Sunday, 26 November 2017 00:00

17ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬና ነገ በከፍተኛ ድምቀት ይካሄዳል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)


          • ከ24 የተለያዩ አገራት ተሳታፊዎች ይኖራሉ፡፡
          • ቪቪያን ቼሮይት እና ሎረንህ ኪፕላጋት ከክብር እንግዶቹ ይገኙበታል፡፡
          • በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሙዚቃና ስፖርት መተሳሰራቸው ያስደስታል፡፡ ጃማይካዊው የሬጌ ሙዚቀኛ ሉችያኖ

   17ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶችና የስፖርት አካዳሚ  3500 ህፃናት በሚሳተፉበት ሩጫ  የተጀመረ ሲሆን በነገው እለት ደግሞ የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫው  ከ44ሺ በላይ ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በድምቀት ይካሄዳል፡፡ በትናንትናው እለት በሒልተን ሆቴል በተሰጠው መግለጫ ላይ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድር ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደተናገረው ዘንድሮ በውድድሩ ላይ ከ24 የተለያዩ አገራት ተሳታፊዎች  የመጡ ሲሆን፤ እውቋ የኬንያ አትሌት ቪቪያን ቼሮይት፤ እንዲሁም በዜግነት ሆላንዳዊ እና በትውልድ ኬንያዊት የሆነችው ሎረንት ኪፕላጋት የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫውን በክብር እንግድነት የሚያደምቁት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ባለስልጣን በመግለጫው ላይ ባሰሙት ንግግር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር የምንሰራው በዋናነት ውድድሩ ትውልድን እንዲያነሳሳ ስለምንፈልግ ነው። በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ ግዝፈትና ድምቀት ያለው የጎዳና ላይ ሩጫው “ላንድ ኦፍ ኦርጅንስ” በሚል  አገር ለማስተዋወቅ ዘመቻ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡  የቶታል ኢትዮጵያ ሃላፊ በበኩላቸው ታላቁ ሩጫ ከውድድርም በላይ ብዙዎችን የሚያሳትፍ ፌስቲቫል  መሆኑ እንደሚያደንቃቸው ተናግረው ተሳታፊዎችም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች መምጣታቸው አብረን የምንሰራበትን ሁኔታ የሚያጠናክር ነው፡፡ ወደፊት በኢትዮጵያ ስፖርት ለመስራት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያበረታታ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በቅርብ አጋርነት ለመስራት ያለውን ስምምነት ማደሱን የተገለፀ ሲሆን ከ3 ሳምንታት በኋላ በ5 የክልል ከተሞች ማለትም፡- በአዋሳ፣ በመቐሌ፣ በባህርዳር፣ በአዳማና በአዲስ አበባ የሚደረጉትን ውድድሮች በስፖንሰር ለማድረግ እንደሆነ ታውቋል፡፡  
ይህ በእንዲህ እንዳለ በየዓመቱ አዳዲስ ነገሮችን በማካተት መገዘፉን የቀጠለው ውድድሩ  ዘንድሮ  ኤችአይኤም ኢንተርናሽናል እና ቢግ በዝ ጋር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በፈጠረው ትብብር በተዘጋጀው የመጀመርያው ‹‹ግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት›› በድምቀት የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡  ከ10ሺ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚኖረው ኮንሰርት ላይ ከባህር ማዶ ታዋቂ የሬጌ ሙዚቀኞች ለመሳተፍ ከጃማይካ መጥተዋል። እነሱም ለ6ኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው  ሉችያኖ   እንዲሁም ካሉ ፒ፤ ቲዋይኔ  እና ታሻ ቲ ናቸው፡፡ ትናንት በሂልተን ሆቴል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባዘጋጀው መግለጫ ላይ ሉችያኖ በታላቁ ሩጫ  በኢትዮጵያ ላይ ሙዚቃና ስፖርት መተሳሰራቸው የሚያደስት መሆኑን ገልፆ የውድድሩ አካል የሆነ ኮንሰርት በመዘጋጀቱ የሚደነቅ ነው ብሏል፡፡ በኮንሰርቱ ላይ  ከአገር ውስጥ የሚሳተፉት እውቆቹ ድምፃያን ንዋይ ደበበ፤ ማዲንጎ አፈወርቅ፤ ሚካኤል በላይነህ፤ ራስ ጃኒ ፤ መሃሪ ብራዘርስ ባንድ እና  ኮሜዲያን ቶማስ ጋር ነው፡፡
በዋናው  የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ላይ ከ500 በላይ ፕሮፌሽናል አትሌቶች   ተሳታፊ እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች በነፍስ ወከፍ የ100ሺ ብር ሽልማት እንደተዘጋጀ እና በአጠቃላይ ለሽልማት የቀረበው ገንዘብ ከ300ሺ ብር በላይ መሆኑን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡ የሽልማት መጠን ማስተካከያው የተደረገው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለብዙ ጀማሪ አትሌቶች የወደፊት ዓለማቀፋዊ ተሳትፎ ፈር ቀዳጅ መድረክ መሆን አንዱ አላማው እንደመሆኑ አትሌቶችን ለማበረታታት ታስቦ የተደረገ ነው። በሌላ በኩል ዘንድሮ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተሳታፊዎች ውድድሩን ለመሳተፍ ከሚለብሱት የሩጫ ቲ-ሸርት በተጨማሪ የመሮጫ ቁጥር በደረት ላይ ማድረግ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ መሆኑንም አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡

Read 1179 times