Sunday, 03 December 2017 00:00

የህወሓት ግምገማ፣ ሹም ሽርና ራስን ውንጀላ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

“አመራሩ በቀጣይነት የሚመራ ብቁ ሃይል እንዳይፈጠር እንቅፋት ሆኗል”

የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ለስድስት ሳምንታት ረዥም ስብሰባና ግምገማ ካደረገ በኋላ አመራሩን ክፉኛ የሚተችና የሚወነጅል የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ “- አመራሩ የሃሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፣ ፀረ ዴሞክራቴክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፣ በተልዕኮ ዙርያ በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር የማይሰጥ፣ህዝብንና አላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርና ጥቅም
የሚያስቀድም መሆኑ ታይቷል፡፡” በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ውንጀላው ይቀጥላል፡፡ “ለህዝብ ያለው ወገንተኝነት እየተሸረሸረ፣ ከኣገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደ ተገልጋይ እየቆጠረ፤ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬታማ የህዝብ ዙርያ መለስ እንቅስቃሴ ከመጠመድ ይልቅ በተደማሪ ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር እየሆነ፣ በአጠቃላይ ራሱን ወደ ጥገኛ ገዢ መደብ የመሸጋገር አዝማሚያ የተጠናወተው መሆኑን በትክክል አስቀምጧል፡፡--” ይላል፡፡ በመጨረሻም፤”ህወሓት/ኢህኣዴግ የጋራ ሃገራችን በሆነችው ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ፤ ለልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት
ግንባታ ላይ የተጫወተውን ገንቢ ሚና ኣጠናክሮ ለመወጣት የሚያስችለውን አቅጣጫዎች ከህዝቦች ጋር በመመካከር የሚያከናውን ይሆናል፡፡” ብሏል - ማዕከላዊ ኮሚቴው በአቋም መግለጫው፡፡ይሄ ረዥም ጊዜያትን የፈጀው የህወሓት ስብሰባና ግምገማ እንዲሁም የአመራር ለውጥ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለአገሪቱ ፖለቲካ ፋይዳው ምንድን ነው? ለህዝብ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጥ ይሆን?
የህወሓት ግምገማ  በቀድሞ ታጋዮች እንዴት ይገመገማል? የህወሓት መስራቾችና አንጋፋ ታጋዮች ከነበሩትና አሁን በተቃውሞ ጎራ ከተሰለፉት መካከል አቶ ገብሩ አሥራትና አቶ አስገደ ገ/ስላሴን፣ የአዲስ
አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡

“የህወሓት ትልቁ ድክመት የአስተሳሰብ ነው”

አቶ ገብሩ አስራት

ከህወሓት ሳምንታት የፈጀ ግምገማ  ምን  ውጤት ይጠብቁ ነበር?
ይሄ ግምገማ ምንም አይነት ውጤት እንደማይኖረው እገምት ነበር፡፡ አሁንም እየሆነ ያለው የጠበቅሁት ነው፡፡ የግምገማው መነሻ ሲንከባለል ከርሞ ዛሬ ላይ የደረሰው የሁለት ጎራዎች ሽኩቻ ውጤት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሲጠበቅ የነበረ ነው፡፡ ህውሓት ውስጥ ሁለት ቡድኖች እንደነበሩም የሚታወቅ ነው፡፡ አንደኛው ቡድን “የመለስ ሌጋሲን አስቀጥላለሁ” የሚልና በዚህ መፈክር ስር ስልጣን ተቆናጥጦ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ የሚፈልገው ነው፡፡ ይሄ የእነ አባይ ወልዱና የእነ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቡድን ነው፡፡ ሌላው ቡድን ደግሞ የመለስ ሌጋሲን ብቻ እናስቀጥላለን የሚለውን ቡድን አስወግዶ፣ የራሱን ሰዎች ማስቀመጥ የሚፈልግ ቡድን ነው። በዋናነት የእነ አባይ ስብሃትና የህወሓት አንጋፋ መሪዎች የሚባሉትን የያዘ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል የቆየ ሽኩቻ ነበር፡፡ ይሄ ሽኩቻ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ቀውስ የበለጠ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡
ህዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች በማንኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፅዕኖአቸው ቀላል አይደለም። የነበረው አመራር ደግሞ ለጥያቄዎቹ  በቂ ምላሽ አልሰጠም፡፡ እርስ በእርሱ በቡድን የተደራጀ ነው፤ ዲሞክራሲንም ያሰፈነ አይደለም፡፡ ለተፈጠረው የመልካም አስተዳደር እጦትና የሙስና መባባስ ተጠያቂ ነው ተብሎ በሌላኛው ቡድን እንዲመታ መደረጉንም ከሰሞኑ የጉባኤው ውጤት ያረጋገጥነው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እርስ በእርስ ከስልጣን መፈነጋገልና መወጋገድ፣ ድርጅቱ የፖለቲካ አይዲኦሎጂውንና ፖሊሲውን እስካልቀየረ ድረስ ለኢትዮጵያ ህዝብም ይሁን ለትግራይ ህዝብ የሚያመጣው አዲስ ለውጥ አይኖርም፡፡
በግምገማው ዋና ዋና ግለሰቦች ጭምር ከስልጣን መነሳታቸውን በመጥቀስ፣ አንዳንድ ወገኖች  ምናልባት ለስር ነቀል ለውጥ እርሾ ሊሆን ይችላል እያሉ ነው፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
በጭራሽ! በአንድ ድርጅት ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ የሚችለው መጀመሪያ ፍጭቱ በሀሳብ ዙሪያ ሲሆን ነው፡፡ በፖለቲካ ርዕዮተ አለምና በፖሊሲ ዙሪያ የሀሳብ ፍጭት መፈጠር አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በሰሞነኛው ስብሰባቸው ላይ የታየ ምንም ፍንጭ የለም፡፡ የግለሰቦች የእርስ በእርስ ሽኩቻ ነው ፈጦ የወጣው፡፡ ህዝቡ ደግሞ እያነሳቸው ያሉ ጥያቄዎች በርዕዮተ አለምና በፖሊሲ ደረጃ ያሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የነፃነት፣ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ናቸው፤ በመሰረታዊነት ከህዝቡ እየተነሱ ያሉት፡፡ እነዚህ ከፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ታግደዋል ወይም ከስልጣናቸው ዝቅ ተደርገዋል የተባሉት ግለሰቦች፣ ከተጠቀሱት የህዝቡ ጥያቄዎች አንፃር ታይተው አይደለም የተገመገሙት፡፡ እነዚህን ገምግመው ከስልጣን ዝቅ ያደረጓቸውም የህዝቡን ጥያቄ በትክክል ተረድተው፣ ሁነኛ የመፍትሄ አቅጣጫ ሲያስቀምጡም አላየንም፡፡ ያው እንደተለመደው፤”ህውሓትን እናድን” የሚል እንቅስቃሴ ነው እያደረጉ ያሉት፡፡ ርዕዮተ አለሙም ያው የምናውቀው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው፤ የፖለቲካ አቅጣጫውም ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት የሚል ነው፤ አስተሳሰቡም ማዕከላዊ ዲሞክራሲያዊነት ነው፡፡ ስለዚህ ምንም አይነት ስር ነቀል ለውጥ አያመጣም፡፡
በኦሮሚያ ክልል ወደ አስተዳደሩ አዳዲስ አመራሮች መምጣታቸውን ተከትሎ ለውጥ ተስፋ የሚያደርጉ ወገኖች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ህውሓት በአዳዲስ አመራሮች ከተደራጀ የለውጥ ተስፋ አይኖርም ይላሉ?
አንድ መገንዘብ ያለብን፣ ዋናው ለውጥ የሚያመጣው የትውልድ ጉዳይ አይደለም፤ አስተሳሰብ ነው፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ያለው አዲሱ አመራር የነበረውን አስተሳሰብና ፖሊሲ የሙጥኝ ብሎ ከያዘ ለውጥ ይመጣል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ህውሓት ውስጥ ደግሞ ምንም ፍንጭ ያልታየው የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ነው። ለውጥ ሲመጣ ዋናው ነገር የአስተሳሰብ ነው እንጂ የትውልድ አይደለም፡፡ በዚህ ዙሪያ እስካሁን በኢህአዴግ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ አልተመለከትኩም፡፡ ህውሓትም፣ ኦህዴድም ሆነ ብአዴን ውስጥ ምንም የአስተሳሰብ ለውጥ አልተመለከትኩም፡፡ ህውሓት ውስጥ ደግሞ አመራሩን የሚያሽከረክረውም ቢሆን የቆየው ታጋይ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ አሁንም ድርጅቱ የሚቃወማቸውን “ጠላት” ብሎ ነው የሚፈርጀው። በተለይ ተቃዋሚው በሙሉ “ጠላት” ተብሎ ነው የሚፈረጀው፡፡ ትግራይ ውስጥ “አረና”ን እንደ ጠላት ነው የፈረጁት፡፡ ይሄ በፖለቲካው መስክ ምንም አይነት ለውጥ ለማምጣት እንደማይፈልጉ ምስክር  ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቶች ወደ አመራሩ ቢመጡም የራሳቸውን ርዕዮተ አለምና አስተሳሰብ ይዘው የሚመጡ ከሆነ ብቻ ነው ለውጥ የሚመጣው፡፡ በቆየው አስተሳሰብ ዙሪያ ብቻ የሚሰሩ ከሆነ ግን የባሰ ችግር የሚፈጥር እንጂ አዲስ ነገር ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ይሄን ለውጥ ብለው የጀመሩትን እንቅስቃሴ እየመሩ ያሉት ደግሞ የድሮ ሀሳብ አራማጆች ናቸው፡፡  
እርስዎ በዋናነት የህወሓት ድክመት የሚሉት ምንድን ነው?
ትልቁ ድክመት የአስተሳሰብ ነው፡፡ የሰው ኃይል አይደለም፡፡ ቀደም ብሎም ኢህአዴግ ውስጥ የአመራር ለውጥ ተደርጎ፣ በርካታ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች የተካተቱበት ካቢኔ ተቋቁሟል፡፡ ግን እነዚህ ሰዎች ምን ለውጥ አመጡ? ምንም ጠብ የሚል ለውጥ አላመጡም፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት አሁንም አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ማዕከላዊ ዲሞክራሲያዊነት እያሉ እየዘመሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቅርቡ አረጋግጠውታል፡፡ ታዲያ በዚህ መንገድ እንዴት አዲስ ለውጥ ይጠበቃል? ህወሓትም ልክ እንደ ሌላው የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች የሰዎች ሹም ሽር አድርጓል፡፡ ግን ምን ለውጥ አመጣ? ምንም ለውጥ አላየንም፡፡ ድክመቱ ያለው የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት አለመፈለጉ ላይ ነው፡፡
ህወሓት አሁን  በትግራይ ወጣቶች ዘንድ ያለው ተቀባይነት  ምን ያህል ነው?
ይሄ እኮ እራሳቸውም በግልፅ ያስቀመጡት ነው፡፡ በተለይ አመራሮችን ከሃላፊነት ዝቅ ሲያደርጉ አንዱ ያነሱት ጉዳይ፣ ወጣቱን ማሳተፍ አልተቻለም የሚል ነው፡፡ ወጣቱ በትግራይ ከፖለቲካው ተገልሎ እንደቆየ የሚታወቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ወጣቱ እነሱ በሚያስቡት አቅጣጫ ለመሄድ አይፈልግም፡፡ ለዚህ ደግሞ አንዱ ማሳያ የሚሆነው፣ የራሳቸው አባላት የሆኑ ወጣቶች ጭምር በፌስ ቡክ የሚያቀርቡት ተቃውሞና ትችት ነው፡፡ ወጣቱ ለውጥ እፈልጋለሁ ብሎ ትልቅ ትግል እያደረገ ያለው በትግራይ ውስጥ ነው፡፡ ወጣቱ ትንሷን የዘበኝነት ስራ ሳይቀር ለማግኘት መዛመድ ያስፈልገዋል፡፡ የትግራይ ወጣት እኮ ስራ በማጣት እየተሰደደ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ተገልሏል፡፡ የፖለቲካ መድረኩ  ያደረገው ማህበራዊ ሚዲያን ነው፡፡ በግምገማቸው አንዱ በጉልህ ያነሱትም፣ ወጣቱ ወደ አመራር እንዲመጣ አልተደረገም የሚል ነው፡፡ እንዴት ነው ወጣቱን ወደ አመራር የሚያመጡት? ዝም ብለው እየጎተቱ ነው? ለምንስ ወጣቱ ወደ እነሱ ሊቀርብ አልፈለገም? እነዚህ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ትንሽ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚሞክሩ ደግሞ እየታሠሩ ነው፡፡ አብርሃ ደስታ የትግራይ ወጣቶች ማሣያ ነው፡፡ የተለየ ሃሣብ ስላራመደ ታስሯል፤ ተሠቃይቷል፡፡ ወጣቱ ልቡ ከሸፈተና ለውጥ ከፈለገ ቆይቷል፡፡
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ተቃውሞ ሲደረግ የትግራይ ህዝብ ተቃውሞ አላሰማም በሚል ህወሓት የህዝቡ ድጋፍ እንዳለው አድርገው የሚቆጥሩ ወገኖች አሉ ----
አንድ ነገር በግልፅ ማስቀመጥ የምፈልገው፣ በኦሮሚያ ወጣቱ በግልፅ ወጥቶ ከመቃወሙ በፊትም ሆነ በአማራ ክልል የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከመደረጉ በፊት ትላልቅ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ የነበሩት ትግራይ ውስጥ ነው፡፡ የእምባ ሰኔት ከ30 ሺህ በላይ ህዝብ ሠላማዊ ሠልፍ የወጣበት ጊዜ የሚታወስ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ምንም እንቅስቃሴ እንዳላደረገ አስመስለው ለማቅረብ የሚፈልጉ አካላት፤ “የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት አንድ ናቸው” ብለው እውነታውን ለማድበስበስ የሚፈልጉ ናቸው፡፡
የተንቤን ህዝብ ለብዙ ጊዜያት ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርግ ቆይቷል፤ ግን ሚዲያው ይሄን አይቶ እንዳላየ ለማለፍ ነው የሚሞክረው፡፡ ምክያቱም ቀላል የፍረጃ መንገድ የሚሆነው የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው በሚለው መምታት ስለሆነ ነው እንጂ ህዝቡ በየጊዜው በስርአቱ ላይ ያለውን ምሬት ሲያንፀባርቅ ቆይቷል፡፡ አምና የ4 ቀን የታክሲዎች የስራ ማቆም አድማ የተደረገው ትግራይ ላይ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ አለ፡፡
ከዚህ በላይ ምንድን ነው የሚፈለገው? በነገራችን ላይ ህወሓት/ኢህአዴግ ዋና መሠረቴ ትግራይ ውስጥ ነው ብሎ ስለሚያስብ እፈናው ከሌላው አካባቢ የበለጠ ነው የሚሆነው፤ ተቃውሞን ሊቀበል አይችልም፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሣይቀሩ ትግራይ ውስጥ ምንም አይነት ስንጥቅ መፈጠር የለበትም ብለው በ2002 ምርጫ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ የአፈናውን ሁኔታ ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው አንድ ስርአት  ነው፡፡ ይህ ስርአት በአንድ አካባቢ ቅዱስ ሆኖ በሌላው ሠይጣን ሊሆን አይችልም፡፡ ሠይጣን ከሆነ የሚሆነው በሁሉም አካባቢ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ዝም ብሏል የሚሉ ሰዎች የፖለቲካው ትንታኔ እየገባቸውም ቢሆን፣ ሆን ብለው የትግራይን ህዝብ ከህወሓት ጋር ለመፈረጅ የሚታትሩ ፅንፈኛ ኃይሎች ናቸው፡፡ ህዝቡ ግን በተለያየ መንገድ እየታገለ ነው፡፡ አሁን የምናየው የአመራሩ እርስ በእርስ መባላትም የዚህ የህዝቡ ትግል ውጤት ነው፡፡
የህውሓት ስብሰባና ግምገማ ከ3 እና 4 ሳምንታት በላይ ጊዜ የመፍጀቱ አንድምታ ምንድን ነው?
አንድምታው ግልፅ ነው፡፡ አንድ ድርጅት ወይም ፓርቲ ቀውስ ውስጥ ሲገባ የመፍትሄ ሃሳቦች ይጠፉታል፡፡ በተለይ የጠራ አስተሳሰብ ነጥሮ ባልወጣበት ሁኔታ እዚያው በዚያው እሽክርክሪት ነው የሚሆነው እና ህውሓት ደግሞ የትግራይን ህዝብ መምራት አልቻለም፤ በህብረተሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ አለበት፡፡ ይሄን ሁኔታ ለመፍታት አንድ መፍትሄ መፈለግ ነበረበት፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲስ አስተሳሰብ ማምጣት ስለተሳነው የተወሰኑ ግለሰቦችን መርጦ “እናንተ ናችሁ ጉድለት የፈጠራችሁበት” ብሎ ዋጋ ማስከፈል ነበረበት፤ ያደረገውም ይሄንኑ ነው፡፡ ይሄን ያደረገው ደግሞ ሄዶ ሄዶ አዲስ ሀሳብ በማጣቱ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ጎራዎች መካከል የኃይል ሚዛኑ ተመጣጣኝ ስለነበረም በቀላሉ ማስወገድ የሚፈልጉትን ማስወገድ ያልተቻለበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከአንድ ወር በላይ ስብሰባም ተቀምጧል፡፡ በህወሓት የስብሰባ ታሪክ ይሄ ሪከርድ ጭምር ነው፡፡ ኮሚቴው ይሄን ያህል ሲሰበሰብ ምን ያህል የህዝብ ሀብትና ጊዜ እንደተሻማ ደግሞ መገመት ይቻላል፡፡ ጊዜው የረዘመው የሃይል ሚዛኑ ተመጣጣኝ ስለነበረ እንጂ አዲስ ሀሳብ ለማምጣት አይደለም፡፡ በመጨረሻም  አንዱ ቡድን፣ አንዱን መጣል ችሏል ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ ከጉባኤው በኋላ  ምን ለውጥ ይመጣል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ?
ምንም ለውጥ አይመጣም፡፡ እንዳልኩት በሁለት ቡድኖች መካከል የሚደረግ የስርወ መንግስት (Dynasty) ሽኩቻ ስለሆነ ምንም ለውጥ አይመጣም፡፡ አሁን የእነ አቶ መለስ ቡድን ተመቷል፤ ሌላው የእነ ስብሃት ቡድን ስልጣን ይዟል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚያመጣው ለውጥ አለ ብዬ አልገምትም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳርን አያሰፋም፣ የህዝቡንም ጥያቄ አይመልስም፤ነገርየው የስልጣን ሽኩቻ ብቻ ነው፡፡ ለውጥ ቢመጣማ ከማንም በላይ ደስተኛ እሆን ነበር፡፡
በአሁኑ የአገሪቱ ፖለቲካ  ውስጥ የህወሓት ሚና እና ተፅዕኖ ምን ድረስ ነው ማለት ይቻላል?
እርግጥ ነው ቀደም ሲል ህወሓት በኢህአዴግ ውስጥ ካሉ ድርጅቶች የበለጠ ተፅዕኖ ነበረው። በተለይ ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ ግን ይሄ ተፅዕኖው በጣም ቀንሷል፤ እንዲያውም ወደ ዳር የተገፋበትን ሁኔታ ነው እኔ የማየው፡፡ አሁን ህወሓት የድሮውን ያህል ተፅዕኖ አለው፤ ሌሎችን ያሽከረክራል የሚለውን አተያይ ትክክል አድርጌ አላየውም፡፡ በተለይ አሁን በብአዴን እና በህውሓት፣ በህውሓት እና በኦህዴድ፣ በኦህዴድ እና በብአዴን መካከል ሽኩቻዎች በግልፅ መታየታቸውም የህውሓት የአሿሪነት ሚና በመዳከሙ ነው፡፡ ሃይ ባይ ሃይል ነጥሮ ስላልወጣ ነው ይሄ ሽኩቻ የታየው። ያለፉት ሶስትና አራት ዓመታት የሽኩቻ ጊዜ ነበር፡፡ ህወሓት አሁን የፖለቲካ ተፅዕኖው ተዳክሟል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በቀጣይ የህውሓት ሚና /ድርሻ/ ምን ሊሆን ይችላል ብለው ይገምታሉ?
ይሄ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ በአጠቃላይ ህውሓትን ጨምሮ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከህዝቡ ሙሉ ለሙሉ ከተነጠሉ ቆየት ብሏል፡፡ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መመለስ ቀርቶ ሊያዳምጥም እየፈለገ አይደለም፡፡ ስለዚህ ህዝቡና ህውሓት፣ ህዝቡና ኢህአዴግ ሆድና ጀርባ ሆነዋል፡፡ ይሄ በሆነበት ሁኔታ በዚህች ሀገር አንድ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ካልመጣ ሀገሪቱ ከቀውስ አትወጣም፡፡ ኢትዮጵያ በርዕዮተ አለም ቀውስ ውስጥ ነች የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሄ ቀውስ መፍትሄ የሚያገኘው ለህዝቡ ጥያቄ መጣኝ ምላሽ ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ግን የምናያቸው ግጭቶች ሊባባሱ ይችላሉ፣ ኢኮኖሚው ሊዳከም ይችላል፣ የግብፅም ሆነ የሌላ የውጭ ሃይሎች ተፅዕኖም እያየለብን ሊሄድ ይችላል፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ የመረጠው ስልጣኑን እንደምንም ብሎ ማስቀጠልን ብቻ ነው፡፡ ይህቺ ሃገር ምን እየፈለገች ነው የሚለውን እስካሁን ቆም ብሎ አልተመለከተም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም ይሄን የሃገሪቱን ችግር ቆም ብለው ለማየት የሚችሉም አይመስለኝም፡፡ አሁን በይፋ ያልታወጀ የፀጥታ እቅድ የሚል ሽፋን በተሰጠው የአስቸኳይ አዋጅ ስር ነው ያለነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያን ያህል ብዝኃነት ያለበት ሃገር ማስተዳደር ይቻላል ወይ? ይሄ ግልፅ ጥያቄ ነው፡፡
እርስዎ  ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄ የሚሉት ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ ህዝብ መተንፈስ አልቻለም ስንል እኮ፣ መተንፈስ መቻል አለበት እያልን ነው፡፡ ነፃነት በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ ፕሮፓጋንዳው አሠልቺ ሆኗል፤ አሁን ተግባር ይፈለጋል፡፡ ፍትህ መስፈን አለበት፡፡ አሁን ጉልበት ነው ያለው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር እኔ የሚታየኝ መፍትሄ፣ በሃገር ውስጥም በውጭም ያሉ የአገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሃይሎች፣ ሃሳባቸውን የሚገልፁበት ምህዳር መከፈት አለበት፡፡ እነዚህ አካላት በነፃነት ተገናኝተው፣ የሃገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ የሚተልሙበት እድል መፈጠር ይኖርበታል፡፡ በኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ አዲስ ነገር እንደማይመጣ ተረድቻለሁ፡፡

===========================

“የህወሓት ግምገማ የሁለት ቡድኖች ፍልሚያ ነው”

አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ

ከወር በላይ የቆየውን የህወሓት ስብሰባና ግምገማ ምን ያህል ተከታተሉት?
እኔ በአትኩሮት እየተከታተልኩት ነው፡፡ ግምገማው 6ኛ ሣምንቱን አስቆጥሯል፡፡ የህወሓት ማዕላዊ ኮሚቴ ብቻውን እንዲህ ያለ ግምገማ ማድረጉ፣ በዚህች ሃገር ውስጥ ለውጥ አያመጣም። እንደኔ አተያይ፣ ውጤቱም ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ ነው፡፡ ድርጅቱም ራሱ እንዳመነው፣ አብዛኛው አመራር ተበላሽቷል፡፡ በተለይ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ የቤተሠብ አይነት አመራር ነው፡፡ የቤተሠብ ስብስብ አመራር ደግሞ ወዴትም ሊቀየርና አዲስ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። ግምገማው እንዴት ስልጣናችንን ማስቀጠል እንችላለን ከሚል እንጂ ከህዝብ ጥያቄና ፍላጎት የመነጨ አይደለም፡፡
እርስዎ ከህወሓት ስብሰባ በዋናነት የተገነዘቡት ምንድን ነው?
ለ26 ዓመታት ሃገር እያስተዳደርን ቆይተናል እያሉ፣ መልሰው “እስከ ዛሬ ስትራቴጂካዊ አስተዳደር አልፈጠርንም፤ ህዝቡን በስትራቴጂካዊ አመራር አልመራነውም” ማለታቸው አስገራሚ የሆነብኝ ጉዳይ ነው፡፡ “የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ መለስ ለዚህች ሃገር ለ50 እና ከዚያ በላይ ለሚሆን ዓመት ስትራቴጂ ነድፎላታል” ሲሉን የነበሩ ሰዎች፤ “በስትራቴጂ ህዝቡ አልተመራም” ማለታቸው በራሱ የሚያስጠይቃቸው ነው፡፡ ላለፉት 26 አመታት በሃገሪቱ እዚህም እዚያም ያሉ ግጭቶች ያለመፈታታቸው መንስኤ ምንድን ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የህወሓት ስብሰባ ያመላከተው አንድም አቅጣጫ የለም፡፡ የተደረገው አባይ ወልዱን ወይም ሌላውን ከስልጣን ማውረድ ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በህወሓት ደንብ መሠረት፣ አባይ ወልዱን ማዕከላዊ ኮሚቴው ማገድ እንጂ ከስልጣን ማውረድ አይችልም፤ ይሄን ማድረግ የሚችለው ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡ ሊቀመንበር የሚመርጠውም የሚያወርደውም ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡
ከስብሰባው እርስዎ የጠበቁት ሌላ ውጤት ነበር?
ውጤት ባልጠብቅም ድርጅቱ መሠረታዊ ሥር ነቀል ለውጥ አመጣለሁ የሚል ከሆነ፣ መጀመሪያ አመራሩን በቀጥታ በህዝቡ ማስገምገም ነበረበት። አሁን የተደረገው ግን የሁለት ቡድኖች ፍልሚያ ነው፡፡ አንደኛው ቡድን ማለትም በአንጋፋዎቹ አዛውንቶች የሚመራው “መልካም አስተዳደር ያላሰፈኑ ይወገዱ” ሲል ሌላው በአቶ አባይ ወልዱ የሚመራው ቡድን ደግሞ “ዋና ችግራችን ሙስና ነው፤ ስለዚህ ሙስናን ከስሩ እንገርስስ” ነው ያለው፡፡ ይሄ ከሆነ ደግሞ አዛውንቶቹን ሊነካ ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስብሰባው የእነዚህ ሁለት ሃይሎች ፍልሚያ ነበር፡፡ የቂም በቀል መመላለሻ ነበር ማለት ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫም፤ “አመራራችን በመጠላለፍና በቂም በቀል የሚንቀሳቀስ ነው፤ብድር በመመላለስ ነው ጊዜያችንን ያሳለፍነው” ብሎ ነበር፡፡ ከሠሞኑ ያደረጉትም ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ ሲጠቃ የነበረው ቡድን ወደ አጥቂነት ነው የተሸጋገረው፡፡ በቃ ይሄው ነው ስብሰባውና የግምገማው ውጤት። ግምገማቸው “የአድዋ” ወይም “የአክሱም” ተወላጆች ወደሚል ደረጃ ሁሉ ነው የወረደው፡፡ ለውጥ እናመጣለን ብለው ወደ ጎጥ መውረዳቸው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ግምገማቸው አካባቢዊነት ይዞ የመጣ እንጂ ለትውልዱ ጥሩ ተሞክሮና ውርስ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ክልሎችን የሚመሩ ሌሎች ገዥ ፓርቲዎችም የህወሓትን አርአያ ተከትለው መሰል ግምገማ ለማድረግ መሞከራቸው አይቀሬ መሆኑ ነው። በዚህ መንገድ መከፋፈል ለእነሱም ለሃገርም አይጠቅምም፡፡
“ህወሓት በይፋ ከክልሉ ህዝብ እንደ ሌላው ክልል ጠንካራ ተቃውሞ አልቀረበበትም” የሚሉ ወገኖች፣ ለምን ይሄን ያህል ጊዜ የፈጀ ግምገማ ማካሄድ አስፈለገው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ፣ የትግራይ ህዝብ በስርአቱ የተበደለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መረዳት ያለበት፣ የክልሉ ህዝብ ጭቆና ውስጥ እንዳለ ነው፡፡ ህዝቡ በስርአቱ የሚራመደውን የዘረኝነት ሴራ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ለዚህ ነው ከእነሱ ጋር የማያብረው፡፡ በዝምታ እየቀጣቸው ነው ያለው። ተባባሪያቸው አይደለም፡፡ በዚያው ልክም ከፍተኛ ጫና ውስጥ ያለ ህዝብ ነው፡፡ በትግራይ ክልል እኮ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሚሊሻ አለ፡፡ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች እኮ እጅና እግራቸውን ተጠፍረው ነው ያሉት፡፡ አብዛኛው ሰው ልቡ ከእነሱ ጋር አይደለም፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ የትግራይ ህዝብ ብዙ ትግል እያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ህወሓት “የትግራይን ህዝብ ካጣሁ ቀፎው እንደተሰበረበት ንብ እሆናለሁ” ብሎ ስለሚያስብ ጠንካራ አፈና በማድረግና ህዝቡን በመከፋፈል ዕድሜውን ለማራዘም ጥረት እያደረገ ነው፡፡ አሁንም የግምገማው ዓላማ ይሄንኑ አገዛዝ አጠናክሮ ለማስቀጠል ነው፡፡
ህወሓት አሁን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለው አቅምና ተቀባይነት ምን ያህል ይመስልዎታል?
ደርግን አስወግደን የገባን ጊዜ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ ምሁሩን  መንካት ሲጀምር ነው ነገር የተበላሸው፤ ያኔ ነው ራሱን ማዳከም የጀመረው። በወቅቱ “ተው እኛ የበረሃ ታጋዮች ነን ስልጣን አያስፈልገንም፤ ምሁሩ ስልጣን ይረከብ” ተብሎ ነበር፤ ነገር ግን “ይሄ ሃሳባችሁ በህወሓት መቃብር ላይ ነው የሚፈፀመው” የሚል ምላሽ ነው የተሰጠን፡፡ በዚያው ኢህአፓ እንደ ጠላት ታየ፣ ምሁርም በጥርጣሬ አይን መታየት ጀመረ፡፡ ያኔ ነው ህወሓት ራሱን በዕውቀት ከማጠናከር ይልቅ ጉልበትን ብቻ የመረጠው፡፡ ህወሓት ለዚህ ህዝብ ጀግና የነበረው ከደርግ ጭቆና ነፃ ያወጣው ጊዜ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ፀረ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ነው የተላበሰው፡፡ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ደግሞ ይበልጥ ከህዝቡ እየተራራቁ መጥተው፣ አሁን ላይ እንደኔ እይታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተጠቃሽ ሚና የላቸውም፡፡ ሹመት የያዙ ቢኖሩም አሁን እንደ ድሮው ዝም የሚላቸው የለም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ነቅቷል፡፡ አሁን በጭንቀት ተውጠው ነው  ያሉት። የግምገማው መርዘም አንዱ  ምክኒያትም ይህ ጭንቀት ነው፡፡
በአጠቃላይ ህወሓትም ሆነ ሌሎች እህት ድርጅቶች የሚያደርጉት ግምገማ፣ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምን ያህል ፋይዳ አላቸው?
እነዚህ ሠዎች ቢናጡ፣ ቢናጡ የአስተሳሰብ ለውጥ እስካላመጡ ድረስ ውጤት አያመጡም፡፡ ሲጀመር ሃገሪቱን ያለ ስትራቴጂ ሲመሩ እንደነበር በራሳቸው አንደበት ተናግረዋል፡፡ ቁልፉ መሠረታዊ ለውጥ የአስተሳሰብ ነው እንጂ የግለሰቦች ለውጥ አይደለም፡፡ ህዝቡ እየጠየቀ ያለው ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ነፃነት--- ነው፡፡ እነሱ እያሉን ያለው አቶ እገሌን በእገሌ ተክተናል ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ከህዝቡ ጥያቄ ጋር ይሄ ሊስማማ የሚችለው፡፡

Read 6623 times