Saturday, 25 November 2017 10:13

“ሞቴን ያድርገው በአገሬ” ያሉት ሙጋቤ፣ ያለመከከስ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ኤመርሰን ማንጋግዋ ቃለ-መሃላ ፈጽመው ስልጣን ተረክበዋል

   ላለፉት 37 አመታት ዚምባቡዌን የመሩትና የአገሪቱ የጦር ሃይል ስልጣኑን በጊዜያዊነት መረከቡን ተከትሎ፣ ለቀናት ሲያንገራግሩ ቆይተው ባለፈው ማክሰኞ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ በጦር ሃይሉ ባለስልጣናት ያለመከሰስ ዋስትና እንደተሰጣቸው ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል።
ሙጋቤ “እስከ ዕለተ ሞቴ በአገሬ ምድር ላይ መኖር እፈልጋለሁ፤ ቀሪ ዘመኔን በስደት መገፋት አልሻም፤ ስለሆነም ለእኔም ሆነ ለባለቤቴ ደህንነት ዋስትና ከተሰጠኝ ስልጣኔን እለቃለሁ” በሚል ለጦሩ መደራደሪያ ሃሳብ መላካቸውን ተከትሎ፣ እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ግሬስ በአዲሱ መንግስት ደህንነታቸው እንደሚጠበቅላቸው ቃል እንደተገባላቸው አንድ የአገሪቱ የጦር ሃይል ባለስልጣን መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሙጋቤ ጡረታቸው እንደሚከበርላቸውና የመኖሪያ ቤት ክፍያና የጤና ዋስትናን የመሳሰሉ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እያገኙ፣ ቀሪ ህይወታቸውን ከቤተሰባቸው ጋር በሰላም እንዲገፉ ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል መባሉን ዘገባው የጠቆመ ሲሆን፣ ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፤ ሙጋቤ ከሶስት አስርት አመታት በላይ በዘለቀው የስልጣን ዘመናቸው፣ የግል ሃብት ለማካበት ያልዳዱና ከአገር ውጭ ምንም አይነት ሃብትም ሆነ ንብረት እንደሌላቸው ዘግቧል። ሚስታቸው ግሬስ በአንጻሩ፤ የከብት እርባታና የወተት ምርቶች ማቀነባበሪያን ጨምሮ በርካታ ንግዶችን እንደሚያከናውኑም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ዋዞዌ በተባለው የአገሪቱ የገጠር መንደር ውስጥ የሚገኘው የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ንብረት የሆነ እርሻና የከብት ማድለቢያ ድርጅት፣ ባለፈው ረቡዕ በመቶዎች በሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መዘረፉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ .
በቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣናቸው መባረራቸውን ተከትሎ፣ወደ ደቡብ አፍሪካ የተሰደዱትና ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው የ75 አመቱ ኤመርሰን ማንጋግዋ፤ በትናንትናው ዕለት ቃለ መሃላ ፈጽመው ስልጣን ይዘዋል፡፡
አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ በበኩሉ፤ ዚምባቡዌ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደመዘፈቋ፣ አዲሱ የአገሪቱ መንግስት ከወጪ፣ ከውጭ ብድርና ከሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አፋጣኝ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባው ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ማንጋግዋ በበኩላቸው ተቀዳሚ ስራቸው ኢኮኖሚውን ማቃናት እንደሆነ ተናግረዋል። የሙጋቤን ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ በርካታ የውጭ አገራት ኢንቬስተሮች ወደ አገሪቱ ለመግባት ፍላጎት እያሳዩ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ይህም የዶላር እጥረትን ለመቅረፍና ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የያዙትን ዕቅድ በማሳካት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

Read 2296 times