Print this page
Sunday, 26 November 2017 00:00

“የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያውያን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(51 votes)

“የአባይ ውሃ ለግብፃውያን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው”

  ግብጽ በህዳሴው ግድብና በአባይ ውሃ ላይ የምታደርገው እንቅስቃሴ  አገራቱ የተፈራረሙትን ስምምነቶች የሚጥሱ ናቸው ያለው የኢትዮጵያ መንግስት፤ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን በጉዳዩ ዙሪያ የሚያቀርቡት ዘገባም እንዳስቆጣው ተገለጸ፡፡  
የግብፅ መንግስት፤በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከሱዳንና ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገው ቴክኒካዊ ድርድር መክሸፉን ያስታወቀ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤”ኢትዮጵያ አሁንም በግድቡ ጉዳይ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ተባብራ መስራቷን ትቀጥላለች” ብሏል፡፡  የግብፅ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ሞሃመድ አብደል አተይ አልሞኒተር ለተሰኘው የአገሪቱ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት፤“ግብፅ የቴክኒካል ድርድሩ መክሸፉ ያስጨንቃታል፣ ከሱዳንና ከኢትዮጵያ ጋር በጉዳዩ ላይ የሚደረገው ትብብርም አደጋ ተጋርጦበታል” ብለዋል፡፡ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፤ “የአባይ ውሃ ለግብፃውያን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው” ማለታቸውን የዘገበው ዋሽንግተን ፖስት፤ “ማንም አካል የግብፅን የውሃ ድርሻ ቅንጣት ታህል እንኳ መንካት አይችልም” ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ጠቁሟል፡፡    ፕሬዚዳንቱ ይሄን ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ያስተላለፉት ሰሞኑን በናይል ሰርጥ (ዴልታ) ላይ የተገነባ የዓሳ ማርቢያ ጣቢያ መርቀው  በከፈቱበት ወቅት መሆኑን ዘገባው አመልክቷል። “ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና ወዳጆቻችን፣ ለእድገት ያላቸውን ፍላጎት በበጎ እንመለከተዋለን” ያሉት አል ሲሲ፤“እኛም የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ኃላፊት አለብን፣ ውሃው ለኛ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡
በሰሞኑ የአባይ እና የህዳሴው ግድብ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በበኩላቸው፤ “ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግብፅን ይጎበኛሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ዋዜማ ላይ  እንዲህ ያሉ አፍራሽ አስተያየቶች መቅረባቸው ተገቢ አይደለም” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት፣በግብፅ መገናኛ ብዙኃንና በአንዳንድ የመንግስት ተቋማት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ያውቃቸዋል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በሆደ ሰፊነት የሚያልፍበት ምክንያት ትብብር ብቸኛው በጋራ የመስሪያ አማራጭ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ በግብፅ በኩል አሁን ያለው እንቅስቃሴ በሶስቱ
የተፋሰሱ ሀገራት የተፈረመውን “የመርህ ስምምነት” (Declaration of Principle) የሚጥስ ነው ያሉት አቶ መለስ፤”
ይህ የመርህ ስምምነት አሁንም እንዲከበር ኢትዮጵያ ታሳስባለች” ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ በግብፅ የተደረገው የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ በስኬታማነት ያልተጠናቀቀውም “የ1929 እና የ1959 ስምምነትን ተቀበሉ፣አንቀበልም” በሚል መሆኑን ቃል አቀባዩ አውስተዋል፡፡  
በጉዳዩ ላይ ሰፊ ሀተታ ያቀረበው አል ሞኒተር ጋዜጣ በበኩሉ፤ በድርድሩ ላይ የተሳተፉ የግብፅ ባለስልጣናት ነግረውኛል ብሎ ባሰፈረው
መረጃ፣ግብፅ ግድቡ በውሃ ኮታዋ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ የቴክኒክ ቡድኑ በግልፅ ያሳውቀኝ በማለቷና የ1959 ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ከመፈለጓ ጋር በተያያዘ ድርድሩ ያለ ስምምነት ሊቋጭ መቻሉን ጠቁሟል፡፡ አቶ መለስ አለም በበኩላቸው፤ኢትዮጵያ ይህን የ1959 ስምምነት ፈፅሞ አትቀበልም ብለዋል፡፡
 “የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጉዳይ ብቻ ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ግድቡ ከኳታር በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እየተገነባ እንደሆነ አስመስለው  የሚያቀርቡት መረጃ ተገቢ አይደለም ብለዋል - የግድቡ የገንዘብ ምንጭ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በመግለጽ፡፡ “የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው” ያሉት አቶ መለስ፤”ሀገሪቱ ድህነትን ለመዋጋት በምታደርገው መሰል ጥረት የማንንም ቡራኬና ይሁንታ አትጠብቅም፤የተፈጥሮ ሃብታችንን መጠቀም መብታችን ነው” ብለዋል፡፡

Read 10330 times