Saturday, 25 November 2017 10:26

የዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ አስተያየቶች…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 ኢትዮጵያን በቅርጫት ኳስ ዓለም ካርታ ላይ አሰፍራታለሁ በሚል ቃል ነበር የቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት  ከዚያም በኋላ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡ አሁን ደግሞ ለ6 ዓመታት ወደ አገለገሉበት እግር ኳስ ፌደሬሽን በፕሬዚዳንትነት ምረጫ በመወዳደር ለመመለስ ፈልገዋል፡፡ የቅርጫት  ኳሱን ራእይ ለማን ተዉት?
 በእኛ አገር የስፖርቱ አስተዳደር የሚሰራበት መዋቅር በክልሎች ውክልና ላይ እንደሚወሰን ይታወቃል፡፡ እግር ኳሱን በትክክለኛ መምራት እንደምችል አምኖ ለወከለኝ ክልል ታማኝ ነኝ፡፡ የደቡብ ክልል  ከቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን ለቀህ ወደ እግር ኳስ ተመለስ ሲለኝ በተሰጠኝ ኃላፊነትና አቅጣጫ በሚመራኝ መንገድ ነው የምሄደው፡፡  ይህን ወደፊትም የማደርገው ነው፡፡ እግር ኳሱ አሁን ያለበት ደረጃ አሳፋሪ ነው፡፡አገራችን ካለችበት እድገት አኳያ ለህዝባችን ለመንግስትም የማይመጥን ነው፡፡ ስለዚህ የደቡብ ክልል አንተ ወደ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ብትገባ ይህን መጥፎ ታሪክ ትለውጣለህ፤ ለአመራርነቱ በተሟላ ብቃት ትመጥናለህ ብሏል፡፡ እኔም በዚህ ሁኔታ ስላማምንብት ነው፡፡
የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሆኜ በመራሁበት ወቅት ከነበርንበት 143ኛ ደረጃ ወደ 86ኛ አድርሼው ነበር። የመካከለኛውና የምስራቅ አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ላይ 3 ዋንጫዎችን አሸንፊያለሁ፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ከክቡር አቶ ይድነቃቸው ቀጥሎ የመካከለኛውና የምስራቅ አፍሪካ የእግር ኳስ ምክር ቤትን (CECAFA) ሴካፋን በፕሬዝዳንትነት ለማገልገል ችያለሁ፡፡ አሁንም የስፖርት መሪ ነኝ፡፡ በስፖርት አመራርነት ብዙ ብዙ ልምድ አካብቼያለሁ፡፡  በፖለቲካውም  ጥሩ ልምድ አለኝ፡፡ በአገር አቀፍ  ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ፖለቲካውን መምራት ችያለሁ፡፡ በአውሮፓ፤ በተባበሩት መንግስታት ግዙፍ መድረኮችን ተሳትፊያለሁ፡፡ በተጨማሪ ጥሩ ዲፕሎማትም ነኝ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ፕብሊክ ዲፕሎማሲን ዛሬም በሚሆን የምሰራ እና የማስተባብር ነኝ፡፡
በተለይ ደግሞ ወደ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከመጣሁ በኋላ በስፖርት አመራሩ በአጭር ጊዜ የተገነዘብካቸው ወሳኝ ተመክሮዎች አሉ ሁላችንም እንደምናውቀው ከዚህ በፊት የነበረው አመራር የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውነው የስልጣን ዘመኑ ሊያበቃ 3 እና 4 ወራት ሲቀሩ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንት ከሆንኩ በኋላ ገና ከጅምሩ በመውረድ ክልሎች ወርዶ በረጅም ጊዜ እቅድ መስራትን የማምንበት ስለሆነ እየተገበርኩት ነው፡፡ ለምሳሌም ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈውን የተጨዋቾች ስብስብ መጥቀስ ይቻላልእኔና አቶ መላኩ ጴጥሮስ በሰራነው ፕሮጀክት የተገኘ ውጤት ነው። እነደጉ፤ ሳላሃዲን ከዚያ ፕሮጀክት መገኘታቸው ይታወቃል። ወደ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከመጣሁ በኋላ በየክልሉ እየዞርኩ የሁሉንም ስፖርቶች አመራር፤ አስተዳደርና ባለድርሻ አካላት በመገናኘት ተመካክሬያለሁ፡፡ ሀቁን ለመናገር የአማራ ክልል ተወካይ በስፖርቱ ክልሉ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ከእኔ የተሻለ ግንዛቤ አይኖረውም፡፡ በየትኛውም ክልል ሄጄ የሰራሁት ነው፡፡ ከፈረስ ቤት እስከ ደጋ ዳሞትእስከ አገረሰላም፤ ከማይጨው እስከ ጋምቤላ፤ እስከ ቤኒሻንጉል ዞሬ ነው የምሰራው፡፡
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ታች ወርደህ ከስር መሰረቱ መገንባት አስፋላጊ ነው፡፡ አለበለዚያ ስፖርቱን ልትቀይረው አትችልም፡፡ አሁን ባለንብት ደረጃ የነበሩ አመራሮች አዲስ አበባ ቁጭ ብለው እዚህ ያለውን ውድድር ዳኝነት ለማስተዳደር ነው ግዚያቸውን የሚያቃጥሉት፡፡ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት። በአጠቃላይ የእግር ኳሱን እድገት ማምጣት አለብህ ብሎ የደቡብ ክልል የሰጠኝን ኃላፊነት ማሳካት የምችልበት የተሟላ ብቃት፤ የስራ ልምድ እና እውቀት ስላለኝ ነው ፡፡
የኦሎምፒክ ኮሚቴን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ሃላፊነት ደርበው በመስራት አይቸገሩም ወይ? ሁለቱም ትልልቅ የስፖርት ተቋማት ሰፊ የስራ ድርሻዎች አሏቸው፡፡ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ በአመራር ደረጃ ብዙ ስራዎች ያስፈልጉታል፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ደግሞ በስሩ ያሉ የስፖርት ፌደሬሽኖችን በሙሉ በብቃት ማስተዳደር አለበት፡፡
በእኔ እምነት ሁለቱንም መስራት ይቻላል፡፡ ምንም አይነት የስራ መደራረብ ሊፈጥር አይችልም፡፡ በኦሎምፒክ ኮሚቴ በየክልሉ ተዘዋውረን በቀሰምነው ተመክሮ ብዙ ስራዎች በእግር ኳሱና በአትሌቲክሱ እንደሚያስፈልጉ ተገንዝበናል፡፡ ይህን በጥልቀት ገብቶ ለመስራት ያለው ህግ ሊፈትን ይችላል የእኔ እምነት በሁለቱም የስራ ድርጅቶች ያሉትን ኃላፊነቶች አዋህዶ ከተሰራ ስርነቀል ለውጥ መፍጠር ይቻላል ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል የስፖርት መሰረተልማቶች በተለይ ስታድዬሞች ተስፋፍተዋል፡፡ ይህን ክልሎች ከአካዳሚ እና ከፕሮጀክት እንቅስቃሴዎች ጋር አጣጥመው እንዲሰሩበት ተወያይተን ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ የፖለቲካ መሪዎች፤ የስፖርት መሪዎች ለስፖርተኞቹ እንደወላጅ ቤተሰብ ማሰብ እንዳለባቸው ነግረናቸዋል፡፡ ታዳጊዎችን ከስር መሰረቱ ኮትኩተው አሳድገው፤ መሰረታዊ ስልጠና ሰጥተው፤ ሙሉ ጤንነታቸውን ተንከባክበው፤ በትምህርታቸው እንዲጠነክሩ ድጋፍ አድርገው ጥሩ ደረጃ ለማድረስ መትጋት አለባቸው ለኢትዮጵያ ምን አበቃው በማለት እንዲሰሩ ነው፡፡ ስለዚህም የኦሎምፒኩንም የእግር ኳሱንም አመራርነት ጠቅልለን ብንይዘው በስፖርቱ የምንፈልገውን እድገት የምናሳካበትን አቅጣጫ የበለጠ ያሳልጠዋል እንጅ ምንም ተፅእኖ የሚፈጥር አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው የፌደሬሽኑ 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ፤ ከዚያም ከሳምንት በኋላ በተካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በስብሰባ አዳራሽ በአባላቱ መካከል የውዝግብ መንፈስ ገንኖ ወጥቷል፡፡ እርስዎ ለ 6 ዓመታት ባገለገሉበት የእግር ኳስ ፌደሬሽን ብዙ ጉባዔዎችን የመምራት እድል ነበርዎት፡፡ የጠቅላላ ጉባዔ አባላቱን በሆነ ባልሆነ የሚያወዛግበው ምንድነው? ንትርኩ ለስፖርቱ እንስራ ከሚል ቁጭት፤ በፌደሬሽኑ አስተዳደር ካለመርካት፤ ከተለያዩ የህግና ደንብ ክፍተቶች ነው? አወዛጋቢ አጀንዳዎችን የሚያነሱት ዶክተሩና ደጋፊዎቻቸው ናቸው የሚል ማጉረምረምም አለ፡፡
እግር ኳሱ ላይ ውዝግብ መብዛቱን በቅንነት ካሰብነው ከቁጭት የተፈጠረ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ባሻገር ግን በጉባዔው መካከል አንዳንድ አባላት በውድድር ካለማመናቸው በመነጨ የሚፈጠሩ ስሜቶች ነፀብራቅ ነው፡፡ እከሌን አስወጥቼ እከሌን አወዛግቤ  ወደምርጫ ልግባ በሚል አስተሳሰብ የሚመሩት ናቸው፡፡ ተፎካካሪን በውድድር አላሸንፍም በሚሉ የተለያዩ ስሜቶች የሚሸበሩ ናቸው፡፡ ይህ ለእኔ ሳይወዳደሩ መሸነፍ ነው፡፡ በራስህ የምትተማመን ከሆነ ለመወዳደር መግባት አለብህ፡፡ ምርጫው ለሁሉም እኩል እድል እንደሚሰጥ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በትምህርት ዝግጅት፤ በአመራር ብቃት፤ በልምድና ጠቃሚ ተመክሮ የተሻለ ተወዳዳሪ በምርጫ ለመወዳደር ሲገባ ምንም የሚያስጨንቀው ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ይህ አይነት አስተሳሰብ ባለመኖሩ ነው በጉባዔው አባላት ውዝግብና መከፋፈል የበዛው፡፡
በአስረኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ምርጫው መካሄድ ነበረበት፡፡ ፊፋም ምርጫው ይካሄድ ብሎ ነበር። የተሻሻለው ደንብ ሳይፀድቅ ምርጫ መካሄድ የለበትም… የምርጫ አስፈፃሚ ለቅድመ ምርጫው ሂደት ሊመሰረት ይገባል በሚሉ አስተያየቶች የጉባዔው አባላት ውዥንብር ውስጥ እንዲገቡ በመፈለጉ ነው፡፡ ጉባዔው ካሳወቃቸው አጀንዳዎች ውጭ የሚፈጠሩ አጀንዳዎች ናቸው አላስፈላጊ ውዝግቦችን የሚፈጥሩት፡፡
ሌላው ስህተት የተፈፀመው ደግሞ ጉባኤውን በሚመራበት ሂደት ነው በየትኛውም ዓለም በሚተገበር አሰራር ለምርጫ የሚወዳደር ሰው ጉባኤ መምራት እንደሌለበት የሚታወቅ ነው፡፡ አቶ ጁነዲን ባሻ እና የስራ አስፈፃሚ አባላቱ ጉባኤውን የሚመሩበት አጀንዳ የላቸውም፡፡ በተለይ ደግሞ የጉባዔው አጀንዳ ደግሞ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ሲሆን ማለቴ ነው፡፡ ፐሬዝዳንቱ ጉባዔው በምርጫ አጀንዳው ላይ ሲወያይ እኔ ተወዳዳሪ ነኝ ስብሰባውን በምርጫ የማይወዳደር ገለልተኛ አካል ይምራው በሚል አለመፍቀዳቸው ነው፡፡ ምናልባትም ይህ እምቢተኛነት በተንኮል ላይሆን ይችላል፡፡ አሰራርን ካለማወቅና ልምድ ከማጣት ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ትክክለኛ የምርጫ ሂደት በሚከተለው የፓርላማ አሰራር መገንዘብ ይቻላል፡፡  በአፍሪካ ፓርላማ ደረጃ ምርጫ ሲካሄድ ለምርጫ አስፈጻሚነት የሚገቡ ተወዳዳሪዎች የአህጉሪቱን የተለያዩ ዞኖች በመወከል ነው ከአምስቱ የአፍሪካ ዞኖች ከምርጫው በጣም ቀደም ብሎ አንድአንድ አስፈፃሚዎች እንዲወከሉ ይጠየቃል። እነዚያ የተወከሉ ምርጫ አስፈፃሚዎች ሂደቱን ይተገብራሉ እንጅ ተወዳዳሪ ሆነው ምርጫውን ማስፈፀም አይችልም፡፡ በፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ቢሆን ሂደቱን የሚመራው ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚ ነው፡፡
ለመሆኑ የምርጫ አስፈፃሚ እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች በተቋቋሙበት አስቸካይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተሳታፊ እንደመሆንም በስብሰባው ላይ እጅዎን በማውጣት እድል እንዲሰጥዎት ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካልዎትም፡፡ በጉባዔው የነበሩ የክብር አባላትም የተፈጠረውን ውግዝብ የሚያበርዱ አስተያየቶች ለመስጠትና፤ ሃሳባቸውን ለመግለፅ ተመሳሳይ ጥረት አድርገው አልሆነላቸውም
እኔ እጄን ያወጣሁት ለምርጫ የሚወዳደር ጉባዔውን መምራት የለበትም የሚለውን ሃሳቤን ለመግለፅ ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም አቀፍ አሰራር ምርጫ የሚወዳደር ምርጫ አይመራም ለማለት ነው፡፡ አለበለዚያ የምርጫ መወዳደርያው ሜዳ እኩል አይሆንም፡፡ እጄን አውጥቼ የነበረው አቶ ጁነዲንን ለመምከር ነበር፡፡ ተወዳዳሪ በመሆናቸው በምርጫው አጀንዳ ጉባኤውን በሰብሳቢነት መምራታቸው ተገቢ አልነበረም፡፡ ምናለበት ለገለልተኛ ኣካል መድረኩን በክብር ቢሰጡ የሚል ሃሳቤን ለጉባዔው ለመግለፅ ነው፡፡ እድሉ አልተሰጠኝም፡ ጉባኤተኛውም ስብሰባውን በመምራታቸው በአመዛኙ ደስተኛ እለነበረም፡፡ አባላቱ ገለልተኛ አካል ስብሰባውን ይምራው ቢሉም በእምቢተኝነታቸው ቀጠሉ፡፡ በመጨረሻም ጉባኤው በተቃና መንገድ ሄደ፡፡ በአቋራጭ መፍትሄ አግኝቶ ነው። የምርጫ አስፈፃሚ እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ከእያንዳንዱ ክልል በውክልና ይቅረብ በሚለው ተስማማ፡፡
ለክብር አባላቱም እድል አልተሰጠም ያልከው እኔ የክብር አባል አይደለሁም፤ በጉባኤው የተገኘሁት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት በመሆኔ በነገራችን ላይ የክብር አባል በዓለም አቀፍ ደንብ መሰረት በምርጫ ሊወዳደር አይችልም፡፡ በፖለቲካውም እንደዛው ነው፡፡  ለምሳሌ ክቡር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከፕሬዝዳንት ስልጣን ሲወርዱ የክብር አባል ነበሩ፡፡ ወደፖለቲካው እገባለሁ ብለው ሲወስኑ ግን የክብር አባልነታቸውን ተነስቷል፡፡ ህግ መንግስቱ ስለማይፈቅድ ነው፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽን የክብር አባል የሆኑ በምርጫ ሊወዳደሩ አይገባም፡፡ ፊፋ በደንቡ የሚለው የክብር አባል የሚሆኑት ከስፖርቱ በጡረታ የተገለሉ ናቸው፡፡ በምርጫ ለመወዳደር የክብር አባልነትን መተው ግድ ይላል፡፡
ከዚህ ቀደም እግር ኳስ ፌደሬሽኑን ለስድስት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ማገልገልዎ ይታወቃል፡፡ አስቀድሞ እንደጠቀሱት በርስዎ የአመራርነት ዘመን የተመዘገቡ ውጤቶች ይኖራሉ፡፡ ግን የተለያዩ ውዝግቦችም ነበሩ፡፡ እና ዳግም እድሉን አግኝተው ወደፌደሬሽኑ ቢመለሱ በአወዛጋቢ ሁኔታዎች እንደማይገቡ ምን ማረጋገጫ አለ ?
በመጀመርያ ደረጃ እኔ የውዝግብ ሰው አይደለሁም፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴውን በፕሬዝዳንትነት ስመራው እነሆ አንድ አመት ሊሆነኝ ነው፡፡ ምን አይነት ውዝግብ ተፈጥሯል ታድያ? በፖለቲካ ውስጥም እየሰራሁ ነኝ፤ እስካሁን አንድ ውዝግብ ውስጥ ገብቼ አላውቅም፡፡ ይህ የሚያሳየው ችግሩ ከእኔ አለመሆኑን ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ስሰራም መልካም ተመክሮ ነው ያለኝ፡፡ በውዝግብ ውስጥ የሚገባው አገርን በህግና ስርዓት ለመገንባት ሳይሆን በጉልበት ለመናድ የሚፈልግ ሃይል ነው፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትነት በሰራሁባቸው ጊዜያት ውዝግብ ውስጥ የከተተንም ይህ አይነት ተግባር ነው፡፡ መንግስት ባለበት፤ የህግ የበላይነት በተከበረበት አገር፤ የፌደሬሽኑን የፊፋን ህግ ደንብ በመጣስ በጠራራ ፀሃይ በር ሰብረው በመግባታቸው ነው፡፡ በዚያን ወቅት እኔ የውዝግብ ሰው አድርጎ ሊስለኝ የተገደደውም ሚዲያው ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ሚዲያው ብዙ ምርጫ አልነበረውም፡፡ በጉልበተኞች ይሸማቀቁ፤ ድብደባ እና ጥቃት ይደርስባቸዋል ስለሆነ እነዚያን ውዝግብ ፈጣሪዎችን ሊያወግዝ አልቻሉም ነበር፡፡ ዛሬ እነዚህ ሃይሎች የሉም ፡፡ ከዚህ አኳያ ወደ ሃላፊነቱ የምመለሰው ለውዝግብ እንደማይሆን መታወቅ አለበት፡፡ የምፈልጋቸውን ስራዎች እና እቅዶች ከዳር ለማድረስ እና ለመቀጠል ነው፡፡ እኔ የስራ ሰው ነኝ፤ ስልጣኑን በማግኘት በግሌ ለማሳካት ምንም የምፈልገው ነገር የለም፡፡ የክለብ ደጋፊ አይደለሁም፡፡ የቦርድ አባልም አይደለሁም እኔ ወደ ስፖርቱ ስመጣ ስፖርቱንና ስፖርቱን ማዕከል አድርጌ ለመስራት ነው፡፡
አሁን ወደ እግር ኳሱ ለመመለስ ከተነሱ ወዲህ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለይ በሚዲያዎች ላይ አስተያየቶችዎን ስሰማ ብዙዎቹ የረጅም ጊዜ እቅድ ናቸው፡፡ ምናልባትም አንድ የስራ ዘመን ወይንም አራት ዓመት ላይበቃዎ ይችላል፡፡ በፌደሬሽኑ ታሪክ ደግሞ ፕሬዝዳንት ከአንድ የስራ ዘመን በላይ መቀጠል ያጠያይቃል፡፡ የጀመርኩትን ስራ ልቀጥል ብሎ እድል ቢሰጠው እንኳን በ6ኛው ዓመቱ በውዝግብ ከኃላፊነት የሚነሳበት ሁኔታ አጋጥሟል፡፡ እና ጅምር ስራዎችን ሳይጨርሱ በአንድ የስራ ዘመን የሚወርዱበትን ስልጣን ለማግኘት ምን ያተጋዎታል?
ወደ ፌደሬሽኑ ብመለስ የምሰራቸው ስራዎች በአጭር፤ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ እቅዶች የሚመሩ ይሆናሉ፡፡ ያለኝን ራእይ እና እቅድ በፌደሬሽኑ አስተዳደር በጽኑ መሰረት ለማስቀመጥ ነው የምፈልገው፡፡ በተለያየ የእቅድ ምዕራፍ ለምናከናውናቸው ተግባራት የምናተኩርባቸው የተለያዩ ወሳኝ አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ በመጀመርያ በአብዛኛው በልማት ላይ አተኩረን ከታዳጊዎች ከስር መሰረት ተነስተን በየክልሉ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ የልማት ስራዎችን ለማቀላጠፍ በየክልሉ የፋይናንስ የገቢ ምንጮችን የሚያጠናክሩ ስራዎች መተግበር እንፈልጋለን፡፡ የስትራቴጂክ እቅዱን ከመንግስት እና ከየክልሉ እቅዶች ጋር በሶስትዮሽ አዋህደን በመሄድ ነው፡፡ ሌላው የፌደሬሽኑን የፅህፈት ቤት የስራ አቅምና አገልግሎት ለማሳደግ የምንከተለው አቅጣጫ ነው፡፡ የፅህፈት ቤቱን ስራዎች ባለሙያዎች በማደራጀት እና በማጠናከር ፕሮፌሽናል ለማድረግ ነው፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ውድድርን በተመለከተ ነው ውድድርን ክለቦች በሊግ ኮሚቴ እንዲያስተዳድሩ በመተው በብሄራዊ ቡድን ግንባታ፤ በአሰልጣኞች ስልጠና፤ በሙያቶች የአቅም ግንባታ ፌደሬሽኑ በንቃት እንዲንቀሳቀስ ማስቻል ነው፡፡ በአራተኛ ደረጃ የምጠቅሰው የአገሪቱን እግር ኳስ ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የምንከተለው አቅጣጫ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ የስፖርት ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በተሻለ አጠናክሮ ለመስራትም ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ላነሳ እችላለሁ፡፡ አገራችን ለብዙ የስፖርት የሚመቹ የአየር ሁኔታዎች መልክዓምድሮች እንዳሏት ይታወቃል፡፡  ይህን ከሚፈልጉ አጋራት ጋር በአጋርነት ለመስራት የጀመርናቸው እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ በእግር ኳስ የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገራት በአካዳሚዎቻቸው ታዳጊዎቻችን እንዲያሰለልጥኑ እኛ ደግሞ በአትሌቲክስ ስፖርት ድጋፍ ልናደርግላቸው የምንችልበት ግንኙነት ነው፡፡ በሁለትዮሽ ጥቅም የምንሰራበት፤ በምንችልባቸው እንድናግዛቸው በማንችልባቸው እንዲያግዙን በማቀድ ነው፡፡ በመጨረሻም በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ዋና የትኩረት አቅጣጫ አድርገን መስራት እንፈልጋለን በተሟላ እቅድ ከክለቦች ጋር ለመስራት የምንጥርበት ነው፡፡ ሁሉም የስፖረት ባለድርሻ አካላት በስፖርታዊ ጨዋነት ጉልህ ለውጥ በሚፈጥሩበት የጋራ እቅድ እንዲሰሩ ማስተባበር ነው፡፡
በትልቅ የስፖርት አመራር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰመራ ላይ በሚደረገው የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ምን ይጠብቃሉ?  የሚያስተላልፉትስ መልዕክት ምንድነው?
የእኔ መልዕክት ግልፅ ነው፡፡ በምርጫ ለመወዳደር የመጣሁት የደቡብ ክልልን ወክዬ ነው፡፡ ከአማራ፤ ከድሬዳዋ፣ ከኦሮሚያ ተወክሎ ወደ ምርጫው የሚገባ አለ፡፡ ሁላችን የአቅማችንን በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ ለመስራት መጥተናል ብዬ ነው በበጎ ጎኑ የማስበው ፡፡ ስለዚህም እያንዳንዱ የጉባኤው አባልና ድምፅ የሚሰጥ መራጭ ማዕከል ማድረግ ያለበት የወከለውን 100 ሚሊዮን ህዝብ ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ህዝብ ውክልናው አግኝቶ  ወደ ምርጫው ቢገባ ምን ሊደግፍ  እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው፡፡  በምርጫው ለመፎካከከር የቀረብነውን እጩዎች በቅንንት አወዳድሮ  የምመርጠው ከሁሉ የሚሻለውን ነው በሚል መተማመን በውክልናው እንዲወስን ነው ጉባኤውን የምጠይቀው፡፡ ህዝቡን ፤ አገራችንን መንግስትን፤ የወደቀውን ስፖርት ከግምት ውስጥ አካቶ ለፈለገው አካል ድምፁን እንዲሰጥ ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

Read 1869 times