድረጋቸው መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ህዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም በቦረና ዞን አሬሮ አረዳ እና መልካ ሃልቱ፣የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል በከፈተው ተኩስ 13 ሰዎች መገደላቸውንና 23 መቁሰላቸውን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ አዲስ አረጋ አስታውቀዋል፡፡   
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ በምትገኘው ጭናቅሰን ወረዳም በከባድ መሳሪያ የታገዘ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ መሰንበቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡   የፌደራል መንግስት በብሄራዊ ደህንነት ም/ቤት በኩል በሃገሪቱ የሰው ህይወት እየቀጠፉ ያሉ መሰል ግጭቶችን ለማስቆም ለ1 ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ የፀጥታ እቅድ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን በተደረገው ተጠርጣሪዎችን የማደን ዘመቻም፣ ከ130 በላይ በግጭት ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን መንግስት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ሄግ ኢንተርናሽናል ሙቭመንት የተሰኘ የሰብአዊ መብት ተቋም በበኩሉ፤ ግጭቶቹን ተከትሎ፣ የሰዎች መፈናቀል መቀጠሉን ጠቁሞ፤ እስካሁንም ከ400ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ሪፖርት አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል፤ ባለፋ ረቡዕ ህዳር 20፣በአዳማ ከተማ ህገ ወጥ ቤቶችን ከማፍረስ ጋር በተያያዘ በተከሰተ ግጭት አንድ ሰው መቁሰሉንና ሁለት የፖሊስ ሞተር ሳይክሎች መቃጠላቸውን የጠቆሙት የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አዲስ አረጋ፤ ግለሰቡን ያቆሰለው የፖሊስ ባልደረባም በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታውቀዋል።

Read 6761 times