Saturday, 25 November 2017 09:47

አለንጋውን የደበቀ ልጆቹን መረን ይለቃል!

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(5 votes)

    ከዛሬ 25 ዓመት በፊት የብሄር፣ ብሄረሰቦችን እኩልነት፣ ነፃነትና፣ መብት ለማስከበር በሚል በመላ ሀገሪቱ የተዘራው የዘርና የጎጥ ፖለቲካ፤ እነሆ ዛሬ መኸሩ እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡ ዛሬ በዘርና፣ በጎጥ ተቧድኖ እርስ በርስ መጋጨት፤ በግጭቱም የተነሳ በሺ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን፣ በአስከፊ ሁኔታ አካላቸው ሲጎድል፤ ቤት ንብረታቸው ሲዘረፍና የእሳት ሲሳይ ሲሆን፤ እንዲሁም ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉ ማየት የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡
ይልቁንም ደግሞ በዚህ የዘርና ጎጥ ተኮር የእርስ በርስ ግጭት የተነሳ እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ህይወታቸውን ያጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግፉአን ወገኖቻችንን በጥቂት ቀናት ውስጥ መቅበር ተራ የአዘቦት ጉዳይ ሆኖአል። ዘርና ጎጥን መሰረት አድርጎ የተዘረጋው የሀገሪቱ የፌደራል ሥርአት ፕሮጀክት፤ በመሠረታዊ ባህሪው የተነሳ የታሰበውን ያህል የብሄር ብሄረሰቦችን ነፃነትና እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የፖለቲካ ጥያቄዎችን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመመለስ፣ በተለይ ደግሞ ብሄር ብሄረሰቦች በመተማመንና በመፈቃቀድ በሰላም እንዲኖሩ ለማድረግ አላስቻለም፡፡
ጭርሱኑ በዘርና በጎጥ እየተቧደኑ፣የልዩነት የእሾክ አጥር መስራት፤ በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን በእኩል አይን አለማየት እንዲሁም በሌላ ክልል የሚኖርን ህዝብ “የሌላ ህዝብ” አድርጎ መቁጠር  በሀገሪቱ እንዲነግስ አድርጓል። ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ ክልሎች ለዘመናት ተስማምተውና ተጋባብተው የኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችን ሆን ብሎ በማፈናቀል፣ አንዱን ብሄር ለይቶ በልዩ ክብካቤ በአውሮፕላን አሳፍሮ በመሸኘት፣ ሌላውን ብሄር ደግሞ ከቀዬው ነቅሎ፣ ሀብትና ንብረቱንም ዘርፎና አቃጥሎ የትም እንዲበተን ማድረግ ልክ እንደ ህጋዊነት የሚቆጠር ሆኗል፡፡  ይህን ድርጊት የፈፀሙ የክልል ባለስልጣናት፣ የወንጀል ጀብዷቸውንና አሳፋሪ ዝናቸውን፣ በመንግስት ጋዜጣ ዘና ብለው በግልጽ የሚተርኩት፣ ስለ ነገ የታሪክና የህግ ተጠያቂነት ቅንጣት ታህል እንኳ ሳይጨነቁ ነው። ላለፉት 26 ዓመታት ፈር በለቀቀ ሁኔታ አለመጠን የተራገበው የዘር ፖለቲካ፤ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል አለመተማመንና መቃቃር በመፍጠሩ፣ በየቦታው የብሄር ግጭት እንዲፈጠርና የወገኖቻችን ሞት እንዲረክስብን አድርጓል፡፡
የሀገሪቱን የወደፊት እድል የሚወስኑ የተማሩና የሰለጠኑ ዜጎችን እንዲያፈሩ በየክልሉ የተቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በዘርና በጎጥ ተቧድነው፣ የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ተወላጅ የሆኑ ተማሪ ወገኖቻቸውን “በባዕድነት” በመፈረጅ፣ ጥቃት ለማድረስ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ ህገወጥ ወጣቶች መፈልፈያና መሸሸጊያ ዘመናዊ “ጎራ” መሆን ጀምረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ እርስ በርስ ከሚለያያቸው ጥቂት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ የታሪክ እንቅፋቶች ይልቅ በጋራ የሚያስተሳስራቸውና አንድ የሚያደርጓቸው እጅግ በርካታ የአብሮነትና የብዝሀነት እሴቶች እንዳሏቸው በመረዳት የተዘረጋውን የፌደራል ስርአት፣ ብሄር ብሄረሰቦችን የሚያገናኝ ድልድይ በመስራት ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና ይጫወታሉ ተብለው ሲጠበቁ ከነበሩት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ውስጥ ቁጥራቸው ቀላል የማይባለው፣ ሌት ተቀን የሚባትሉት፣ በዘርና በጎጥ ተቧድነው፣ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የልዩነት ግንብ በመገንባት ነው።
ላለፉት 26 ዓመታት ያለ ገደብ ሆን ተብለው የተነዙትንና የሀገሪቱን ህዝቦች ድንቅ አብሮነት ያዛቡትን በርካታ ማስረጃ የሌላቸውና እውነትነታቸው ፈጽሞ ያልተረጋገጠ የታሪክ ንግርቶችን በማስተካከል፣ እንዲያው ቢያንስ እንኳ ለልጅ ልጆቻቸው እጅግ የተሻለች፣ ህብረ-ብሄራዊ ስሜት የዳበረበት ሀገር ለማቆየት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና ይጫወታሉ ተብለው ከተገመቱት ምሁራን ውስጥ በርካታዎቹ ተሰልፈው የተገኙት፣ እነዚህን ሀሰተኛና ጨርሶ ያልተረጋገጡ የታሪክ ንግርቶች ከሚፈበርኩትና ከሚያሰራጩት ጎራ ውስጥ ነው፡፡
ማንም “ጊዜ የሰጠኝ ነኝ” ባይ ሁሉ፣ እነዚህን ሀሰተኛ የታሪክ ንግርቶች እየተንተራሰ፣ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ያለ አበሳቸው “የአያት ቅድማያታችሁን ሂሳብ አወራርዱ” በማለት የቻለውን ያህል ሲገድልና ሲያቆስል፤ “ኧረ በህግ!” የሚል መንግስታዊ አካል ድምፁ ከጠፋ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የብሄር ግጭቶችና ጥቃቶች ጉዳይ በመንግስት በኩል እስካሁን ድረስ ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ እናም ከግጭቶቹ በቂ ትምህርት መውሰድ አልተቻለም፡፡ በተለይ ደግሞ ከተካሄዱት የብሄር ግጭቶችና ጥቃቶች ጋር በተያያዘ፣ በዜጎች ላይ የተፈፀሙ እጅግ በርካታ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን፣ ነገሬ ብሎ ያጤናቸውና አጥፊዎችን ህግ ፊት ለማቅረብ የጣረም የቻለም የመንግስት አካል እስካሁን አልተገኘም፡፡
በዚህ የተነሳ ህግ ፊት ቀርበው እንደ እጅ ስራቸው መጠን ዋጋቸውን ሊያገኙ ይገባቸው የነበሩ ወንጀለኞች፣ በጎዳናው ላይ በነፃነት እንዲመላለሱና ሌላ የብሄር ግጭት እንዲቀሰቅሱ፤ ሌላ የብሄር ጥቃት እንዲፈጽሙ በድጋሚ እድሉን እነሆ ዛሬም ማግኘት ችለዋል፡፡ ትናንት በሐገሪቱ ውስጥ ፍትሀዊ ያልሆነና ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ሳያንስ፣ ያሻቸውን ነገር ባሻቸው ሰው ላይ የሚፈጽሙበት የግል “እስር ቤት” ሲያቋቁሙ፣ “ኧረ በህግ አምላክ ግደፉ!” ያልተባሉት “ጉደኛ” ነጋዴዎችና የጥቅም ተጋሪ የመንግስት ባለስልጣናት፤ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴአቸውንና የዶላር የኮንትሮባንድ ዝውውራቸውን የበለጠ ለማሳለጥ ብለው ዛሬ የብሄር ግጭት እየቀሰቀሱ ህዝብ ማጫረስ ጀምረዋል፡፡ እንደ ሌሎቹ ሁሉ በመቶና በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑትን እነዚህን ወንጀለኞችም “ዝንባቸውን እሽ” ለማለት ድፍረቱም ሆነ ፍላጎቱ ያለው ወገን፤ እስካሁን “እኔ አለሁ” አላለም፡፡
የማታ ማታም ልክ ሴኔጋላውያን፤ “የኮከነት ፍሬ አናቱ ላይ የተፈረከሰበት ሰው፣ ቀጥ ብሎ መቆም አይችልም” እያሉ እንደሚተርቱት፣ ዜጎች ዛሬ በህገ መንግስቱ በተደነገገው መሰረት፣ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በነፃነት የመኖር፣ የመንቀሳቀስና ሰርቶ የመኖር መብታቸውን የመጠቀም ፍላጎታቸው እንዲጨልምና በተዘረጋው የፌደራል ስርአት ላይ እምነት እንዲያጡ እንዲሁም በኢህአዴግና በሚመራው መንግስት ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ተገደዋል፡፡
እንግዲህ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ መቅረብ ያለበት አንድ ወሳኝ ጥያቄ አለ፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ያለ ነገር እንዲፈጠርና በተለያየ አካባቢ የብሄር ግጭት ቀስቅሰው ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋትም ሆነ ለበርካታ የመንግስትና የህዝብ ንብረት መውደም  ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችም ሆኑ የመንግስት አመራሮች፣ በህግ ተጠያቂ ሆነው፣ የእጃቸውን ያላገኙበት ሚስጥር ከቶ ምንድ ነው?
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን ጥያቄ ለመመለስ፡ የመጠቀ አሰተሳሰብ ባለቤት መሆን ወይም ደግሞ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ማካሄድ ጨርሶ አያስፈልግም፡፡ የህግ የበላይነት በሌለበት በየትኛውም ሀገር ቢሆን፣ ህገ ወጦችና ወንጀለኞች የልባቸውን እየሰሩ፣ ያለ ህግ ተጠያቂነት በነፃነት የመፏለል እድል ማግኘት እንደሚችሉ፣ በጣም ግልጽ ነው፡፡ ለህግ የበላይነት ቁብ የሌለውና ራሱ ያወጣውን ህግ፣ ከሁሉ ቀድሞ ራሱ የሚጥስ እንደ ኢህአዴግ ያለ ገዢ ፓርቲ ያላት፣ የሀገራችን የኢትዮጵያ ነገርም እንዲሁ ነው፡፡
ጉዳዩ አይሁዳውያን “አለንጋውን የደበቀ ልጆቹን መረን ይለቃል” እንደሚሉት አይነት ነው፡፡ ኢህአዴግ የዲሞክራሲ ሥርአት አልፋና ኦሜጋ ለሆነው የህግ የበላይነት መከበር እንዲህ “ኬሬዳሽ” እንዲሆን ያደረገው በዋናነት የመነጨው፣ ከድርጅቱና ከአመራሩ አምባገነናዊ ባህሪ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከውልደቱ ጀምሮ እስካሁን ያለው ታሪኩና ነገረ ስራው በግልጽ እንደሚያስረዳው፤ በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ከዋናው መሪ ተዋናይነት በቀር ቅንጣት ታህል ዝቅ ያለ ሚና ለመጫወት የማይፈልግ፤ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ከደጋፊ ተዋናይነት የዘለለ ሚና እንዲጫወቱ ፈጽሞ የማይሻና የማይፈቅድ፤ በተለይ ደግሞ ሌሎችን እየገፋ፣ ሁሉን ለኔና “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚል አምባገነን ድርጅት ነው፡፡
ጠላቶች የሚላቸውን ሀይሎች በሀይል በማንበርከክና በማስገበር መርህ ጥርሱን የነቀለው “የእሳቱ አብዮተኛ” ትውልድ አካል የሆነው የመጀመሪያው የኢህአዴግ አመራርም፣ ለዲሞክራሲ ሥርአት ግንባታ፣ አፋዊ ብቻ የሆነ አመለካከትና ቁርጠኝነት ያለውና፣ በእጅጉ አምባገነንነት የተጠናወተው አመራር ነበር፡፡
በዚህ የተነሳም ላለፉት 26 አመታት የዘረጋው ስርአት፣ ህዝቡ መልካም አስተዳደር ተነፍጎት በከፍተኛ ሁኔታ የተማረረበት፤ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ሙሉ በሙሉ ያልተከበሩበት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ የፖለቲካ ምህዳሩ ሆን ተብሎ የጠበበበት፣ የብዝሀ ፓርቲ ስርአት በማዳፈን በምትኩ የኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ሥርአት የተገነባበት፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ እንዳይሆኑ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር በማድረግ፣ከህዝባዊ ተቋምነት ወደ ኢህአዴግ መር የፓርቲ ተቋምነት የተቀየረበት፣ አማራጭ ሀሳቦችና የተሟላ የህዝብ ውክልና እንዳይኖር ሁሉም መንገዶች በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ የተደረገበት የፖለቲካ ስርአት ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የህገ መንግስቱንና የፌደራል ስርአቱን ዋነኛ መርሆዎች ሆን ብሎ በመጣስ፣ “የሀገሪቱን ብሄራዊ ኬክ” የመብላት ሂደቱ ፍትሀዊ እንዳይሆን የተደረገበት፣ በዚህም አንዱ የሀገሪቱ የበኩር ልጅነት እንዲሰማውና የስርአቱ ተጠቃሚነት “ባለ ልዩ መብት ነኝ” እንዲል፤ ሌላው ደግሞ የበይ ተመልካች ከመሆን አልፎ ከእርሻ መሬቱ በመናኛ ካሳ እየተነቀለ፣ የትም የተበተነበት ስርአት፤ በሀገሪቱ እግር እንዲተክል አደርጓል። ከሁሉ የከፋው ደግሞ የኢህአዴግ አመራር፣ ለህግ የበላይነት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ትኩረት በመስጠቱ፣ የድርጅትና የመንግስት ባለስልጣናቱ፣ ከጥቅም ተጋሪዎቻቸው ጋር በመላ ሀገሪቱ አለ አንዳች ሀይ ባይ፣ ያሻቸውን እንዲያደርጉ መረን መለቀቃቸው ነው፡፡
አሁን ያለው አመራርስ እጁ ከየት ነው? እንዲያው ሌላውን ነገር ትተን ከራሱ ከአህአዴግ ወቅታዊ ግምገማ እንኳ ብንነሳ፣ አሁን ያለው የኢህአዴግ አመራር፣ ከጊዜው ጋር መራመድ አቅቶት፣ በኋላ ቀርነትና በችግር ውስጥ ተደብቆ ለመኖር የሚፈልግ፤ ችግሮቹ በወሳኝ መልኩ እንዳይፈቱ የተለያዩ እንቅፋቶችን የሚፈጥር አመራር ነው፡፡ አሁን ያለው የኢህአዴግ አመራር፣ ህዝቡን በተለይም ወጣቱን በስራ ፈጠራ ወደ ልማት ከማስገባት ይልቅ ፊቱን ወደ ሁከትና ግጭት እንዲመልስና ከዋናው የእድገትና የተጠቃሚነት አጀንዳ እንዲወጣ ለማድረግ የሚጥር ነው፡፡ አሁን ያለው የኢህአዴግ አመር፣ “አመለካከቱ ጨርሶ ያልጠራና ጎራው የተደበላለቀበት”፤ በራሱ በኢህአዴግ አገላለጽ፣ በከፍተኛ “የኪራይ ሰብሳቢነትና ጥገኛ አመለካከት” ክፉኛ የተዘፈቀ ነው፡፡ አሁን ያለው የኢህአዴግ አመራር፣ ከደሀው ህዝብ ግብርና ከውጭ በብድር ተሰብስቦ፣ ለስራ የተመደበላቸውን ባጀት በምን ላይ እንዳዋሉት እንኳ ማስረዳት የማይችሉ ዘራፊ ባለስልጣናቱን በቁርጠኝነት አምርሮ ከመታገልና ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ አድበስብሶ የሚያልፍ፤ መልካም አስተዳደር በመንፈግ ህዝብን ያማረሩና በተለያየ መንገድ በህዝብ ላይ በደል የፈፀሙ ባለስልጣናትን ህግ ፊት አቅርቦ፣ ከመፋረድ ይልቅ ከአንዱ ቦታ አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ በመመደብ መሸሸግ የሚመርጥ ኋላ ቀር አመራር ነው፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው፤ የኢህአዴግ አመራር፣ ለዜጎች በገባው ቃል የማይገኝ፣ ሙስናንና ህገወጥነትን ለመታገል ቁርጠኝነት ጨርሶ የጎደለው፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ከማሻሻል ይልቅ ራሳቸውን ለማበልፀግ ተግተው የሚሰሩ ዘራፊ ባለስልጣናትን አይቶ እንዳላየ የሚያልፍ፣ ተልዕኮ አልባ የሆነና ከፍተኛ የመበስበስ ደዌ የተጠናወተው ነው፡፡
የሆነ ሆኖ እንግዲህ በመጨረሻ የሚነሳው ጥያቄ፤ “ለመሆኑ ከዚህ አዙሪት የመውጫው መላ ምንድን ነው?”    የሚለው ነው፡፡ መላ አለን የምትሉ ግቡ ተብላችኋል፡፡

Read 2070 times