Sunday, 03 December 2017 00:00

ያየኸው ያለፈውን ወንዝ እንጂ የሚመጣውን አይደለም!

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ የወደፊት የአገዛዝ ዕጣ-ፈንታውን ለማወቅ ወደ አንድ አዋቂ ዘንድ ይሄዳል፡፡ አዋቂውም ተመራምሮና አስቦ፤
“አገዛዝህ እንዲቃና ሰው መሰዋት አለብህ፡፡ ይህ የምትሰዋው ሰው እጅግ ሀብታም ነጋዴ መሆን አለበት” አለው፡፡
ንጉሡ፤ “ከአገሩ ነጋዴዎች ሁሉ እጅግ የናጠጠ ሀብታም የሚባለውን አምጡልኝ” ብሎ አዘዘ፡፡
የታወቀው ሀብታም ግን በጣም ራቅ ወዳለ ዳር-አገር ሄዶ ኖሮ ሊገኝ አልቻለም፡፡
ውሎ አድሮ ግን ያ ነጋዴ ከሄደበት አገር እየተመለሰ ሳለ፣ ወንበዴዎች ያገኙትና እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ደብድበው፣ እጅ እግሩን ሰባብረው፣ ገንዘቡን ሁሉ ዘርፈው፣ ሜዳ ላይ ይጥሉታል፡፡
ሌሎች በዚያ መንገድ የሚመጡ ነጋዴዎች፣ ያ ታላቁ ነጋዴ፣ እንዳይሆን ሆኖ ወድቆ ያገኙትና አዝነው ተሸክመው ያመጡታል፡፡
ይሄንን ያወቁት የንጉሡ ባለሟሎች፤
“ንጉሥ ሆይ! የምንፈልገው ነጋዴ መጥቷል፡፡ ሆኖም በጣም ተጎድቶ ከሰውነት ውጪ ሆኗል፡፡ ምን እናድርግ?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
ንጉሡም፤
“ዋናው በህይወት መገኘቱ ነው፡፡ አምጡትና ወደ አዋቂው ይዤው እሄዳለሁ” ይላሉ፡፡
ነጋዴው ተይዞ መጣ፡፡ ወደ አዋቂውም ይዘውት ሄዱ፡፡ ለአዋቂውም፤
“መሰዋት ያለበት ነጋዴ መጥቷል” ሲሉ አሳወቁ፡፡
አዋቂው ነጋዴውን፤
“ተነስና እስከዛሬ የት እንደነበርክ አስረዳኝ” አለው
ነጋዴው ግን፤
“መቆም አልችልም፡፡ እግሬም፣ እጄም ተሰባብሯል” አለው::
አዋቂው ወደ ንጉሡ ዞረና፤
“ንጉሥ ሆይ! በጣም አዝናለሁ፡፡ አማልክቱ ከሰውነቱ ምንም ነገር የጎደለን ሰው በመስዋዕትነት አይቀበሉም! ይህ ማለት ዙፋንዎ አደጋ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ነጋዴም በሽፍቶች መደብደቡ ለበጎ ቢለው ነው! ከእንግዲህ የሚመጣውን መቀበል ብቻ ነው ያለብዎት!” ብሎ አሰናበታቸው፡፡
ዕጣ- ፈንታችን አስቀድሞ የተፃፈልን ነው፤ ቢባልም የየዕለት ክፉና ደግ ተግባራችን አጠቃላይ ጥርቅም ነው! ስለሆነም የየቀኗን ተግባራችንን ማታ በተመስጦ ካላሰብናት ክፉና ደጉን ለመለየት ይሳነናል፡፡ ምናልባትም በሰው ላይ ያደረግነው ሁሉ ተጠራቅሞ ምሬትን፣ ብሶትንና ሐዘንን ባንድነት እያቆርን ይሆናል፡፡ ያም በቀልን፣ አመፃንና አሰቃቂ ፍፃሜን እየወለደ ሊመጣ ይችላል። የቆምንበትን መሠረት ቀስ በቀስ እየሰነጣጠቀ እየናደ ህልውናችንን ከናካቴው ሊያሳጣንም ይችላል። አበው  የፖለቲካ ጠበብት፤ “ገዢው መግዛት ሲያቅተው፤ ተገዢው በቃኝ፣ አልገዛም ሲል፣ ህሊናዊና ነባራዊው ቅድመ፣ ሁኔታ ተሟልቶ ላዕላይ-መዋቅሩ (Super-structure) ይፈረካከሳል። ያኔ ዝግጁ የሆነ የተደራጀ ኃይል አካል ከሌለ አገር ወዳልተጠበቀ ውጥንቅጥ ውስጥ ትገባለች፡፡ ይህንን የሚያስተውል አርቆ አሳቢ ያስፈልጋል” ይሉናል፡፡ ይህንን ጉዳይ ማንም የነቃ ዜጋ ሊስተው አይገባም፡፡ የፓርቲ የፖለቲካ መሸርሸር እንደ ፀጉር መመለጥ ሁሉ፤ አይታወቀንም። ፀጉር ከግንባር ሲሳሳ፣ ያልተመለጠውን ፀጉር በማበጠሪያ ወደፊት በመላግ ፀጉር አለን ማለት የተለመደ ሂደት ነው፡፡ ነፋስ ሲመጣ ግን የተሸፋፈና ፀጉር መገላለጡ ግድ ይሆናል፡፡ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ነው፡፡ ሂደቱን መግታት እጅግ አዳጋች ነው! በየጊዜው ራሳችንን ሳንመረምር ቆይተን፣ ቁስሉ ካንሠር ደረጃ ከደረሰ በኋላ ልናድነው ብንሞክር የጭንቅ የምጥ ጉዞ ነው የሚሆንብን፡፡ በእርግጥ በፖለቲካ ህይወት አይቀሬ (inevitable) የሚባሉ ደረጃዎች አሉ። ያረጀው ይቀረፋል፡፡ አዲሱ ይተካል፡፡ ቀራፊውና ተተኪውም እንደዚያው በተራው የፋንታውን ይገኛል፡፡
“አንተም እሳት ነበርክ፣ እሳት አዘዘብህ
እንደገና ዳቦ፣ እሳት ነደደብህ”
የሚለው የአገራችን ባለቅኔ ይሄንኑ አጥልሎ ሲገልፅ ነው፡፡ ያረጁት ያፈጁት ፖለቲከኞች ይወገዳሉ፡፡ እነ ሌኒን፤ “The party purges itself” ይሉ ነበረ፡፡ ፓርቲው ራሱን ይቀጣል፤ የራሱን ሰዎች ያስወግዳል እንደማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲ ባለበትና ራሱን በገመገመ ቁጥር የሚከሰት ነው፡፡ አጥርቶ ላየው ነባሩ እየሳሳ፣ አዲሱ እየወፈረ መምጣቱ ይገነዘባል፡፡
“ነገሩ አልሆን ብሎ፤ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር”
ያለው በረከተ-መርገም ዛሬም ያስኬዳል፡፡ ወደድንም ጠላንም ከሮበርት ፍሮስት ጋር “The road less travelled”ን መዘመር አለብን፡፡ ያልተሄደው መንገድ፣ እግር ብዙ ያልረገጠው መንገድ የቱ ነው? መባባል አለብን፡፡ የሲቪል ተቋማትን ማስፋፋት አለብን፡፡ ያልተሳተፉ አካላትንና ግለሰቦችን ከፖለቲካው ማዕድ ይቋደሱ ዘንድ በራችንን መክፈት አለብን፡፡ የ “እኔ ብቻ” ፖለቲካ ወንዝ እንደማያሻግር መገንዘብ አለብን፡፡ ብልጣብልጥነት ሁልጊዜ እንደማያበላ ቆም ብለን ማሰብ አለብን፡፡
“የማትረባ ፍየል፣ ዘጠኝ ትወልዳለች
ልጆቿም ያልቃሉ፣ እሷም ትሞታለች” የሚባለውን የጥንት የአብዮታዊ እርምጃ መግቢያ ከመዝገበ-ቃላታችን ለማውጣት መታገል አለብን፡፡ ራሳችንን ጨርሰን ከመብላት ተደጋጋሚ የታሪክ ህፀፅ ለመዳን ሆደ-ሰፊ መሆን፣ መካርን እህ ብለን ማዳመጥ፣ ተሳስቼ ይሆን?  ብለን ራስን መጠየቅ፤ ብልህነት ነው፡፡ ደጋግመን ራሳችንን እንይ! ራሳችንን ሳንፈራ እንውቀስ! ህዝብ እስኪነሳብን ድረስ አንደባበቅ! ጨዋታው ካበቃ በኋላ አየር ጠባይ አልተሰማማንም፣ ዳኛው በድሎን ነው፣ በቂ ልምምድ አላደረግንም ወዘተ ብንል የሚተርፈን “ቢሆን ኖሮ” ማለት ብቻ ነው! ከዚህ ይሰውረን። ዛሬ ላይ ቆመን ትላንት ያለፈውን ታሪክ እንጂ ነገ የሚከሰተውን ታሪክ እናውቅም፡፡ ትላንት ያየናቸውን ሰዎች እንጂ ነገ የሚመጡትን ወዳጆችም ሆኑ ጠላቶች አናውቅም፡፡ በጥሞናና በአደብ ነገን ለማውጠንጠን ዕድል አለን፡፡ ያ ደግሞ የብዙዎች  አዕምሮ ጥርቅም እንጂ የጥቂቶች ግምት፤ የጥቂቶች ጥንቆላ፣ የጥቂቶች አስገዳጅ እርምጃ ውጤት አይደለም፡፡ “ያየኸው ያለፈውን ወንዝ እንጂ የሚመጣውን አይደለም” የሚለውን ተረት ልብ ማለት ያለብን ለዚህ ነው!    

Read 6599 times