Saturday, 14 April 2012 12:45

ጁሊያ ሮበርትስ ተፈላጊነቷ እየቀነሰ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት ለእይታ የቀረበው “ሚረር ሚረር” የተሰኘውና ጁሊያ ሮበርትስ የሰራችው ፊልም 18.1 ሚ. ዶላር ያስገባ ሲሆን የተዋናይቱን ደረጃ አይመጥንም በሚል ትችት ተሰንዝሮበታል፡፡ የጁሊያ ሮበርትስ ተፈላጊነትም አየቀነሰ ነው ተብሏል፡፡ ፊልሙን ለመስራት 80 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን ለማስተዋወቅ 20 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበታል፡፡ የፊልሙ በፋሲካ በዓል ሰሞን መውጣትና ታሪኩ ጭብጥ ገበያውን እንዳዳከመበት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጁሊያ ሮበርትስ የመጨረሻ የትወና ዘመኗ  ላይ እንደደረሰች በርካታ ሃያሲያን መግለፃቸውን የጠቀሰው ፎርብስ መፅሄት፤ ተዋናይቷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰራቻቸው አምስት ያህል ፊልሞችም ስኬታማ እንዳልነበረች አመልክቷል፡፡ ጁሊያ በአንድ ፊልም እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር ከሚከፈላቸው የሆሊውድ ምርጥ ሴት ተዋናዮች አንዷ እንደነበረች ያስታወሰው ፎርብስ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ተፈላጊነቷ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክቷል፡፡

በስኖው ዋይት ተረት ላይ ተመስርቶ በተሰራው “ሚረር ሚረርን” ፊልም ላይ የተወነቻትን እኩይ ገፀባህርይ እንደወደደች ተናግራለች፡፡ የገፀባህርያት አለባበስ በተደነቀበት በዚህ ፊልም ላይ ጁሊያ ሮበርትስ በቀረፃ ወቅት ልብሶቿን ለመልበስና ለማውለቅ ከግማሽ ሰዓት በላይ ይፈጅባት እንደነበር አስታውሳለች፡፡

የ44 ዓመቷ ጁሊያ ሮበርትስ ከ20 ዓመት በፊት በተወነችበት “ፕሪቲ ውመን” የተሰኘ ፊልም ላይ በሆሊውድ መንደር የምትሰራ ሴተኛ አዳሪ ሆና የተጫወተች ሲሆን ፊልሙ በመላው ዓለም 464 ሚ. ዶላር ማስገባቱ ይታወሳል፡፡ “ፕሪቲ ውመን” ለተዋናይቷ ተወዳጅነት መሰረት የጣለ ፊልም እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ከ38 በላይ ፊልሞች ላይ የተወነችው ጁልያ ሮበርትስ፤  በመላው ዓለም ከ5.17 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝታለች - በሰራቻቸው ፊልሞች፡፡

 

 

Read 1272 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 12:49