Saturday, 25 November 2017 09:55

የሃይማኖትና የዘመናዊነት ግብግብ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(3 votes)

“--ዘመናዊ ትምህርት የመጣውም፣ መካከለኛው ዘመን ከሰው ላይ የነጠቀውን ሥልጣን ለማስመለስ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከቤተ ክህነት ሥልጣን የቀነሱት
ለሰው ልጅ ሥልጣን ለመጨመር ነው፡፡ የአብነት ት/ቤቶች እንደ አሸን በፈሉበት ሀገር ላይ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመናዊ ት/ቤቶችን ሲያስፋፉ የነበረው፣
በአብነት ት/ቤቶች የተነጠቀውን የሰው ልጅ ሥልጣን ለባለቤቱ ለማስመለስ ነው፡፡---

አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ከማወጣቸው ፍልስፍናዊ ፅሁፎች ትንሽ እረፍት አድርጌ እመለሳለሁ ብዬ ባስብም አንባቢዎች ግን በፅሁፎቼ ላይ አስተያየት በመፃፍ እየጠሩኝ ስለሆነ አልፎ አልፎ ብቅ ማለቴ አልቀረም፡፡ ለዛሬ መጣጥፌም መነሻ ምክንያት የሆነኝ፣ ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 9 ቀን 2010 ዓ.ም አቶ ዘርይሁን አሰፋ ከብራስልስ “ህዳሴና እምነት፣ ቀንና ሌሊት” በሚል ርዕስ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ያስነበቡን ፅሁፍ ነው።
አቶ ዘርይሁን ይሄንን ፅሁፍ ያዘጋጁት፣ እኔ መስከረም 20 ቀን 2010 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “የባህልና ትውፊት ተቋምን ያገለለው የህዳሴ ፕሮጀክት” በሚል ርዕስ ላወጣሁት ፅሁፍ ተቃውሟቸውን ለመግለፅ ነው። እኔ በዚህ ፅሁፌ ላይ ካቶሊክ ቤ/ክ ከአውሮፓ የህዳሴና የዘመናዊነት ፕሮጀክት ጋር ግብግብ ገጥማ የደረሰባትን ጉዳት በመጥቀስ፤ “ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ ላለፉት 160 ዓመታት ሲሞከር የቆየው የኢትዮጵያ የህዳሴና የዘመናዊነት ፕሮጀክት ያልተሳካው፣ የኦርቶዶክስ ቤ/ክ በባለቤትነት ስላልተሳተፈችበት ነው። አሁንም የሀገራችን ህዳሴ ከፖለቲካ ፕሮጀክትነት ወጥቶ፣ ለኦርቶዶክስ ቤ/ክ ይሰጣት፤ በዚህ ውስጥ ፖለቲካው አጋዥ ብቻ ይሁን” የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ አቅርቤያለሁ፡፡
አቶ ዘርይሁን ለዚህ ሐሳብ ምላሽ በሰጡበት ፅሁፋቸው ላይ የካቶሊክንና የአውሮፓን ህዳሴ ግብግብ በመጥቀስ “ሃይማኖት ከህዳሴ (ከዘመናዊነት) ጋር በፍፁም ሊታረቅ አይችልም፡፡ በመሆኑም ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ለህዳሴ ትልቅ አቅም ቢኖራትም ዝግጁነቱ ግን የላትም” የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ ይህ የአቶ ዘርይሁን ሐሳብ፣ ኦርቶዶክስ ቤ/ክን ለህዳሴ ዝግጁ ትሆናለች ብሎ ማሰብ ከንቱ ድካም ነው ወደሚል ድምዳሜ የሚወስደን ነው፡፡
ምናልባት የኔ ሐሳብ ከንቱ ድካም ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ይሄንን ማድረግ ያለባት ከማንም በላይ ለራሷ ስትል ነው። ምክንያቱም የዘመናዊነት ፕሮጀክት የመጀመሪያ ተግባሩ ከነባሩ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ጋር ግብግብ መግጠም ነው። ለዚህም ነው የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት በመጀመሪያ የተላተመው ከኦርቶዶክስ ቤ/ክ ጋር የነበረው፡፡ ምናልባት ሃይማኖታዊው አስተሳሰብ አፄ ቴዎድሮስ ላይ ድል መቀዳጀቱ የኦርቶዶክስ ቤ/ክንን የማይበገር ጉልበት ያሳይ ይሆናል፡፡ በሌላው ዓለም ላይ ያሉ ነባር ሃይማኖቶች፣ በዘመናዊነት ጉልበት የተነሳ እየተዳከሙ ባሉበት በዚህ በ21ኛው ክ/ዘ ላይ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ አሁን ድረስ ይሄንን ጥንካሬዋን እንደያዘች መቆየቷ አስገራሚ ሊመስለን ይችላል። “ጥንካሬ” ስል የተከታዮቿን ብዛትና በተከታዮቿ ዘንድ አሁን ድረስ ያላትን ከፍተኛ ተሰሚነት ለማመላከት ነው፡፡
አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ግን፣ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ እስከ አሁን ድረስ ይሄንን ጥንካሬዋን ይዛ ልትቆይ የቻለችው በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ፖለቲካ ላይ በተንሰራፋው የብሄር ፖለቲካ የተነሳ ነው፡፡ የብሄር ፖለቲካ የፍርሃት ቆፈን ውስጥ የከተታቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች፣ ልባቸውን ለዘመናዊነት ከመስጠት ይልቅ በሃይማኖታቸው ውስጥ በመከለል፣ የፖለቲካውን ትኩሳት ማሳለፍን መርጠዋል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ እስከ አሁን ድረስ ይሄንን ጥንካሬዋን ይዛ ልትቆይ የቻለችው በተደጋጋሚ የተሞከሩት የዘመናዊነት ፕሮጀክቶቻችን ስለከሸፉ ነው፡፡
በመሆኑም ለኦርቶዶክስ ቤ/ክ ፈታኙ ጊዜ የሚመጣው የብሄር ፖለቲካው ሲያከትም ነው። ያን ጊዜ ከዘመናዊነት ጋር ግብግቡ ይነሳል፡፡ ፖለቲካችን ሲሰክንና የሰመረ የዘመናዊነት አፈፃፀም ማስመዝገብ ስንጀምር፣ ህዝባዊ አደባባዩ ከፖለቲካ ይልቅ በሃይማኖትና በዘመናዊነት መካከል በሚፈጠረው ግጭት የተሞላ ይሆናል፡፡ አሁን ይህ ግጭት ለጊዜው በብሄር ፖለቲካ ተሸፍኗል። ኦርቶዶክስ ቤ/ክ እዛ ደረጃ ላይ ሳትደርስ ከአሁኑ ልታስብበት ይገባል፡፡
ለመሆኑ ዘመናዊነት ከሃይማኖት ጋር ግብግብ መግጠሙ የግድ ነው?
አዎ ግድ ነው!! ይሄን የምለው የአውሮፓ ዘመናዊነት ያለፈበት ታሪክ ስለሆነ አይደለም። ይልቅስ ከራሱ ከሰው ልጅ የዘመናዊነት ጥማት ተነስቼ እንጂ፡፡ አውሮፓውያን ፈላስፎች ዘመናዊነትን ያዩበት መንገድ የሰው ልጅ ለዘመናዊነት ያለውን ተፈጥሯዊ ፍላጎት በማጤን ነው፡፡
በጥንቱና በመካከለኛው ዘመን ላይ የሰውን ልጅ ህይወት የሚቆጣጠሩት ተፈጥሮና ሃይማኖት ነበሩ። እነዚህ ሁለቱ ኃይሎች ውጫዊ ናቸው፡፡ ፈላስፋው ኒቸ እንደነገረን ደግሞ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቱ የኃይል የበላይነት ነው፡፡ እናም በዚህ መሰረታዊ ፍላጎቱ በመመራት (የኃይል የበላይነትን ለመቀዳጀት) የሰው ልጅ ራሱን ከውጫዊ ኃይሎች (ከተፈጥሮና ከሃይማኖት) ነፃ በማድረግ ህይወቱን ከራሱ ውስጠት በሚወጣ ኃይልና ፍቃድ መምራት ይፈልጋል፡፡ አንዱ የዘመናዊነት መገለጫ ይሄ ነው - ከውጫዊ ኃይሎች ነፃ በመሆን የሰውን ልጅ ባለ ሥልጣን ማድረግ፡፡ በዚህም ሥነ ምግባርንና የህይወት መመሪያን ከውጫዊ ኃይሎች ከመቀበል ፋንታ ከሰው ልጅ ውስጣዊ ኃይልና ፈቃድ በሚገኝ አስተምህሮ መዘወር ነው፤ አንዱ የዘመናዊነት መገለጫ፡፡
ዘመናዊ ትምህርት ከሃይማኖታዊው ትምህርት የሚለይበት ዋነኛው ነገር ከሰው ልጅ ሥልጣን ጋር በተገናኘ ነው፡፡ ከ4ኛው ክ/ዘ እስከ 20ኛው ክ/ዘ ድረስ ለ1700 ዓመታት በቆየው የገዳማቱ ሥርዓተ ትምህርታችን ውስጥ የህዝባችንን ኑሮ የሚቀይር አንዲት ነገር መስራት ያልቻልነው፣ ሥርዓተ ትምህርቱ የሰውን ልጅ ሥልጣን ስለሚከለክል ነው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት የመጣውም፣ መካከለኛው ዘመን ከሰው ላይ የነጠቀውን ሥልጣን ለማስመለስ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከቤተ ክህነት ሥልጣን የቀነሱት ለሰው ልጅ ሥልጣን ለመጨመር ነው፡፡ የአብነት ት/ቤቶች እንደ አሸን በፈሉበት ሀገር ላይ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመናዊ ት/ቤቶችን ሲያስፋፉ የነበረው፣ በአብነት ት/ቤቶች የተነጠቀውን የሰው ልጅ ሥልጣን ለባለቤቱ ለማስመለስ ነው፡፡
በመሆነም፣ ዘመናዊ ትምህርት የሰውን ልጅ ባለ ሥልጣን የማድረግ ሂደት ነው፡፡ የሰው ልጅ ባለ ሥልጣን ባልነበረበት ዘመን ላይ ሲነገሩ የነበሩ አፈ ታሪኮችን፣ ተአምራትን፣ ልማዶችንና አስተሳሰቦችን ሳይፈትሹ እንዳለ ይዞ በዚህ ዘመን ላይ (የሰው ልጅ ባለ ሥልጣን በሆነበት ዘመን ላይ) መሄድ አዳጋች ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ቤ/ክ የወደፊቱ ፈተናዋ ይሄ ነው።
“የባህልና ትውፊት ተቋምን ያገለለው የህዳሴ ፕሮጀክት” የሚለው ፅሁፌ ላይ አንደኛው ያነሳሁት ሐሳብ “ኦርቶዶክስ ቤ/ክ የሰውን ልጅ ባለ ሥልጣን ታድርግ፤ ለሰው ልጅ ውስጣዊ ኃይልና ችሎታ ዕውቅና ትስጥ፡፡ የህዳሴያችን ፕሮጀክት መጀመር ያለበት ለህዝቡ በየዕለቱ በሚነገሩ ታሪኮችና ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ውስጥ ያለውን የስነ ሰብዕ ይዘት በመጨመር ነው፤ ወይም ደግሞ የመንፈሳዊና የሰብዓዊ ይዘታቸውን በማመጣጠን ነው፡፡ ይሄንን ማድረግ የምትችለው ደግሞ የባህሉና የትውፊቱ ባለቤት የሆነችው ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ናት። ኦርቶዶክስ ቤ/ክ የተመሰረተችበትን ቀኖና ሳትነካ ይሄንን ማድረግ ትችላለች፡፡” የሚል ነው፡፡
ይሄንንም ሐሳብ ለማስረዳት ያነሳሁት የቅዱስ ያሬድን ሁለት ዓይነት (መለኮታዊና ሰዋዊ) አተራረኮችን ነው፡፡ የአለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ ሰዋዊ አተራረክ፣ ቅዱስ ያሬድን ዜማን ለመቀመር ያደረገውን ሰውኛ ጥረትና ችሎታ ዕውቅና የሚሰጥ ነው - ለቅዱስ ያሬድ ሰዋዊ ሥልጣንን የሚያቀዳጅ ነው፡፡
ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ከመለኮታዊው ሥልጣን እየቀነሰች ለሰው ልጅ ሥልጣን መጨመር ያለባት ደግሞ ጥናትና ምርምር (እውነት) ላይ ተመስርታ ነው፡፡ ለምሳሌ ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን በቅርቡ ቅዱስ ያሬድ ላይ የሰሩት አንድ ጥናትና ምርምር አለ፡፡ በቆየው የቤተ ክርስትያኗ መለኮታዊ አተራረክ መሰረት፤ ቅዱስ ያሬድ በድንግልና ኖሮ በስተመጨረሻም ሞትን ሳይቀምስ ተሰውሮ እንደጠፋ ይናገራል፡፡ ይሄ እንግዲህ የቅዱስ ያሬድን ሰዋዊ ባህሪና ሥልጣን በማኮሰስ፣ መለኮታዊ ኃይልን ለማግነን የተነገረ ዘዴ እንጂ እውነትነት ኖሮት አይደለም፡፡
ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን፤ አክሱም ድረስ በመሄድ ቅዱስ ያሬድ ላይ ያደረጉት አዲስ የጥናት ውጤት ግን የሚያሳየው ሌላ ነገር ነው፡፡ “እሴተ ትሩፋት” በሚለው መፅሐፋቸው ላይ ያሰፈሩት ይህ ጥናት የሚያሳየው፣ ቅዱስ ያሬድ በድንግልና የኖረ ሳይሆን በጋብቻ የኖረ፣ ሞትን ሳይቀምስ የተሰወረ ሳይሆን ሞትን ሞቶ ሥርዓተ ቀብር እንደተፈፀመለት ነው፡፡ አለቃ ተክለየሱስም “በኢትዮጵያ ታሪክ” መፅሐፋቸው ላይ “ቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቶችን መቀመር የቻለው በራሱ ሰውኛ ጥረት ነው” ብለውለታል፡፡ ይሄ ነው የሰውን ልጅ ባለ ሥልጣን ማድረግ ማለት፡፡
ኦርቶዶክስ ቤ/ክ በራሷ ልጆች በሚደረጉ በእንደዚህ ዓይነት ጥናትና ምርምሮች፣ የቀማቻቸውን የቅዱሳናቱንና የሰማዕታቱን ሰውኛ ሥልጣን መመለስ አለባት፡፡ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ይሄንን ስታደርግ ብቻ ነው ከብሄር ፖለቲካ በኋላ ከዘመናዊነት ጋር የሚፈጠረውን “የሰውን ልጅ ባለ ሥልጣን የማድረግ” ግብግብ ድል ማድረግ የምትችለው፡፡ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ከዘመናዊነት ጋር ግብግብ ውስጥ ያልገባው “የሰውን ልጅ ባለ ሥልጣን ማድረግ” በሚለው ሐሳብ ላይ ከዘመናዊነት ጋር በመስማማቱ ነው። የአውሮፓን ህዳሴና የዘመናዊነት ፕሮጀክት የካቶሊክ ቤ/ክ ልትቀበለው ስላልቻለች፣ አውሮፓ ያንን አስቸጋሪ ጊዜ የተሻገረው የፕሮቴስታንት ሃይማኖትን በመያዝ ነው፡፡ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ውልደትና ዕድገት በአውሮፓ የዘመናዊነት ፍልስፍና ውስጥ ለምን ትልቅ ስፍራ እንደያዘ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።
ጀርመናዊው ፈላስፋ ሄግል ደግሞ ዘመናዊነትን ከነፃነት ጋር ያስተሳስረዋል፡፡ “የሰውን ልጅ ባለ ሥልጣን የማድረግ ሐሳብ” የሚያያዘው ከኃይል ጋር ብቻ ሳይሆን ከነፃነትም ጋር ነው፤ ኃይል ነፃነትን ያመጣልና፡፡ በመሆኑም ዘመናዊነት ማለት ከውጫዊ ኃይሎች ሥልጣን በመላቀቅ፣ ውስጣዊ ፍቃድንና ነፃነትን መቀዳጀት ነው። ሌላው ኦርቶዶክስ ቤ/ክ የሰውን ልጅ ባለ ሥልጣን ማድረግ ያለባት፣ የሰው ልጅ ውስጣዊ ፍቃድንና ነፃነትን ለመቀዳጀት መቼም ቢሆን የማይታክት ፍጡር መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ጭምር ነው፡፡ ዘመናዊነት ለዚህ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ዕውቅና ይሰጣል፤ ኦርቶዶክስም ዕውቅና መስጠት አለባት፡፡
ይህ ትንቢት ነው፡፡ ምናልባት አሁን ላይ ሐሳቡ የማይረባና እንቶ ፈንቶ ሊመስለን ይችላ። ወደፊት ግን አስቀድመን የፈራነው ይደርሳል። ምናልባት ያን ጊዜ እነዚህ ሐሳቦች ይፈለጉ ይሆናል፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊው “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)
ማይበገርስችበት@gmail.com

Read 3485 times