Saturday, 25 November 2017 10:30

‹‹… በወር አበባ መቋረጥ ወቅት ባል ለሚስቱ …››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

ባለፈው እትም ለንባብ ያልነው የሴቶች የወር አበባ መቋረጥ ምክንያትና የሚያስከትለውን የባህርይና የጤና ችግር ቀጣይ ጽሁፍ በዚህ እትም እነሆ ለንባብ ብለናል። በዚህ ርእሰ ጉዳይ አብረውን የሚቆዩት ዶ/ር ማለደ ቢራራ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና የየጽንስና ማህጸን ሕክምና ክፍል ምክትል ኃላፊ ናቸው።
ባለፈው እትም እንደተገለጸው Menopause ማለት በቋሚነት የወር አበባ መቋረጥን የሚያመ ለክት ስያሜ ሲሆን ይህ ወቅት በአማርኛው ማረጥ ይባላል፡፡ ሴቶች በዚህ የእድሜ ክልል ሲገቡ ልጅ ማርገዝ መውለድ የሚባለው ተስፋም አብሮ ይቋረጣል፡፡ የወር አበባ ከመቋረጡ በፊት ሂደቱን ምናልባትም ከ10/አመት ባላነሰ ጊዜ ይጀምራል፡፡ ይህም የሚሆነው ማህጸን ቀስ በቀስ እንቁላል ማምረቱን እያቆመ ሲሄድ እና ሆርሞኖችም መፈጠራቸው እየቀነሰ በመሄድ ላይ ስለሚሆን ነው፡፡ ወደ Menopause ወይም የወር አበባው ወደ መቋረጥ አካባቢ ሲደርስ በትክክለኛ ጊዜው መምጣቱን እያወዛገበ ጊዜውን መጠበቁን እየተወ ስለሚመጣ ይህ ምልክቱ ሊሆን ይችላል፡፡
ሴቶች ሲወለዱ በቁጥር የተወሰኑና በሁዋላም ወደ እንቁላልነት የሚለወጡ ትናንሽ የተፈጥሮ አካሎችን Follicles ይዘው ነው፡፡ እነዚህ እንቁላሎች ከሚፈጠሩበት ቦታ በእርግዝና ምክንያት ወደ ማህጸን እንዲሄዱ የሚያደርጉዋቸው የተለያዩ ሆርሞኖች አሉ፡፡ ሴቶች እድሜያቸው ሲጨ ምርና ለመውለድ ሲደርሱ የወር አበባ በየወሩ ያያሉ፡፡ በዚህም ሂደት የእንቁላሎቹ ቁጥርም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ የወር አበባ ወደመቋረጡ እድሜ ሲደርስ ሆርሞኖቹም በነበሩበት ሁኔታ ስለማይቀጥሉ  ቀስ በቀስ ሴቶች ቀድሞ ከነበሩበት የአካልና ስነልቡና ሁኔታ ለውጥን ያያሉ፡፡ በዚህም ሂደት ኢስትሮጂን የተባለው ሆርሞን በጣም ስለሚቀንስ የወር አበባ መኖሩም እያከተመ ይሄዳል፡፡ በዚህም ጊዜ የሚከሰቱት የጤና እና የስነባህርይ ችግሮች ጎልተው ይሰማሉ፡፡
ዶ/ር ማለደ ቢራራ እንደገለጹት በሴቶች የዘር ፍሬ የሚመረተውን የወር አበባ እንዲመጣ የሚያደርጉት ኢስትሮጂንና ፕሮጀስትሮን የተባሉት ሆርሞኖች መመረት ሲያቆሙ ሴቶች እድሜ ልካቸውን በጭንቅላት እንዲሁም በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸው ውስጥ ሆርሞኖቹ ያላቸው ተጽእኖ በማይኖርበት ጊዜ የተለያዩ ስሜቶች ይፈጠራሉ ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሆርሞኖች በዝቅተኛ መጠን በመስጠት ስሜቶቹ እንዲቀንሱ ማድረግ ይቻላል፡፡ በእርግጥ ስሜቶቹ እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ ውስጥ ህክምናም ባይደረግ በራሳቸው ጊዜ ሊጠፉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ስሜቶቹ ዘላቂ ሊሆኑ ስለሚችሉ የሆርሞን ሕክምናው ሊሰጥ ይችላል፡፡
ከሕክምናውም በተጨማሪ ይህንን የሴቶች የወር አበባ መቋረጥ ወቅት ቤተሰብ በተለይም ባልተቤቶቻቸው ሊረዱላቸው ይገባል፡፡ ወንዶች ለሴቶች ሊያደርጉ የሚገባቸው እገዛ ተከታዩን ይመስላል፡፡
ላብ ማልብ፡-
ሴቶች በወር አበባ መቋረጥ እድሜ ወቅት የሚሄድ የሚመጣ አይነት የሙቀት እና የላብ ማላብ ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ ይህም ያልተለመደ ሁኔታ በመሆኑ ደስታ ከሴቶቹ ሊርቅ ይችላል፡፡ መበሳጨት እና ማዘን ሊታይባቸው ይችላል፡፡ ተስፋ መቁረጥ ስለሚታይባቸው ለባለቤቶቻቸው ቅን ምላሽ ላይሰጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ወንዶች በሚስቶቻቸው ባህርይ ላይ እንደዚህ አይነት  ምልክት ሲያዩ ከእስዋ ቁጥጥር ውጭ መሆኑን ሊገነዘቡና በትእግስት ሁኔታዎችን ሊከታተሉ የስዋንም ሁኔታ ሊረዱ ይገባል፡፡
በመኝታ ወቅት፡-
በእንቅልፍ ጊዜ ሴትየዋ የተኛችበት ትራስና አንሶላ እስኪረጥብ ድረስ ሙቀትና ላብ ሊኖራት ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜም ሴትየዋ ባልተጠበቀ ሁኔታ በድንገት ከእንቅልፍዋ ልትባንንና ከተኛችበት ልትነሳ ትችላለች፡፡ ምናልባትም የመኝታ ቤቱ መስኮት ክፍት እንዲሆንላት ትፈልግ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ባልየው ከእንቅልፉ በድንገት እንዲነሳ በመደረጉ ምክንያት ከመበሳጨት ይልቅ ሚስ ትየው ወደሚመቻት ቦታ እንድትተኛ እንዲሁም ስስ ፒጃማ እንድትለብስ ወይንም ውሀ ካስፈለ ጋት በመስጠት በመተባበር ሊያስተናግዳት ይገባል፡፡
የወሲብ ግንኙነት፡-
አንዲት ሴት Menopause ወይንም የወር አበባ መቋረጥ ሲገጥማት የወሲብ ተነሳሽነት ላይ ኖራት ይችላል፡፡ ፈሳሽ ወይንም እርጥበት ላይኖራትም ይችላል። ባጠቃላይም ወሲብ ለመፈጸም ደስተኛ ላትሆን ትችላለች፡፡ በዚህ ጊዜ ከባልየው የሚጠበቀው ነገር ሴትዋ ለወሲብ ዝግጁ እስክ ትሆን ድረስ ትእግስት ማድረግ ነው፡፡  ሴትየዋ እንደዚህ ያለው የአካል ለውጥ ሲገጥማት በራስ የመተማመን ብቃቷን ሊቀንሰው ስለሚችል ባልየው ለእስዋ የነበረውን ፍቅር እና ቅርበት ሳይቀንስ ሊያስተናግዳት ይገባል፡፡
የማስታወስ ችሎታ፡-
የሆርሞን መዛባት አንዳንድ ጊዜ ትኩረትንና የማስታወስ ችሎታን ሊቀንስ ይችላል፡፡ ስለዚህም ባልየው በሚስቱ ላይ እንደዚህ ያለ ችግር ሲያይ ትእግስተኛ በመሆን ሊረዳት ይገባል፡፡
የጡት ሕመም፡-
ሴቶች የወር አበባ መቋረጥ  እድሜ ላይ ሲደርሱ የኢስትሮጂን መጠን መለዋወጥ ስለሚከሰት አንዳንዶቹ ላይ የጡት ሕመም ወይንም ሲነካ የቁስለት ስሜት ሊኖራቸው ችላል፡፡ ይህ ሕመም ከሌሎቹ ማለትም ላብ ማላብ ወይንም ትኩሳት ከመሳሰሉት ጋር ሲገጣጠም የበለጠ ችግር እንዲሰማት ያደርጋታል፡፡ ስለዚህም ባልተቤትዋ ይህን የጡት ሕመም እሚያስታግስላትን ዘዴ መቀየስ ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌም በረዶ የያዘ ከረጢት ማዘጋጀት፣ ወደሐኪም ዘንድ እንድትቀርብ ማድረግ የመሳሰሉትን መሞከር ይጠበቅበታል፡፡
የሰውነት ጠረን፡-
አንዲት ሴት የወር አበባ መቋረጥ እድሜ ላይ ስትደርስ በሚፈጠረው የሆርሞን መዛባት ምክንያት ከሚደርሱ ችግሮች አንዱ የጠረን ለውጥ ነው፡፡ ምናልባት ባልየው የሰውነት ጠረን የማይመቸው ቢሆን እንኩዋን የሚስቱን ሁኔታ ግን መረዳት ይጠበቅበታል። ስለዚህ ለሚስቱ የተሳሳተ አመለካከት ወይንም ልክ ያልሆነ ንግግር በማድረግ ቀረቤታን ማራቅ አይገባውም፡፡ ይህ ችግር ከሴትየዋ አቅምና ቁጥጥር ውጪ መሆኑን በመረዳት በምን መንገድ ጠረንዋን ልታስተካክል እንደምትችል ማማከርና ከአጠገብዋ መሆን ይገባዋል፡፡
ባጠቃላይም አንድ ወንድና ሴት ተጋብተው ልጅ ወልደውም ይሁን ሳይወልዱ አመታትን አብረው በደስታ ከኖሩ በሁዋላ በእድሜ ምክንያት የሚከሰት ለውጥን በአገራችን አባባል አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ እንደሚባለው መቀበልና አንዳቸው የአንዳቸውን ሁኔታ መረዳት ይገባቸዋል፡፡   
ዶ/ር ማለደ ቢራራ እንዳሉት ወንዶችም የሜኖፖዝ ወቅት ነገር ግን Andropause የሚባል ጊዜ አላቸው። ይህም በእድሜ ምክንያት ቴስቴስትሮን የተባለው ሆርሞን መመረቱን ስለሚቀንስ ወይንም ስለሚያቋርጥ የሚከሰት ነው፡፡ በእርግጥ ከሴቶቹ ጋር ልዩነቱ  በዚህ እድሜ ይከሰታል የሚባል የተወሰነ የእድሜ ገደብ የሌለው መሆኑ ነው፡፡
ቴስቴስትሮን የተባለው እጢ ወንዶች ለታዳጊነት እድሜ ሳይደርሱ መጠኑ ዝቅተኛ ሲሆን ወሲብ ለመፈጸም እድሜያቸው ሲደርስ ግን መጠኑ ይጨምራል። ቴስቴስትሮን ወንዶች በታዳ ጊነትና በወጣትነት እድሜያቸው የጡንቻ እድገትና ጥንካሬን፣ በሰውነት ላይ ጸጉር እንዲኖር፣ ድምጽ እንዲጎረንን የመሳሰሉትን ለውጥ የሚያመጣ ነው፡፡ ነገር ግን እድሜያቸው 30/ አመት ሲደርስ በየአመቱ 1% እየቀነሰ ይሄዳል፡፡እድሜያቸው 80/ አመት ሲደርስ ግን በጠቅላላው ከነበ ራቸው ውስጥ 20% ይቀራቸዋል፡፡ አቀናነሱ ግን በአንዳንድ የጤና ጉድለት ምክንያት ፈጠን ያለ ሊሆንም ይችላል፡፡
ባጠቃላይም ወንዶች ወደ Andropause ሲገቡ የአካልና የስነልቡና እንዲሁም የወሲብ ድርጊት ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የአቅም ማነስ፣ ድብርትና ብስጭት፣ በራስ የመተማ መን ብቃት አለመኖር፣ ትኩረት ማጣት፣ የእንቅልፍ ችግር፣ የክብደት መጨመር፣ የአጥንት መሳሳት የመሳሰሉት ይገጥሙዋቸዋል፡፡

Read 3908 times