Sunday, 26 November 2017 00:00

ከ‘ሰርቫይቫል’ ወደ ‘ኑሮ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

“-በእርግጥም የህክምና ተቋሙ ሙያዊ ሥራ አስደሳች ላይሆን ይችላል፡፡ በችሎታ ማነስ፣ ወይም
በግዴለሽነት ስህተቶች ተሠርተው ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ለ‘ሰርቫይቫል’ ስንል…“ዶከተር፣ እድሜህን
የማቱሳላን እጥፍ በእጥፍ ያድርገው!” እንላለን፡፡--”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
2010 ሩቧን እያገባደድናት ነው፡፡ አኔ የምለው…ሌላው ዓለም ያሉ ሰዎች ጊዜ፣ የዴንዘል ዋሺንግተን ‘አንስቶፐብል’ ፊልም ላይ እንዳለው አይነት ረጋ ማለት ያቃተው ባቡር ይሆንባቸዋል እንዴ! ምናልባት ብዙዎቹ ከእኛ የተሻለ እንቅልፍ ስለሚያጣጥሙ የጊዜ መሮጥም፣ መንቀርፈፍም አይታወቃቸው ሆናል፣ በነጋ በጠባ የሚጨቀጭቃቸው ነገር ስሌለ አይታወቃቸው ይሆናል፣ የኑሮ ትርጉሙ እስኪጠፋቸው ድረስ መሽቶ ሲነጋ ደስ በማይሉ ዜናዎች አእምሯቸው ስለማይሞላ አይታወቃቸው ይሆናል፡፡ ልዩነታችን ግልጽ ነው፣ እነሱ ስለ ኑሮ ስለ ነገ፣ ተነገወዲያ ያስባሉ፣ ለእኛ ደግሞ ሁሉም ነገር የኑሮ ጉዳይ ሳይሆን የ‘ሰርቫይቫል’ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡
ግን ደግሞ እንዲህም ሆኖ የማይመቹን ነገሮች እየበዙ፣ ‘መብት’ ማለት ቅንጦት ነገር እየሆነብን፣ ለምናያቸው፣ ለምንሰማቸው ድርጊቶች ሁሉ ሰብአዊ ምክንያት እያጣንላቸው…በ‘ሰርቫይቫል’ ቀጥለናል፡፡ ስለ አንዱ ጉዳይ በአደባባይ የምንለውና በጓዳችን የምንለው ‘ቆዳ ግልበጣ’ የሆነብን፣ በአሁኑ ጊዜ አእምሯችን ውስጥ ያለው አንድ ነገር ብቻ ስለሆነ ነው…‘ሰርቫይቫል!’   
የሆነ ባለስልጣን ነው እንበል፣ የሆነ መሥሪያ ቤት ኃላፊ፡፡ እና ጓዳ፣ ጓዳውን አንድ መቶ አንድ ወሬዎች ይወሩበታል፡፡
“ሰውየው በሆነ ባልሆነው እያሳበበ፣ የመሥሪያ ቤቱን ካዝና ሙልጭ አደረገው እኮ! እንደውም ሮፓክ ምን የመሰለ የናጠጡ ሀብታሞች ቤት ገዝቷል ይባላል፡፡”
“ደግሞ በእሱ ብሶ ኩራቱ! አናውቀውምና ነው፣ ከፖለቲከኞች ተለጥፎ ስልጣን እንዳገኘ የማናውቅ መሰለው እንዴ! የሆነ የአራተኛ ነው አምስተኛ ክፍል ስፖርት ምናምን አስተማሪ ነበር አሉ፡፡”
“የመሥሪያ ቤቷ ሴት አንዷም አልተረፈችውም ይባላል፡፡ እንደውም ማነው ያ ፔርሶኔል ክፍል ያለው ቀልደኛው፤ ‘ቢሯችሁ ቀሚስ የለበሰች ሴት ስዕል እንዳትለጥፉ’ ሲለን ነበር፡፡ ሰውየው ግድግዳውን ሊጥስ ይችላላ!” ሳቅ! እግረ መንገድ… አንዳንድ ጊዜ እንዲህ የሚሉ እንስቶች፣ ሌሎች ደግሞ ስለ እነሱ እኮ እንዲሁ ነው የሚሉት፡፡
“እሷ እኮ አንደኛውን የትርፍ ጊዜ ሚስቱ ሆናለች፡፡”
“የትርፍ ጊዜ ሳይሆን ቤንች ላይ ያለች ተቀያሪ ሚስት ነው የሚባለው፡፡” እንዲህ ብለውም ይሳሳቃሉ፡፡
“መፈክሩን ታውቃላችሁ…ወይ አምጪ ወይ ውጪ ነው፡፡”
እናማ… እንግዲህ ዘንድሮ ያው ማንም ሰው፣ በፊት ለፊት የሚያይ እየመሰለ፣ በጎን አይደል የሚያየው… ሰው በርከት ብሎ ሰብሰብ ባለበት ቦታ ታሪኩ ይለወጣል፡፡ ቆዳዎች ይገለበጣሉ፡፡
“እንዴት አይነት እግዜር የባረከው አለቃ መሰላችሁ!”
“ተስማምቷችኋል ማለት ነው፡፡”
“እሱ ያልተስማማን ማን ሊስማማን ነው! የሚገርማችሁ እኮ እቤቱ ከሄደ በኋላ የመሥሪያ ቤቱን ሥራ ነው የሚሠራው፡፡ ሚስቱ ሁልጊዜ በዚህ ትበሳጨለች አሉ፡፡ ከራሱ ህይወት ይልቅ ለመሥሪያ ቤቱ እድገት የሚያስብ ነው፡፡”
“ደግሞስ ጠባዩስ ቢሆን፣ ኩሩ፣ ሰው እንዲህ አይነት የመልአከ ባህሪይ ይኖረዋል!”
“ከመሥሪያ ቤቱ ገንዘብ ሁሉም የድርሻውን እየወሰደ፣ እሱ እንኳን ሊወስድ ለነዳጅ እንኳን የሚሰጠውን እየቆጠበ ይመልሳል ነው የሚባለው፡፡”
“በዚህ ላይ ለሴቶች ያለው አክብሮት…” እንዲህ፣ እንዲህ እየተባለ በአደባባይ ‘ቆዳ ግልበጣው’ ይቀጥላል፡፡ ነገራችን የ‘እውነት’ ‘ሀሰት’ ሳይሆን የ‘ሰርቫይቫል’ ሆኗላ! የተናገርነው ነገ ሰውየው ዘንድ ደርሶ ጉድ ቢያደርገንስ!
“ዶክተር፤ በጣም ነው የምናመሰግነው፡፡ አንተ ባትኖር ኖሮ ምን እንደምንሆን አናውቅም፡፡ እህታችን አሁን እፎይ ብላለች፡፡”
“ምንም አይደል፣ ሥራዬ ነው፡፡ ዋናው ነገር ሁኔታዋን በቅርበት ተከታተሏት፡፡ ችግር ካለ ወዲያውኑ ይዛችኋት ኑ፡፡”
ከዛ በኋላ ቤታችን እንሄዳለን፡፡ ታማሚያችን ማቃሰቷን አላቆመችም፡፡ እኛም ቆዳ ግልበጣ እንጀምራለን፡፡
“ልትታከም ገብታ ጭራሽ ብሶባት ትውጣ! ምን አይነት የጉድ ዘመን መጣ! መድሀኒት ብለው የሚወጓቸው መርዝ ነው እንዴ!”
“እነሱ እንደሁ ጉንፋን የያዘውንም፣ ራሱን ያመመውንም፣ ‘ጎኔን ወጋ አደረገኝ፣” ያለውንም፣ ቢላዋ ይዘው መቅደድ ብቻ ነው፡፡”
“እነሱ ምን ያድርጉ፡፡ ፋሻ መጠቅለል ያሳዩዋቸውና በቃ ‘ዶክተር ሆነሀል፣ ዶከተር ሆነሻል’ ይሏቸዋል…”
እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡
እናማ… አስቸጋሪ ነው፡፡ ዶክተሩን፤ የሚመስለንን ፊት ለፊት ነግረነው፣ ማለትም… “ዶክተር፣ ኦፕራሲዮን ካደረግሀት በኋላም ለውጥ የላትም፣ እንደውም ማቃሰቷ ብሷል፣” ብለነው ነገ የት ልንገባ! ለህክምና ተመልስን ስንመጣ ምን ልንሆን! እናማ በእምነት ሳይሆን በፍርሀት ለተበላሸው ሥራ ሁሉ “እጃቸው እኮ ወርቅ ነው”! የምንለው የመልስ ምቱን ፈርተን ነው፡፡
ነገራችን የ‘እውነት’ ‘ሀሰት’ ሳይሆን የ‘ሰርቫይቫል’ ሆኗላ!
ከወራት በፊት የሆነ ነው፡፡ ዘመዳሞች ነገሮች እያወሩ ሳለ፣ አንዲት የሩቅ ዘመዳቸውን ስሟን መንገድ፣ ለመንገድ ይጎትቱታል፡፡
“እንደው ማን ይሙት አሁን እሷ-- እውነት የእኛ ዘመድ ነች! እኛ ዘመዶች ውስጥ እንደ እሷ አይነት ሰው የለም…”
“ይሄኔ እኛ ሳናውቅ ኮንትሮባንድ ትሆናለች፡፡”
“ብታዩዋት እኮ ሰው፣ ሰው አይመስላት! ስትቆናጠር ዓለምን የተቆጣጠረች ነው የምትምስለው…”
ብቻ ልጅቱ በሌለችበት ያልተባለችው የለም፡፡
ከሳምንታት በኋላ በርከት ያለ ዘመድ በሆነ ምክንያት ይሰባሰባል፡፡ እሷም አለች፣ “እንደውም ከወትሮው ይልቅ በጣም ዘንጣ” ነው የመጣችው። እና ያኔ እንደዛ ምን የነካው እንጨት ሲያደርጓት የነበሩት ሁሉ ቆዳቸውን ገልብጠዋል፡፡
“አንቺ! ዘመድ እንኳን አይናፍቅሽም! እኛ እኮ በተገናኘን ቁጥር ሳናነሳሽ ውለን አናውቅም…”
“አለሁ፣ ባንገናኝ ነው፡፡”
“እንዲህ ሰዉ በተጨካከነበት በአሁኑ ጊዜ እንዳንቺ አይነት የሚቀናበት ዘመድ ማግኘት እኮ ጽድቅ ነው…”
ምናምን ይሏታል፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ነገሩ ሞልቶ ፈሰሰባት መሰለኝ፣ ሰው ሁሉ እየሰማ ጮክ ብላ ተናገረች።
“ከመቼ ወዲህ ነው የሚቀናብኝ ዘመድ የሆንኩት? በቀደም እሷ የእኛ ዘመድ አይደለችም፣ ኮንትሮባንድ ሳትሆን አትቀርም ስትሉ አልነበረም እንዴ!” አለችና ሳቅ ሞልቶበት የነበረውን ቤት አሳቀቀችው አሉ፡፡ አብሮ ሲያማ ውሎና አድሮ ሄዶ ሹክ የሚል መአት ነው።  በመሀላቸው የሚኖረውን እርስ በእርስ መጠራጠር አስቡት፡፡ ፊት ለፊቷ ያ ሁሉ “ስናፍቅሽ ነጋ” አይነት ወሬ ዝም ብሎ አልነበረም፣ ዓላማ ነበረው፡፡
ነገራችን የ‘እውነት’ ‘ሀሰት’ ሳይሆን የ‘ሰርቫይቫል’ ሆኗላ!
በእርግጥ በጓዳችን የምናወራው ሁልጊዜ የሀሰት አሉባልታ ነው ማለት አይደለም፡፡ ምንም የማይወጣለት እውነት ሊሆን ይችላል። ግን በአደባባይ ብንናገረው፣ ብንተነፍስው የሆነ ነገር ይቀርብናል፣ የሆነ ነገር እንነጠቃለን ብለን ስለምንሰጋ ነው፡፡ የ‘ሰርቫይቫል’ ነገር አስቸጋሪ ነው።
በእርግጥም የህክምና ተቋሙ ሙያዊ ሥራ አስደሳች ላይሆን ይችላል፡፡ በችሎታ ማነስ፣ ወይም በግዴለሽነት ስህተቶች ተሠርተው ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ለ‘ሰርቫይቫል’ ስንል…
“ዶከተር፣ እድሜህን የማቱሳላን እጥፍ በእጥፍ ያድርገው!” እንላለን፡፡
በየስብሰባው ላይ “ሌሎቹ ብለውታል፣ እኔ እንኳን የምጨምረው ነገር የለኝም፣” ብሎ ከእሱ በፊት የተናገሩት ሰዎች ያሉትን ሁሉ የሚደግመው ሰው፤ ምናልባት ቤቱን እያሰበ ይሆናል፤ ሚስትና ልጆቹን እያሰበ ይሆናል፤ የእሱን እርዳታ ከወር ወር የሚጠብቁ የቤተሰብ አባላትን እያሰበ ይሆናል፡፡ ስለሆነም…
“በእውነቱ በአሁኑ ጊዜ ማኔጅመንቱ የጀመረው ድርጅቱን መልሶ የማዋቀር ተግባር በጣም የሚያስደሰት ነው፡፡ ሠራተኛው ሁሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፣” ሲል ልቡ የነገረችው እውነት ስለሆነ አይደለም። “መልሶ ማዋቀሩ መሥሪያ ቤቱን ፈርሶ የተረሳ መንደር አስመስሎታል፣” ቢል “እኔንም አፍረሰው ይረሱኛል” ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡
ነገራችን የ‘እውነት’ ‘ሀሰት’ ሳይሆን የ‘ሰርቫይቫል’ ሆኗላ!
ስለ ‘ሰርቫይቫል’ ብቻ ሳይሆን ስለ ‘ኑሮ’ የምናስብበትን ጊዜ ያቅርብልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4066 times