Saturday, 02 December 2017 08:18

የኦቦ ለማ መገርሳ ሱስ -- ኢትዮጵያዊነት!

Written by  ታምራት መርጊያ utdtaman@gmail.com
Rate this item
(12 votes)

  በቅርቡ ታሪካዊ ሊባል በሚችል ደረጃ ተካሒዶ በነበረው የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች የምክክር መድረክ ላይ፥ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦቦ ለማ መገርሣ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ ለየቅል የሆኑ አስተያየቶችና ምልከታዎች ሲንፀባረቁ ቆይተዋል፡፡ ታዲያ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይሰነዘሩ ከነበሩ ሐሳቦች ውስጥ አመዛኙ ከአዎንታዊ ትርጓሜና ግንዛቤ የመነጩ ነበር ማለት ቢቻልም፥ ከዚህ በተቃራኒ የርዕሰ መስተዳድሩን ንግግር በአሉታዊ መንገድ የተረጎሙና የተገነዘቡ ወገኖችም አልጠፉም፡፡
አዎንታዊ የነበሩትን ሐሳቦች ወደ ኋላ እናቆያቸውና፤ ከሰውየው ንግግር ጋር ተያይዘው በአሉታዊ መልኩ የተነሱትን ሐሳቦች አመክንዮአዊ መሰረት (logical ground) ስንመለከት፥ እንደ ሐሺሽ ያሉ ማሕበራዊ ነውሮች ተደርገው በሕብረተሰቡ የሚወሠዱ ነገሮችን ለመልካም እሴቶች ማነፃፀሪያነት ወይም መገለጫነት ማዋል ተገቢ አይደለም በሚል ነጋሪ እሴት (argument) አመክንዮ ዙሪያ ያጠነጠኑ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ከዚህ በተፃራሪ የቆሙ ወገኖች ደግሞ፤ ከሰውየው ንግግር ጀርባ የሚገኘውን የሰውየውን ጥልቅ የሆነ ሐገርን  የመውደድና የሐገር አንድነትን በፅኑ የመሻት ትልቅ ሐሳብ (Intention) ፥ እንዲሁም ቅን ልቦና (good faith) ላይ ማተኮር ተገቢ መሆኑን በመግለፅ፥ የቀዳሚዎቹ ወገኖች አመክንዮ በዚህ ረገድ ዉሃ የሚያነሣ መከራከሪያ እንደማይሆን ይገልፃሉ፡፡
ኦቦ ለማ መገርሳ በዚህ ንግግራቸው ላይ ኢትዮጵያዊነትን ሲገልፁ የተናገሩትን ቃል በቃል ስንመለከት፦
“ኢትዮጵያዊነት፤ ስሙ ባያምርም፤ ሞክሬው ባላውቅም፤ ሐሺሽ ነው፤ ሱስ ነው ኢትዮጵያዊነት። የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ልብ ቢቻልና ተከፍቶ ቢታይ፥ በያንዳንዳችን አዕምሮና ልብ ውስጥ ያለው ዛሬ ያየነው ነው”  ነበር ያሉት፡
እንግዲህ ከንግግራቸዉ በተረዳነው መሠረት፤ ሰውየው ምንም ዐይነት ሌላ ደባል ሱስ የለባቸውም፡፡ የእርሳቸው ሐሺሽን ያክል ሰቅዞ የሚይዝ ብቸኛ ሱስ፥ አንድና አንድ ነው፡፡ ይኸውም ኢ.ት.ዮ.ጵ.ያ.ዊ.ነ.ት!!!!  አራት ነጥብ፡፡
እዚህ ላይ የርዕሰ መስተዳድሩን ውስጣዊ ስሜት ፈንቅሎ፥ ያለ አንዳች ይሉኝታ እንዲህ በአደባባይ ያናገራቸዉ ኢትዮጵያዊነት፥ ከስያሜ ባለፈ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡
ይኸንን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳን ዘንድ በአንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር በተፃፈ መፅሐፍ ላይ ሰፍሮ ያገኘሁትና በአንድ ወቅት ወደ ማስታወሻ ደብተሬ ገልብጬው የነበረን የኢትዮጵያዊነት ማጣቀሻ ለአፍታ እንመልከት፡፡
ይኽ መፅሐፍ፥ ኢትዮጵያዊነት ከአምስት አምዶች የታነፀ መኖሪያ እልፍኝ ነው ይላል፡፡ አምስቱን አምዶች ሲዘረዝርም፦
ኢትዮጵያዊነት፡
1ኛ. ጥልቅና ሠፊ እውቀት
2ኛ. መዛል የሌለበት ትጋት
3ኛ. በትዕግስት የታሸ ጀግንነት
4ኛ. እርኩሰት የሌለበት ቅድስና
5ኛ. ግብዝነት የሌለበት ምስጢራዊ ህይወት
መሆኑን ያመለክታል፡፡
ታዲያ እነኝህን የመሳሰሉ ውብ የሰብዕና እሴቶች ስንመለከት፥ ኢትዮጵያዊነት ከሐሺሽ ከፍ ያለ ሱስ ቢሆንስ ምን ይገርማል?
አንደ እውነቱ ከሆነ ደግሞ፥ ሰዎች በንፁህ ልብና በእውነተኛ ስሜት ውስጥ ስንሆን ነገሮችን ስሜታዊነት (emotivity) በተላበሰ መልኩ መግለፃችን ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እናም በዚህ አግባብ ከተመለከትነው፥ ኦቦ ለማ የተናገሩት ከጥልቅ የኢትዮጵያዊነት ስሜትና ሐገርን የመውደድ አውድ እስከሆነ ድረስ ማነፃፀሪያቸው ከቶውንም በአሉታዊ መንገድ ሊተረጎም አይገባውም፡፡ ይልቁንም እንዲህ እንደ አርሳቸው የሐገርን ፍቅር በጥልቅ ስሜት የሚረዱ ሐገር ወዳድ መሪዎች እንዲበዙልን በጽኑ ብንመኝ የተሻለ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ሰውየው ከተናገሩት ንግግር ጀርባ ያለው ታላቅ ቁምነገር ለሁሉም የሚበጅ ነውና፡፡
በእርግጥ ሐገርን መውደድ በቃላት ብቻ የሚገለፅ ነገር እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም ኦቦ ለማን ጨምሮ ሁሉም ሀገር ወዳድና ኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ የገባው ዜጋ፣ በድርጊትም ጭምር ሐገር መውደዱን ሊያሳይ እንደሚገባ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ቢሆንም ለሐገር ያለንን ጥልቅ ፍቅር በቃላት ያውም በአደባባይ መግለፅ የሚመሰገን ተግባር መሆኑን መካድ አይችልም፡፡
በመጨረሻም፥ የዘመናችን  ቁጥር አንድ ከያኒ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “የሰለሞን እፅ ነሽ፤ የቅዱሳን እምባ...”  ብሎ የተቀኘላት፤ ከየሠሞነኛ  ቁርቁሶች በላይ የሆነች ኢትዮጵያ፤ በዘረኝነት ንግርትና በጠባብነት አባዜ መሰረቷ ሳይናወጥ ለዘመናት ፀንቶ የኖረ፥ በአምባገነኖች ጠንካራ መዳፍ ያልተደፈጠጠችና የማትደፈጠጥ፥  ዘለግ ባለው ታሪኳ ውስጥ በማያባራ የውዝግብና የጦርነት  ወጀብ መሐል ፀንታ ዘመናትን የተሻገረች፥  በዉድ ልጆቿ የመስዋዕትነት ተጋድሎ ሉአላዊነቷን ለባዕድ ወራሪዎች ሳታስደፍር የኖረች  ኢትዮጵያ!!  ሁሌም በክብር ትኑርልን፡፡ የሚወዷትን መሪዎች እንደ አሸን ያብዛላት!!
የከርሞ ሰው ይበለን አቦ!!

Read 6558 times