Sunday, 26 November 2017 00:00

“እውቀት የራቀውና የዞረበት ነፃ ውይይት” መፍትሄ አይደለም!... ችግር ነው!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(11 votes)

የፓርቲዎች ውይይትና ድርድር - አዳዲስ ፓርቲዎችን መገደብ
ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለድርድር ተሰብስበው፣ በውይይት የተስማሙበት የመጀመሪያው ውሳኔ ምን እንደሆነ አስታውሱ።
የአዳዲስ ፓርቲዎች እንደአሸን እንዳይፈሉ ለመከልከል፣ መሰናክሎችንና ገደቦችን እንደአሸን ማፍላት!
ፓርቲዎቹ በዚህ ተስማምተዋል። እንዲህ እንዲህ አይነት ነገር ላይ ይግባባሉ።
በቃ፣ የፖለቲካ ገደቦችን መደርደር ችግር የለውም። የጋራ ውሳኔ ነዋ፣ በውይይትና በድርድር የተገኘ።
መንግስት ለፓርቲዎች የድጎማ በጀት ይመደባል በማለትም ተስማምተዋል። ፓርቲዎች ገንዘቡን ይከፋፈሉታል።
ድጎማ ለመቀራመት ብለው በየቦታው የሚቀፈቀፉ ፓርቲዎች እንዳይመጡ ለመከልከልም፣ ዘዴ ተገኝቷል - የፖለቲካ ገደቦችን መደርደር!     

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በር ላይ፣ ብሄር ብሄረሰቦች ለአቤቱታ ሊሰለፉ?
“የሕዝቦች፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እንዲከበር አሳሰቡ” ይላል ዜናው። ማን ናቸው ማሳሰቢያ ያወጁት? የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰራተኞች።
ቀደምት ትውልዶችና የወደፊት ትውልዶች፣... አህጉራትና ፕላኔቶችም መብታቸው ይከበር ቢሉ አይሻልም?
ማመልከቻ ይዞ የሚመጣ ብሔር ብሔረሰብ እንደማይኖር፣ በወረፋም እንደማያጥለቀልቃቸው ያውቃሉ።
የሰው መብት (የእያንዳንዱ ግለሰብ ነፃነት) እንዲከበር ማሳሰብማ፣ ትልቅ አላማ፣ ከባድ ስራ ይሆናል።
የምር የእያንዳንዱን ሰው መብት የሚያስከብር ከሆነ፣ አቤቱታ ይዞ የሚመጣ ሰው መብዛቱ ይቀራል?

“ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት”፣ እውቀት ሲርቀው ምን ይሆናል?
“ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት”፣ እውቀት ሲርቀው... ቢበዛ... ቀልድና ቧልት ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም። ከዚያም የከፋ ሊሆን ይችላል።
የኢቢሲ ፕሮግራም አለ፤ ‘ሃሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት’። የዓመቱ 4 ወቅቶች ምን ይባላሉ? ብሎ ይጠይቃል።
“ደጋ፣ ቆላ፣ እ... ወይናደጋ፣ እ... ሌላኛውን ረሳሁት” ብሎ ሃሳቡን በነፃነት ይገልፃል አንዱ። ወይናቆላ... አላለም።
“ብርዳማ፣ ፀሃያማ፣... ዝናባማና.... እ...ቀዝቃዛ”... ትላለች በነፃነት ሌላኛዋ። ይሻላል። ግን፣ ውርጭ፣ ነፋስና ጎርፍስ?
በኢትዮጵያ የሚታወቁ ቅኝቶችስ እነማን ናቸው የሚል ጥያቄም ተነስቷል። በዚሁ ጥያቄ ዙሪያ የተሰነዘሩ የበርካታ ሰዎች አስተያየት፣ በኢቢሲ ፕሮግራም ተስተናግደዋል። ተንሸራሽረዋል።
“በኢትዮጵያ የሚታወቁ ቅኝቶች?... እ... ኖታ አለ” ብሎ ይጀምራል አንዱ። እ... ከበሮ፣... ማሲንቆ፣... ከውጭ ደግሞ ጊታር! ብሎ ይዘረዝራል ሌላኛው።
ይሄ ሁሉ አስቂኝ ሊሆንላችሁ ይችላል። በቀላሉ የሚስተካከል የአላዋቂዎች ቀሽም ስህተት ጎልቶ ሲወጣ ማየት፣... ዘና የሚያደርግ አስቂኝ ቀልድ መሆን ይችላል። ነገር ግን፣ ለሁሉም ሰው ያስቃል ማለት አይደለም። ወቅቶችንና ቅኝቶችን የማያውቅ ሰው፤ የሌሎች ሰዎችን ቀሽም ስህተት አይቶ ሊስቅ አይችልም።
ግን ደግሞ፣ ለማንኛውም ሰው ጨርሶ አስቂኝ የማይሆንበት ደረጃ ላይ እየደረስን ይመስላል።
ለወትሮውማ፣... ጥቃቅንና ጥቂት ቀሽም የአላዋቂ ስህተቶች ያስቃሉ። ግን፣ አላቂነት ሲነግስስ ያስቃል?
የተማሩ ወጣቶች፣ ከሀዲስ አለማየሁና ከፀጋዬ ገ/መድህን ጋር የሚተዋወቁት፣ በቴዲ አፍሮ ዘፈን ሲሆን... በጭራሽ አያስቅም!
ትምህርት ሚኒስቴር፣ ነገ በንዴት ገንፍሎ፤ “በዘፈን... ማስተማር አይቻልም” የሚል አዋጅ እንደማያወጣ ብትሰጉ አይገርምም። ማስተማር ቢያቅተው እንኳ፣ አዋጅ ማውጣት ላይከብደው ይችላል።   

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የጤፍ ፈጠራ
“የጤፍ የፈጠራ መብት (ፓተንት ራይት) ለማስመዝገብ ቆርጫለሁ” ብሏል - የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር።
የጤፍ የፈጠራ ባለቤቶች፣ የጤፍ ፈጣሪዎች፣... የኢትዮጵያ አርሶአደር ትውልዶች ናቸው ብሏል ሚኒስቴሩ።
“ጤፍ፣ ወፍዘራሽ የሰፊው ሕዝብ ፈጠራ ነው” ቢል አይሻለውም? ትንሽ ቆይቶ ደግሞ፣ “የብሔር ብሔረሰብ ፈጠራ ነው”፣ “የሴቶችና የወጣቶች ፈጠራ ነው” እያለ ቢቀጥል፣ ማን ይከለክለዋል? በእርግጥ...
1ኛ. ለሺ ዓመታት የሚታወቅ ጤፍ፣ አዲስ ፈጠራ አይደለም - የተሻሻለ አዲስ የጤፍ ዝርያ በምርምርና በአዲስ ዘዴ ካልተፈጠ በቀር።
2ኛ. የጅምላ ፈጠራ የለም። የእገሊትና የእገሌ ብሎ፣ የፈጠራ ድርሻ ያላቸው ሰዎችን መዘርዘር ይቻላል።
3ኛ. ‘ሁላችንም አለንበት’ ብሎ የፈጠራ ባለቤት ሊኮን ነው? “ጤፍን ፈጥራችኋል ሁላችሁም አላችሁበት”!  
4ኛ. “በእግዜር ስራ? እኔ የለሁበትም። የሚናገሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ የሚፀልይ ገበሬ የሚኖር አይመስላችሁም? ከበርካታ ገበሬዎች ጋር በዚህ ምክንያት ጭቅጭቅ ሲፈጠር ይታያችሁ። “እናንተ ገበሬዎች፣ ጤፍን ፈጥራችኋል” ይላሉ ሚኒስቴሩ አንዳንድ ባለስልጣናትና ኤክስፐርቶች። “ጤፍ እዘራለሁ እንጂ አልፈጠርኩም” ይላሉ በርካታ ገበሬዎች። አደራዳሪና አስታራቂ ኮንፈረንስ በማካሄድ ችግሩን በውይይት ለመፍታት እንሞክር እንዴ?  
እንዲህ አይነት፣ የተሳከረና የተምታታበት ሃሳብ፣ እንደአዋቂነት የሚቆጠርበት የቅዠት አዘቅት፣ በእርግጥም በየቦታው ተበራክቷል።

የአገር አለኝታው የእግር ኳስ ፌደሬሽን
እንግዲህ፣ “ለአገር ብልፅግና መስራት፣ ለአገር እድገት መቆም አለብን” ተብሏል – የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ጉባኤ ላይ። የኢኮኖሚክስ ምሁራንና ባለሙያዎች ጉባኤ ይመስላል። ለአገር ብልፅግናና እድገት? የአምስት ዓመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አዘጋጅ ጉባኤ ነው እንዴ?
ማለቴ... የእግር ኳስ ፌደሬሽን፣ አሪፍ የእግርኳስ ብቃትና ችሎታ ጎልቶ እንዲወጣ ከማድረግ የበለጠ ወይም ያነሰ አላማ ሊኖረው እንደማይገባ የሚያውቅ ሰው ጠፋ? አይጠፋም። ግን፣ ቁምነገር መናገር ብዙም አያዋጣም - መያዣና መጨበጫ በሌለው የውዝግብ አተካራ ውስጥ፣ የሰከነ ሃሳብ ቦታ የለውም። በተቃራኒው፤ በጥላቻ ስሜት የጦዙ ውንጀላዎችና ዘለፋዎች ናቸው ተሰሚነትን የሚያገኙት። ወደ ውንጀላና ዘለፋ ከመሸጋገሩ በፊት ግን፣ አላስፈላጊ ባዶ የእልህ እንካሰላንተያ ይቀድማል። በጭፍን ስሜት የሚፍለቀለቁ አባባሎችና ቃላትም ይዥጎደጎዳሉ።  
“ምርጫ ባለመካሄዱ ትልቅ ድል ተመዝግቧል”
“ተወዳዳሪዎች አለማቀፍ ቋንቋ ማወቅ አለባቸው”
“የተዛባ የምርጫ ደንብ ሳይስተካከል ምርጫ የለም”
“ደንቡ ይከበር። ደንብ ሳይከበር ምርጫ አይኖርም”
“አላማዬ፣ የኢትዮጵያን ክብር ማስመለስ ነው”
“ኢትዮጵያን ከውርደት ለማውጣት እታገላለሁ”
የእግር ኳስ ፌደሬሽን ባይኖር ምን ይውጠናል። ኢትዮጵያን ከውርደት አውጥቶ ወደ ክብር የሚያስመልስ ፌደሬሽን ከየት ይገኛል?
ይሄ ሁሉ ቅዠት፣ ይሄ ሁሉ የጨለማ ውዥንብር፣ በእግር ኳስ ፌደሬሽን ላይ ብቻ የሚታይ ልዩ ትዕይንትና የአጋጣሚ ክስተት አይደለም። ከጓዳ እስከ አደባባይ፣ ተመሳሳይ ቅዠት ሞልቶ ተትረፍርፎ!

ጥንታዊ ኋላቀርነትና ስልጣኔን የማንቋሸሽ ዘመናዊ ፈሊጥ ሲቀላቀሉ
  ዘመናዊ የእውቀት፣ የብልፅግናና የመከባበር ስልጣኔ፣ በቅጡ ያልተስፋፋበት አገር ውስጥ፤... “ስልጣኔ ጊዜው አልፎበታል” የሚል የጨለማ ፍልስፍና ሲቀላቀል ምን ይፈጠራል? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ፣ ትንሽ ፍንጭ ከፈለግን፣... በዙሪያችን ሞልቶልናል። ዛሬ ዛሬ፣ኢትዮጵያ ውስጥ በየእለቱና በየአካባቢው የምናያቸው ውዥንብሮች በሙሉ፣ ፍንጭ ሊሆኑን ይችላሉ።
በአንድ በኩል፣ የኢትዮጵያ ኋላቀርነት አለ - ማለትም፣ ስልጣኔን በወጉ የማያውቁ ሰዎች የበዙበት፣ ገናና ኋላቀር ባህል ጎልቶ ይታያል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣... ዓለም በፀረ ስልጣኔ የጨለማ ፍልስፍና የተንበሻበሸበትና የተሳከረበት ዘመን ውስጥ ነን - postmodernism እንደጭስ ከጓዳ እስከ አደባባይ የተንሰራበት ዘመን። የተገነባን ከመሸራረፍና ያማረውን በጥላሸት ከማበላሸት ውጭ እውቀትም፣ አላማም ሆነ ብቃት የሌለው አስቀያሚ ውርጋጥ... እንደማለት ልትቆጥሩት ትችላላችሁ።
የተሻለ እውቀት ይዣለሁ በማለት አይደለም ስልጣኔን የሚያንቋሽሸው - postmodernism። እውቀትና እውነት? ሳይንስ? ሳይንስማ ከየትኛውም ባህላዊ እምነት የተለየ ብልጫ የለውም። “ከፈለጋችሁ፣ ሳይንስን፣ እንደ አንድ ባህላዊ እምነት ልትቆጥሩት ትችላላችሁ” በማለት ነው ስልጡን አስተሳሰብን ለመናድ የሚሞክረው።
እውቀትና እውነት?  እነዚህ ቃላትማ ትርጉም አልባ ማታለያዎች ናቸው በማለት ነው የስልጣኔን ስረመሰረቶች የሚንደው። “...Postmodernism constitutes an attack on... claims about the existence of truth and value - claims that stem from the Enlightenment of the 18th century.” ተብሎ የለ?
እውነትና ሃሰት፣ ትክክልና ስህተት... ትርጉም የላቸውም ብሎ እንደዝገት የስልጣኔ ስረመሰረቶችን በመቦርቦር አያቆምም። ጠቃሚና ጎጆ፣ የሚያጠራና የሚያጠፋ፣ ጥሩና መጥፎ፣ ስኬትና ውድቀት... የሚሉ ቃላትም ትርጉም የለሽ ከንቱ የማጭበርበሪያ ቃላት ናቸው በማለት፣ የመልካም አላማና የግብረገብነት መርሆችን ሁሉ በጥላሸት ይደመስሳቸዋል።
በዚህ ጨለማ የቅዠት ዓለም ውስጥ፣ እነማን እየገነኑ እንደሚመጡ አስቡት።
በሃሰተኛ መረጃ እያጨናበረ፣ በጭፍን እምነት እየቆሰቆሰ፣ በጥላቻ ስሜት እያደናበረ... በዚህም በዚያም ሰዎችን  ለማሳመን የሚንጥና እንዲደግፉት የሚያነሳሳ ፖለቲከኛ ምንም ጉድለት የለበትም።
እውነተኛ መረጃ አቅርቦ፣ በማስረጃ አገናዝቦ፣ በትክክል አመሳክሮ... ሰዎችን ለማስረዳትና እንዲደግፉት የሚጠይቅ ፖለቲከኛም፣ ምንም ብልጫ የለውም።
ሁለቱም ያው... ተፎካካራ ፖለቲከኞች ናቸው።
እውነትና ሃሰት፣ በእኩያነት ትርጉም አልባ በሆኑበት በዚህ የተሳከረ የውይይት አውድማና ጨለማ የክርክር ፍልሚያ ውስጥ፣... የትኛው ፖለቲከኛ ውጤታማ እንደሚሆን መገመት ትችላላችሁ። በሃሰት አጭበርብሮ፣ በጭፍን እምነት ንጦ፣ በጥላቻ ስሜት አደናብሮ ለመሄድ የሞከረ፣ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ይሳከለታል።
ግን፣... በማግስቱ፣ ከሱ የባሱ ይመጡበታል። “ውይይትና ክርክር”፣ “ምርጫና ፉክክር” ተብሎ የተጀመረው ነገር ሁሉ እየጦዘ፣ ወደ መናጨት ለመሸጋገር ጊዜ አይፈጅበትም። እለት በእለት የሚፈጠሩና በጭካኔ ብልጫ የሚያሳዩ አዳዲስ ክፉ መሪዎች፣... ሌላውን “ተወያይና ተፎካካሪ” ሁሉ ጨፈላልቀው ሲያበቁ፣ ከመካከላቸው አንዱን ያነግሳሉ - እጅግ ለሚፈሩት ጨካኝ አምሳያቸው ተገዢ ይሆናሉ። አልያም፣ ለጊዜው አንዱን ደካማ ለጊዜው አንግሰው፣ አድፍጠው ውስጥ ለውስጥ ይሻኮታሉ። ወይም ደግሞ፣ በየፊናቸው ትናንሽ ግዛት ላይ ለመንገስ ማለቂያ በሌለው ፍጅት አገር ምድሩን ያተራምሱታል።
በአጭሩ፣ ከስልጣኔ ውጭ የሚሞከር ቁንፅል የስልጣኔ ገፅታ፣... ለእውነተኛ መረጃና ለትክክለኛ ሃሳብ ደንታ የሌለው አእምሮ አልባ ውይይት፣ መግባባትንና ሰላምን አያስገኝም - ያሳጣል እንጂ። ትክክለኛ አላማው የማይታወቅ፣ ተገቢ ስራው ያልተለየና የስኬት መለኪያ የሌለው ፉክክርና ምርጫ፣... መጨረሻው አያምርም። ከውዝግብ ማጥ ውስጥ መውጣት ሲያቅተው፣ የእሳት ረመጥ ለመፍጠር መፎካከር ይጀምራል። ከጉልበተኛ ትዕዛዝና ጡጫ በስተቀር የሚያስቆማቸው ይጠፋል። ልክ እንደ እግርኳስ ፌደሬሽን።

Read 3960 times