Sunday, 19 November 2017 00:00

የአቶ ጁነዲን ባሻ አስተያየቶች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን  ባለፈው ሳምንት ያካሄደው 10ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በስፖርቱ  ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል።  በአባላቱ ብዛት ከአፍሪካ ግዙፉ የሆነውና በአንጋፋነቱ ሊጠቀስ የሚበቃው የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ አሁን የሚገኘው በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ከ38 ቀናት በኋላ በአፋሯ ከተማ ሰመራ የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር  በታዛቢነትና በአማካሪነት እየሰራ ሲሆን የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጠቅላላ ጉባዔው ሳይመሰረት መቅረቱም ሰሞኑን ተተችቷል፡፡ ፌደሬሽኑ ባለፈው 1 ወር በተለያዩ የውዝግብ አጀንዳዎች ከየአቅጣጫው እየታመሰ ነበር። በተለይ ከሳምንት በፊት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተሳታፊዎች ተረጋግተው ወደ የጋራ ግብ ለመድረስ ሲቸግራቸው ታዝበናል፡፡ ለመሆኑ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ወዴት እያመራ ነው? ኳሱንስ ሊመራው ነው? ላለፉት 4 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት አቶ ጁነዲን ባሻ ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የሚከተሉትን አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡

በ10ኛው ጠቅላላ ጉባዔ የውዝግብ መንፈስ ላይ…
ምርጫው ስነስርዓቱን በጠበቀ ሂደት ማለፍ ነበረበት፡፡ የተወዳዳሪዎች ብቁነት፤ ህጋዊነትና ተገቢነት ታይቶ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንን፤ የካፍ እና የፊፋ  እንዲሁም የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ደንቦችን በመፈተሽ ሊሰራ ይገባል፡፡ እኔም በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ በማለፍ በፕሬዝዳንትነት ምርጫው የምወዳደረው፡፡
በዘልማድ የነበረው አሰራር  እንዲቀጥል ፍላጎት የነበራቸው ጥቂት የጉባኤው ተሳታፊዎች  ምርጫው አስቀድሜ የገለፅኳቸውን ወሳኝ ሂደቶች ሳያልፍ በችኮላ በ10ኛው ጠቅላላ ጉባኤው የመጀመርያ ቀን ካልተካሄደ ብለው ነበር፡፡ አብዛኛው  የጉባዔው ተሳታፊ ግን ይህን አልተቀበለውም ፡፡ በዘልማድ ምርጫው መካሄዱ ተገቢ አይደለም ፤ ተወዳዳሪዎች ማንነታቸው በዝርዝር ታውቆ፤ በውክልናቸው አስፈላጊው ማጣራት ተሰርቶ፤ ህግና ደንብ በተከተለ አካሄድ መከናወን አለበት በሚል መክሯል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫው ለአስር ቦታዎች አስራ አንድ ሰዎች ብቻ መወዳደራቸው ሂደቱን የተሟላ አያደርገውም ነው። ምርጫ ተካሄደ ሳይሆን በተዋፅኦ ሃላፊነት ተሰጠ ወይንም ምደባ ተካሄደ ስለሚሆን ነው። ስለዚህም ይህ መቀየር እንዳለበት ጉባዔው ተወያይቶበታል፡፡ ፌደሬሽኑ ለስራ አስፈፃሚ አባልነት በሚወዳደሩ እጩዎች ላይ ገደብ ማድረግ የለበትም ነው፡፡ ጉባኤው ላይ ምርጫው እንዲራዘም የተወሰነው በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተቃራኒ ሃሳቦች በተሳታፊዎቹ ተንሸራሽረው ነው።  በጉባኤው ላይ የኦዲት ሪፖርት፤ የ2010 በጀት ዓመት እቅድ  እና በተሻሻሉ ደንቦች ላይ በቂ ውይይት ተደርጓል፡፡ ሆኖም ግን የተወሰኑ ግለሰቦች የግል ተልዕኳቸውን ለማድረስ ሲሉ ተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረብና ቤቱን ወደየማይሆን አቅጣጫ ለመውሰድ ሲሞክሩ ነበር፡፡ ፌደሬሽኑ የሰራቸውን መልካም ጎኖች ወደጎን በመተው እና ደካማ ጎኑ ላይ በማተኮር ሚዛናዊ ያልሆነ አስተያየት ሲሰጡ ነበር፡፡ ዋና ትኩረት መደረግ ያለበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በሚያድግበት አንኳር ጉዳዮች ላይ፤ ትክክልኛ ግለሰቦች ወደውድድር መድረኩ በሚመጡበት፤ ለህግ በምንገዛበት አሰራር ላይ ነው፡፡

ስለፕሬዝዳንትነቱ?
በእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትነት ማገልገል የማያመሰግን ሊሆን ይችላል፡፡ ባለፉት አራት ዓመት በወንበሩ ላይ በሃላፊነት ሳገለግል በመቆየቴ ብዙ  ልምድና እውቀት አግኝቻለሁ፡፡ ከዚያ በመነሳት ደግሞ አዳዲስ ለውጦች ለመፍጠር የሚያስችሉ ዝግጅቶች በእጄ ላይ ይገኛሉ። የእግር ኳሱ ፕሬዝዳንት ሆኖ መስራት ብዙ ድካም የሚጠይቅ፤ ትችት የሚበዛበትና በተለያየ አቋም አስታራቂ ሆኖ ለመምራት የሚፈትን ነው፡፡ በእግር ኳሱ አስተዳደር ውሳኔ ላይ የሚያገባውም የማያገባውም ጣልቃ  ለመግባት ሲሞክር ይታያል። ይህን ተቋቁሞ አመራር መስጠትን የሚጠይቅ ሃላፊነት ነው፡፡ በሁለተኛ የስራ ዘመን በሃላፊነት ለመቀጠል የተነሳሁት በሃላፊነቱ በነበረኝ ቆይታ የነበሩ ጠንካራ ጎኖች ለማሳደግ ነው፡፡ እንዲሁም የቀሰምኳቸውን መልካም ልምዶችና ተመክሮዎችን በመተግበር ውጤት ለማምጣት ነው፡፡ በፌደሬሽኑ በኩል ለመስራት በምንፈልጋቸው እቅዶች እና የእድገት አቅጣጫዎች የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማሳደግ የምንሰራበት ሃላፊነት ይሆናል፡፡ ከመንግስት፤ ከክልሎች፤ ከእግር ኳሱ ባለሙያዎች ጋር ያለንን ቅርበት የመጀመርያው የስራ ዘመናችን መጨረሻ ላይ ስንደርስ እንደተጠናከረ እገነዘባለሁ። ስለዚህም በፌደሬሽኑ በሁለተኛ የስራ ዘመን ለመቀጠል የተነሳነው የፕሬዝዳንትነት ልምዱ ስላለለ ነው፡፡ በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ያለንን የስራ ግንኙነት በማጠናከር የምናገለግልበት ነው፡፡ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንና (ካፍ) እና ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ፊፋ) ጋር ያሉን ግንኙነቶች የሚያበረታቱ ናቸው። ከእነዚህ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ባለን የስራ ግንኙነት ትልልቅ ስብሰባዎችን በማስተናገድ እንዲወሰን አንፈልግም፡፡  በስፖርቱ ልማት በስፋት ለመስራት ያሉትን ትውውቆች እና እድሎች ተጠቅመን መስራት እንፈልጋለን፡፡

ምን ለመስራት ይፈልጋሉ?
ባለፉት 4 ዓመታት በፌደሬሽኑ አመራርነት በመንገድ ላይ የሆኑ፣ እንዲሁም ተያይዘን ጫፍ ያደረስናቸው በርካታ ስራዎች አሉ፡፡ እነሱን በመስራት ለመቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የምጠቅሰው የክለቦች ሊግ ምስረታ ተግባራዊ እንዲሆን የያዝነውን አቅጣጫ ነው፡፡ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ክለቦች ውድድራቸውን በራሳቸው ዘመናዊ አስተዳደር፤ የገቢ ምንጫቸውን በሚያሰፋ አቅጣጫናነ ራእይ እንዲካሂዱት ይፈልጋል፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ፕሮፌሽናሊዝምን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለመተግበር በሙሉ ፍላጎት ከተነሱበትና ከተዘጋጁበበት የሊግ ኮሚቴው ምስረታ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች በአግባቡ ተከናውነው በ2 እና በ3 ወራት ሊያልቅ የሚችል ነው፡፡
በሌላ በኩል ትኩረት የሰጠነው  ፌደሬሽኑ የራሱ ህንፃ ባለቤት የሚሆንበትን እቅድ ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ፈር ቀዳጅ ሆኖ የሚጠቀሰውና በአባላቱ ብዛት ከአህጉሪቱ ግዙፉ የሚባለው ፌደሬሽናችን በህንፃ ኪራይ መስራቱ መቀጠል የለበትም፡፡ ዋና መስርያ ቤት የሚሆን የተደራጀ ፅህፈት ቤት የሚገኝበት ህንፃ ባለቤት መሆን እንደሚገባው አምነንበታል፡፡አሁን ያለንበት ደረጃ ህንፃውን ለመገንባት የሚያስችለን አይደለም፡፡ ለተሟላ የፌደሬሽኑ እንቅስቃሴ በቂ ቢሮዎችን ያቀፈ ህንፃ መግዛት ነው የምንፈልገው፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከፊፋ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ አግኝተናል፡፡ ይሁንና ህንፃውን ለመግዛት በየአቅጣጫቸው በምናደርጋቸው ጥረቶች እንቅፋቶች እየገጠሙን ነው፡፡ ከ70 እስከ 80 ሚሊዮን ብር በማጣት ህንፃውን ለመግዛ በተለያዩ ጨረታዎች ገብተን  ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ያሸነፍናቸው ጨረታዎችን ለመጨረስ ያልቻልንባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ ጣልቃ ገብነቶች አሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ የራሱን ፅሕፈት ቤት የሚያደራጅበት ህንፃ እንዳይገዛ የሚፈልጉ ሳይኖሩ አይቀሩም፡፡ በተለያየ መንገድ ተፅእኖ እያደረጉብን ናቸው፡፡  መሰል ተፅእኖዎች ካልገጠሙን ፌደሬሽኑን በ2 ወራት ውስጥ የራሱን ህንፃ ባለቤት በማድረግ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እናሸጋግረው ነበር።
በ3ኛ ደረጃ የምጠቅሰው በወጣቶች ላይ ለመስራት የያዝናቸውን እቅዶች ነው፡፡ ባለፉት 4 ዓመታት በዚህ ረገድ ያከናወንናቸው ተግባራት ለእቅዶቻችን ምቹ መደላደል የፈጠሩ ናቸው። ባለፉት የውድድር ዘመናት በሀ-15፣ በሀ-17 እና በሀ-20 ቡድኖች ያካሄድናቸው ውድድሮች በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥሉ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በ2010 የበጀት ዓመት ለመጀመር ያሰብነው ይህን በታዳጊዎች እግር ኳስ ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ወደ ትምህርት ቤቶች ለማውረድ ነው። በሁሉም ክለሎች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ጋር ለመስራትና ውይይት ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡ በእቀዳችንም ትምህርት ቤቶችን የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በማድረግ እንደፌደሬሽን ለአስተማሪዎች የስልጠና ድጋፍ እየሰጠን እንዲሁም የትጥቅ እና የኳስ ድጋፎችን በማቅረብ ስፖርቱን ለማስፋፋት እንፈልጋለን፡፡
እግር ኳስን ወደ ፕሮፌሽናሊዝም ደረጃ ለማሳደግና የገቢ ምንጮቹን ለማስፋት የሰጠነው ትኩረት ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚጠቀስ ነው፡፡ ባለፉት 4 ዓመታት በፌዴሬሽኑ በኩል በተለያዩ አቅጣጫዎች ስፖርቱን ወደ ቢዝነስ አቅጣጫ ለማስገባት የሚያስችሉ ሙከራዎች ተደርገዋል። ወደፊት የበለጠ አጠናክረን የምንሰራባቸው ይሆናሉ፡፡ በእግር ኳሱ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የተነሱና የተለያዩ የንግድ እድሎችን በመፍጠር ተጠቃሚ ለመሆን  የሚፈልጉ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ስለሆነም እነሱን በቅርበት እያነጋገርን ሲሆን ይህም ፌዴሬሽኑ እና ክለቦች የገቢ ምንጮቻቸውን በሚያጠናክሩበት እንዲሁም ከፍተኛ ሀብት ሊሰበስቡ በሚችሉበት አስተዳደር እንዲገቡ ነው፡፡
በመጨረሻም የባለሙያዎችን አቅምና የብቃት ደረጃ ለማሳደግ በሚያስችሉ እቅዶችም የምንቀሳቀስ ይሆናል። በተለይ የአሰልጣኞች፣ የተጫዋቾች፣ የዳኛኞች የሙያ ማህበራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንፈልጋለን፡፡ በርግጥ የዳኞች ማኅበር በጥሩ መሰረተ ያለና በአበረታች እንቅስቃሴዎች በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን። ሌሎችም የሙያ ማህበራት በተሻለ አደረጃጀት እንዲጠናከሩ  ነው የምንፈልገው፡፡ የአሰልጣኞች እና የተጫዋቾች ማህበራት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ያፈልጋቸዋል ብለን ተነስተናል፡፡
ስለዚህም በየአቅጣጫው የተለያዩ ድጋፎች እና የአሰራር አቅጣጫዎችን እንዲቀይሱ በማበረታታ አስፈልገውን አስተዋፅኦ ለእግር ኳስ እንዲያደርጉ አስበናል፡፡  በቅርቡ  ለአሰልጣኞች ማህበር የሰጠነውን እድል የእቅዶቻችንን ሁኔታ የሚያመልክት ምሳሌ ነው፡፡ አሰልጣኞች ወደ ሞሮኮ ተጉዘው የስልጠና ዕድል እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ ተመሳሳይ ስራዎችን በማከናወን እንቀጥላለን ብለን ተስፋ አድርገናል፡፡የክልል እግር ኳስ ፌደሬሽኖች፤ የክለቦች አደረጃጀትና አሰራር ለማሻሻል ከሚመለከታቸው የፊፋ እና የካፍ አካላት ጋር በመነጋገር እንሰራለን፡፡

ከአህጉራዊ ውድድሮች መስተንግዶ በተያያዘ…
ከአህጉራዊ ውድድሮች መስተንግዶ ጋር በተያያዘ በቅድሚያ የማነሳው በ2020 እ.ኤ.አ ላይ የአፍሪካ አገራት ሻምፒየንሺፕ (ቻን) እንድናተናግድ የተሰጠውን እድል ነው፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ይህን እድል የሰጠው በስፖርት መሰረተልማት የደረስንባቸውን ደረጃዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቻንን በማስተናገድ ረገድ የተሰጠንን ዕድል በመጠቀምና በውጤትም ስኬታማ በመሆን የአገሪቱን እግር ኳስ ለማነቃቃት እና ገፅታ ለመገንባት እንፈልጋለን።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ደግሞ በ2025 እ.ኤ.አ ላይ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ በማቅረብ በጀመርናቸው ጥረቶች የሚያበረታቱ ተስፋዎች መኖራቸው ነው፡፡ ካፍ በአህጉራዊ ውድድሮች መስተንግዶ ለምስራቅ አፍሪካ የሰነውን ትኩረት በመገንዘብ በርካታ የማግባባት ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በ2025 እ.አ.አ የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያስተናግዱ የመጨረሻ እጩ ካረጋቸው 3 አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት። እንደውም ከካፍ የቅርብ ምንጮች የምሰማው አስቀድመው የተመረጡ አዘጋጆች ካልተሳካላቸው በ2023 የአፍሪካ ዋንጫው ለኢትዮጵያ በምትክነት የሚሰጥበት እድል እንደሚኖር ይታመናል።
በመጨረሻም….
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ለምርጫ ሲባል በተፈጠሩና በተሟሟቁ እሰጥ አገባዎች ከአንድ ወር የማያፉ ሁኔታዎች ናቸው። ተስፋ በሚያስቆርጥ ደረጃ ግን አይደለም፡፡ በፌዴሬሽን አስተዳደር በአመራሮች ምርጫ ዙሪያ ውዝግቦችና ትርምሶች በአፍሪካ ደረጃ የተለመዱ ክስተቶች ናቸው። ምናልባትም ይህ ሁሉ የውዝግብ ሂደት በስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን በመረከብ በተሻለ የእድገትና የልማት አቅጣጫ ለማገልገል ከመነጨ ቅን ፍላጎትም ሊሆን ይችላል፡፡
የጠቅላላ ጉባኤው አባላት፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት፣ ሚዲያው በአጠቃላይ የስፖርት ቤተሰቡ በተፈጠሩት ሁኔታዎች ላይ በተረጋጋ መንፈስ  ማሰብ አለባቸው። የስፖርት ቤተሰቡ በአመራሮቹ የሚታየው ውዝግብ ከዚያም ባሻገር በብሔራዊ ቡድኖች የውጤት ክፍተት የሚያዝን ቢሆንም  መልካም ጅማሮዎችን በማድነቅ የነበረው አመራር ያሉትን ተመክሮዎች አሳድጎ መስራቱን እንዲቀጥል ማነሳሳት አለበት፡፡ በአጠቃላይ  በሁሉም ወገን መረጋጋት ያስፈልጋል፡፡
የፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫው በተረጋጋ ሁኔታ እንዲካሄድ ተስፋ ስለማደርግ ነው ይህን መልክት የማስተላልፈው። በእኛ በኩል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበን በመመካከር ለመስራት ነው የምንፈልገው፡፡ ምርጫው ህጉን ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ነው። ሁላችንም ስለ እግር ኳስ የምናስብ  ከሆነ ለአገር በሚጠቅም አቅጣጫ ለመስራት ትኩረት መስጠት ይኖርብናል፡፡

Read 2076 times