Sunday, 19 November 2017 00:00

ሌላኛው ሰው

Written by  ደራሲ፡- ሩዲያርድ ኪፕሊንግ ትርጉም፡- ዮናስ ነማሪያም
Rate this item
(8 votes)


   ማስታወሻ
ሩዲያርድ ኪፕሊንግ   (1865   -   1936)   እንግሊዛዊ   የአጭርና ረጅም ልቦለድ ደራሲ እንዲሁም ባለቅኔ ነው፡፡ አብዛኛውን የወጣትነት ጊዜውን በህንድ አሳልፏል፡፡  በ1907   በሥነ-ፅሁፍ ዘርፍ የኖቤል   ሽልማት   በማሸነፍ   የመጀመሪያው   እንግሊዛዊ   ደራሲ   ለመሆን   በቅቷል፡፡   ይህ   “ሌላኛው ሰው”   (The   Other   Man,   1888)   “Plain   Tales   from   the   Hill”   ከተሰኘው የአጭር ልብወለዶች መድበል የተወሰደ ነው፡፡
*   *   *
…በ1870ዎቹ   “ሲሚላ”   ገጠር ቀመስ ከተማ ነበረች፤ አንድም መሥሪያ ቤት ያልታነፀባት። በ“ጆኮ” ዙሪያ ያለው አውራ ጎዳና ከመዘርጋቱ በፊት፤ ወ/ሪት ጋውሪ በወላጆቿ ግፊት ኮሎኔል ሸራይደሪሊንግን ለማግባት ተገደደች፡፡ ያን ያህል የዕድሜ ልዩነት በመሃላቸው አልነበረም፤ እርግጥ ነው! ኮሎኔሉ  በ35   ዓመት እንደሚበልጣት ማጋነኑ ምን ዋጋ አለው -   ምንም፡፡  በወር  የ200  ሩፒ ደመወዝ ተከፋይ ነው፤ ተቀማጭ ጥሪት ስለነበረው “ተንቀባሮ መኖር የሚችል” የሚባልለት ሰው ነው። ብቻ ያቺ ቀሳፊ ብርድ ስትነሳበት በደረቅ ሳል ይንተከተክ ነበር፤ ሞቃቱም አየር ሰውነቱን አዝሎ እያንዘፈዘፈው ወደ ሞት ወሰድ ያደርገው ነበር፤ ጨርሶ እንኳን ባይወስደውም፡፡  ለጎጆው ታማኝ፣ ፀባየ ሸጋ አባወራ ነው፡፡ ፀባዩ ለወጥ የሚለው በህመም ተደቁሶ አልጋ ሲይዝ ብቻ ነው፤ ይህም በየወሩ 17 ቀናት ብቻ መሆኑ ነው፡፡   
…በገንዘብ አወጣጥ ረገድ ቋጣሪ የሚባል አይነት አይደለም፤ በተለይም ለሚስቱ ቸር ነበር። ወ/ሮ ሸራይደርሊንግ ግን ደስተኛ አልነበረችም፡፡ ያለ ፍላጎቷ ከመዳሯ በፊት፣ ምስኪን ልቧን ለሌላ ሰው ሰጥታ ነበር፡፡ የሰውዬውን ስም ዘነጋሁት-   “ሌላኛው ሰው”  የሚል ስያሜ እንስጠውና ትረካዬን ልቀጥል…
…በሠራዊቱ ትራንስፖርት ክፍል በመናኛ ደመወዝ ተቀጣሪ ነው፤ ከዕለት ጉርሱ ያለፈ ገንዘብ የሌለው መናጢ ድሃነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀው አንዳችም የተስፋ ጭላንጭል እንደሌለ ያስታውቃል፡፡ በዚህም ላይ ከተራ መልክ ያለፈ መስህብ አልነበረውም፡፡ ቢሆንም ግን በፅኑ ታፈቅረው ነበር፤ ፍቅራቸውንም በጋብቻ ሊያስሩ በቃልኪዳን ተማምለዋል፡፡ በዚህ መሃል የሸራይደርሊንግ የጋብቻ ጥያቄ መጣ፡፡ እናቷ ከ”ሌላኛው ሰው” ጋር የነበራትን መተጫጨት ተቃወመች፤   ያውም እንባዋን እያፈሰሰች፡፡  አሮጊቷ ክብሯ ሲነካ  በእንባዋ ነበር  የምትገልፀው፡፡   ልጅቷ ግን በእናቷ አልወጣችም፤  እንባ  አያውቃትም።   “ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ” የሚለው ብሂል እሷ ላይ አልሰራም፤ የሰርጓ ዕለት አንዳችም ጠብታ እንባ አልወጣትም፤ ልበ-ደንዳና የሚሏት ዓይነት ሴት ነበረች…
ቀናት ተቆጠሩ፤ ወራት ተቀመሩ፡፡ ወ/ሮ   ሸራይደርሊንግ በህመም ፍዳዋን ማየት ጀመረች። በትረካ መፅሐፍ እንደሚገኙ ህመምተኛ ገፀ-ባህሪያት በስቃይ ማቃ፣ መንምና ሳር ባታክልም፣ በዘርፈ ብዙ በሽታዎች ላሽቃለች፡፡
በሙሉ ጤናማነቷ ጊዜ ከተራ መልክ የዘለለ ውበት አልነበራትም፤ ህመሟ ደግሞ መልከ-ጥፉ አድርጓት አረፈው፡፡  ይህንን የምለው እኔ ተራኪው አይደለሁም፤ የገዛ ባለቤቷ ሸራይደርሊንግ እንጂ። “አካፋን አካፋ” ማለቱ ያኩራራው ነበር፡፡  የወጣትነት ወዘናዋ ሲሟጠጥ “በይ ደህና ሰንብቺ!” ብሎ ወደ ላጤነቱ ተመለሰ - አቶ  ሸራይደርሊንግ፡፡…
“ከጋብቻችን በኋላ እንዲህ ጭርንቁስ ፉንጋ እንደምትሆን ባውቅ ኖሮ አላገባትም ነበር…   በፍፁም አላደርገውም!!” ሲል ተደምጧል፤ ሸራይደርሊንግ የሚሰማውን እንደወረደ በመናገሩ ይኩራራል ብያችሁ አልነበር?…
በወርሃ ነሀሴ እሷን እዚያው “ሲሚላ” ትቷት ወደ ጦር ሰፈሩ ጠቅልሎ ገባ፡፡ …በቅርቡ ከመሸታ ቤት አካባቢ  ያ  “ሌላኛው ሰው”  ወደ   “ሲሚላ”   ሊመጣ እንደሆነ ጭምጭምታ ሰማሁ፤ እንደሚባለውማ የተቆራኘው ክፉ ደዌ በይበልጥም የልብ ህመሙ ከሞት አፋፍ አድርሶት የመኖር ተስፋውተሟጦ   …አምላክ የህይወቱን ሻማ እፍ! ሊላት በተቃረበ ጊዜ ነበር፣ ለመምጣት የወሰነው፡፡ ይህን ሁሉ እሷ ታውቃለች፤ የሚመጣበትን ቀን በደብዳቤ ያሳወቃት ይመስለኛል፡፡  …
አሳዛኙ ታሪክ በዚህ ሁኔታ ቀጠለ…   
ከዕለታት በአንደኛው ቀን ጉዳይ ስላልነበረብኝ፣ ለአይን ያዝ እስኪያደርግ ድረስ  ዶቨደል ሆቴል ነበርኩ፡፡ ወ/ሮ ሸራይደርሊንግ ገበያው መሃል ባልተረጋጋ ሁኔታ ስትወካከብ አየኋት፡፡ ዝናብ እየዘነበ ነበር…
ወደ ዋናው መንገድ ስወጣ አንድ ሰረገላ አልፎኝ ሲሄድ እንደዘበት አየሁት፡፡ ለካስ ወ/ሮ   ሸራይደርሊንግ ከላይ ታች በዝናብ በስብሳ የሰረገላውን መድረስ በመጠበቅ ላይ ነበረች፡፡   የሰረገላው መድረስ የኔ ጉዳይ ባለመሆኑ፣ አልፌያት ሄድ ከማለቴ፣ የሴትየዋ የሳግ ለቅሶ ጆሮዬ ጥልቅ አለ፤   ወዲያው መለስ አልኩ፡፡
አሁን ከገባው ሰረገላ ጀርባ ከጨቀየው መንገድ ላይ ተንበርክካ፣ እዬዬዋን ስታስነካው ግራ ገብቶኝ ወደ እሷ ቀረብ አልኩ፡፡ እኔን እንዳየችኝ፣  ከላቆጠው ጭቃ ላይ በፊቷ ተደፋች፡፡ … ከሰረገላው ከኋለኛው መቀመጫ ላይ እንደደረቀ ቋንጣ ገንትሮ  … አንድ እጁ ከሰረገላው ብረት ጋር ታስሮ   … ባርኔጣውና የተንዠረገገው    ፂሙ እንደ   አሸንዳ ውሃ እያፈሰሱ …  ያ!  ሌላኛው ሰው ተቀምጧል፡፡ ሞቷል።
የስልሳ ማይል አባጣ ጎርባጣ መንገድ ንቅናቄ ለደካማዋ ልቡ ከአቅም በላይ ሳይሆንባት አልቀረም።   ሰረገላ ነጂው፤ “ከሶሎን ነበር የተነሳነው፤ ሁለተኛ ፌርማታ ላይ ሞተብኝ፤   እንዳይወድቅብኝ በገመድ ጥፍር አድርጌ አስሬ እነሆ ሲሚላ ደረስን፡፡ ሂሳቤን የሚሰጠኝ ማነው? እሱ (ወደ ሟቹ ”ሌላኛው ሰው” እያመለከተ)  አንድ ሩፒ ሊከፍለኝ ተስማምቶ ነበር”
“ሌላኛው ሰው” በአደራረሱ ኮሜዲ መሰ ል ትዕይንት፣ ፈገግታ ፊቱ ላይ ታትሞ ዘና ብሎ ተቀምጧል፡፡
ወ/ሮ ሸራይደርሊንግ ከጭቃው ላይ ሳትነሳ፣ መሪር እንባዋን በጩኸት ማፍሰሷን አላቋረጠችም።   ከአራታችን በቀር በዙሪያችን ማንም አልነበረም፡፡   ዝናቡ  ዶፉን  እያወረደው ነው፡፡  ሁለት ነገሮችን ለመተግበር ወሰንኩ፡፡ የመጀመሪያው እሷን ወደ ቤቷ ማድረስ ሲሆን   ሁለተኛው ደግሞ ስሟ በዚህ ጉዳይ እንዳይነሳ የጉዳዩን ደብዛማጥፋት፡፡ ያም ሌላኛው ሰው የተጫነበትን ሰረገላ ወደመጣበት መመለስ፡፡ ለሰረገላ ነጂው ለወ/ሮ  ሸራይደርሊንግ በፍጥነት ጋሪ እንዲያመጣላት አምስት ሩፒ ከፈልነው፡፡  ለሰረገላ ባለቤቱም ስለ ሌላኛው ሰው ሃቁን አስረድቶ፣ አስክሬኑን እንዲያስረክበው፤ ባለቤቱም ማድረግ የሚገባውን በራሱ ውሳኔ እንዲያደርግ ሰረገላ ነጂውን አሳመንኩት፡፡
ወ/ሮ ሸራይደርሊንግን ከዝናብ አስጠለልኳት። ለአርባ አምስት ደቂቃ የጋሪውን መምጣት ስንጠባበቅ ቆየን፡፡ ሌላኛው ሰው ልክ ሲደርስ እንደነበረው ከመተው ውጪ አማራጭ አልነበረንም። ወ/ሮ ሸራይደርሊንግ ማልቀሷን አላቋረጠችም፤ ማልቀሷ የጠቀማት ይመስለኛል፡፡ በመጠኑ ቀለል ሲላት ለሌላኛው ሰው ነፍስ መፀለይ ጀመረች፡፡ ልበ-ንፅህት ባትሆን ኖሮ ለራሷም መፀለይ ነበረባት፡፡  ለራሷ ስትፀልይ ለመስማት ጓጉቼ ነበር፤ ግን አላደረገችውም፡፡
ጋሪው መጣ፡፡ በስንት ልምምጥ እየጎተትኩ ጋሪው ላይ አሳፈርኳት፡፡ አሳዛኙ ገጠመኝ ከጅማሬው እስከ ፍፃሜው ልብን የሚያደማ ነበር። ከሁሉ ከሁሉ ግን ያ   ሌላኛውን ሰው የያዘው ሰረገላና እሷን የያዘው ጋሪ ጎን ለጎን ሲተላለፉ፤ እርሷም በፋኖሱ ብርሃን ከሰረገላው ብረት ጋር የታሰረውን ሌላኛውን ሰው ስትመለከት ማየቱ ልብን የሚያደማ ትዕይንት ነበር!!   …
ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ … ወ/ሮ  ሸራይደርሊንግ እንዲያ ቅስም የሚሰብር ሀዘን ቢደርስባትም እንዲህ በቀላሉ ለሞት እጇን አልሰጠችም፡፡ መልኳ እየጠቋቆረ በማዲያት ተዥጎርጉራ … እየከሳች …   እየከሰመች … በህይወት ቀጠለች፤ እንዳልኳችሁ እንደ  ወ/ሮ   ሸራይደርሊንግ አይነት ሴቶች እንዲህ በዋዛ ለሞት እጃቸውን አሳልፈው የሚሰጡ አይደሉም…
ከጋብቻዋ ዕለተ ቀን ጀምሮ ስለ “ሌላኛው ሰው” ለማንም ትንፍሽ አላለችም፡፡ ስለዚያ ዝናባማ የተረገመ ገጠመኝ … እኔ እማኝ እንደነበርኩ እንኳን፣ አንዳችም ፍንጭ ለማንም አልሰጠችም - ለኔም ጭምር፡፡ “ያ ዘግናኝ  ገጠመኝ ስለመከሰቱ   ከነአካቴው ዘንግታው ይሆን?” ስል ማሰቤ   አልቀረም፡፡
ዘወትር ገበያው መሃል በፈረስ ጀርባ ተቀምጣ፣ ላይ  ታች ትመላለስ ነበር - ከአንዱ ጥግድንገት ብቅ የሚል ሰው የመጠበቅ ቀቢፀ ተስፋ ፊቷ ላይ ይነበባል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ቤተሰቦቿ ተመለሰች፤ በርንማውዝ፡፡ እዚያው ህይወቷ አለፈ…   
ኮሎኔል ሸራይደርሊንግ ስሜቱ ሲነካ…
“የህይወቴ አክሊል - ምስኪኗ - ውዷ ባለቤቴ!”  እያለ በሀዘን ይቆዝም ነበር፡፡ ሁሌም ቢሆን የልቡን በመናገር ያምን ነበር … ብያችሁም አልነበር፤ ሸራይደርሊንግ እንዲያ ነበር … ስሜቱን ፊት   ለፊት   የሚናገር!

Read 2410 times