Sunday, 26 November 2017 00:00

አሜሪካ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የፀረ-ሽብር ህጉን የሚጠቀምበት መንገድ በእጅጉ አሳስቦኛል አለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

    የኢትዮጵያ መንግስት የፀረ ሽብር ህጉን የሚጠቀምበት መንገድ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው የገለፁት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሣደር፤ በሽብርተኝነትና የፖለቲካ አመለካከትን በማንፀባረቅ መካከል ልዩነት መበጀት አለበት ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሥራ ከጀመሩ 6 ሣምንታት ያስቆጠሩት አምባሳደር ማይክል ሬነርን ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከትላንት በስቲያ ባደረጉትቃል ምልልስ፣ ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ በመግለፃቸው የታሰሩና በሽብርተኝነት የተከሰሱ ግለሰቦች ጉዳይ አሜሪካንን በእጅጉ እንደሚያሳስባት ጠቁመው፣ መንግስት ጉዳዩን በደንብ እንዲያጤነው ጠይቀዋል፡፡
በአለማቀፍ የፀረ ሽብር ዘመቻ ኢትዮጵያ የአሜሪካ አጋር መሆኗን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ መንግስት የፀረ ሽብር ህጉን ለሰላማዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች መጨፍለቂያነት ማዋል እንደሌለበትም እስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የፀረ ሽብር ህጉን የሚጠቀምበት ሁኔታ ተገቢነት ላይ መንግስታቸው ጥያቄ እንዳለውም አምባሳደሩ  አስታውቀዋል፡፡
በፖለቲካ ልዩነትና በሽብርተኝነት መካከል ግልፅ ድንበር ሊበጅ እንደሚገባም የተናገሩት አምባሣደሩ፤ ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚገልፁ ዜጎች ይበልጥ መበረታታት እንጂ የፀረ ሽብር ህጉ ሊመለከታቸው አይገባም ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች ጉዳይ መንግስት በደንብ እንዲያጤነው ከሃገሪቱ ባለስልጣናት ጋር እየተመካከሩ መሆኑን አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብት አያያዙን እንዲያሻሽል ሃገራቸው ግፊት እንደምታደርግም ተናግረዋል፡፡
 “አሁን ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ ወቅት ነው” ያሉት አምባሳደሩ፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች መንግስታቸውን በእጅጉ እንደሚያሳስበው ጠቁመው፣ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ መንገድ ተከትለው የፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነታቸውን በነጻነት እንዲያንፀባርቁ እናበረታታለን ብለዋል፡፡

Read 5781 times