Sunday, 03 December 2017 00:00

የእስከዛሬዎቹ “መፍትሄዎች” እና ውጤታቸው

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(8 votes)
  •   ገናና ገዢ ፓርቲ፣ መፍትሄ ነው? ምናልባት “ጠንካራ” ተቃዋሚ ፓርቲስ?

እጅጉን የገነነ ገዢ ፓርቲ፣... የችግሮች መፍትሄ ቢሆን ኖሮ፣ በከፍተኛ ቀውስ እየተንገዳገዱ ወይም በለየለት ትርምስ እየፈራረሱ የሚገኙ በርካታ አገራት፤... ከጥፋት መዳንና ከችግር መገላገል በቻሉ ነበር። ግን አልቻሉም። እንዲያውም፤... ገናና ገዢ ፓርቲ፣ ፈጠነም ዘገየም፣ ለቀውስ እንደሚያጋልጥ የሚያረጋግጡ ምስክሮች ሆነዋል። ከዚምባብዌ እስከ ቬኔዝዌላ፣ ከሊቢያ እስከ ሶሪያ፣... ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ በርካታ የአፍሪካና የአረብ አገራት፣ የዚህ ቀውስ ገፈት ቀማሽ ናቸው - (የቅደም ተከተልና የደረጃ ልዩነት ቢኖራቸውም)።
“ቢሆንም ግን፣... የተደላደለ ጠንካራ ገዢ ፓርቲ፣ የአገሬው ፖለቲካ ውስጥ መግነኑ፣... እፎይታንና እርጋታን የሚያስገኝ ከሆነ፣... ከትርምስ ይሻላል” የሚል ሃሳብ ሊመጣ ይችላል። በእርግጥም፣ ከትርምስ፣ እርጋታ ይሻላል። ነገር ግን፣ ለጊዜው ነው።
በብቸኝነት የገነኑ ፓርቲዎችና የመንግስት መሪዎች፤ ለጊዜው እርጋታን የሚያሰፍኑ ቢመስሉም፣... በዚህችው የእርጋታ ጊዜ ውስጥ የስልጡን ፓለቲካ ጅምር እንዲጠናከር ካልጣሩ፣ የብልፅግና ኢኮኖሚ መልክ እንዲይዝ በትጋት ካልሰሩ፣... እርጋታው ይጠፋል። በየአገሩ እንደምናየውም፣ መጨረሻቸው አያምርም - ጊዜ የማይሰጥ ጥፋት ውስጥ ይዘፈቃሉና።  ውስጥ ለውስጥ ተቦርቡሮ፣ ድንገት እንደሚፍረከረክ ግንብ ናቸው። ድንገት እየተፍረከረኩ፣ መውጪያና ማብቂያ ወደሌለው ትርምስና እልቂት የሚወርዱ በርካታ አገራትን እያየን አይደል!
“ጠንካራ” ተቃዋሚ ፓርቲስ፣ መፍትሄ ሊሆን ይችላል? ያው ስልጣን ሲይዝ፣ ገናና ገዢ ፓርቲ መሆኑ ይቀራል? እንዴት ይቀራል? ያኔ፣ አዲስ የችግር ዙር ተጀመረ ማለት ነው።
ምናልባት፣ ሁሌም “ጠንካራ” ተቃዋሚ ሆኖ የሚቀጥል ፓርቲ ቢኖርስ? ይህም፣... መፍትሄ አልሆነም። ለምሳሌ፣ ለሊባኖስ አልበጃትም። የራሱ ጦር ያለው ሄዝቦላ፣ ሊባኖስ ውስጥ አይነኬ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን ነው። ነገር ግን፣ ሄዝቦላ፣ ለሊባኖስም ሆነ ለሌላ አገር የማይበጅ የጥፋት ቡድን በመሆን ነው የሚታወቀው።

የገዢና የተቃዋሚ ፓርቲ ፉክክርስ?
የተጋጋለ የምርጫ ውድድር፣ የተጧጧፈ የገዢ ፓርቲና የተቃዋሚ ፓርቲ ፉክክርስ መፍትሄ ነው? ለኬንያ መፍትሄ አልሆናትም። የፖለቲካ ምርጫና የፓርቲዎች ፉክክር፣ በምኞት ብቻ አይሰምርም። ስልጣኔን ይጠይቃል።
በዚያ ላይ፣ አንድ ፓርቲ እየወረደ ተቃዋሚ ፓርቲ ስልጣን መቆናጠጡ፤ አንድ መሪ እየለቀቀ በምትኩ ተቀናቃኝ ፖለቲከኛ ቤተመንግስት መግባቱ አይደለም ዋናው ቁምነገር። የፓርቲዎች መፈራረቅ ትርጉም የሚኖረው፤ “የመንግስት ትክክለኛ ስራ ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ ቅድሚያ ሰጥተን መልስ ስናገኝለት ነው። አለበለዚያ፣ የየትኛው ፓርቲ ውሳኔ ጠቃሚና ጎጂ እንደሆነ፣ የየትኛው ፓርቲ ድርጊት ተገቢ አልያም አጥፊ (ጥሩ ወይም መጥፎ) እንደሆነ መለየት አንችልም።
በጭፍንና በዘፈቀደ፣ አገር ምድሩን በእልልታ ወይም በእሪታ የመቀወጥ ሱስ ካልተጠናወተን በቀር፣... እንደማንኛውም ጤናማ ሰው፣ ጥሩውን ከመጥፎ ለመለየት የምንፈልግ ከሆነ፤ የመንግስት ትክክለኛ ስራ ምን መሆን እንደሚገባው ማወቅ ይኖርብናል።
ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች፣ በአመፅም ሆነ በምርጫ፣ ስልጣን ላይ መለዋወጣቸው ትርጉም የሚኖረውም፤ በቅድሚያ “የመንግስት ተገቢ ስልጣንና ልኩ የት ድረስ መሆን አለበት?” ብለን በመጠየቅ፣ መልሱን ያወቅን እንደሆነ ብቻ ነው። አለበለዚያ፣... መመዘኛ ስለማይኖረን፤ አንዱን ፖለቲከኛ ማበረታታትና ሌላኛውን መተቸት፣ አንዱን ውሳኔ መደገፍና ሌላኛውን ውሳኔ መቃወም አይቻልም - በጭፍን ካልሆነ በቀር።
ገዢው ፓርቲ ውስጥ፣ በጎራ የተቧደነ የውስጥ ለውስጥ ፉክክርና ሽኩቻ ቢፈጠርስ? በአንዳች ተዓምር አንዳች ለውጥ ያመጣ ይሆን?
ግን ምን ዋጋ አለው? “አንዳች ለውጥ” ማለት ግን፣ “መልካም ለውጥ” ማለት አይደለም። የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ፣ በዚምባብዌ እንደሚታየው፣ ውስጥ ለውስጥ እየተንተከተከ ቆይቶ፣ አንዳች የለውጥ ፍንዳታ ላይ ሊደርስ ይችላል -  ብዙውን ጊዜም፣ ከማጥ ወደ ረመጥ የሚያስገባ “አንዳች ለውጥ” ሆኖ ያርፈዋል!

ለእስር ተዳርገው መስዋዕት የከፈሉ “የነፃነት ታጋይ” መሪ ቢመጡልንስ?
አዎ፤... አምባገነን መንግስትን መተቸትና መቃወም፣ “በአውቶማቲክ”.... ለግድያ ወይም ለእስር ይዳርጋል። ብዙ ጊዜ እየተደጋገመ የሚታይ አሳዛኝና ዘግናኝ መዘዝ ነው - የአምባገነንነት መዘዝ። ነገር ግን፣ አምባገነን መንግስትን የተቸና የተቃወመ ሰው፣ “በአውቶማቲክ”... ነፃነትን አፍቃሪ፣ መብትን አክባሪ ሰው ነው ማለት አይደለም።
በትችትና በተቃውሞ ሰበብ፣ መታሰሩና መሰቃየቱ... የአሳሪውን ክፋትና በደል፣ የታሳሪውን ስቃይና ተበዳይነት ይመሰክራል እንጂ፤... የታሳሪውን አዋቂነት፣ ቀናነትና ቅድስናን አያረጋግጥም። አምባገነንን መቃወም፣ ለነፃነት መቆም ማለት አይደልም። ለነፃነት የሚበጅ ብቃትን ያቀዳጃል ማለትም አይደለም።
በአምባገነን መንግስት አማካኝነት ለዓመታት የታሰሩ፣ ዓለም ሁሉ የዘመረላቸው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ፣... ከረዥም ጊዜ በኋላ፣ በምርጫ አሸንፈው ለስልጣን መብቃታቸው፣ ችግሮችን የሚፈታ ትልቅ ስኬት ሆኖ ሊታየን ይችላል። ነገር ግን፣ ለማይነማር መፍትሄ አልሆነላትም።

ፈርጣማ ክልሎችስ?
“በፌደራላዊና በዲሞክራሲያዊ” ስርዓት፣ ፈርጣማ የክልል መስተዳድሮች ቢፈጠሩስ መፍትሄ ይሆናል? በስልጡን ፖለቲካ ካልተቃኘ፣ ማለትም በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ ስልጡን ፖለቲካ ከሌለ፣... ከመፍትሄነቱ ይልቅ ችግርነቱ ይብሳል። እንኳን ለአፍሪካ ይቅርና፣.. እንኳን ለአረብ አገራት ይቅርና፣... ወደ ስልጣኔ ደህና የመራመድ እድል አግኝተው ለነበሩ የአውሮፓ አገራትም፣ ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችል እየታየ ነው።
በእንግሊዝ፣ ከአመት አመት እየተባባሰ የመጣውና ስኮትላንድ ላይ ያተኮረው ውዝግብ፣ የክልል መስተዳድርን በማፈርጠም አልተፈታም።
ፈተናው ምንኛ አደገኛ እንደሆነ፣ በቅርቡ በስፔን ታይቶ የለ? ስስ የዘረኝነት ስሜት ቀስበቀስ እየጎላበት የመጣው ፖለቲካ፣ ለማን ጠቀመ? ለጥላቻ አጋፋሪዎች ተመቻቸው - በሰፈር ወይም በዘር ለተቧደኑ የጥፋት ዘማቾች!
በጭፍን የጥላቻ ቅስቀሳ ላይ ያተኮሩና በዘር የተቧደኑ ሰዎች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገነኑ የሚያጦዙት ውዝግብ፣... የትም አገር ቢሆን፣ ወደ ጥፋት እንደሚያደርስ እስካሁን ካልተገነዘብን፤... ጊዜው በጣም እየረፈደብን እንደሆነ ማስተዋል አለብን። እንኳን ኢትዮጵያን በመሰለ ኋላቀርና በቋፍ ያለ አገር ውስጥ ይቅርና፣ እንደ ስፔን በመሳሰሉት የተረጋጉና ደህና የስልጣኔ ጣዕምን የቀማመሱ አገራትም ቢሆኑ፣... ከአደጋ አያመልጡም።
 
ጣልቃ የሚገቡ ሸምጋዮች፣ በማዕቀብ የሚገስፁ አደራዳሪዎችስ?  
“በዘር የተቧደነ ፖለቲካና ቅስቀሳ፣... ነውር፣ ሃጥያት፣ ፀያፍ፣ ክፋት ነው” ብሎ መናገር፣ “ሩቅ ቲዎሪ” አይደለም። በዓለም ዙሪያና በአገራችን፣ አፍጥጦና አግጥጦ፣ በየእለቱ ጥፋትን ሲያስከትል እያየነው ነው።
በዘር የተቧደነ ፖለቲካና ቅስቀሳ፣... ከትኛውም ‘ዓለማ’ ጋር በማዳቀል ልናሳምረው ብንጥር፣... በምንም ሰበብ ልንሸፋፍነው ብንሞክር፣... “ወደ ተግባር አይሸጋገርም፤ ወደ እልቂት አያደርስም” ብለን ራሳችንን ብናታልል፣... “ወደ ዘግናኝ እልቂት ሳይደርስ፣ አደጋውን የሚያስቀርና የሚያስቆም አንዳች ተዓምር ይፈጠራል” ብለን አይናችንን ብንጨፍን፣... እንደዘራነው ከመታጨድ ማምለጥ አንችልም፣ እልፍ አላፍንም ሰለባ ከሚያደርግ ጥፋት አንድንም። ከለኮስነው እሳት የሚያወጣ፣ በነፍስ የሚደርስልን አይኖርም።
እንደ ድሮ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፣ ዲፕሎማቶች፣ ሸምጋዮችና አደራዳሪዎች፣... በገዛ ራሳችን ከገባንበት ረመጥ ሊያወጡን ቢፈልጉ እንኳ፣ ዛሬ ዛሬ በቂ አቅምና ሁነኛ መላ የላቸውም።
ከሃያ ዓመታት በፊት፣... አዎ፣ እዚህም እዚያም ይሳካላቸው ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን፣... በየቦታው ነፍስ ለማዳን መሯሯጣቸው ባይቀርም፣ ሙከራቸው ሁሉ መና እየቀረ፣ አቅምና መላ አጥሯቸው ግራ እየተጋቡ፣... በአብዛኛው ተስፋ ቆርጠዋል። ወደ ጥፋት አለመድረስ ነው እንጂ፣... ከዚያ በኋላ ማንም አይደርስልንም።

ከጥፋት ባንድንም፣... በተወሰነ ደረጃ፣ በተወሰነ ጊዜና በተወሰነ ደረጃ ከተገታስ?
የጥፋት መንገድ፣ እንደማንኛውም ጥፋት፣... ገና ሲጀመር፣... በጣም ቀላልና ትንሽ፣ ቀልድና ጨዋታ ይመስላል። እያንዳንዱ  የጥፋት ተጓዥ፣  ከፊትና ከኋላ ጥላቻን ለማቀጣጠል እንደ እንስሳ መንጋ መሰባሰብ የሚያምራቸው... በዘር አልያም በጎሳ መንዝረው ተቧደኑ፣ ሃይማኖትን አልያም የቀድሞ ትውልዶች ኋላቀር ባህልን እየጠቀሱ፣ በቋንቋ ወይም በትውልድ ሰፈር የተቧደኑ አምስትም ሆኑ መቶ ሰዎች፤... ጎራ ለይተው በጠላትነት የሚጠፋፉ ቢሆኑም፣ እርስ በርስ ተመጋጋቢ ናቸው።
በወዲህኛው ጎራ የተቧደኑት፣ እነዚህኞቹ አምስት ሰዎች የፈፀሙት ጥፋት፣. በተቃናቃኝ ጎራ ላሰፈሰፉ ለእነዚያኞቹ አምስት ክፉ ሰዎች፣... “ሲሳይ” ነው። ‘ጥሩ’ ሰበብ እንዳገኙ ይቆጥሩታል - “አጠፉን፣ ዘመቱብን” የሚል የጅምላ ቅስቀሳ ለማቀጣጠልና ጭፍን ጥላቻን ለማግለብለብ።
ከዚያስ? የእነዚያኞዎቹ የጥላቻ ቅስቀሳና የጥፋት ድርጊት ደግሞ፣ እንደገና በተራው ተመልሶ፤ ለእነዚህኞቹ ‘ሲሳይ’ ይሆንላቸዋል።
እንዲህ፣ እየተመጋገቡ ይጠፋፋሉ። እየተመጋገቡ፣ ሌሎች እልፍ አእላፍ ሰዎችን ሰለባ ያደርጋሉ። እንዲህ አይነት የጥፋት ዘማቾች፣ አምስትም ይሁኑ መቶ ሰዎች፣ የጥፋት ጉዟቸውን የማቋረጥና የማብረድ ፍላጎት የላቸውም፤... ጥፋታቸውን እያጦዙ ይቀጥላሉ እንጂ።
ሊያስቆማቸው የሚችል ሰው የለም ማለት አይደለም። አለ። ዝምተኛ፣ የዳር ተመልካችና ሰለባ የሚሆኑ እልፍ አእላፍ ጨዋ ሰዎች አሉ። ጨዋ ሰዎች፣... በየሰበቡ የሚቧደኑ አጥፊዎችን ማስቆም ይችላሉ። ካልቻሉ ወይም ካልፈለጉ ግን፣ የጥፋት ሰለባ ከመሆን የሚያድን የነፍስ ደራሽ አያገኙም። ደግሞም ማብቂያ የለውም።
የዘረኞች የመቧደኛ ሰበብ፣ ጥቁር እና ነጭ በሚል ጎራ ላይ እንዳልተገታ፣ ማንም ጤናማ ሰው ያውቃል። የአጥፊዎች የመቧደኛ ሰበብ፣ ክርስትያን እና ሙስሊም በሚል ጎራ ብቻ ታጥሮ አይቆምም። ከአንድ የጥፋት ሰበብ፣ ብዙ ሰበብ እየተጎለጎለ፣ ከአንድ ማመካኛም ብዙ እየተመነዘረ፣... ጎሳ፣ ነገድ፣ ወረዳና ቀበሌ እያለ ይቀጣጠላል። ሃይማኖትም እንደዚያው የደርዘን ደርዘን መቧደኛ እሾሆችን ይወልዳል።
ምን አለፋችሁ፤... ሶማሊያን ማየት ነው። ክፉ ሰዎች፣ “አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ዘር ሆነብን” ብለው፣ መቧደኛ ሰበብ አላጡም። ከቀይ ባህር ማዶ ደግሞ፣ የመን አለች - በመጥፋት ላይ ያለች አገር!




Read 3383 times